“የኢትዮጵያ ሴቶች ትንሳኤ”፣ በታሪክም ሆነ ዛሬ በዘመናችን፣ ሴቶች አያሌ ስኬቶችን ቢያስመዘግቡም፣ ብዙዎች እንዳላወቁላቸው በመገንዘብ የተጠነሰሰ ፕሮጀክት ነው። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ባለፉት አስር ዓመታት፣ በመላ የአገሪቱ ክልሎች ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር ባከናወናቸው ስራዎች ላይ በግልፅ እንደታየው፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በአርአያነት የሚከተሉ ተማሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በተማሪያዎቹ ዘንድ በአርአያነት የሚታዩ ሴቶች አሉ ከተባለም፤ በአመዛኙ በምዕራብ አገራት ሚዲያ ተዘውትረው የሚታዩ ዝነኞች ብቻ ናቸው።

ለብዙዎቹ የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴቶች፣ ዛሬም እንኳ፣ ትምህርት ቤት መግባትና ትምህርትን ሳያቋርጡ መቀጠል፤ እንዲሁም የጥናት ጊዜ አግኝቶ በትምህርት ስኬታማ መሆን ቀላል ፈተና አይደለም። በተለይ ደግሞ፣ በባህል ከታጠረው ልማዳዊ የኑሮ መስመር ውጭ፣ የህይወት ህልምን ለማሳካት በልበሙሉነትና በቁርጠኝነት ፀንቶ መጓዝ ከባድ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ‘የሴት እጣ ፈንታ ባል አግብታ ልጆች መውለድ ብቻ ነው” በሚል ልማዳዊ አስተሳሰብ ሳቢያ፤ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአቻ ጓደኞች በኩል የሚፈጠረው ጫናም ፋታ የማይሰጥ ነው። እንዲያም ሆኖ፣ በስኬት ጎዳና የሚጓዙ ልጃገረዶች እየተበራከቱ፣ የትልልቅ ስኬቶች ባለቤት እየሆኑ ነው! – በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ልቀው በመሄድ በወጉ ተቀናብሮ የቀረበው መረጃ የበርካታ ሴቶችን ስኬት የሚተርክ ሲሆን፤  ባለታሪኮቹ የተወለዱበትና ያደጉበት ሁኔታ በእጅጉ የሚለያይ፤ በተለያዩ የስራና የሙያ ዘርፎች የተሰማሩና ዓላማቸውን ለማሳካት የገጠማቸው ችግሮች የተለያዩ መሆናቸው እንዲሁም ያገኟቸው ድጋፎች ከተለያዪ አቅጣጫዎች መምጣታቸው መረጃውን የበለጠ ጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ የጀግኖቹ ታሪክ፣ ወጣት ሴቶችን ያነቃቃል፤ ትልልቅ ግቦችን እንዲያልሙና እንደ ጀግኖቹ ሁሉ  እነሱም ህልማቸውን እውን የማድረግ እምነት እንዲያድርባቸው ያደፋፍራቸዋል ብለን እናምናለን፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት ፕሮጀክቱ  የተመራው ለልጃገረዶች የተሻለ የወደፊት ህይወት እውን መሆን ጥልቅ ፍቅር ባላቸው የሴቶች አማካሪ ቡድን ኮሚቴ  ነው፡፡  የመማክርት ቦርዱ አባላት፣በዚህ የታሪክ ስብስብ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ሴቶችን በመለየትና አድራሻቸውን በማፈላለግ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በትጋት ሰርተዋል፡፡ እባክዎት ስማቸውንና አጫጭር የሥራ ታሪካቸውን ለማየት ከ”የኢትዮጵያ ሴቶች ትንሳኤ” ጀርባ የሚለውን ገጽ ይጎብኙ፡፡ ጊዜያቸውን ሰጥተው ጥናት በማካሄድ፣ ቃለምልልስ በማድረግና ወደ ፅሁፍ በመገልበጥ እንዲሁም ታሪኮቹን በአጭር በአጭሩ በማዘጋጀት፣ በሂደቱም ከድንቅ ሴቶች ጋር የተገናኙ በርካታ ተለማማጅ (የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ (አዲስ ምሩቃንና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች) አሉ፡፡  እባክዎት ስማቸውንና አጫጭር የሥራ ታሪካቸውን ለማየት ከ”የኢትዮጵያ ሴቶች ትንሳኤ” ጀርባ የሚለውን ገጽ ይጎብኙ፡፡ ስኬታማ ሴቶችን በመጠቆምና አድራሻቸውን አፈላልጎ በማግኘት ረገድ  ድጋፋቸውን የለገሱን ቸር ተባባሪዎቻችን ደግሞ፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ፣ ህሩይ አረፋዓኔ፣ ወ/ሮ የምስራች በላይነህ እንዲሁም ሪታ እና ሪቻርድ ፓንክረስት ናቸው። የአማርኛውን ትርጉም በመስራት ኢዮብ ካሣ እንዲሁም ድረገጹን በመፍጠርና ዲዛይኑን በመስራት ኢዮስያስ ይፍሩ፣ሻሎም አበበና መልእክተ ጳውሎስ ላሳዩት ድንቅ ተሰጥኦ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ በመጨረሻም በፈቃደኝነት ለቃለምልልስ ውድ ጊዜያቸውን ለሰጡን እንዲሁም አርአያነታቸው ለወጣት ሴቶች እንዲደርስ በማሰብ ታሪካቸው በዚህ ድረገፅ ለህዝብ እንዲወጣ ድፍረት ላሳዩ ስኬታማ ሴቶች ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳቸው።

ፕሮጀክቱ  የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ነው። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም የተመሰረተ አገር በቀል ማህበር ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም በወጣው የበጎ አድራጎትና የማህበራት አዲስ አዋጅ መሰረት በኢትዮጵያዊ ማህበርነት ዳግም ተመዝግቧል፡፡ ዓላማውም፣ ለሴቶች መብት መሟገት፣ ሴቶች ለአመራር ቦታ እንዲበቁ ድጋፍ መስጠትና በህብረተሰቡ ውስጥ የሴቶች እኩል ተሳትፎ እንዲረጋገጥ መስራት ነው። ስራችንን አይተው ከተደሰቱ፤ በበጎ ፈደኝነትም ሆነ በለጋሽነት ድጋፍዎን እንዲያበረክቱልን የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እየጠየቀ፣ ከወዲሁ ለድጋፍዎ ወደር የለሽ ምስጋናውን ያቀርባል። ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት የበለጠ መረጃ ለማግኘትና ድጋፍ መስጠት የሚችሉበትን መንገድ ለማወቅ ከፈለጉ እባክዎ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡ መቀመጫውን በጀርመን በርሊን ያደረገው ሄንሪች ቦል ፋውንዴሽን፣ የሥነ ምህዳር እውቀትንና ዘላቂ የሥነ ምህዳር አጠባበቅን፣ ዲሞክራሲንና ሰብዓዊ መብቶችን፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰንንና ፍትህን ለማስፋፋት የሚሰራ ድርጅት ነው። ሄንሪች ቦል ፋውንዴሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲና በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሰሩ ሲቪል ማህበራት እርስ በርስ የሚፈጥሩትን ትስስር ለማገዝ ድጋፍ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እና ሄንሪች ቦል ፋውንዴሽን፣ በዚህ ድረገፅ የሰፈሩትን መረጃዎች በስፋት እንድትጠቀሙ ያበረታታሉ። “የኢትዮጵያ ሴቶች ትንሳኤ” ድረገፅን በምንጭነት እስከጠቀሳችሁ ድረስ፤ ባሻችሁ ጊዜ መረጃዎቹን ገልብጣችሁ መውሰድና መጠቀም እንዲሁም ሳይነካኩ አባዝታችሁ ማሰራጨት ትችላላችሁ።

Posted on October 2, 2014 By admin