የራሷን የአጭር ልብወለዶች መድበል በማሳተም የመጀመርያይቱ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት፣ የመጀመርያዋ ሴት የፖሊስ ፕሬስ ክፍል ሃላፊ ሆና አገልግላለች፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ናት፣ ከሰባት በላይ መፃህፍት የፃፈችና ያሳተመች ናት።
የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ
ነሀሴ 1952 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አፍሪካ አንድነት፣ አዲስ አበባ
ካምብሪጅ ቱቶርያል ኮሌጅ /ቱቶርያል/ ፣የመጀመርያ ድግሪ /ቢኤ/ በአድቨርታይዚንግ እና ኮሙኒኬሽን፣ ለንደን፣ ዩኬ
ከሰባት በላይ መፃህፍት ያሳተመች ታዋቂ ገጣሚና የአጭር ልብወለድ ደራሲ የሆነችው የምወድሽ በቀለ፤ ለ26 ዓመታት ባገለገለችበት የፖሊስ ፕሬስ ክፍል ሃላፊ በመሆን የሰራች የመጀመርያዋ ሴት ናት። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበርን በፕሬዚዳንትነት እየመራች ሲሆን የሴቶች መብት ቁርጠኛ ተሟጋች በመሆንም ትታወቃለች። ለሴቶች እድገትና መሻሻል በሚተጉ ቦርዶችና ድርጅቶች ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለች ነው።
በ1952 ዓ.ም ክረምት ላይ በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አካባቢ የተወለደችው የምወድሽ ፤ ለወላጆቿ ብቸኛ ልጅ ስለነበረች ትንሽ የመሞላቀቅ እድል አግኝታለች – በልጅነቷ። ከጥበቡ ዓለም ጋር የመጀመርያ የፍቅር ግንኙነት የመሰረተችው በህንድ ፊልሞች አማካኝነት ነው። የህንድ ፊልም ነፍሷ ነበር።
የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የክፍል ጓደኞቿ የሚሰነዝሯቸውን ቀልዶች በግጥም በመመለስ ትታወቃለች። የፖሊስ መኮንን ልጅ የሆነችው የምወድሽ፤ ከልጅነቷ አንስታ የፖሊስ ጋዜጦችንና ህትመቶችን ታነብ ነበር። በምታነባቸው ታሪኮች ከመደነቅም ባሻገር “አንድ ቀን የፖሊስ ዘጋቢ መሆኔ አይቀርም” እያለች ማለም ጀመረች።
ነፍስ እንዳወቀች ነበር በግጥም ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረችው። በ19 ዓመቷ በባህልና ስፖርት ሚ/ር ድጋፍ በተዘጋጀ የግጥም ውድድር ላይ ተካፍላ አሸነፈች – በ1971 ዓ.ም። በዚህም የተነሳ 12 ግጥሞቿ በስዕል በተደገፈ መድበል “አብዮታዊ ግጥሞች” በሚል ርዕስ ታተመላት። ከግጥሞቿ አንዱ “ከማጀት እስከ ከተማ” የሚል ሲሆን ጭብጡ በሴቶች ትግል ዙሪያ ያጠነጥናል። በ1982 ዓ.ም በ27 ዓመቷ የመጀመርያዋ የሆነውን ሙሉ የአጭር ልብወለድ መድበል “የባከነ ጊዜ” በሚል ርዕስ አሳተመች። በ1990 ዓ.ም“ያላፈራ ፍሬ” የተሰኘ መፅሃፏን ካሳተመች በኋላ ዘጠኝ ሴት ደራስያን በሴቶች ዙሪያ በፃፉት “ዕጣ” የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። ቀጣዩ ስራዋ“እብዷ በለጠች” የተባለው ቤሳ ልብወለድ ነው። ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር 42 ሴት ደራስያንን አወዳድሮ በአሸናፊነት ከመረጣቸው ዘጠኝ ሴት ደራስያን አንዷ በመሆንም “ያልተናበቡ ልቦች” በሚል መድበል ውስጥ ስራዋ ተካቶላታል። ከዚያም “ፍቅር የጠማቸው ነፍሶች” የተሰኘ ጭብጡን በወንጀል ላይ ያደረገ ረዥም ልብወለድ ያሳተመች ሲሆን በመቀጠል “ዋጊኖስ” በሚል ርዕስ የግጥም መድበል አሳትማለች። የበርካታ ደራስያንን ስራዎች ባካተተው “የዋርካ ስር ጉባኤ” የአጭር ልብወለድ መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። የበርካታ ሴት ደራስያን ግጥሞችን ባሰባሰበው “እኛ2” የግጥም መድበል ውስጥም ተካትታለች። የአጫጭር እውነተኛ ታሪኮች ስብስብ ለማሳተም በተዘጋጀው ውድድር ካሸናፊዎቹ አንዷ በመሆንም “የእኔ ዓለም” በሚል መድበል ስራዋ ተካትቷል። በ2004 ዓ.ም በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ድጋፍ በተዘጋጀው ውድድር በማሸነፍ“አዙሪት” በተሰኘው መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። በዚሁ ዓመት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ “ነዋዡ ምሁር” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ አሳትማለች።
ፀሃፊ፣ ገጣሚና የፖሊስ ጋዜጣ ዘጋቢ የመሆን ህልሟን እውን እንድታደርግ እድል የፈጠረላት አንደኛው መፅሃፏ ነው። መፅሃፉ እንደታተመ የተወሰኑ ቅጂዎችን ለመሸጥ ወደ ፖሊስ ቢሮ ጎራ ብላ ነበር። በመፅሃፉ ታሪኮች የተደመመው የፖሊስ ክፍል ሃላፊ፤ በፖሊስ ጋዜጣ ላይ በተለማማጅነት እንድትሰራ ጠየቃት። ዓይኗን አላሸችም። ስራውን የወደደችው የምወድሽ፤በተለማማጅነት ብቻ አልቀረችም፤ የማታ ማታ በዘጋቢነት ተቀጠረች። በኋላ ላይም የፕሬስ ክፍል ሃላፊ ለመሆን በቅታለች።
በዚህ የሃላፊነት ቦታ ላይ ሳለች የመጀመርያዋ ሲቪል ብቻ ሳይሆን የመጀመርያዋ ሴት የፕሬስ ሃላፊ በመሆኗም ጭምር ትላልቅ ፈተናዎች ገጥመዋታል። በፖሊስ ሃይል ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች በየአጋጣሚው ይቃወሟትና ይገዳደሯት እንደነበር ታስታውሳለች። የምወድሽ ግን በችሎታዋና በጥንካሬዋ ትተማመን ነበር። ለስራው ባላት ልባዊ ፍቅርም በስራዋ ለመግፋት ችላለች። የማታ ማታ ሌሎችም ይሄንን ሃቅ ተረድተውታል። በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ በዘጋቢነት ስትሰራ ከቆየች በኋላ ዋና አዘጋጅ ለመሆን የቻለችው የምወድሽ፤ ለስድስት ዓመትም በፕሬስ ክፍል ስራ አስኪያጅነት አገልግላለች። በዚህ ሃላፊነቷም ብቃት ያላቸው ድጋፍ የሚሰጡ ሰራተኞችን አፍርታለች።
ዝነኛው ደራሲ በዓሉ ግርማ አርአያዋ እንደሆነ ትናገራለች። ጥልቀት ያላቸው አጫጭር ዓረፍተነገሮች እንዴት እምቅ ትርጉምና ሰፊ ሃሳብ እንደሚያስተላልፉ ስራዎቹ አሳይተዋታል። በኋላ ላይ ካወቀቻት ዝነኛዋ ገጣሚ ፊርማዬ ዓለሙ ደግሞ መድረክ ላይ ስትወጣ የነበራትን በራስ መተማመንና የእርጋታ መንፈስ አስተውላለች።
“በብዙ ሁኔታዎች ሴትነቴ ለፈተናዎች አልዳረገኝም ማለት እችላለሁ። አንዳንዴ ግን እንደሴትም እንደእናትም መሆኔ አይቀርም፤ የሌሎች ህመምና ስቃይ በጥልቀት ይሰማኛል። በፖሊስ ፕሬስ የስራ ዘመኔ ትልቁ ፈተናዬ ይሄ ነበር። ለምሳሌ የትንሽ ሴት ልጇን መደፈር ልታመለክት የመጣች እናት ስመለከት፣ ራሴን መቆጣጠር የሚያቅተኝ ጊዜ ነበር”ብላለች – የምወድሽ።
በአንድ በኩል ልጆቿን እያሳደገች፣ በሌላ በኩል ከሰባት በላይ መፃህፍትን ለማሳተም የቻለችው በሌላ ተዓምር ሳይሆን ውስጣዊ ጥንካሬዋንና ቁርጠኝነቷን በመገንዘቧ እንደሆነ ታምናለች። የህይወትን ውጣ ውረዶች ያለፈችውና ድል ያደረገችውም በፅናትና በፍቅር ነው – እግዚአብሄርን ከጎኗ አድርጋ።
ከፖሊስ ፕሬስ ብትወጣም ዛሬም መፃፏን አልተወችም። ለሴቶች እድገትና መሻሻል በሚሰሩ በርካታ ድርጅቶች ውስጥም እያገለገለች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ከመሆኗም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሴቶች ቅንጅት ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር ናት።
ለወጣት ልጃገረዶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – መሪዎችና እንስት ጀግኖች ለመሆን ራሳችሁን አለማምዱ። ህልማችሁን እንዳታሳኩ ደንቃራ የሚሆንባችሁን አሉታዊ ተፅእኖ ሁሉ አሻፈረኝ በሉ። ትችት ሲሰነዘርባችሁ በአንክሮ አዳምጡ። ምክንያቱም ለማደግ ያግዛችኋል።
በኦሮምያ ሆለታ፣ አሁንም ድረስ መብራትና ውሃ ባልገባላት ጉቱታ በምትባል የገጠር መንደር የተወለደችው ብርሃኔ ፤ የሶስት ወይም የአራት ዓመት ህፃን ሳለች ነው በሰውነት ልምሻ /ፖሊዮ/ አካል ጉዳተኛ የሆነችው። በቤት ውስጥ ስራ እንደምትረዳቸውና ትዳር ከያዘች በኋላም እንደምትደግፋቸው ለተማመኑት ቤተሰቦቿ ነገሩ አስደንጋጭ ነበር። እናቷን ገና ወጣት ሳለች በሞት ብትነጠቅም ገበሬ የነበሩት አባቷ አለ የተባለ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መፈወሻ ቦታ አልቀራቸውም። በወቅቱ ዘመናዊ የህክምና ማዕከል በአካባቢው ለዓመል ያህል እንኳን አልነበረም።ሴት አያቷ እንደአብዛኛው ማህበረሰብ አካል ጉዳቷ አንድም ቡዳ በልቷት አሊያም ከእግዚአብሄር ቁጣ የመጣ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ስለዚህም ጠበል ለማስጠመቅ ቤ/ክርስትያን ይወስዷት ነበር። በዚህ ጉዳቷ የተነሳም ከእድሜ እኩዮቿ ጋር ት/ቤት ለመሄድ አልታደለችም።
አባቷ በባህላዊ ህክምና አለመፈወሷን ሲመለከቱና እሷን ከሁለት ወንድሞቿ ጋ ለማስተዳደር አቅም ሲያጥራቸው፣ ቼሻየር ሰርቪስ የተባለ የአካል ጉዳተኞች ማገገሚያ ማዕከል ላኳት። በማዕከሉ ህክምና ካገኘችና በመራመጃ ሽመሎች መራመድ ከተለማመደች በኋላ በሚሽኖች የገንዘብ ድጋፍ አዳሪ ት/ቤት ገባች – የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል። ነገር ግን ከቤተሰብ ርቆ መኖሩን አልቻለችውም። ይባስ ብሎ ቤተሰብሽ ጠፍተዋል የሚል መረጃ ደረሳት። ይኼኔ ተስፋ መቁረጥ ጀመረች። በእርግጥ ሚሽኖቹ ደጋፊዎቿ ያበረታቷት ነበር – ራሷን መቻል የምትፈልግ ከሆነ ትምህርቷ በርትታ እንድትገፋ በማነቃቃት። ሆኖም በዙሪያዋ ያሉ በሙሉ ተስፋ እንደሌላትና በትምህርቷም መግፋት እንደማትችል በማሰብ ከንፈራቸውን ይመጡላት ነበር። ይሄ ነው የቀረች ተስፋዋን ያሟጠጠባትና የእለት ተዕለት ህይወቷን ፈተና ያደረገባት። ሴት አያቷ ምንም እንኳን በትምህርት ግስጋሴዋ ቢደመሙም ብዙ ርቀት ትጓዛለች የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበራቸውም።ትምህርቷን ብትጨርስስ — ምን ልትሰራበት ነው እያሉ ይጠይቁ ነበር። ብርሃኔ ግን ራሷን ሰው የምታደርግበት አንድ እድል ይሄ ብቻ መሆኑን አውቃለች፤ እናም ስራዬ ብላ ትምህርቷን ከልቧ መከታተል ያዘች – ስኬታማ እንደምትሆን በመተማመን። በእርግጥ የመማር ዕድል እንድታገኝ ሳይታክቱ የጣሩት አባቷ ባለውለታዋ መሆናቸውን አትዘነጋም።
ከቼሻየር ሰርቪስ ህክምናዋ በኋላ በአዲስ አበባ ወላጅ አልባ ህፃናት ማዕከል የገባችው ብርሃኔ፤ በማዕከሉ ውስጥ ስነስርዓትን ተምራለች። ይሄን ብቻ ግን አይደለም የተማረችው። የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሄርን መፍራት መሆኑንና እግዚአብሄርን በልብ ውስጥ ከያዙ ሁሉም ነገር እንደሚሳካ የተማረችውም በዚሁ ማዕከል ውስጥ ነው። በት/ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሚሽኖች፣ ተማሪዎች በመርህ የሚመሩና ለዓላማቸው የሚሞቱ ሰዎች እንዲሆኑ ቀርፀዋቸዋል። ለደረሰችበት ስኬትና ሌሎችን ለመርዳት ላላት ቁርጠኝነት በማዕከሉ የነበራት እድገት መሰረት እንደሆናት ብርሃኔ ታምናለች።መፃህፍት እንድታነብ፣ በራስ የመተማመን ስሜት እንድታዳብር፣ ጊዜዋን በብልሃት እንድትጠቀምና ያላትን ለሌሎች እንድታካፍል እየተበረታታች ማደጓን ታስታውሳለች። እንደክፍል ጓደኞቿ፣ እሷም በሄደችበት ሁሉ እግዚአብሄር እንደሚከተላት ተምራለች። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለዛሬ ማንነቷ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ፣ በአዲስ አበባ ንግድ ት/ቤት ገብታ በፀሃፊነት ሙያ /ሴክሬቴርያል ሳይንስ/ በዲፕሎም ተመረቀች። ስራ ፈልጎ መቀጠር ግን የማትወጣው አቀበት ሆነባት። ማመልከቻ ያላስገባችበት መ/ቤት የለም፣ የጠየቁትን መስፈርት ሁሉ ታሟላለች፣ የቅጥር መመዘኛ ፈተናዎች ስለሚቀሏት ያለጭንቀት ነው የምትሰራው። ግን ማንም ሊቀጥራት ፍላጎት የለውም። ገና ሲያዩዋት አሁን እቺ እንዴት አድርጋ ልትሰራ ነው የሚል ጥርጣሬ ያድርባቸዋል – ለእሷ ባይገባትም። እንቆቅሎሹ የተፈታላት ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ጋር በጉዳዩ ላይ ከተወያየች በኋላ ነበር። ስራ የመቀጠር እድል የተነፈገችው በአካል ጉዳተኝነቷ መሆኑን ስትሰማ ተስፋዋ ነጠፈ።የአካል ጉዳተኝነቷ የህፃንነት ህይወቷን ያቃወሰባት ሳያንስ በቀሪ ህይወቷም ፈተናው እንደሚቀጥል ተገነዘበች። ደግነቱ ተስፋ አልቆረጠችም፤ ይልቁንም ራሷን አጠንክራ በመንገዷ የሚገጥማትን ሁሉ ለመጋፈጥ ቆርጣ ተነሳች።
ከረጅም ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ በብሄራዊ ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ የተቀጠረችው ብርሃኔ፤ የቤተመፃህፍቱን ካታሎግ በታይፕ የመተየብ ስራ ላይ ተመደበች። በዚህ ተመስጌን ብላ ከመቀመጥ ይልቅ ክህሎቷን ለማሻሻል በማሰብ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማጥናት ወሰነች። ጊዜ ሳታባክን ወዲያው በአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገብታ፣ በማታው መርሃ ግብር ትምህርቷን ጀመረች። ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተሟጋች በመሆን በበጎ ፈቃደኝነት ትሰራ ነበር። ከቦታ ቦታ በታክሲ መጓጓዝ አስቸጋሪ ቢሆንባትም ለችግሮች ሳትፈታ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ የመጀመርያ ድግሪዋን ለመያዝ በቃች። ዛሬ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆነችው ብርሃኔ፤ እዚያው ብሄራዊ ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ ውስጥ በሲስተም አድሚኒስትሬተርነት ትሰራለች።
ብርሃኔ፤ እየሰራች ስትማር በነበረ ጊዜ ነው ከሰባት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበርን የመሰረተችው። ማህበሩ፤ አካል ጉዳተኛ ሴቶች በአካል ጉዳተኝነታቸው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተጋፍጠው ለማሸነፍና ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲገነዘቡ ለመርዳት የተቋቋመ ድርጅት ነው። በእርግጥ የመጀመርያ ሃሳቡ የመነጨው በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ትሰራ ከነበረችው ወ/ሮ መቅደስ ነበር። በኡጋንዳ ጉዞዋ አካል ጉዳተኛ ሴቶች እንዴት ራሳቸውን እንዳደራጁ አይታ የተመለሰችው ወ/ሮ መቅደስ፤ ራሷ አካል ጉዳተኛ ባለመሆኗ እንዴት አድርጋ ተመሳሳይ ድርጅት ለመመስረት እንደምትችል እርግጠኛ አልነበረችም። እናም ይሄን ሃሳቧን ማየት ለተሳናት የዩኒቨርስቲ የክፍል ጓደኛዋ አማከረቻት። እሷ ደግሞ ለብርሃኔ ነገረቻት። ከዚያም ብርሃኔና ሰባት ጓደኞቿ፣ በመቅደስ እገዛ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበርን አቋቋሙ – በ1994 ዓ.ም። ከእነሱ ቀድሞ የተመሰረተ የሴቶች ክንፍ ያለው የአካል ጉዳተኞች ማህበር ስለነበር የእነብርሃኔ ማህበር ተቃውሞ ገጠመው ። ብዙዎች ለሴቶች ብቻ ተብሎ አዲስ ማህበር መቋቋሙን አልወደዱትም ነበር። ብርሃኔና ባልደረቦቿ ግን የሚፈለገውን ያህል እንዳልተሰራ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ልባዊ ፍቅርና ቁርጠኝነትም ነበራቸው። ለበርካታ ወራት በበጎፈቃደኝነት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ለማህበሩ የመጀመርያውን ድጋፍ ከማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አገኙና ዎርክሾፕ መስጠት ጀመሩ። በዎርክሾፑ ላይ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ግለሰባዊና ማህበራዊ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች፣ ማብራሪያዎችና ገለፃዎች ያቀርባሉ – የራሳቸውን ተመክሮ በማካፈልና ሌሎች አካል ጉዳተኛ ሴቶች እንዲናገሩ በማነሳሳት። በክልሎች በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰነዘረው አጉል ማህበራዊ ፍረጃ ከአዲስ አበባም የከፋ ነው። በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ጥቂት አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብቻ ናቸው የሚገኙት። ለምን ቢባል አብዛኞቹ ከቤት ለመውጣት በሃፍረት ስለሚሸማቀቁ ነው።
አንዳንድ አካል ጉዳተኞች የተረጂነት ስሜት እንዲያዳብሩ በመደረጋቸው ከማህበሩ ችሮታ የሚፈልጉ ቢሆንም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ግን ተረጂነትን አያበረታታም- ራሳቸውን እንዲችሉ ያግዛል እንጂ። አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ለማብቃትም የገቢ ማስገኛ ክህሎቶች ስልጠና ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ አካል ጉዳተኝነት በተለይ ሴቶችን ለጥቃት ስለሚያጋልጥ ማህበሩ እንዴት ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንም አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ይሰራል። ዛሬ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ቢሮው ከ800 በላይ አባላት ሲኖሩት፤ በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ /ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌና ናዝሬት/ ከ1ሺ200 በላይ አባላት አሉት።ማህበሩ በአዲሱ አዋጅ መሰረት እንደአገር በቀል የኢትዮጵያ ድርጅት ዳግም ከተመዘገበ ወዲህ፣ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንጮች መቀበል የሚችለው 10 በመቶ ብቻ ሲሆን የቀረውን ከአገር ውስጥ ማሰባሰብ ይጠበቅበታል። ለዚህም ነው ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች የስራ እድል፣ ለማህበሩ ደግሞ መጠነኛ ገቢ የሚሰጥ ዳቦ ቤት የከፈተው። ብርሃኔ ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት እያገለገለች ነው።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰነዘረው አጉል ልማዳዊ ፍረጃ አሁንም ቀጥሏል – በተለይ በሴቶች ላይ – በተለይም በክልሎች። ማህበሩን የመሰረቱት ብርሃኔና ሰባት ጓደኞቿ አስቸጋሪ ፈተናዎችን አሸንፈው የተሳካላቸው ጠንካራ ሴቶች ስለነበሩ ነው። አንዱ የጥንካሬያቸው ምንጭ ደግሞ ትምህርት እንዳይማሩ ተስፋ ያስቆርጧቸው ከነበሩ ቤተሰብና ማህበረሰብ እንዲሁም ከተወለዱበት ከባቢ ማምለጥ መቻላቸው ነው። ህፃናት ከቤታቸው ሳይርቁ በመደበኛ ት/ቤት ትምህርታቸውን መከታተል የሚያስችላቸው ሁኔታና ንቃተ ህሊናው የዳበረ ማህበረሰብ ያለበት ከባቢ መፍጠር ተመራጭ ነው። ልማዳዊ ፍረጃው በከፋበትና በቂና ተገቢ አገልግሎት መስጪያዎች እንዲሁም የሰለጠኑ ባለሙያዎች በሌሉበት ሁኔታ የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ት/ቤቶችንና የወላጅ አልባ ህፃናት ማዕከላትን መዝጋት እንደማይገባ ብርሃኔ ታስጠነቅቃለች። ድህነት የአካል ጉዳተኞችን ፈተና አክብዶባቸዋል። አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ የህክምና፣ የማገገምያና የትምህርት ድጋፎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ፈተና ሆነው የሚጋረጡባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አሌ የሚባል አይደለም። ለምሳሌ እርግዝና፣ የታክሲዎች አመቺነት፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የመሳሰሉት። ነገር ግን ህብረተሰቡ እነዚህን ነገሮች ጨርሶ የማይወጡ ተራሮች አድርጎ በመሳል የበለጠ ያከብደዋል። ብርሃኔ ግን ነገሮች ሰዎች እንደሚሉት ጨርሶ የማይቻሉ አይደሉም – ትላለች። እሷ ለምሳሌ ቤቷን በቅጡ ታስተዳድራለች፤ ዋና ዋና የሚባሉትን የቤት ውስጥ ስራዎችን ታከናውናለች – ልብስ ማጠብና እንጀራ መጋገር የመሳሰሉትን ። የተለያየ የአካል ጉዳት ላሉባቸው ከ800 በላይ የማህበሩ አባላትም ነገሩ ተመሳሳይ ነው።
ብርሃኔ፤ በማህበሩ ስራዎች አማካኝነት በጭለማ ውስጥ ተጋርደው ለነበሩ ወገኖች የብርሃን ተስፋ መፈንጠቅ መጀመሩ ያኮራታል። ግን ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉና ይሄን እንደስራው መነሻ እንደምትቆጥረው ትናገራለች። አካል ጉዳተኞች ሌሎች የሚያገኙት እድል እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ፣ እንዲሁም እነሱም እንደሌሎች ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ማህበረሰቡን ለማስተማር እየሰራች ነው። እሷ ራሷ በልጅነቷ የትም አትደርስም ተብላ ተስፋ ተቆርጦባት እንደነበር ታስታውሳለች። የማታ ማታ ግን ከታላቅ ወንድሞቿ የላቀ ስኬት ለመቀዳጀት በቅታለች። ቁርጠኝነቱ ካላችሁና ወኔያችሁ እንዳይሞት ካደረጋችሁ በህይወት ውስጥ ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ማሳካት ትችላላችሁ ትላለች – ብርሃኔ። አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ለማገዝ ለሚፈልጉ ወላጆች ተስፋ መሆን በመቻሏና ሌሎች ችግራቸውን እንዲፈቱ በማገዟ ወደርየለሽ ደስታ ይሰማታል።በማንነቷ ትኮራለች። አካል ጉዳተኝነቷ ፈፅሞ አያሸማቅቃትም፤ በራሷ ደስተኛ ናት። ልበሙሉዋ ብርሃኔ፤ ግልፅና ቀጥተኛ ስትሆን ሁሌም ትኩረቷ ልታሳካው የምትሻው ዓላማዋ ላይ ነው። እነዚህን ባህርያት ያላበሳት ደግሞ ትምህርቷን የተከታተለችበት ሂደት እንደሆነ ትናገራለች። አሁንም ክህሎቷን ለማዳበር የማትቦዝነው ብርሃኔ፤በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማስተርስ ድግሪዋን ለማግኘት ትምህርቷን የመቀጠል ሃሳብ አላት። አሁን ግን በታክሲ እየተመላለሰች ሳይሆን በርቀት ትምህርትመርሃግብር ነው። መርሃግብሩ ለሌሎች በርካታ አካልጉዳተኞችም የተለየ ጠቀሜታ አለው።
ብርሃኔ ለወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – የንባብ ልማድ አዳብሩ፤ ራሳችሁን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አስተዋውቁ። ሴት እንደመሆናችሁ መጠን የማንም ጥገኛ ልትሆኑ አይገባም፤ ራሳችሁን መቻል አለባችሁ። በንባብ ራሳችሁን ልታስተምሩ ይገባል፤ መፅሃፍ ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው። /ብርሃኔ ቤተመፃህፍት የሚጠቀሙ ሴቶች ከወንዶች በእጅጉ ያነሱ እንደሆኑ በስራዋ አጋጣሚዋ አስተውላለች/ ቅድምያ የምትሰጧቸውን ጉዳዮች በግልፅ አስቀምጡ።በማይረቡ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ራሳችሁን በማበልፀግ ላይ አተኩሩ። በራስ መተማመንን አዳብሩ፤ የራሳችሁን ግቦችም ቅረፁ። ትርጉም ያለው ህይወት ይኑራችሁ። ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሁኑ። አንዴ ግባችሁን ከቀረፃችሁ በኋላ በቁርጠኝነት ለማሳካት ትጉ፤ ሌሎች መጥተው ህልማችሁን እንዲያሳኩላችሁ አትጠብቁ። በጓደኛ ምርጫ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ፤ በአካባቢያችሁ ከምታዩት እውነታ ትምህርት ውሰዱ። ዛሬ ዛሬ ብዙ ልጃገረዶች ፊልም ያዩና የዚያን ዓይነት ህይወት መኖር ይሻሉ። ያ ግን ፊልም እንጂ ተጨባጩ እውነታ አይደለም። በህልም ዓለም መኖር እንደማይቻል እወቁ።
ከወ/ሮ የምወድሽ በቀለ ጋር በሚያዝያ 2004
ሰምሃል ኪሮስ