Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ገነት ገብረ ክርስቶስ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ከእድገት በህብረት ዘመቻ አምስት አንጋፋ የወንድ መሪዎች ውስጥ ብቸኛዋ ሴት አባል ናት፤ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ውስጥ ለ27 ዓመታት አገልግላለች፣ እዚያ ሳለች የመጀመርያቱ ኢትዮጵያዊት ሴት የአገር ተወካይ ሆናለች፣ በአሜሪካና በካሪቢያን የኮሚሽኑ የክልል ተወካይ በመሆን የመጀመርያዋ ጥቁር ናት፣ በፓኪስታን የኮሚሽኑ ተወካይ ሆና በመሾም የመጀመርያዋ ሴት ብቻ ሳትሆን የመጀመርያዋ ጥቁርም ለመሆን በቅታለች፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ ጡረታ የወጣች  የማህበረሰብ በጎፈቃድ አገልጋይ ፤የምዕራብ አዲስ አበባ ሮታሪ ክለብ የድጋፍ አገልግሎት ፕሮጀክት ሊቀመንበር
የትውልድ ቦታ: አስመራ
የትውልድ ዘመን: መስከረም 21 ቀን 1941 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ እና ዋሺንግተን ዲሲ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሊሴ  ገብረማርያም- ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ሊሴ  ገብረማርያም- ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመርያ ድግሪ /ቢኤ/ ፣ በሶስዮሎጂ፣ ሴንትራል ስቴት ዩኒቨርስቲ፣ ዊልበርፎርስ፣ ኦሃዮ፣  ዩኤስኤ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ሁለተኛ ድግሪ /ኤምኤ/፣ በኮሙኒኬሽን ፎር ሶሻል ዴቬሎፕመንት፣ ቺካጎ ዩኒቨርስቲ፣ ቺካጎ፣ ኢሊኖይስ፣ ዩኤስኤ፤ ተጨማሪ የምስክር ወረቀት፣ በስነ ህዝብ ጥናት፣ ቺካጎ ዩኒቨርስቲ፣ አይኤልኦ እና በሴቶች ጥቃት አያያዝ፣  ቦስተን፣  ዩኤስኤ
ዋና የስራ ዘርፍ
ዓለም አቀፍ ጉዳዮች – ሰብዓዊ አገልግሎት – ስደተኞች – በአገራቸው የተፈናቀሉ እና አገር አልባ ሰዎች
የሕይወት ታሪክ
በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ውስጥ በዓለም አቀፍ ኦፊሰርነት ያገለገለችው ገነት ገብረክርስቶስ፤ በመላው ዓለም ለሚገኙ ስደተኞች፣እንዲሁም በአገራቸው ለተፈናቀሉና አገር አልባ ለሆኑ ሰዎች ደህንነት ሳታሰልስ በትጋት ሰርታለች፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ ባገለገለችባቸው 27 ዓመታት  ከማህበራዊ አገልግሎት ኦፊሰርነት እስከ የአገር/ አህጉር ተወካይነት ለመድረስ በቅታለች፡፡ ምንም እንኳን ከመደበኛ ሥራዋ በጡረታ ብትገለልም፣አሁንም ችግረኞችን ከመርዳት አልታቀበችም፡፡ የምዕራብ አዲስ አበባ ሮታሪ ክለብ፣  የድጋፍ አገልግሎት ፕሮጀክት ሊቀመንበር በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡

አምስት ልጆችን ላፈሩት ወላጆቿ ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ገነት፤መስከረም 21 ቀን 1941 ዓ.ም አስመራ ነው የተወለደችው፡፡ ወላጆቿ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር፡፡ ገነት ያደገችው አቃፊ ደጋፊ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡ በሁለቱም ወላጆቿ በኩል የታደለች ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ አባቷ ለልጆቻቸው ሁሉ ትልቅ ትልቁን የሚያልሙና በትምህርት አስፈላጊነት ላይ ጽኑ እምነት የነበራቸው ናቸው፡፡ እናቷ ደግሞ አይዞሽ ባይ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ገነት ባደገችበት ማህበረሰብ ውስጥ ሌሎችን የመርዳት መንፈስ ጠንካራ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በአባቷ ማህበረሰብ ዘንድ የሚታወቁት ሚሲዮናውያን ጥንዶች ስላከናወኑት ስራ በሰማችው ታሪክ መንፈሷ መነቃቃቱንም አትዘነጋም፡፡ በተለይ የበርካታ ሴቶችን ነፍስ የታደገችው ሚሲዮናዊት አዋላጅ ታሪክ  ልቧን ነክቷታል፡፡ ለነገሩ በራሷ ቤተሰብም ተመሳሳይ ታሪክ ሰምታለች፡፡ የአባቷ ሴት አያት /ቅድመ አያቷ/ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የስዊዲን ሚሲዮናዊያን ጋር የሰሩ  ሚሲዮናዊት ነበሩ፡፡

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ ሊሴ ገብረ-ማርያም ት/ቤት ያጠናቀቀችው ገነት፤ሀ ብላ ወደ ስራ ዓለም የገባችው በአውሮፕላን አስተናጋጅነት (ሆስቴስነት) ነበር፡፡ ከአስራ ስምንት ወራት በኋላ ግን ስራውን ትታ ወደ ትምህርት ዓለም ተመለሰች፡፡ በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት፣ሴንትራል ስቴት ዩኒቨርስቲ በመግባትም  በሶስዮሎጂ የመጀመሪያ ድግሪዋን አገኘች፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ፣ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ (ያሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ውስጥ  መጀመሪያ በሶስዮሎጂ ረዳት መምህርነት፣ በኋላም በመምህርነት ሰርታለች፡፡

በዩኒቨርስቲ ሳለች ነበር የደርግ መንግስት የዕድገት በህብረት ዘመቻን ያወጀው፡፡ ያኔ ዩኒቨርስቲው ተዘግቶ ሁሉም ተማሪዎችና መምህራን ወደ ገጠር እንዲዘምቱ ታዘዙ፡፡ ከዘመቻው አምስት መሪዎች ብቸኛዋ ሴት መሪ ሆና የተሾመችው ገነት፤ሴት ዘማቾችን ከመምራቷም በተጨማሪ፣ብሔራዊ ፕሮግራሙን ያዘጋጀውና  የቀረፀው አንጋፋ ቡድን አባልም ሆና ሰርታለች፡፡ ዘመቻው ለሴቶችና ለልጃገረዶች ዓይን ገላጭ እንደነበር የምትናገረው ገነት፤የኢትዮጵያን ሴቶች ነፃ ለማውጣት መንገድ እንደጠረገ ታምናለች፡፡ ከአገሯ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት እንድትተዋወቅም እድል ሰጥቷታል፡፡  የተፈጥሮ ከባቢውን ብዝሃነትና ብልፅግና  ብቻ ሳይሆን የህዝቡንም ብዝሃነትና የበለፀገ የባህል ሃብት ተመልክታለች፡፡  ዘመቻው ሲጠናቀቅ ወደ ዩኒቨርስቲ የማስተማር ስራዋ ተመለሰች፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ1969 ዓ.ም መገባደጃ ላይ የቀይሽብር ዘመቻ በመጀመሩ፣ ትምህርቷን ለመቀጠል ወደ አሜሪካ አቀናች፡፡

ከቺካጐ ዩኒቨርስቲ በኮሙኒኬሽን ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት ሁለተኛ ድግሪዋን የተቀበለችው ገነት፤ከዚያው ዩኒቨርስቲ በሥነ ህዝብ ትምህርት ሰርተፊኬት አግኝታለች፡፡ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ እዚያው አሜሪካ በመቅረት፣ በቦስተን ማሳቹሴትስ ግዛት የማህበራዊ አገልግሎት መምሪያ ውስጥ ጥቃት ለደረሰባቸው ህፃናትና የድብደባ ተጐጂ ሴቶች ድጋፍ በመስጠት ለሁለት ዓመት ሰራች፡፡ እዚያ ያገኘችው ተመክሮ የህፃናት ጥቃትና የሴቶች ድብደባ በድሃ ማህበረሰብ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ባህል፣ዘርና መደብ ሳይለይ ሁሉንም ህብረተሰብ ውስጥ ያለ መሆኑን አስገነዘባት፡፡ ሥራው ሲበዛ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም እርካታ እንደተጎናፀፈችበት ገነት ትናገራለች፡፡ እንዴት ቢሉ  የበርካታ ህፃናትና ሴቶችን ህይወት ለመታደግ ችላለችና፡፡

የገነት የህይወት ጥሪ በጎ መስራት ሲሆን ለሰዎች ምርጥ ሰብዓዊና ሙያዊ እሴቶችን ታጋራለች። የቦስተንን የሁለት ዓመት አገልግሎት ካጠናቀቀች በኋላ፣ ይበልጥ ትርጉም ያለው  አስተዋጽኦ ለማበርከት በሦስተኛው ዓለም አገራት መስራት እንዳለባት ወሰነች፡፡ እናም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን (UNHCR) ተቀላቀለች፡፡ የማህበራዊ አገልግሎት ኦፊሰር በመሆን በጀማሪነት ነበር በኮንጐ ኪንሻሳ ሥራ የጀመረችው፡፡ መቀመጫዋ ኮንጎ ኪንሻሳ ይሁን እንጂ ስራዋ ግን በአጠቃላይ ዘጠኝ የማዕከላዊ አፍሪካ አገራትን ያካልላል – ካሜሩን፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጐ ብራዛቪል፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒና ቻድ፡፡ ከዚያም ወደ ዳካር ሴኔጋል ተዛወረች፡፡ መቀመጫዋን ዳካር አድርጋ ደግሞ አስራ ስድስት የምዕራብ አፍሪካ አገራትን አካላለች – ሴኔጋል፣ ሞሪታንያ፣ ጊኒ ኮናክሪ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያ ሴራሊዮን፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ናይጀርያ፣ ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር እና ኬፕ-ቨርዲ፡፡

የአፍሪካ አገራት የሥራ ሃላፊነቷን ከተወጣች በኋላ ነው ከፍተኛ የማህበራዊ አገልግሎት መኮንንነት ዕድገት አግኝታ በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በጄኔቫ ስዊዘርላንድ መስራት የጀመረችው፡፡ በዚህ ጊዜ ስራዋ ዓለምአቀፍ ክልሎችን የሚሸፍን ሆነ፡፡ ይሄኔ ነው በስደተኞች አያያዝ ላይ የነበረውን ልዩነት፣ የሚሰጣቸውን ድጋፍ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የነበሩ  ስደተኞች ምን ዓይነት እርዳታዎችና አገልግሎቶች እንደሚያገኙ የተመለከተችው፡፡ ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ የክልሉን እንቅስቃሴ በሚመራው የኮሚሽኑ ሠራተኛ የአስተሳሰብ ሁኔታ ላይ  የተመረኮዘ እንደሆነ ተገነዘበች፡፡ በኬንያ የኮሚሽኑ የአገሪቱ ምክትል ተወካይ ሆና ስትሾም የሶማሊያ፣የኢትዮጵያና የሱዳን ስደተኞች ወደ አገሪቱ በገፍ እየጎረፉ ነበር፡፡ ገነት በዚህ ጊዜ ነበር የአፍሪካ ስደተኞች የተሻለ አያያዝና ድጋፍ እንዲያገኙ ሽንጧን ገትራ የተሟገተችውና  የታገለችው፡፡

ከዚያም እድገት በማግኘት በቤኒንና በናይጀርያ እንዲሁም ከእርስበርስ እልቂቱ በኋላ በሩዋንዳ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይ ሆነች፡፡ ከሩዋንዳ ቀጥሎ የተሰጣት እድገት ወደአሜሪካ ወሰዳት – በዋሺንግተን ዲሲ የአሜሪካና ካሪቢያን አገራት ክልላዊ ተወካይ በመሆን አገለገለች፡፡ በመጨረሻም በፓኪስታን የኮሚሽኑ ተወካይ በመሆን ከድርጅቱ ጋር ያሳለፈችውን የ27 ዓመታት የሙያ ዘመን ቋጨች፡፡

በአምስት ዓመት ተኩል የፓኪስታን የስራ ኃላፊነቷ ከባድ ፈተናዎችና ትልቅ ስኬት አስተናግዳለች፡፡ የፓኪስታን ተወካይ ሆና ስትሾም ቅሬታዎችና አለመስማማቶች ቢኖሩም የፓኪስታኑን ቡድን  ለመምራት የተሾመች የመጀመርያዋ ሴትና አፍሪካዊት ኦፊሰር  ሆናለች፡፡ አገሪቱ ለኮሚሽኑ ፈተና ያልሆነችበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ከአገራቸው ተሰደው ፓኪስታን የገቡ የአፍጋኒስታን ተወላጆችን በአንድ ወር ውስጥ ለማስወጣት የተቀመጠው እቅድ  ከፈተናዎቿ የመጀመርያውና ትልቁ ነበር፡፡ ይኼኔ ነው የገነት የድርድር ችሎታ የሚመጣው፡፡ ከፓኪስታን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ጋር ተደራድራ፣ ከሁለቱም ወገን የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቋመች – የስደተኞችን ጉዳዮች የሚመረምርና የመፍትኼ ሃሳብ የሚጠቁም፡፡ በስራዋ ላይ ሁለት ዓመት ያህል እንደቆየች ነው ፓኪስታንን ምድረ በዳ ያስመሰላት አደገኛ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው፡፡ አደጋው ያስከተለው ጥፋት ከአቅሙ በላይ የሆነበት የፓኪስታን መንግስት፤ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽኑ እንዲታደገው ጥያቄ አቀረበ፡፡ ኮሚሽኑ ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተ ማግስት ባሉ ጉዳዮች ላይ ምንም የማድረግ ስልጣን አልነበረውም፡፡ ሆኖም ገነት እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም ፤ ከኮሚሽኑ ዋና መ/ቤት ጋር በመደራደር ልዩ የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ ለማሰባሰብ ፈቃድ አገኘች፡፡ እናም ቢሮዋ በፓኪስታን የሚሰሩ ኤምባሲዎችንና ዓለምአቀፍ ተቋማትን አስተባብሮ ፣ ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ  ለአደጋው ሰለባዎች ትርጉም ያለው ድጋፍ መስጠት ቻለ፡፡ በዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የተነሳ የፓኪስታን መንግስት የስደት ጉዳዮችን የሚፈታበት መንገድ አቻቻይና እንደሁኔታው የሚለዋወጥ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ገነትና የአመራር ቡድኗ፣ ቀሪዎቹ 2 ሚሊዮን የአፍጋን ዜጎች ጉዳይ በአዲስ መንገድ እንዲስተናገድ  ከመንግስት ጋር ተደራደሩ፡፡ እናም የአፍጋኒስታን ዜጎች ከ30 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ተመዝግበውና ፋይል ተከፍቶላቸው ትክክለኛ መታወቂያ ተሰጣቸው – በአፍጋኒስታን ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ በፓኪስታን እንዲቀመጡ የሚያስችላቸው፡፡

የስራ ጊዜዋን ከፓኪስታን ስታጠናቅቅ የተለያዩ ሽልማቶችን ከተለያዩ መንግስታት አግኝታለች፡፡ የፓኪስታን መንግስት በስራዋ ላበረከተችው አስተዋፅኦ  “Sitara – I – Khidmat” ሜዳልያ ሸልሟታል፡፡ የራሷም ድርጅት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች  ከፍተኛ ኮሚሽን፣ በሙያ ዘመኗ ለስደተኞች ለሰጠችው የላቀ አገልግሎት ሽልማት አበርክቶላታል፡፡ የአሜሪካ መንግስትም እንዲሁ ለስደተኞችና ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላበረከተችው ግሩም አገልግሎት ሽልማትና የምስጋና ሰርተፊኬት ሰጥቷታል፡፡ ከቤኒን መንግስትም ሜዳልያ ተሸልማለች፡፡

በፓኪስታን ትልቁ ፈተናዋ የነበረው አሸባሪዎች በሶስት የስራ ባልደረቦቿ ላይ የፈፀሙት ዓላማቢስ ግድያና በሌላ ባልደረባዋ ላይ የተፈፀመው አፈና ነው፡፡ በእርግጥ እቺ ባልደረባዋ ከስድስት ወር እልህ አስጨራሽ ድርድር በኋላ ተለቃለች፡፡ የገነት ከሰዎች ጋር ትስስር የመፍጠርና የመደራደር ችሎታ ለዚህ ወሳኝ ነበር፡፡ ገነት ይሄንንም እንደ ትልቅ ስኬቷና በረከቷ ትቆጥረዋለች፡፡

ለ27 ዓመታት በዘለቀው የሙያ ዘመኗ ወንዶችና ነጮች በገነኑበት ድርጅት ውስጥ ከጀማሪ ኦፊሰርነት ተነስቶ ከፍተኛ የሃላፊነት ደረጃ ላይ መድረስ ለገነት ቀላል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ታታሪነቷና ጠንካራ የሙያ ክህሎቷ  እንዲሁም እንደአለት የፀኑ እሴቶቿ ክብርን አቀዳጅተዋታል፡፡ የድርድር ችሎታዋ ፣ ሃሳቦችን ለመቀበል ዝግጁነቷና  ከምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አሪፍ ነገር የመፍጠር አቅሟ ለድርጅቱ እንደትልቅ ሃብት የሚቆጠር ነበር፡፡ ገነት የስራ ቡድኗን በማክበርና ለስራቸው ዋጋ በመስጠት ትታወቃለች፡፡ ለተባባሪዎቿም እውቅናና ምስጋና ነፍጋ አታውቅም፡፡ በዚህ ስራዋ ትልቁ ሃብቷ በሌሎች ላይ ለመፍረድ አለመቸኮሏ ነው – ስደተኞች ይሁኑ አጋሮቿ፣ መንግስታት ሆኑ  መንግስታት ያልሆኑ፣ ከመፍረዷ በፊት ራሷን በሌላው ሰው ቦታ አስቀምጣ “እኔ ብሆን ምን አደርግ ነበር” በማለት ጉዳያቸውን ልትረዳላቸው ትሞክር ነበር፡፡

በህይወት ጎዳና ላይ አያሌ ፈተናዎችን ያስተናገደችው ገነት፤ፈፅሞ ተስፋ አትቆርጥም፡፡  ሁሌም ሳታሰልስ ውጤታማ በሆነ መንገድ ከመስራት ቸል ብላ አታውቅም፡፡ ለእሷ መነጫነጭና ማለቃቀስ ትርጉም የለውም፡፡ ትኩረቷ ስደተኞችና ኮሚሽኑ ለህይወታቸው በሚፈነጥቅላቸው ተስፋ ላይ ነው፡፡ በህዝቡን፣በአገራቱና በሚሊዮኖች የሚገመቱ ሰዎች ህይወት ላይ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት በተሰጣት እድል ተደስታበታለች፡፡ የሙያ ዘመኗን ባሳለፈችባቸው ዘጠኝ የተለያዩ አገራት ጓደኞችን አፍርታለች፡፡ ከገጠማት ሁኔታዎች ሁሉ በጎ ነገሮችን መፍጠር ችላለች፡፡ ከመደበኛ ስራዋ በጡረታ ብትገለልም ችግረኞችን ከመርዳት ወደ ኋላ አላለችም፡፡ ገነት የምእራብ አዲስ አበባ የሮታሪ ክለብ የድጋፍ  አገልግሎት ፕሮጀክት ሊቀመንበር ስትሆን በአዲስ አበባ ጎስቋላ አካባቢዎች ባሉ ት/ቤቶች የሚማሩ ችግረኛ ተማሪዎችን ቁርስና ምሳ የመመገብ የሙከራ ፕሮጀክት እያካሄደች ነው፡፡ ዓላማዋ ተማሪዎች ምግብ ሳይበሉ ት/ቤት እንዳይሄዱና በምግብ እጦት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ መደገፍ ሲሆን ለዚህም በጎ አድራጎት በማቋቋም የስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም ለመፍጠር ትሻለች፡፡

ለብዙ ሴቶች የቤተሰብ ህይወትንና ስኬታማ ዓለምአቀፍ ሙያን አጣምሮ ማስኬድ አስቸጋሪ መሆኑን ገነት ትናገራለች፡፡ እሷ ግን ልጇና ባለቤቷ ምስጋና ይግባቸውና ይሄን አሳክታለች፡፡ በሙያ ዘመኗ ሁሉ እሷን በመደገፍ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለውላታል፡፡ ያለ እነሱ ድጋፍና ያለ እግዚአብሔር ፀጋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስራዋ ስኬታማ መሆን አይቻላትም ነበር፡፡

ገነት ለወጣት ሴቶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – ሁልጊዜም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤሊያኖር ሩዝቬልት ያሉትን አስታውሱ“የእናንተ ፈቃድ ሳይጨመርበት ማንም የበታችነት እንዲሰማችሁ ሊያደርግ አይችልም”  መቼም ቢሆን በራሳችሁ እምነት ይደርባችሁ፡፡ ሁሌም ትልልቁን አልሙ፡፡ ህልማችሁን እውን ለማድረግም ተግታችሁ ስሩ፡፡ ፍላጎታችሁን አሳኩ፡፡ በምትሰሩት ሁሉ የላቃችሁ ሁኑ፡፡ ለራሳችሁ ሃቀኛ ልትሆኑ ይገባል፡፡ መሆን የምትሹትን ለመሆን ፈፅሞ ጊዜው አይረፍድም፡፡ የሙያ ህይወታችሁን ስትገነቡ ቤተሰቦቻችሁንና የቅርብ ባልንጀሮቻችሁን አትዘንጉ፡፡ የስራና የቤተሰብ ህይወታችሁን ሚዛን ጠብቃችሁ የመምራት ችሎታችሁን አዳብሩ፡፡ ሴት በኢኮኖሚ ራሷን መቻል እንዳለባት ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ቤተሰብና ማህበራዊ ትስስርም አስፈላጊ ነው፡፡ የፈለገው ቢመጣ ከጎናችሁ የማይጠፉና የሚወዷችሁ ሰዎች እንደሚያስፈልጓችሁ አትዘንጉ፡፡ በእውኑ ዓለም የሚያዋጣው ትብብርና ራስን ከሁኔታዎች ጋር ማጣጣም እንደሆነ እወቁ፡፡ ማንም ቢሆን ሁሌም ትክክል አሊያም ሁሌም ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ በሌላው ሰው ላይ ከመፍረዳችሁ በፊት “እኔ በሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር?” ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ይቅር ባይ ሁኑ – ለጤናችሁና ለአዕምሮአችሁ ሰላም ይበጃችኋል፡፡ ሰዎችን ማክበርና በአክብሮት  መያዝ  ለህይወታችሁ ስኬታማነት ይጠቅማችኋል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ በረከቶቻችሁን ቁጠሩ፡፡ ተመስገን በሉ፡፡ ስኬታችሁንም ለሌሎች አጋሩ፡፡

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከገነት ገ/ክርስቶስ ጋር በሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ሊዲያ ቱጁባ አቶምላ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>