Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ፅጌ ኃይሌ ወልደጊዮርጊስ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ሴቶችን ለአመራር በማብቃት በአፍሪካ ደረጃ የላቀ የሙያ ማዕከል ለመሆን የበቃ “ዋይዝ” የተሰኘተቋም የመሰረተችና በዋና ዳሬክተርነት የምትመራ ናት። በሺ የሚቆጠሩ ችግረኛ ሴቶችና ልጃገረዶችአቅማቸውን አዳብረው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብቃት እንዲጎናፀፉ በማገዝ ረገድ፣ “ዋይዝ”ከቀዳሚዎቹ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም በበርካታ ተቋማት ቦርዶች ውስጥታገለግላለች።
ወቅታዊ ሁኔታ የራስ አገዝ የሴቶት ድርጅት (ራሴድ) ዳሬክተር
የትውልድ ቦታ: ቀጨኔ አካባቢ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ነሐሴ 1944 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
እቴጌ መነን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ተፈሪ መኮንን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ዲፕሎማ፣ በሰክሬታሪያል ሳይንስ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ)፣ በሥራ አመራር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ማስተርስ ዲግሪ (ኤምቢኤ)፣ በቢዝነስ አስተዳደር፣ ኔዘርላንድስ (በፎርድ ፋውንዴሽን ስፖንሰርነት)
ዋና የስራ ዘርፍ
በበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ፣ ለሴቶች የጥቃቅንና አነስተኛ የቢዝነስ ተቋማት ግንባታ
የሕይወት ታሪክ
ችግረኛ ሴቶችና ልጃገረዶች የቢዝነስ ሥራ እየፈጠሩ ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመደገፍ ራስ አገዝ የሴት ጅርጅት (ራሴድ) የተሰኘውን ተቋም በመክፈት በፈርቀዳጅነት የተሰለፈችው ፅጌ ኃይሌ፤ የበርካታ ሺ እህቶቿ ህይወት ሲለወጥ ለማየት በቅታለች። በኢትዮጵያ የሴቶችንና የልጃገረዶችን አቅም በመገንባት፣ ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ  ብቃት የሚያጎናፅፍ ሁሉን አቀፍ ፕሮግራም  በማዘጋጀት ተጠቃሽ የሆነው ራሴድ፤ በሥራና በቢዝነስ ፈጠራ ዙሪያ የላቀ የልማት አገልግሎት ለመስጠት በመቻሉ በአገር ደረጃ ታዋቂ ሆኗል። ከ23 ሺ ሴቶችና ልጃገረዶች የራሳቸውን ቢዝነስና ሥራ በመፍጠር ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ያገዘ በመሆኑም፤ በአፍሪካ ደረጃ የሴቶችን የአመራር ብቃት በማዳበር ረገድ የላቀ የሙያ ማዕከል እንዲሆን በአለማለማቀፍ የትምህርት ተቋም ተመርጧል።
በአዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ ነሐሴ 1944 ዓ.ም የተወለደችውና ለወላጆቿ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ፅጌ፣ እንደ ልቧ ነው ያደገችው። እንደሌሎች ሕፃናት ቤት ውስጥ ሳህን እጠቢ ቤት ጥረጊ፣ ወጥ አማስይ፣ እንጀራ ጋግ የሚላት አልነበረም። እንዲያውም እስከ ዛሬ ድረስም እንጀራ መጋገር አትችልበትም። ሥራ በመጥላት ግን አይደለም። ተግቶ የመሥራትን ጥቅም በእናቷ አርአያነት ተምራለች፤ ለስኬቷም አንድ ምሶሶ ሆኖላታል። በቀድሞው እቴጌ መነን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረችው ፅጌ፣ ተፈሪ መኮንን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ገብታ በሴክሬታሪያል ሳይንስ ዲፕሎማ ተቀብላለች። ወደ ሥራ ዓለም ወይስ ወደ ተጨማሪ ትምህርት ሊሂድ ብላ አንዱን ለመምረጥ አልተገደደችም። ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬት ተያያዘችው። ሀምሌ 1962 ዓ.ም በፀሐፊነት በተቀጠረችበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለማታ ትምህርት የተመዘገበችው ፅጌ፤ በ1970 ዓ.ም በሥራ አመራት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኘች። ከፀሐፊነት ወደ አስተዳደር ሥራ  እድገት ብታገኝም፤ እንደገና ጎን ለጎን ትምህርት ጨመረችበት – በተማሪነት ሳይሆን በአስተማሪነት። ብዙም ሳትቆይ ከፎርድ ፋውንዴሽን ባገኘችው የትምህርት እድል ኔዘርላንድስ ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ በ1977 ዓ.ም በቢዝነስ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ (ኤምቢኤ) ለመያዝ በቃች።
ፀሐፊነት በተቀጠረችበት ዩኒቨርስቲ ወደ አስተዳደር ስራና ወደ አስተማሪነት፤ ከዚያም የሥራ አመራርና የህዝብ አስተዳደር ዲፓርትመንት ሃላፊ ወደ መሆን በመሸጋገር ብዙም ያልተለመደ ታሪክ ሰርታለች። እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካገለገለች በኋላ፤ ልማት ላይ ባተኮረው አለማቀፍ የረድኤድ ድርጅት በ”አክሽንኤይድ ኢትዮጵያ”  ተቀጥራ የሰው ሃይል ልማት ሥራ አስኪያጅ ሆናለች።
ነገር ግን፣ አልቀጠለችበትም። ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ችግረኛ ሰዎችን ማገዝና ማገልገል እችላለሁ አለች። እንዴት እንደምትችልም ለይታ አውቃለች። በችግረኛ ልጃገረዶችና ሴቶች ላይ ያተኮረ አገር በቀል የረድኤድ ድርጅት በማቋቋም የተሻለ ውጤት አስመዘግባለሁ ብላ ያመነችው ፅጌ፤ በ1989 ዓ.ም የሴቶች ራስ አገዝ ድርጅት (ራሴድ) አቋቋመች። በቀጣዩ አመት ወደ ሥራ የጀመረው ራሴድ፣ የሴቶችንና የልጃገረዶችን አቅም የመገንባት አላማ በመያዝ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መስክ ድጋፍ እየሰጠ የሴቶችን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ያበረታታል። ለየት ብለው ከሚታዩ የድርጅቱ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፤ የሴቶችን የፋይናንስ አቅም ለመገንባት የተከተለው ዘዴ ነው። 51 የሴቶች የቁጠባና የብድር ማህበራትን በማደራጀት፤ በጋራ ማህበራቱ ዩኒኔን እንዲቋቋም ተደርጓል። ራሴድ በስፋት የሚያካሂደው ሌላው ሥራ ስልጠና ነው። በሥራ ፈጠራ፣ በቢዝነስ፣ በጤና፣ በአመራር፣ በሥራ አካሄድ እንዲሁም በራስ አገዝ ልማት ዙሪያ ስልጠና ይሰጣል። በአዲስ አበባ ጅርጅቱ በቀጥታ ትኩረት ሰጥቶ ያቀፋቸው 23ሺ የሚጠጉ ችግረኛ ሴቶችና ልጃገረዶች የስልጠናው ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በሌሎች የረድኤድ ደርጅቶች፣ በመንግስትና በግል ዘርፍ አማካኝነት የተሰባሰቡ (ጥቂት ወንዶችን ጨምሮ) 13 ሺ ያህል ሴቶች በራሴድ የስልጠና ፕሮግራም ጥቅም አግኝተዋል። ይህም ብቻ አይደለም። በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ የያዙ ተቋማት እንዲጠናከሩ፣ የአሰልጣኞች ስልጠና ያካሂዳል። የሴቶችን አቅምና ብቃት የመገንባት አላማ የጥቂት አመታት ጥረት አለመሆኑን የተገነዘበችው ፅጌ፤ የራሴድ የስልጠና ተቋም ለወደፊቱ ትውልዶችም የሴቶችን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚቆምና መሆን ስላለበት በሴቶች ባለቤትነት የሚመራ የራሱ ህንፃ እንዲኖረው አድርጋለች።
ራሴድ፣ የብዙ ችግረኛ ሴቶችና ልጃገረዶች ሕይወታቸው ላይ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ለውጥ እንዲያመጡ ረድቷል። ግን በምፅዋት አይደለም። በኑሮ ራሳቸውን ለመቻልና ነፃነት ለመጎናፀፍ የሚያበቃ ጠንካራ መሰረት እንዲገነቡ ነው ያገዛቸው። የኢኮኖሚ አቅም የሚቀዳጁበት ክህሎት በባለቤትነት እንዲጨብጡ ነው የደገፋቸው። ብዙዎቹም ራሳቸውን ችለው፣ ኑሯቸውን ለማሻሻልና ልጆቻቸው ወደተሻለ ትምህርት ቤት ለማስገባት በቅተዋል። የጤና ኢንሹራንስም ለማግኘት ችለዋል። መደራጀት ሃይል እንደሆነ በአፅንኦት የምታምነው ፅጌ፤ በቁጠባና ብድር ማህበራት የተደራጁ በርካታ ሴቶች በዩኔናቸው ውስጥ የአመራር ቦታዎችን እስከመያዝ መድረሳቸውን ትጠቅሳለች። ለዚህም የራሴድ የስልጠና ዘዴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ስልጠናው ሲቀረፅ፣ ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ሴቶችም ጭምር በቀላሉ እንዲገነዘቡትና እንዲገባቸው ተደርጎ ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ማንበብና መፃፍ እንዲማሩ በውጤታማነት ላይ ያተኮረ የቤት ውስጥ ስልጠና ያዘጋጅላቸዋል። ከስልጠና በተጨማሪ፣ ክህሎትን ለማጠናከርና ለማነቃቃት፣ እንዲሁም እርስ በርስ ተመክሮ ለመለዋወጥ የሚያስችል፣ በቢዝነስ ሃሳብ ፈጠራ አመታዊ ውድድር በማዘጋጀት ሽልማት ይሰጣል። በእነዚህና በተመሳሳይ የራሴድ ሁሉን አቀፍ ፕሮግራሞች አማካኝነት፤ ችግረኛ ሴቶች የራሳቸውን እምቅ አቅም ለማወቅ፣ ክህሎት ለመገንባትና በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ችለዋል። በቤት ውስጥ የፆታ ግንኙነትን ለማስተካከል ድፍረት አግኝተዋል። የራሳቸውን ኑሮ ከማሻሻልና ልጆቻቸውን ከማስተማር አልፈው፣ ለሌሎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። የሴቶችን ሕይወት ለመለወጥ መጣጣር ማለት፣ ማህበረሰቡንና በአጠቃላይ አገሪቱን ለመለወጥ መታገል ማለት መሆኑን በፅኑ የምታምነው ፅጌ፤ ሴቶች የአገርን ኢኮኖሚ የማሳደግ አቅም እንዳላቸው በአለም ደረጃ እየታመነበት መምጣቱን ትጠቅሳለች።

የበርካታ ሴቶችን ሕይወት በመለወጥ ውጤታማ የሆነው ራሴድ፣ ዓለማቀፍ እውቅናን አግኝቷል። የሴቶችን የአመራር አቅም በማሳደግ የላቀ የሙያ ማዕከል በሚል በዓለማቀፍ የትምህርት ተቋም ከተመረጡት አራት የአፍሪካ ድረጅቶች መካከል አንዱ ራሴድ ነው። ሌሎቹ ሦስት ድርጅቶች፣ ከሩዋንዳ፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ የተመረጡ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ኮዲ የተሰኘው የካናዳ ተቋም በኢኮኖሚያዊ አቅም ግንባታና በምግብ ዋስትና መስኮች በጋራ ለመሥራት፣ ሦስት የአፍሪካ ድርጅቶችን ሲመርጥ፤ ራሴድ አንዱ ለመሆን ችሏል። ሌሎቹ ሁለት ድርጅቶች ከዛምቢያና ከጋና የተመረጡ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ማህበራትንና የረድኤት ድርጅቶችን አቅፎ በመያዝ የሚታወቀው ትልቁ ተቋም ሲአርዲኤ፣ በቅርቡ ባካሄደው ውድድር ላይም ራሴድ ክብር ተጎናፅፏል። ከበርካታ የረድኤት ድርጅቶችና ማህበራት መካከል፤ የላቀ ውጤትና ብቃት ያሳዩ ተቋማት በየዘርፋቸው የተሸለሙ ሲሆን፤ ራሴት የከተማ ድህነትን ለማቃለል ባደረገው ጥረትና ባስመዘገበው ውጤት አንደኛ ወጥቶ ተሸልሟል።  ራሴድ ለአርአያነት የሚመረጥ የላቀ የሙያ ማዕከል ሆኖ ዓለማቀፍ እውቅናው እንዲጨምርም ፅጌ በትጋት መሥራቷን ቀጥላለች።
ራሴድን በዳሬክተርነት ከመምራት በተጨማሪ፣ ፅጌ በበርካታ የረድኤት ድርጅቶችና ማህበራት ውስጥ ትሳተፋለች። በሲአርዲኤ የ35 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የቦርድ ሊቀመንበር ሆና ሰርታለች። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ውስጥም ከመስራች የቦርድ አባላት መካከል አንዷ ነች። ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ሴት ምሁራንን ባለሙያዎችንና የቢዝነስ ባለቤቶችን በአባልነት  በሚያሰባስበው ሶሮፕቲሚስት ኢንተርናሽናል የተሰኘ ክለብ የአዲስ አበባ ፕሬዚዳንት በመሆኑ ለሁለት አመታት ያገለገለችው ፅጌ፤ ለስድስት አመታት የማህበራዊ ጥናት መድረክ ቦርድ አባል ሆናለች።  ERSHA እና Peace Microfinance በተሰኙ ተቋማት በጠቅላላ ጉባኤ አባልነት፤ እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ከሚዘጋጁት ዓለማቀፍ የገንዘብ ድጋፎች መካከል ጥቃቅኖቹን ተግባራዊ ለማድረግ ዩኤንዲፒ ባቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት ስረታለች። የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የአደራጅ ኮሚቴ አባል ነበረች፤ አሁን ደግሞ የባንኩ ቦርድ አባል ናት።

ፈተናዎች ሲያጋጥሟት አትማረርም፤ ልዩ የመፍትሄ ሃሳብ ለማፍለቅ እድል ይሰጡናል ትላለች። ታታሪ እንደመሆኗ፣ ከብዙ ሰዎች በላቀ ሁኔታ በርካታ ሰዓታትን በሥራ ታሳልፋለች። እንዲያም ሆኖ፣ ሚዛን ጠብቆ ሥራንና ቤተሰብን ማስኬድ አስፈላጊ እንደኖነና በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ የጋራ ሃላፊነት ሊኖር እንደሚገባ ታምናለች። ሥራዋ ትልቅ የእርካታ ምንጭ እንደሆነላት ስትገልፅ፤ “የተባረከ ሕይወት ማለት ይሄው ነው” ትላለች። ለኢትዮጵያ ያላት ህልም፣ ሴቶች እውቀት ላይ ተመስርተው የራሳቸውን ሕይወት የሚመሩባትና ከወንዶች ጋር እኩል ታይተው እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባት አገር እንድትሆን ነው።

ልጃገረዶችንና ወጣት ሴቶችን እንዲህ ስትል ትመክራለች፡ በየትኛውም መስክ ቢሆን፣ ልባዊ የስራና የሙያ ፍቅር ሊኖራችሁ ይገባል – ያ ነው ትልቁ አለኝታችሁ። የማንበብ፣ የመፃፍ፣ የቋንቋ እና የመግባባት መሰረታዊ ችሎታዎች ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ናቸው። ተነሳሽነት፣ ትልልቁን የማለም መንፈስ፣ እና ደግሞ ለተጨማሪ ሰዓታት በተጨማሪ ትጋት መሥራት የስኬት ቁልፎች ናቸው።

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከወ/ሮ ፅጌ ኃይሌ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፤ ሰኔ 2004
አጥኚ
ወደረየለሽ አበበ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>