Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ንጋትዋ ላሳብ ወልደጊዮርጊስ

Negatwa Lasab

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በ90ዎቹ  የመጀመርያ ዓመታት የቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበርን ከመሰረቱት ስድስት ሴቶች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ ከ3000 በላይ ቤተሰቦችን ይደግፋል፡፡ በ1994 ዓ.ም በግሪክ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሸክላ ሰሪዎች በተሳተፉበት ውድድር ላይ ሁለተኛ በመውጣት ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሴት ሸክላ ሰሪዎችን አሰልጥናለች፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ ሸክላ ሰሪና የቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበር አባል
የትውልድ ቦታ: ደራ፣ ሰሜን ሸዋ፣
የትውልድ ዘመን: 1948 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣
ዋና የስራ ዘርፍ
የሸክላ ሥራ
የሕይወት ታሪክ
የቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበርን ከቆረቆሩት ስድስት መስራቾች አንዷ የሆነችው ንጋትዋ ላሳብ፤ ማህበረሰቧን በማብቃትና የለውጥ ሐዋርያ በመሆን ከ20 ዓመት በላይ በትጋት የሰራች ተሸላሚ የሸክላ ሥራ ባለሙያ ናት፡፡ በሙያዋ ብቃትና ልምድ የታጠቀችው ንጋትዋ፤ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በደቡብ ከተሞች በመዘዋወር ሸክላ ሰሪዎችን በተማረችውና በተካነችው የሸክላ አሰራር ሙያ ታሰለጥናለች፡፡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሸክላ ሰሪዎች በተሳተፉበትና በ1994 ዓ.ም በግሪክ አቴንስ በተካሄደ ውድድር ላይ ሁለተኛ በመውጣት አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡

በ1948 ዓ.ም  በሰሜን ሸዋ፣ ደራ ከተማ የተወለደችው ንጋትዋ፤ ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላት ድረስ እዚያው ከኖረች በኋላ፣ ወላጆቿ በፍቺ በመለያየታቸው ከአባቷና አዲሷ ሚስታቸው ጋር ወደ ስላሌ ሄደች፡፡ ሆኖም ብዙ አልቆየችም፡፡ አሥራ አንድ ዓመት ሲሆናት አባቷ፣ አዲስ አበባ ወደሚኖሩት አክስቷ ጋ ላኳት – በቤት ውስጥ ሥራ እያገዘቻቸው እንድትኖር፡፡ ንጋቷ ለሸክላ ሥራ አዲስ አልነበረችም፡፡ እናቷ ብቻ ሳይሆኑ አያቷም ሸክላ ሰሪዎች  ናቸው፡፡ ማናቸውም ቢሆኑ ግን አክስቷን አያህሉም፡፡ ንጋቷ ከአክስቷ ጋር በኖረችባቸው ጊዜያት አዳዲስ የሸክላ አሰራር ዘዴዎችን የመማር እድል አግኝታለች፡፡ አገር ቤት ሄዳ ከእናቷ ጋ መኖር የጀመረችው ንጋቷ፤ ብዙም ሳትቆይ ግን አዲስ አበባ ተመልሳ  የሽመና ባለሙያ አገባች፡፡ ከዚህ በኋላ የሸክላ ሥራን ህይወቴ ብላ ተያያዘችው፡፡ የራሷን የሸክላ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን የባለቤቷን የሽመና ውጤቶች መርካቶ ወስዳ መሸጥም የእሷ ሃላፊነት ሆነ፡፡ ልጆች ስትወልድም እንኳን ሥራዋን አላቆመችም፡፡ መደበኛ ትምህርት የመከታተል ዕድል ያልነበራት ንጋቷ፤ በደርግ መንግስት በተጀመረው የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም እስከ አራተኛ ክፍል ተምራ፣ማንበብና መፃፍ ችላለች፡፡ ሸክላ ሰሪነት ለንጋቷ የምርጫ ጉዳይ አልነበረም፤ ቤተሰቧ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ ያወረሳት ሙያ ነው፡፡

ንጋቷ በአርአያነት የምትከተለው ሰው ፍለጋ የትም  ቦታ መባከን አላስፈለጋትም፡፡ ቤተሰቧ ውስጥ በርካታ አርአያዎች ነበሯት፡፡ እናቷና አያቷ የሸክላ ሥራ ሀሁን አስተምረዋታል፡፡ በተለይ ደግሞ በቅርቡ የሞቱት አክስቷ ባለውለታዋ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ በጌጣጌጥ የተራቀቁ የተለያዩ የሸክላ አሰራር ዘዴዎችንና ዲዛይኖችን ያስተማሯት እሳቸው ነበሩ፡፡ አክስቷ ያስተማሯትን ብቻ እየደጋገመች መሥራት ግን አልመረጠችም፡፡ እሷም እንደአክስቷ ፈጠራ ትወዳለች፡፡ በሥራዋ ስኬታማ የሆነችውም በታታሪነቷና በፈጠራ ችሎታዋ እንደሆነ ታምናለች፡፡ በግሏ መስራት የምትመርጠው ትላልቅ ባህላዊ እንስራዎችን  ሲሆን ይሄ የአብዛኛዎቹ ወጣት ሸክላ ሠሪዎች ምርጫ አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ — ከፍተኛ ችሎታ ይጠይቃል፡፡ በዚያ ላይ ብዙ ጉልበትና ጊዜ ስለሚፈጅ ነው፡፡ ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ያላቸው አንድ አይነት የሸክላ ውጤቶችን መስራት ለአብዛኞቹ ሸክላ ሰሪዎች አስቸጋሪ ነው፡፡ ንጋቷ ግን አንዱን ከሌላው ለመለየት የሚያስቸግሩ ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሸክላዎችን የመሥራት ልዩ ችሎታ ባለቤት ናት፡፡

የደርግ ወታደራዊ መንግስት ማብቂያ ላይ፣ ሚስ ማርጋሬት የተባለች ካናዳዊት፣ የሴቶች ሸክላ ሰሪዎች ማህበር ለማቋቋም  ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ፣ ትኩረት ውስጥ የገባችውም ጥራት ያላቸው የሸክላ ሥራዎች በማምረት ሰዎች እያወቋት ስለመጣች ነበር፡፡ ንጋቷን የምታውቃትና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትሰራ የነበረችው ወ/ሮ ገነት የተባለች ሴት ናት  ከሚስ ማርጋሬት ጋር ያስተዋወቀቻት፡፡ በአዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያው የነበረው “የቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበር” ን ካቋቋሙት ስድስት  መሥራች  አባላት መካከልም  አንዷ ልትሆን በቃች፡፡ ማህበሩ የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቶት ሥራ እንደጀመረ አካባቢ  አባላቱ ቤታቸው የሰሯቸውን የሸክላ ውጤቶች ነበር ወደ ማዕከሉ የሚያመጡት፡፡ የማታ የማታ ግን  ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር ኮንትራት ለመዋዋል ድርድር ጀመሩ – እነሱ ያልተጠበሱ ጥሬ የሸክላ ምርቶቻቸውን እያቀረቡ  የኮሚሽኑ ንብረት በሆነ ምድጃ ውስጥ በመጥበስ ለገበያ ለማውጣት፡፡ እነሆ ድርጅቱ ከ20 ዓመት በላይ በስኬት  መዝለቅ ችሏል፡፡ በእርግጥ ይሄን ሁሉ ርቀት የተጓዘው ብቻውን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከአጋዦቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የአነስተኛና ጥቃቅን የብድር አገልግሎት ተቋም እንዲሁም የተለያዩ  የሸክላ ሥራ ባለሙያዎች ማህበሩን ማገዝ ይዘዋል፡፡ በባለሙያዎች በተቋቋመ የህብረት ሥራ ማህበር ጥላ ሥር መስራት ጠቀሜታ እንዳለው ጽኑ እምነት ያላት ንጋትዋ፤ ለምርትም ሆነ ምርትን ለሽያጭ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ትናገራለች፡፡ ማህበሩን ከመቀላቀሏ በፊት ሸክላዎቿን የምትጠብሰው እቤቷ ስለነበር፣ ጭሱ በቤተሰቧ ውስጥ የጤና ችግር አድርሶባታል፡፡ እንዲያውም አንዴ የጽንስ ማቋረጥ ያገጠማት፣ አየር በማያስገባ ክፍል ውስጥ ሸክላ ሲጠበስ በሚፈጠረው ጭስና ሙቀት ሳቢያ ሊሆን እንደሚችል ታምናለች፡፡

ከሌሎች በመማር የምታምነው ንጋቷ፤ የሸክላ አሰራርን ከዜሮ ጀምራ ካስተማረቻቸው ወጣት የማህበሩ አባላት ሳይቀር ትምህርት ለመቅሰም ወደ ኋላ ብላ አታውቅም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው  በርካታ ሸክላ ሰሪዎች የመማር ዕድልም አግኝታለች፡፡ በተለይ ደግሞ አትዮጵያዊ ደምና ፈረንሳዊ ዜግነት ካላት እትዬ ዲማ ፓውልሰን ብዙ ተምራለች፡፡ በአዲስ አበባ ለስምንት ወራት የቆየችው እትዬ ዲማ፤  ለቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበር አባላት፣ አዳዲስ የሸክላ አሰራር ዘዴዎችን ያስተማረች ሲሆን ከአዳዲስ ስታይሎችና ዲዛይኖችም ጋር አስተዋውቃቸዋለች፡፡ ለምሳሌ ቀይና ጥቁር ቀለም የተቀባ ሸክላ ለማምረት የሚያገለግል የአጠባበስ ዘዴ፤ ካስተማረቻቸው መካከል ይጠቀሳል፡፡ እትዬ ዲማ ለማህበሩ አባላት አዳዲስ ክህሎቶችን ብቻ በማስተማር ሳትወሰን፣ ሥራዎቻቸውን ለዕይታ በማቅረብ እንዲያስተዋውቁና እንዲሸጡ መድረኮችን በመፍጠርም  አግዛቸዋለች – አሊያንስ ፍራንሴስን ጨምሮ በበርካታ ባዘሮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ፡፡

ንጋቷ በ1994 ዓ.ም በግሪክ አገር በተካሄደ ዓለምአቀፍ የሸክላ ስራ ውድድር ላይ እንድትካፈል ሁኔታዎችን ያመቻቸችላትም እትዬ ዲማ ነበረች፡፡ በአቴንስ በተደረገው ውድድር ላይ የተሳተፉት ሸክላ ሰሪዎች ግሪክን ጨምሮ ከስድስት የተለያዩ አገራት የተውጣጡ ነበሩ – ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከፈረንሳይ፣ ከሊባኖስ እና ከኢትዮጵያ፡፡ በዚህ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት ያሸነፈችው ንጋቷ ፤ የእጅ  ሰዓትና  3ሺ ብር ለመሸለም በቅታለች፡፡ በእርግጥ ውድድሩ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በተለይ ለእሷ ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምክንያቱም  ተፎካካሪዎቿ  በሙሉ  የሸክላ ስራዎቻቸውን በማሽን እየታገዙ ሲሰሩ፣ እሷ  ግን አንድ ሜትር ቁመት ያለው የኢትዮጵያ ባህላዊ እንስራ የሰራችው በሌጣ እጇ ነበር፡፡ የውድድር ሂደቱ አስቸጋሪ እንደነበር የምትናገረው ንጋቷ፤ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የራሷና አንደኛ  የወጣው የሸክላ ሥራ ሲቀር ሌሎቹ በሙሉ በነጋታው በዝናብ መፈራረሳቸውን ታስታውሳለች፡፡ በውድድሩ ያገኘችው ስኬት ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈላት ሲሆን በግሪክ እየሰራች እንድትኖርም  ግብዣ ቀርቦላት ነበር፡፡ ሆኖም  ለረዥም ጊዜ ከልጆቿ ተለይታ መኖር ስላልፈለገች ግብዣውን ሳትቀበለው ቀረች፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ እድል ለንጋቷ የመጀመርያዋ አልነበረም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊትም በሳኡዲ አረብያ የሸክላ ሥራ እያስተማረች እንድትኖር በሚስ ማርጋሬት በኩል ተመቻችቶላት ነበር፡፡ ያኔም ልጆቿን ጥላ ላለመሄድ  ስትል በእድሉ አልተጠቀመችበትም፡፡ ከአቴንስ እንደተመለሰች ታዋቂው “የአለቤ ሾው” አዘጋጅ  አለባቸው ተካ፤ በግሪክ ቆይታዋ ዙሪያ ቃለመጠይቅ አደርጎላት ነበር፡፡ ቃለመጠይቁ ሙያዋን ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረላት ሲሆን በማህበሯ በኩል በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይ በደቡብ ከተሞች በመዘዋወር ሸክላ ሰሪዎችን የማሰልጠን ዕድል አግኝታለች፡፡ ይሄ  የማስተማርና የማሰልጠን ሥራዋም  ልብ የሚነካና እርካታ የሚያጎናፅፍ እንደሆነላት ንጋትዋ  ትናገራለች፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት በቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበር ልዩ ልዩ የአመራር ቦታዎች ላይ አገልግላለች፡፡  በእነዚህ ጊዜያትም ማህበሩ ብዙ ፈተናዎች ነበሩበት – አሁንም ድረስ ያልተፈቱ፡፡ ማህበሩ የሸክላ ምርታቸውን የሚጠብሱበት የራሱ ምድጃ ቢኖረው ኖሮ ሥራቸውን ከማቅለሉም በተጨማሪ ቀላል የሚይባል ትርፍ ያስገኝላቸው ነበር፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ምድጃውን መግዛት አልቻሉም፡፡ አሁን ደግሞ የባሰ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ማህበሩ ካለበት ሥፍራ የመልቀቅ አደጋ አንዣቦበታል፡፡ ምክንያቱም ሸክላው ሲጠበስ የሚወጣው ጭስ በቅርቡ ከጎናቸው ለተገነባው የጤና ማዕከል ጎጂ መሆኑን  የቀበሌ ሃላፊዎች ተናግረዋል ፡፡ የአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋም ለማህበሩ አዲስ ቦታ ለማፈላለግ ቃል ቢገባም አባላቱ ግን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከሰሩበት ሥፍራ የመልቀቅ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ገበያችንን ይጎዳዋል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ለነገሩ ቢሰጉም አይፈረድባቸውም፡፡ ዛሬ ከማህበሩ በሚገኘው ገቢ ከ3ሺ በላይ ሰዎች ይተዳደራሉ፡፡

የንጋትዋ ጥንካሬ በሙያዋ  ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከአስራ ስድስት ዓመት በፊት የባለቤቷን ህልፈት ተከትሎ ስምንት ልጆቿን ለብቻዋ በማሳደግ እጅግ ብርቱ ሴት መሆኗን አስመስክራለች፡፡ አዳዲስ ነገሮችን ለመሥራትና ለመሞከር ድፍረትና ወኔ የታጠቀችው ንጋትዋ፤ ሥራዋን አብጠርጥራ የምታውቅ የሙያዋ እመቤት ናት፡፡ መታወስ የምትሻው “በህይወቷ የገጠማትን ፈተናና ውጣ ውረድ ተጋፍጣ በሥራዋ የላቀች ጠንካራ ሴት” ተብላ ነው፡፡ የወደፊት ግቧ ሥራዎቿን በዲዛይንም ሆነ በአሰራር እያሻሻለች፣ ጥራታቸውን የጠበቁ የሸክላ ምርቶች ማምረቷን መቀጠል ነው፡፡

ለሴቶች ደህንነት የሚሰጠው ትኩረት መሻሻሉን የምታደንቀው ንጋትዋ፤ ሴቶች በአሁኑ ጊዜ በርካታ እድሎች እንዳላቸው፣ ለሥራና ራሳቸውን ለማሳደግ ቅድምያ ድጋፍ እንደሚያገኙም ትናገራለች፡፡ በተዛባ ማህበራዊ አመለካከት ሳቢያ ሸክላ ሰሪነት እንደ ተዋረደ ሥራ የሚቆጠርበትን፣ ባለሙያዎቹም ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸው የነበረበትን ጊዜ ታስታውሳለች፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ታሪክ ሆኗል ባይ ናት፡፡ እሷና የቀጨኔ ሴት ሸክላ ሰሪዎች ማህበር ባልደረቦቿ፣ ሥራቸውን በደስታና በእርካታ እየሰሩ፣ የላባቸውን  ማግኘት ችለዋል፡፡ ለዚህ ትልቅ ለውጥ መፈጠር ደግሞ የአሁኑን መንግስት አመራር ታመሰግናለች፡፡

ንጋቷ ለኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች ምክሯን ስትለግስ እንዲህ ትላለች፡-

  • ተግታችሁ ሥሩ
  • ከበሽታዎችና ለዚያ ከሚያጋልጣችሁ የአኗኗር ዘይቤ ራቁ፣
  • ሥራ ለመስራት ያሉትን አዳዲስ ዕድሎች በመጠቀም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ ውጡ፤ ራሳችሁን ቻሉ፡፡
ዋና የመረጃ ምንጮች
በ2004 ዓ ም ከንጋትዋ ላሳብ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ቤተል በቀለ ብርሐኑ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>