Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

እማሆይ ወለተማሪያም ገላው

Emahoy2

ዋና ዋና ስኬቶች:
በምስራቅ ጎጃም የመንፈሳዊ ማህበር (ገዳም) መስራች፤ የአካባቢን ተፈጥሮ የሚጠብቅ አስተራረስ ዘዴ አስተማሪ፤ የተፈጥሮን ክብካቤ መሰረት ያደረገ አኗኗር እና የደን ጥበቃ ተቆርቋሪ፤24 ሄክታር መሬት ለደን ልማት፣ ለእርሻ እና ለህብረተሰብ አገልግሎት እንዲውል በማድረግ 70 ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረጉ
ወቅታዊ ሁኔታ መነኩሴ እና 70 የሚሆኑ ሰዎችን አስተዳዳሪ
የትውልድ ቦታ: ቋሺባ ቂርቆስ ማቻክል ወረዳ፤ ምስራቅ ጎጃም፣
የትውልድ ዘመን: 1961-1963
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ:
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
መደበኛ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልተማሩም
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  እማሆይ ወለተማሪያም በምንኩስና አገልግሎት 70 የሚሆኑ ማህበረሰቦችን የሚመሩና  እና የሚያስተዳድሩ፤ የአካባቢን ጥበቃ መሰረት ያደረገ አስተራረስን በመከተል በምስራቅ ጎጃም ያሉ ነዋሪዎችን የሚያስተምሩ መነኩሴ ናቸው፡፡  በቋሺባ ቂርቆስ መንደር በምስራቅ ጎጃም ማቻክል ወረዳ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለዱት እማሆይ ለቤተሰባቸው አምስተኛ ልጅ ነበሩ፡፡  ምንም እንኳ በደረግ ስርዓት የመሰረተ ትምህርት እንዲማሩ ቢገደዱም፤ በፈተናም ባለማለፋቸው ቢቀጡም እንኳ፤ ለትምህርት የነበራቸው ፍላጎት በጣም አናሳ ነበር፡፡ እማሆይ በ 10 አመታቸው ለጋብቻ ተሰጥተው በሃያዎቹ መጀመሪያዎች ሁለት ልጆችን ወልደዋል፤ ኑሮአቸውን ልጆች በማሳደግ፤ እና በእርሻ ቀጠሉ፡፡ እማሆይ ገና ወጣት ሳሉ ነበር ቤተሰቦቻቻው፤ እና ብዙ ቤተዘመዶቻቸው በህመም ያለቁት፡፡ እናም የእኔምህይወት እንደቤተዘመዶቼ አጭር ይሆናል የሚል እምነት አደረባቸው፡፡ ሆኖም ህይወታቸውን አደጋ ላይ ከሚጥል ህመም ሲድኑ ህይወት ለእርሳቸው የተለየ እጣ ፈንታ እንዳዘጋጀችላቸው አመኑ፡፡
ፈጣሪ አለማዊ ህይወት እንዲኖሩ እንዳልፈቀደ በማመን ቤተሰቦቻቻን ጥለው አምላክን ለማገልገል ወደ ገዳም ገቡ፡፡  ከመንደራቸው ርቀው ወደ ላሊበላና ግሸን ለመሄድ ምኞት ቢያድርባቸውም፤በህልማቸው  በተደጋጋሚ ዋሻ ይታያቸው ነበር፤ ይህንንም አምላክ እዚያ ሄደው እንዲኖሩ እየተናገረኝ ነው ብለው አሉ፡፡ ግራራም ማርያም በሚባል አካባቢም የቤተክርስቲያን ግምባታን አስተባብረው አሰሩ፡፡ እዚያው አካባቢም ዋሻ አለ ሲባል ሰምተው ወርደው ሲያዩት በህልማቸው በተደጋጋሚ ይታያቸው የነበረው አይነት ሆኖ በማግኘታቸው እዚያው ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡ ዋሻው አጠገብ የምንጭ ውሃ ያለበት፤ የዱሩ አራዊቶች ጅብ፤ ነብር እና ሌሎችም የሚኖሩበት ነበር፡፡ እማሆይ በዚህ ዋሻ ውስጥ እንስሳቶቹን ሳይፈሩ ለሁለት አመታት ሲኖሩ ማንም መጥቶ የሚያያቸው አልነበረም፡፡ በ 1984 ከሁለት አመታት በኋላ በፋሲካ እለት ሁሉም እንስሳት ከሁለት ነብሮች በቀር ዋሻውን ለቀው ተሰደዱ፤ እማሆይም ይህ እግዚአብሄር ዋሻውን ገዳም ሊያደርገው በማቀዱ የላከው ምልክት ነው አሉ፡፡ በ 1986 የአቡነ ተክለሃይማኖት እና የቅዱስ ኡራኤል ታቦቶች ገብተው ዋሻውና አካባቢው ገዳም ሆኖ ተቆረቆረ፡፡ ወደ ገዳሙም የመንፈሳዊ አገልግሎትን በመሻት ብዙ ሰዎች የሚመጡበት ሆነ፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ ሌሎች ገዳማት በተለየ መልኩ ገዳሙ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ማህበረሰባዊ አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ፡፡ ሌሎች ሴት መነኮሳት የሚኖሩበት ከመሆን ባሻገር፤ እነዚህ መነኮሳት የእራሳቸውንና የሌሎችን ህይወት ለማሸነፍና ለማሻሻል በከባድ ስራ የተጠመዱ ናቸው፡፡  በ1988 ዓ.ም ለግብርናና መሬት አስተዳደር ለምነቱን ያጣና የተራቆተ መሬት እንዲሰጣቸው ባገቡት ማመልከቻ 24 ሄክታር መሬት እንዲያለሙ ተሰጣቸው፡፡ ዛፎች በመትከል የጀመሩት የተፈጥሮ ክብካቤ የአካባቢው ነዋሪ ዛፎቹን በመቁረጥ፤ መሬቱን ለከብቶቹ የግጦሽ መሬት እንዲውል በማድረግ ቢያስችግራቸውም በጸሎት እና በትምህርት የአካባቢውን ህብረተሰብ ትብብር ለማግኘት ችለዋል፡፡ ይህ ቦታ አሁኑ በማህበረሰቡ ትልቅ ሃብት ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ አካባቢው በደን በመልማቱ እና የተፈጥሮ ልምላሜውን በማግኘቱ ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ የዱር እንስሳት መኖሪም ሆነ፡፡ እማሆይ እያደረጉ ያሉትን ጥረት በመመልከት አራት የእህል ወፍጮ እና አንድ የዳቦ መጋገሪያ ከደጋፊዎቻቸው አጠገባቸው ከምትገኝ አማኑኤል ከተባለች ከተማ በስጦታ አገኙ፡፡ አሁን የክልሉ መስተዳድር 12 ኪ.ሜ የሚሆን ገዳሙን ከዋናው መንገድ የሚገናኝ መንገድ ላይ በመስራት ላይ ይገኛል፤ ለገዳሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በእቅድ ላይ ነው፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ የሆኑት እማሆይ ሃይል ቆጣቢ ምድጃ አለ መባሉን ሰምተው ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ የጂቲዜድ ሰራተኞችን አግኝተው ስለስራቸው አነጋገሩቸው፡፡  በዚህን ግዜ አቶ ሙሉአለም ብርሃኔ እና ወ/ሮ ውብ አለም መንግስት የተባሉት ሰዎች እነዚህን ሃይል ቆጣቢ ምድጃዎች እንደሚሰሩና የአረንጓዴ ሽልማት ተሸላሚዎች መሆናቸውን ከጂቲዜድ ሰራተኞች ሲነገራቸው ወደ እነርሱ በመሄድ ትምህርት ይቀስማሉ፡፡ አሁን እማሆይ ከሚስተዳድሩት ማህበረሰቦች ጋር በመሆን ሃይል ቆጣቢ የሆኑ ምድጃዎችን በማምረት ለአካባቢው ገበሬ በመጠነኛ ዋጋ ያቀርባሉ፡፡ የዘመናዊ ንብ እርባታ እና ከብት ርቢ በማካሄድ ለአካባቢው የመጀመሪያ ናቸው፡፡ በስራቸው የሚያስተዳድሯቸው ሴቶችም ሆኑ ወንዶች መነኮሳት እርሻውን ጠንክረው በመስራት የተለያዩ አይነት ፍራፍሬዎችን፤ የአትክልት ምርቶችንና የሸንኮራ ምርት ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ትርንጐ የመሳሰሉትን እያመረቱ ለገበያ በማቅረብ ከሚገኘው ገቢ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ከመደገፍም ባሻገር 7 ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ማሳደጊያ እንዲውል አድርገዋል፤ አረጋውያንንም ይጦራሉ፡፡ የቆሎ ትምህርት ቤትም ለአካባቢው ተማሪዎች አቋቁመዋል፡፡ አሰራሩ ይኖሩበት የነበረውን ዋሻ በሚመስል መልኩ በማድረግ እማሆይ ለአካባቢው ነዋሪ ቤተክርስቲያን አሰርተዋል፡፡
እማሆይ ባለ ብዙ እቅድ የሆኑ መናኝ ናቸው፡፡  ለመነኮሳቱ መኖሪያ የሚሆን ቤት የማሰራት፤ የቅኔና ዜማ ትምህርት ቤት የማቋቋም፤ ዘመናዊ ትምሀርት ቤትና ህክምና መስጫ ጣቢያ የማቋቋም፤ መኪና ገዝተው ምርቶችን ወደገበያ ለመውሰድ ህልም አላቸው፡፡ እማሆይ ለስኬቶቻቸው ያጋጠሟቸው ውጣ ውረዶች ጥንካሬ እንደሆኗቸው ይናገራሉ፡፡ ገዳሙ ቀደም ሲል የተፈጥሮ ሃብትን  በአግባቡ የማይጠቀም ለነበረው የአካባቢው ነዋሪ እንደሞዴል ወይም እንደማስተማሪያ ተደርጎ እንደሚታይ እማሆይ ይናገራሉ፡፡
እማሆይ ወለተማሪያም በገዳማዊ ህይወት ለየት ያለ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ይህም እግዚአብሄር ጠንክረን በመስራት፤ የተሰጠንን ችሎታ በመጠቀም ሌሎችን እንድንረዳ እንደሚፈልግ ያምናሉ፡፡ ጠንክሮ የሚሰራ ሰው የስራውን ዋጋ ያገኛል ይላሉ፡፡ እማሆይ በስራ ይረካሉ፡፡
ወጣት ሴቶች በጥንካሬ ፈታኝ ሁኔታዎችን ማለፍ እንደሚችሉ፤ እራሳቸውን እንዲጠብቁ፤ ከእግዚአብሄር የተሰጣቸውን ስጦታ ብቃታቸወን በማሳደግ እንዲጠቀሙ እና እራሳቸውን ለእግዚአብሄር እንዲያስገዙ፤ ማህበረሰብን እንዲያገለግሉ ይመክራሉ፡፡

 


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከእማሆይ ወለተማሪያም ገላው ጋር የተደረገ ቃለመጠይቅ፣ ግንቦት 2004
አጥኚ
ወደር አበበ እና ሜሪ ጄን ዋግሌ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>