Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ካሚሌ ደ ስቱፕ

Camille De Stoop

ዋና ዋና ስኬቶች:
ENDAን በኢትዮጵያ የመሰረተች ሲሆን ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ፎረም ቀደምት መስራቾች አንዷ ናት
ወቅታዊ ሁኔታ
የትውልድ ቦታ: ኮርትሪጅ፣ ቤልጂየም
የትውልድ ዘመን: 1949
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሴንት ኒከላስ፣ ኮርትሪጅ፣ ቤልጂየም
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  በትውልድ ቤልጂየማዊት የሆነችው ካሚሌ ደ ስቱፕ እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም በ23 ዓመቷ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው – በወላይታ ሶዶ አካባቢ ለሴት ገበሬዎች የጎልማሶች ትምህርት ከሚሰጠው አግሪ – ሰርቪስ ጋር ለመስራት። ከስራዋና በኋላ ካገባችው ኢትዮጵያዊ ወንድ ጋር በፍቅር የወደቀችው ካሚሌ፤ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በመቅረት ለ40 ዓመት ገደማ ኖራለች። ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ቀደምት ጠንሳሾች አንዷ ናት። በአዲስ አበባ ማህበረሰብ – ተኮር የቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀም እንዲሁም የከተማ ግብርናን በፈር ቀዳጅነት በማስፋፋት የሚታወቀውን ENDAን ቅርንጫፍ ድርጅት በኢትዮጵያ ያቋቋመችውም እሷ ናት – እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም። የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ፎረምን /FFE/ በጨቅላ እድሜው ኮትኩታ ያሳደገችው ካሚሌ ስትሆን በኋላ ላይ ከኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል። የአረንጓዴ ሽልማት /ግሪን አዋርድ/ መፈጠሪያና መቀመጫም ነው – ድርጅቱ።በፈረንሳይ ድንበር አቅራቢያ ፍላንደሮች በሚኖሩበት የቤልጂየም ክልል፣ ኮርትሪጅ ውስጥ የተንደላቀቀ ኑሮ ከሚሹ ባለፀጋ ቤተሰቦች የተወለደችው ካሚሌ፤ 17 ዓመት እስኪሞላት ድረስ በቤልጂየም ነው ያደገችው። 14 ዓመት ገደማ ሲሆናት አባቷ በመክሰራቸው የቤተሰቡ እጣፈንታ በአስገራሚ ሁኔታ ተለወጠ። ወላጆቿ ግን ብርቱዎች ነበሩ። እሷም ሆነች ወንድም እህቶቿ ችግርና መከራ አልጎበኛቸውም። ካሚሌ ስለድንገተኛው ለውጥ አሉታዊ ትውስታ የላትም። እንደውም እንኳንም አየሁት ባይ ናት። ምክንያቱም ዓለምን በተለየ መነፅር ለማየት መልካም አጋጣሚ ሆኖልኛል ባይ ኗት። የሃብታሞች መኖርያና መናኸርያ በነበረችው ኮርትሪጅ፣ ለቱጃር ቤተሰቦች በሞግዚትነት ተቀጥራ ስትሰራ፣ በዙሪያዋ ባየችው ግልብ የህይወት አስተሳሰብና እምነት ተስፋ ቆረጠች። ንባብን ቁርስና እራቷ ያደረገችው ካሚሌ፤ በዓለም ላይ በሃብታምና በድሃ መካከል በሚታየው የኑሮ ልዩነት ቆሽቷ አርሮ ነበር። ይሄም ኢ-ፍትሃዊነትን በቁርጠኝነት እንድትዋጋ አነሳሳት።

ሁለቱ እጅግ ጉልህ ተፅዕኖ ያሳደሩባት አርአያዎቿ ሴት አያቶቿ ነበሩ። በእርግጥ አንዳቸው ከሌላኛቸው ፍፁም የተለዩ ነበሩ። አንደኛዋ አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ የሌላትና በካንሰር ክፉኛ የታመመ ባል ቢኖራትም ህይወቷን በጨዋታ እያዋዛች፣ ኑሮዋን በወኔ ትመራለች። ያሻትን በግልፅ የምትናገርና የምትፈልገውን ጠንቅቃ የምታውቅም ነበረች። ሌላኛዋ ደግሞ ሲበዛ ዝምተኛ ናት። ለካሚሌ ግን ተመችታታለች፣ ሁሉን ነገር የምታወያየው ለእሷ ነበር። ያለምክንያት ግን አይደለም። በትዝብት ዓይን ሳታይ ስለምታዳምጣት ነው። እቺ አያቷ የ15 ዓመት ታዳጊ ልጃገረድ ሳለች ብቻዋን ከቤልጂየም ተነስታ ወደ እንግሊዝ ተጉዛ ነበር። በ19ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ላይ ላለች ልጃገረድ ይሄ ያልተለመደ ቢሆንም እሷ ግን አደረገችው። ካሚሌ ከሁለቱም ጠንካራ ሴቶች ብዙ ትምህርት ቀስማለች።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በቱጃሮች ቤተሰብ ውስጥ ትኖር የነበረችው ካሚሌ፤ በዙሪያዋ  የከበባት ህይወት ላይ በማመፅ ነው ወደ እስራኤል በ17 ዓመቷ የተጓዘችው። በእስራኤል ኪቡትዝ ያየችውን የህብረት ስራ ማህበር ዓይነት አኗኗር ወዳላቸው ነበር፣ ግን ምን ያደርጋል። ወላጆቿ ትምህርቷን እንድታጠናቅቅ ሲጎተጉቷት ወደ ቤልጂየም ተመለሰች። የእርሻ ሙያ ት/ቤት ገብታ የቆላማ አካባቢ ግብርና ላይ ያተኮረ ትምህርት ተከታትላ  ስትመረቅ፣ በወንዶች መሃል ብቸኛዋ ሴት ነበረች። ከሶስት ዓመት በኋላ ወደ ብራዚል ለመሄድ አሰበች- የገበሬዎችን ህይወት የሚያሻሻል የጎልማሶች ትምህርት ላይ ለመሳተፍና በእስራኤል እንዳየችው የኪቡትዝ ዓይነት ማህበረሰብ እንዲመሰረት ለማገዝ። ከዚያ በፊት ግን መዘጋጀት ነበረባት። እናም ወደ ፖርቹጋል ሄዳ፣ በትላልቅ እርሻዎች ላይ ጥቂት ጊዜ  አሳለፈች – የፖርቱጊዝ ቋንቋ ለመማርና ጥቂት የእርሻ አሰራር ተግባራዊ ልምድ ለመቅሰም። በኋላ ግን ላቲን አሜሪካ የራሷን የጎልማሶች ትምህርት /ከፓኦሎና ከትምህርት ጋር የተያያዘ ንቅናቄ/                                                                                                                                                                                                      በመተግበር ሂደት ላይ እንደነበረች ስትገነዘብ፣ ወደ ላቲን የመሄድ ሃሳቧን ተወችው። ከዚያም ያኔ በንፅፅር በአውሮፓውያን ዘንድ እምብዛም ወደማትታወቀው ኢትዮጵያ መሄድ ጀብድ ሆኖ ታያት። አገር ለመጎብኘት ግን አልነበረም። አግሪ-ሰርቪስ ኢትዮጵያ በተሰኘ ድርጅት ውስጥ ስራ አግኝታ ነው። ከአቢጃኑ የአፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ልማት ተቋም ጋር ትስስር ያለው ይኸው ድርጅት፤ የገበሬዎችን ችግር የምንፈታው ከሴቶች ጋር ስንሰራ ነው በሚል መርህ የሚንቀሳቀስ ነበር። የሚገርመው ደግሞ ካሚሌ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰራ ሌላ ድርጅት ስራ አመልክታ፣ በኢትዮጵያ ከገበሬዎች ጋር መስራት ለሴቶች የሚሆን ስራ አይደለም ተብላ ነበር። ሆኖም በ23 ዓመቷ ከገበሬዎች ጋር ለመስራት ወደ ወላይታ ሶዶ አካባቢ ተጓዘች።
ከአካባቢው የመስክና የማህበረሰብ ሰራተኞች ጋር በመሆን ስትሰራ አማርኛና ወላይትኛ ቋንቋዎችን መልመድ እንደጀመረች የምትናገረው ካሚሌ፣ የሶዶና ከምባታ የገጠር ሴቶችን ችግሮች በማወያየት መፍትሄዎችን ትዘይድ ነበር። ኑሮዋቸውን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክራለች- በተግባርም ጭምር እያሳየች። ቀላል የቤት ውስጥ የባልትና ሙያ፣ ጤናና የግል ንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም  የህፃናት እንክብካቤ ስትራቴጂዎችን አስተምራለች – በአካባቢው ሰዓሊ የተሳሉ በርካታ ስዕሎች የተካተቱበትና በቀላል አማርኛ የተዘጋጁ የመቀስቀሽያ መፅሄቶችን በመጠቀም። ስለ እርግዝናና የልጅ አስተዳደግ ሂደት ከወጣት ሴቶች ጋር መረጃ መጋራቷ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ታስታውሳለች። እንዴት ቢሉ — ኤችአይቪ/ ኤድስ ከመምጣቱ በፊት ስለስነተዋልዶ ጤና ምንም ዓይነት መረጃ አልነበራቸውም። በዚህም የተነሳ የእርግዝናና የልጅ አስተዳደግ ጉዳይ እንደአንዳች ጉድ ነበር የሚያስፈራቸው። ካሚሌ አንዳንድ የሞኝ የሚመስሉ ስህተቶችን መስራቷን ስታስታውስም፣ የገጠር ሴቶች ለህፃናት ልጆቻቸው ዳይፐር እንዲጠቀሙ ሃሳብ ማቅረቧ ትጠቅሳለች።

አግሪ ሰርቪስ በሚያዘጋጃቸው ቀላልና ውጤታማ የቅስቀሳ መፅሄቶቹ እየታወቀ በመምጣቱ፣ ሌሎች ክልሎች መፅሄቱ በኦሮሚኛ፣ በአፋርና በሌሎች ቋንቋዎች እንዲዘጋጁላቸው ጠይቀዋል። አግሪ ሰርቪስ ዋና መስሪያ ቤቱን ወደ አዲስ አበባ ሲያዛውር ካሚሌና ባለቤቷም አብረው ተዛወሩ። ካሚሌ ከዘጠኝ ዓመት አገልግሎት በኋላ እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም አግሪ ሰርቪስን በመልቀቅ፣ ኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ሴንተር ፎር አፍሪካን /ILCA በኋላ ILRI  / ተቀላቀለች። እዚያ በቆየችባቸው ጊዜያት በአስተዳደር ረዳትነት፣ በፅሁፍ አራሚነት፣ የእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ አስተርጓሚ በመሆን አገልግላለች – በድርጅቱ የህትመት ክፍል። ቀደም ሲል መንግስታዊ ባልሆነው ድርጅት በ ENDA ከሰራች በኋላ በምርምር ማዕከል ውስጥ የመስራት እድል ያገኘችው ካሚሌ፣ የሳይንቲስቶችን ጥናት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከአካባቢው ማህበረሰብ እንቅስቃሴዎች ጋር ማስተሳሰር ያለውን ፋይዳ ተገንዝባለች።

በ ILCA ለ13 ዓመት ከሰራችና ሶስቱ ልጆቿ ካደጉላት በኋላ እንደገና ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ጋር የመስራት ጥብቅ ፍላጎት ያደረባት ካሚሌ፤ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም ተቀማጭነቱን በሴኔጋል ዳካር ያደረገው Environmental Development Action ቅርንጫፍ ድርጅትን በኢትዮጵያ ከፈተች። የድርጅቱ የልማት አቅጣጫ ከታች ከህዝቡ ወደ ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሃብትና እውቀት ላይ የመገንባት አሰራሩም ጭምር ተመችቷት ነበር። የድርጅቱን ስራ የጀመረችው በባዶ እጇ ነበር። በአንዲት ቢሮና ባለቤቷ በሰጣት ኮምፒውተር፣ ከአዲስ አበባ ግብርና ቢሮ የሴቶች ልማት ዘርፍ ጋር ቅርብ የስራ ትብብር በመፍጠር ተንቀሳቅሳለች።

በኢትዮጵያ የ ENDA የመጀመርያ ፕሮግራም፣ ድርጅቱ በሌሎች ታዳጊ አገራት ካገኛቸው ተመክሮዎች በመነሳት የጠነሰሰው ሲሆን የተቀናጀ የቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነበር። ያኔ በከተማዋ ቆሻሻ የትም ቦታ ይጣል ስለነበር ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር ሃላፊዎች ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጉ ነበር። የENDA ፕሮግራም ትምህርት መስጠት፣ ማህበረሰብ ተኮር የቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀምና ቆሻሻን መልሶ ለጥቅም ማዋልን ያካተተ ሲሆን ይሄን ሁሉ ያካተተው ፕሮግራሙ ለችግረኞች መተዳደርያ ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ  በአንድ በኩል ለችግረኞች የገቢ ምንጭ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የከተማዋን የቆሻሻ ችግር በመፍታት አስተዋፅኦ አድርጓል። ተጠቃሽ ከሆኑ ፕሮጀክቶቹ  ፌስታልአርት /የፌስታል ጥበብ/ ይገኝበታል። የተጣሉ ትናንሽ ፌስታሎችን በማጠብ፣ በቁመታቸው ከቆራረጡ በኋላ፣ ዘንቢል በመስፋት ለገበያ ይቀርብ ነበር። ፕሮጀክቱ እጅግ ስኬታማ ከመሆኑ የተነሳ ሴቶች የተጣሉ ፌስታሎችን መልሰው ወደ ምርት ከመቀየር ይልቅ አዳዲስ ፌስታሎች እየገዙ ዘንቢል በመስራት መሸጥ ጀመሩ። ይሄኔ ነው ድርጅቱ የፌስታል ቆሻሻን የመከላከል ፕሮጀክቱን ያቆመው። ድርጅቱ በሪሳይክሊንግ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች /በሙያቸው የተነሳ በአጠቃላይ የሚናቁና በደርግ ዘመን እንደ ሰላይ ይቆጠሩ የነበሩትን/ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ ስራዎችን እንደሰሩ ለማሳየት፣ የተለያዩ የእደጥበባት ስራዎቻቸውን /ለምሳሌ የሰርግ ጫማዎችን ጨምሮ ከጎማ በየተለያዩ ስታይሎች የተሰሩ ጫማዎችን/ በመቅረፅ አሳይቷል። የወጥ ቤትና ሌሎች ቆሻሻዎችን ለማዳበርያነት እንዲውሉ መቅበር ሌላው የቆሻሻ አወጋገድና ቁጥጥር መንገድ ሲሆን የከተማ ግብርናን ማስፋፋት የ ENDA ቀደምት ፕሮጀክት ነበር። በኋላ ላይ ይሄን ፕሮጀክት ሌሎች ተቋማት በመውሰድ የከተማ ልማት ፕሮግራሞቻቸው ውስጥ አቀናጅተው ተጠቅመውበታል።

እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም በካሚሌ እና በእርዳታና ማስተባበሪያ ማዕከል በምትሰራው /የቀድሞ የፍሬንድስ ኦፍ አርዝ ኖርዌይ ዋና ፀሃፊ/ ዳግ ሃሪድ አነሳሽነት ለአካባቢ የሚቆረቆሩ የተለያዩ ሰዎች መሰባሰብ ጀመሩ። በቡድኑ ውስጥ ከተካቱት መካከል  ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሄር፣ ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ፣ ክፍሌ ለማ፣ አልማዝ ተረፈ እና ባለቤቷ ጉንደር ኢድስትሮም፣ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ሌሎችም የሚገኙበት ሲሆን በወር አንዴ በእራት ላይ እየተገናኙ በኢትዮጵያ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ጀመሩ። ይሄ ብቻ ግን በቂ አልነበረም። ስለአካባቢ ጥበቃ ለማስተማርና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚጣጣሙ ፖሊሲዎችና አሰራሮች እንዲቀረፁ መሟገት ይቻል ዘንድ ህጋዊ ድርጅት ለማቋቋም ወሰኑ። በ ENDA ስር የሚተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ፎረምም መሰረቱ። ቡድኑ ከቢሮክራሲ ጋር መታገልና መነሻ የድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰብ ፈተና ቢሆንበትም፣ ጨቅላው ድርጅት ራሱን ችሎ ለብቻው እስኪቆምና የራሱን አስተባባሪ እስኪቀጥር ድረስ ካሚሌ በህይወት አቆይታዋለች።
ሁለተኛው የፎረሙ ዳይሬክተር በሆኑት በንጉሱ አክሊሉ አመራር፣ ድርጅቱ  ዛሬ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ታዋቂና ጠንካራ ተሟጋች ለመሆን በቃ። አሁንም ድርጅቱ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን የማስፋፋት ስራ እያካሄደ ይገኛል።
እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም ENDA ለቀድሞዋ የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ለአዜብ ግርማይ ብልህ አመራር አስረክባ የወጣችው ካሚሌ፤ የቤልጂየም መንግስት የልማት ተራድኦ እንቅስቃሴ ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ፕሮግራምን መምራት ጀመረች። እዚያ በሰራችባቸው አምስት ዓመታት ከሌሎች ድርጅቶች በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች ድጋፍ አድርጋለች።

የቤልጂየሙ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ከተዘጋ በኋላ በአማካሪነት፣ በፀሃፊነት፣ በአርታኢነትና በተርጓሚነት የሰራችው ካሚሌ፤ አልፎ አልፎም የግምገማ ስራዎች ላይ ተካፍላለች። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን፣ ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን ከመንግስት ባለስልጣናትና የፓርላማ አባላት ጋር ያገናኘውንና በአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲና አሰራር ዙሪያ ያወያየውን የሄንሪክ ቦል ፋውንዴሽን ግሪን ፎረም አስተባብራለች። በአሁኑ ሰዓት ቀጣይ ትኩረቷ ምን እንደሚሆን ለመወሰን \\\\\\\”ጥሪዋን እየጠበቀች\\\\\\\” ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ በሁለት እግሩ እንዲቆም አስተዋፅኦ እንዳደረገች ታስባለች። አሁን ደግሞ አዲስ ተመክሮ የምታፈላልግበት ጊዜ ላይ ናት። ምናልባት በእስያ አገራት የተመረጡ ተመክሮዎች ላይ ጥናት /case studies/ እያደረገች መፃፍ ትጀምር ይሆናል።

ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ለውጭ ዜጎች ትሁት በመሆናቸውና ካሚሌ በአብዛኛው ንቃተ ህሊናቸው ከዳበረ ባልደረቦች ጋር በመስራቷ፣ እንደ ሴት በሙያዋ ላይ ብዙ ፈተናዎች አልገጠሟትም። ሆኗም የኢትዮጵያ ሴቶች የሚጋፈጧቸውን ችግሮች አሳምራ  ታውቃለች። ለሃሳባቸውና ለችሎታቸው ትኩረት የሚሰጥ እንደሌለና ክብራቸውን ለማስጠበቅ ያላቸውን የዓላማ ፅናት ትረዳለች። ዕድሉ በገጠማት ጊዜ ሁሉ ሴቶችን በስራ መስካቸው በማሳደግ አበረታታለች። ሴቶች ታማኝ፣ ሃቀኛ እና ጠንካራ መሆናቸውን ከራሷ ልምድ በመነሳት የምትመሰክረው ካሚሌ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ በሚሰሩ ጊዜም ጥሩ ለመስራትና ለውጥ ለማምጣት በልባዊ ፍቅር ይነሳሳሉ ትላለች።

አገሪቱ ህዝቦች እንደህዝብ ያላቸውን እሴት ሳታጠፋና አካባቢን ሳትጎዳ ድህነትን እንደምታጠፋ ተስፋ የምታደርገው ካሚሌ፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የአካባቢ ጉዳት እየደረሰ  ነው ባይ ናት። ኢትዮጵያውያን አካባቢያቸውን ለጉዳት ሳያጋልጡ የተፈጥሮ ሃብታቸውን በብልህነት እንደሚጠቀሙበትም ታልማለች። ወጣቶች በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ላይ በስፋት መሳተፋቸው ቢያበረታታትም የማታ ማታ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚችሉት የመንግስት ፖሊሲዎችና ህጎች ናቸው ትላለች። ኢትዮጵያ የቻይናን ዱካ በመከተል ፈጣን እድገትና ለውጥ ማስመዝገብን መርጣለች የምትለው ካሚሌ፤ ነገር ግን ቻይና ግዙፍ የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች እንዳሉባት፣ይሄንንም ኢትዮጵያ እንደምትገነዘብ ተስፋ ታደርጋለች። ለእድገት ቅድምያ ሰጥቶ በኋላ ለአካባቢ ጥበቃ መጨነቅ እንደማያዋጣ በመግለፅም ነገሩ ቻይናን ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ ትናገራለች። የኋላ ኋላ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናት።
ለዛሬ ታዳጊ ሴቶች ካሚሌ ስትመክር እንዲህ ትላለች – ሳትታክቱ ተጣጣሩ፣ አይቻልም ወይም አይሆንም የሚል ምላሽ ፈፅሞ አትቀበሉ። በአንድ ነገር ከልባችሁ ካመናችሁ እንደምትፈፅሙት ቅንጣት ታህል አትጠራጠሩ። አንደኛው መንገድ አልሆን ቢል  ሌሎች መንገዶች አሉ። ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥታችሁ አስቡ። ሌላ መንገድ፣ ሌላ መላ ፈልጉ። ደግሞ ብቻችሁን አትሁኑ። መስራት ስለምትፈልጉት ነገር ለሌሎች አወያዩ። ለምትሰሩት ስራ ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ማግኘታችሁ አይቀርም። እነዚያን ሰዎች ለማግኘት ሃምሳ ሰዎች ማናገር ቢኖርባችሁ እንኳን ወደ ኋላ አትበሉ። ከዚያ ደግሞ የስራ ባልደረቦች ይኖራችኋል። ከአንድ ጭንቅላት ሁለት ይሻላል። ሶስት ሲሆን ደግሞ የበለጠ ነው። ወጣቶች ለሚያምኑበት ነገር መታገልና ዓለምን የሚለውጥ ዘር መዝራት አለባቸው። ጋንዲ እንደሚለው፤ \\\\\\\”መስራት የምትችሉት ትንሽ ሊሆን ይችላል።  ግን የምትችሏትን መስራት አለባችሁ። ዓለምን የምንለውጠው በዚህ መንገድ ነው።\\\\\\\”
በሰዎች ማመን በጣም አስፈላጊ ነው ብላ ታምናለች – ካሚሌ።  ወጣቶች ሊያነጋግሩን ወደ እኛ ሲመጡ ሌላ ምንም ባናደርግላቸው እንኳን ዝም ብለን በማዳመጥና ሃሳባቸውን በመደገፍ ልናበረታታቸው ይገባል። ሰዎች የሚያዳምጣቸውና \\\\\\\”አዎ ትሰሩታላችሁ፤ ታደርጉታላችሁ\\\\\\\” የሚላቸው ካገኙ ከምንገምተው በላይ ብዙ ሊሰሩ ይችላሉ።

 


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከካሚሌ ዴ ስቱፕ ጋር እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም
አጥኚ
ሜሪ – ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>