አይዳ ሙሉነህ

አይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ ባለሙያና ፊልም ሰሪ ስትሆን የሽልማት አሸናፊ የሆነላት ሥራዋ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታይቶላታል፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ ፎቶ ፌስት የተሰኘው የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ ፌስቲቫል መሥራችና ዳይሬክተር ናት፡፡ ማሊ ባማኮ ውስጥ RencontresAfricaines de la Photographie በሚል በተካሄደው ውድድር የ1999 የአውሮፓ ህብረት ሽልማት አሸናፊ ስትሆን በጣልያን ስፒሊምቤርጎ በ2002 የተካሄደው የCRAF ዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊም ናት፡፡

አዜብ ግርማይ

አዜብ ግርማይ በአካባቢ ጥበቃ አድቮኬሲና ፖሊሲ ላይ የምትሰራ አማካሪ ናት፡፡ የENDA ኢትዮጵያ የቀድሞ  ዳይሬክተርስትሆን ENDA ዘላቂነት ያለው የኑሮ መተዳደርያ ለመፍጠር የማህበረሰብ እንቅስቃሴዎችን በማነሳሳትና በማጎልበት መርሃ ግብሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ መቀመጫውን በአፍሪካ ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ አድቮኬሲና ፖሊሲ ድርጅት ነው፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት በአብዛኛው መንግስታዊ ባልሆነ ዘርፍ በአካባቢ ጥበቃ አድቮኬሲ ዙርያ አተኩራ ስትተጋ ቆይታለች፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ዋና ዋና ችግሮችንና ተግዳሮቶችን መፍታት ማለት የአፍሪካ ሴቶችንም ዋና ዋና ጥያቄዎች መፍታት ነው ብላ ታምናለች፡፡

ብዙአለም ገበዬ

የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር የሆነችው ብዙአለም ገበዬ፤ አሁን ማህበሩን ለሁለተኛ ዙር እያገለገለች ሲሆን  በመጀመርያ ዙር የሊቀመንበርነት ዘመኗ ማህበሩ  በሴቶች ዙሪያ ያደረጋቸውን የተለያዩ ጥረቶች በማገዝ ከፍተኛበጎ ለውጦችን እንዲያስመዘግብ አድርጋለች፡፡ ከእነዚህም መካከል ለሴት ነጋዴዎች ድጋፍ መስጠት፣ በእናቶች ጤናና በሴቶች የሥነተዋልዶ ጤና ክብካቤ እንዲሁም ሴቶች ከጥቃት ነፃ የሆነ ህይወት የመምራት  መብት እንዳላቸው የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ በልጃገረዶች ትምህርት ተደራሽነትና የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በተመለከተ የተገኙ ለውጦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ከ154 ሺ በላይ ሴቶች አባላት ያሉት ሲሆን 6ሺ600 ወንዶች አባላትም አሉት፡፡ በጎንደር የተወለደችው ብዙአለም፤ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበርን መምራት ከመጀመሯ በፊት ለ14 ዓመታት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በሂሳብ ባለሙያነት ሰርታለች፡፡

ቻቺ ታደሰ

ዘፋኝ፣ሞዴልና በጎ አድራጊ የሆነችው ቻቺ ታደሰ፤ ኢትዮጵያዊ መሰረቷን ሙያዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመገንባት ተጠቅማበታለች፡፡የሬጌን የሙዚቃ ስልት ከአማርኛ ጋር አዋህዳ በማቀንቀን ከመጀመርያዎቹ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች አንዷ እንደሆነች የምትታወቀው  ቻቺ፤ የራሷን  የሙዚቃ ዘይቤ በተሳካ ሁኔታ ፈጥራለች፡፡ በዘፋኝነት የተቀዳጀችውን ከፍተኛ ዝናና ስም በኢትዮጵያ ስላሉ የጎዳና ህፃናትግንዛቤ ለመፍጠርና ለህፃናት መብትለመሟገት ተጠቅማበታለች፡፡ ህልሟ ለአፍሪካ ህፃናት ደህንነት መትጋት ሲሆን በሚሊዮንየሚቆጠሩ ህፃናትንና ወላጆቻቸውን በሙዚቃ፣በሚዲያና በትምህርታዊ መሳሪያዎች  ለማስተማርም ታልማለች፡፡

እሌኒ መኩሪያ

በኢትዮጵያ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነትን በፈር ቀዳጅነት ከጀመሩ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች አንዷ የሆነችው እሌኒ መኩሪያ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት የመጀመርያዋ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮግራም አቅራቢ ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምሥረታ የመጀመርያ ዓመታትም በአስተዋዋቂነት፣በፕሮግራም አዘጋጅነት፣በአቅራቢነት፣በዜና አንባቢነት እና በፊልም ክፍል ሃላፊነት የሰራች የመጀመርያዋ ሴት ጋዜጠኛ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ሚዲያ ማህበር መስራች የሆነችው እሌኒ፤ በጡረታ ዘመኗም በሴቶች መብት ተሟጋችነቷና በደራሲነቷ ገፍታበታለች፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የበርካታ ኦሪጂናል መረጃዎች ምንጭ በመሆንና አድናቆት የተቸራት ኤዲተር ሆና ያገለገለች ሲሆን የፕሮጀክቱ ገንዘብ አሰባሳቢ አጋርም ነበረች፡፡

እመቤት ከበደ

የህግ ባለሙያዋ እመቤት ከበደ፤ለሴቶች መብት በመታገል የብዙ ዓመታት ልምድ ያላት  ናት፡፡ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከለጋሽ ተቋማት ጋር በሥርዓተ ፆታና በፍትህ ጉዳዮች ላይ ለበርካታ ዓመታት ሰርታለች፡፡ በመንግስት ዘርፍ ማሻሻያ በተለይ በፍትህ ሰፊ ልምድ አላት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡

ሂሩት በፈቃዱ

ዓለም አቀፍ የመንግስት ሠራተኛ በመሆን ከ40 ዓመት በላይ ያገለገለችው ሂሩት በፈቃዱ፤ አሁን የማህበረሰብ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ፣ መንፈስ አነቃቂ ንግግር አድራጊና  የሴቶች መብትና ጤና ተሟጋች  ናት፡፡ በአፍሪካ ህብረት የሴቶች ዘርፍ ሃላፊሆና ባገለገለችበት የሥራ  ዘመኗ  ከዚያም በሴራሊዮን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ቡድን አባል ሆና ስትሰራ ለሴቶች መብትና እኩልነት መከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሟግታለች፡፡ በ1987 ዓ.ም ለቤጂንጉ የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉባኤ፣ የአፍሪካን የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት በመላው አፍሪካ ከሚገኙሴቶች ሃሳቦችን በማሰባሰብ ያደረገችው ተሳትፎ በረዥም ዘመን ሙያዋ ከሚጠቀሱላት ስኬቶቿ አንዱ ነው፡፡ ሂሩት በዚህ ፕሮጀክት ላይ አድናቆት የተቸራት ኤዲተር በመሆን አገልግላለች፡፡

ዶ/ር ሂሩት ተረፈ ገመዳ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ የሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰሯ የሆነችው ዶ/ር ሂሩት ተረፈ ገመዳ፤ በዩኒቨርስቲ ውስጥ በማስተማር ከ32 ዓመታት በላይ ልምድ አካብታለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ፆታ ጥናቶች ተቋም ዳይሬክተር ሆናም ከየካቲት 2002 እስከ ታህሳስ 2003 ዓ.ም አገልግላለች፡፡ በርካታ የጥናት ፅሁፎቿንም ለህትመት አብቅታለች፡፡

ቆንጂት ሥዩም

 ቆንጂት ስዩም በ1955 ዓ.ም ነው በአዲስ አበባ የተወለደችው፡፡ በጣልያን አገር ትሪስቴ (Trieste) ዩኒቨርስቲ በስኩል ኦፍ ኢንተርፕቴሽን ኤንድ ትራንስሌሽን በተርጓሚነት ሰልጥናለች፡፡ በ1988 ዓ.ም አስኒ ጋለሪን ከፈተች – የሙከራ ስራዎች ላይ በማተኮር ዘመነኛ የኢትዮጵያ ሥዕሎችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ወጣትና አዳዲስ አርቲስቶችን ለማበረታታት በማለም፡፡ በርካታ የግልና የቡድን የስዕል አውደርዕዮችን ያሰናዳችው ቆንጂት፤ውይይቶችን፣ ዎርክሾፖችን፣ሰዓሊያን በምቹ ድባብ ውስጥ ሆነው ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑበት ከባቢ በመፍጠር እና የህፃናት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ትታወቃለች፡፡የራሷ የቆንጂት የሥነጥበብ ስራዎች መጀመርያ ላይ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚፈትሹና  ኢንስታሌሽን ተብሎ በሚታወቀው የአሰራር ዘዬ የተቃኙ ነበሩ፡፡ የቅርብ ጊዜ ሥራዎቿ ግን ሴትነትን፣ ፆታዊነትን፣ ግላዊና መንፈሳዊ ህይወትን በጥልቀት የፈተሸችበትና የጥጥ ፈትልን ከቀለም አልባ የፎቶግራፍ ጥበብ ጋር አዋህዳ ያቀረበችባቸው ናቸው፡፡ ቆንጂት በጋለሪዋ ውስጥ በኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ መነሻነት በፈጠረቻቸው አዲስ የምግብ አዘገጃጀቶች ለአትክልት ተመጋቢዎች የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች እያሰናዳች ታቀርባለች፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ቆንጂት፤ በጉባኤ አስተርጓሚነት በግሏ መስራቷን ቀጥላለች፡፡

ሜሪ-ጄን ዋግል

በጡረታ ላይ የምትገኘው  ሜሪ-ጄን ዋግል፤ በጎ ፈቃደኛና የሴቶች መብት ተሟጋች  ስትሆን ኢትዮጵያን መጎብኘትና ስለአደናቂ እንስቶቿ ማወቅ የጀመረችው በመጋቢት 2003 ዓ.ም ነበር፡፡ በከተማ ፕላን ቀያሽነት የሰለጠነችው ሜሪ-ጄን ዋግል፤ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቷ በፊት በአሜሪካ በኢኮኖሚና ህብረተሰብ ልማት፣ በከፍተኛ የቤቶች ልማት፣በዝቅተኛ ገቢ የቤቶች ልማት እንዲሁም በሴቶች የሥነተዋልዶ ጤና ክብካቤ አገልግሎትና አድቮኬሲ ዘርፎች ሰርታለች፡፡

ንግስት ኃይሌ

ንግስት ኃይሌ የሴንተር ፎር አፍሪካን ውመን ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት መስራችና ዋና ዳይሬክተር ስትሆን ድርጅቱ የሴቶችን የንግድ ሥራ ፈጠራ ለማሳደግ የሚሰራ ነው-ኤክስፖርትን በማሳደግ እንዲሁም በአምራችና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ላይ በማነጣጠር፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የሴቶች ባንክ የሆነው እናት ባንክ መሥራች አባል ስትሆን በአሁኑ ወቅት በቦርድ አባልነት ታገለግላለች፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመምሪያ ሃላፊ ነበረች፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ለማሳደግ የምትተጋው ንግስት፤ በክልልና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአያሌ ቦርዶችና የዳኞች ቡድን ውስጥ በንቃት ትሳተፋለች፡፡ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴቶችና ከዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት የ2004 ፓን-አፍሪካን ሽልማት ተቀባይ ስትሆን በካናዳ የዓለም አቀፍ ሴቶች አጋርነት የ2004 TIAW ሽልማትም አሸናፊ ናት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአሜሪካ መንግስት የተሸለመች ሲሆን ሁሉንም ሽልማቶች ያገኘችው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበትና በሴቶች የሚመሩ ቢዝነሶችን ለማሳደግ ባከናወነቻቸው ሥራዎች ነው፡፡ ንግስት የግንኙነት መረቧን በመጠቀም ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

ናሁሰናይ ግርማ

በአሜሪካ በግሉ ዘርፍ ለትርፍ ባልተቋቋመ ዘርፍና በምክር አገልግሎት ስትሰራ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ናሁሰናይ ግርማ፤እዚህም ለኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት የቢዝነስ ማስፋፊያ አገልግሎቶች የሚሰጥ ኦፕቲማ ኮንሰልተንሲ ኤንድ ማርኬቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተሰኘ ድርጅት አቋቁማ ትመራለች፡፡ ለግልና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአመራር ክህሎት ስልጠና ፕሮግራሞችን የምታዘጋጅ ሲሆን ለአነስተኛ ሴት  ነጋዴዎች ምክርና ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ የሴት ነጋዴዎች ማህበር መስራች ስትሆን የቅርብ ጊዜ የማህበሩ ፕሬዚዳንትም ነበረች፡፡ ናሁ ለዚህ ፕሮጀክት ግሩም ቃለመጠይቅ አድራጊ በመሆን አገልግላለች፡፡

ኦሪጂናል ወልደጊዮርጊስ

የህግ ባለሙያዋ  ኦሪጂናል ወልደጊዮርጊስ፤የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ለበርካታ አመታት አገልግላለች፡፡በ1987 ዓ.ምከሌሎች ሴት የሙያ ባልደረቦቿ ጋር ሆና የሴቶችን መብት በሁሉም ዘርፎች ለማሻሻል ያለመውን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስርታለች፡፡ ኦርጂናል በሁሉም የማህበሩ ሥራዎች የተሳተፈች ሲሆን ከእነዚህም መካከል በህግ ድጋፍና አቅም የሌላቸውን ሴቶች በፍርድ ቤት በመወከል እንዲሁም በስነተዋልዶ መብቶች፣ በፆታ ተኮር ጥቃት፣ በፖለቲካዊ ተሳትፎ፣በውሳኔ ሰጪነትና በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙርያ ቅስቀሳና የምርምርና ሥልጠና ስራዎች ይገኙበታል፡፡ በወታደራዊው የደርግ መንግስት ለእስር የተዳረገችው ኦሪጂናል፤ ለሴቶችና ለተጨቆኑ ወገኖች ደፋር ተሟጋች ናት፡፡

ሳባ ገብረመድህን

ሳባ ገብረመድህን ላለፉት ስምንት አመታት የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ያገለገለች ሲሆን በእነዚህ ጊዜያትም በልማትና የሴቶችን መብት በማስከበር፣ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ለአባል ድርጅቶች የድጋፍ ገንዘብ በማፈላለግ እና ለሴቶች መብት የሚደረጉ የህብረተሰብ እንቅስቃሴዎችንና ዘመቻዎችን በመምራት ተግታለች፡፡ የህግ ባለሙያ የሆነችው ሳባ፤ ቀደም ሲል በረዳት ዳኝነት እንዲሁም በልዩ አቃቤያን ቢሮ በልዩ አቃቤ ህግነትና በረዳት ዋና አቃቤ ህግነት አገልግላለች፡፡

ሳባ ኪዳነማርያም ገብሩ

ሳባ ኪዳነማርያም ገብሩ የIpas ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናት፡፡ Ipas አስተማማኝ የፅንስ መቋረጥን ጨምሮ የተሟላ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለመላው ዓለም ሴቶች ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግ የሚሰራ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተሻሻለ የሥነተዋልዶ ጤና ህግ እንዲወጣ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ስትመራ ቆይታለች፡፡ ሳባ የዚህም ፕሮጀክት ደጋፊ ስትሆን የሴቶችን ታሪክ የመሰነዱን ጥረት ለዋና ዋና ድጋፍ ሰጪዎች በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡

 ያሬድ ፈቃደ

ያሬድ ፈቃደ በኢትዮጵያ ካናዳ የትብብር ቢሮ በግል ዘርፍ አማካሪነት እየሰራ ይገኛል፡፡ አቶ ያሬድ በአነስተኛ ንግድና በግል የልማት ዘርፎች የ22 ዓመት ልምድ ያለው ሲሆን በእሴት መጨመር፣ በአነስተኛ የገንዘብ ድጋፍና በሴቶች የንግድ ፈጠራ ልማት የዳበረ ሙያ ባለቤት ነው፡፡ በኢኮኖሚክስና በቢዝነስ ድግሪ ያለው ሲሆን የኢትዮጵያ አነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ልማት ስትራቴጂን በመቅረጽ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

የምወድሽ በቀለ

የምወድሽ በቀለ የግጥም፣ የአጭር ልብወለዶች መድበልና ኖቬላን ጨምሮ ሰባት መፃህፍትን ያሳተመች ደራሲ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ሊቀመንበር ሆና  እያገለገለች ትገኛለች፡፡ በኢትዮጵያ የበርካታ ገጣምያን – ወንዶችም ሴቶችም – የመንፈስ እናት በመሆን የምትታወቅ ሲሆን የእርሷም ሆነ የሌሎች ሥራዎች በአዲስ አበባ በርካታ የግጥም መድረኮች ላይ እንዲቀርብ አድርጋለች፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋዜጣ የነበረው ፖሊስና እርምጃው አዘጋጅ ነበረች፡፡የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ቦርድን ሊቀመንበር ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡

 ዶ/ር የትናየት አስፋው

 ዶ/ር የትናየት አስፋው የሴቶች  የቤተሰብ ምጣኔ፣ ኤችአይቪ/ኤድስ  እንዲሁም ሌሎች የእናቶችና የሥነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ጥራት እንዲሻሻል በመሥራት ከ15 ዓመት በላይ ልምድ ያላት ሃኪምና የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢንጀንደር ኸልዝ የኢትዮጵያ ቢሮ ተጠሪ ዳይሬክተር በመሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ዶ/ር የትናየት ሴቶች ልዩ ፍላጎቶቻቸውን ያሟላና ጥራቱን የጠበቀ የሥነተዋልዶ ጤና እንክብካቤ አገልግሎት የማግኘት መብታቸው እንዲከበርላቸው በፅናት በመሟገት ትታወቃለች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣት ሴቶችን በማማከር ንቁ ተሳታፊ ናት፡፡

 

Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>