Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

እናና ውበት

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ከባዶ ተነስታ፣ በርካታ ፈተናዎችን አሸንፋ፣ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኗ ሳያግዳት በራሷ ጥረት ስኬታማ ለመሆን የበቃች የንግድ ባለሙያ፤ ሰራተኞቿንና የአካባቢዋን ማህበረሰብ በለጋስነት የምትደግፍ
ወቅታዊ ሁኔታ የንግድ ባለሙያ እና የንግድ ህንፃዎች ባለቤት
የትውልድ ቦታ: ኢንፍራንዝ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ኢትዮጵያ
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: ጎንደር
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ጀምራ ያላጠናነቀቀች
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ከልጅነት እስከ እውቀት በበርካታ ፈተናዎች ተከብባ የኖረችው እናና፣ ራሷን ሰው ለማድረግና ስራዋን ለማቅናት ትንሽ ትልቁን ችግር ተቋቁማ በማሸነፍ በጎንደር ከተማ የተዋጣላት የንግድ ባለሙያ ሆናለች። ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ብትሆንም፤ ለሌሎች ወገኖቿ ምሳሌና አርአያ ናት። ከቫይረሱ ጋር መኖር፣ ሰዎች የፈለጉትን ከማሳካት ሊያግዳቸው እንደማይገባ በራሷ ህይወት አሳይታለችና። ሞራሏና የስራ መንፈሷ፣ ቅንጣትም ታህል አልተነካም – እንደተነቃቃ ቀጥሏል። ለእናና፣ ሃብት ማካበት ዋና ጭንቀቷ አይደለም። ይልቅ፣ ለወገኖቿ የምታስብ አዛኝና ሩህሩህ ሴት ናት፤ ለበጎ አድራጎት ስራ ዘወትር ደፋ ቀና ትላለች።

በሰሜን ጎንደር በኢንፍራንዝ ከተማ ከድሃ ቤተሰብ የተወለደችው እናና፣ በልጅነቷ ትምህርት ቤት የገባችው ለወደፊት ህይወቷ የተሻለ እድል ይፈጥርላታል በሚል አይደለም። ወላጆቿ እጅግ ደሃ ከመሆናቸው የተነሳ ባል ሊያገኙላት ስላልቻሉ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ ወላጆቿ በፍቺ ተለያዩ። እናቷ ኑሮን ለማሸነፍ ጠላ እየጠመቁ ሲሸጡ፤ ታዳጊዋ እናና ቀን ተሌት በጓዳና በኩሽና እየዳከረች እናቷን ማገዝ ነበረባት። በስራ ብዛት በአተላና በጥቀርሻ የተልኮሰኮሰ ልብሷን አድርጋ በመሄዷ፣ ከትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ በተደጋጋሚ ተባራለች። ለነገሩ ብዙም አልዘለቀችበትም። የማታ ማታ ከነአካቴው ትምህርት ቤት መሄዱን አቆመች። ተባርራ ሳይሆን፤ እናቷ “ትምህርት ዕጣ ፈንታሽ አይደለም” ብለው ስለከለከሏት ነው። ከዛ በኋላማ መከራዋ በዛ። ከወትሮው የኩሽና ስራዋ በተጨማሪ፤ ወንዝ ሄዶ ውሃ የመቅዳት እዳ ተጣለባት። የእናቷ ሃሳብ፤ በእናና ፋንታ ወንድሞቿ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ነው። እናና ያንን የልጅነት ጊዜዋን ስታስታውስ፤ በገዛ እናቴ ቤት ውስጥ፣ እንደ ቤት ሰራተኛ ነበርኩ ትላለች።

እናና በ18 አመቷ ከእናቷ ቤት የወጣችው፤ በደብረታቦር ወህኒ ቤት ታስሮ ከነበረ ሰው ጋር ትዳር ለመመስረት ነው። ሰውዬው ለሙሽሪቷ ለእናና ያመጣላት ጥሎሽ፤ አንድ ቀሚስ፤ አንድ “ኮንጎ” ጫማና አንድ ነጠላ ሲሆን፤ ለጥሎሹ የወጣው ጠቅላላ ወጪ 15 ብር ብቻ ነበር። ከባሏ ጋር ወደ ጎንደር ያቀናችው እናና፤ እጇን አጣጥፋ ያለ ስራ መቀመጥ ስላልሆነላት፣ መጀመሪያ ባቄላ መሸጥ ጀመረች፤ ከዚያም ጌሾ። ባሏ የሚያውቀው ጥልፍ መስራት ብቻ ነው – ወህኒ ቤት ሳለ የተማረው። እንዳለመታደል ሆኖ የእናና ባል ብዙም አላዛለቃትም። በደርግ የቀይ ሽብር ዘመን ለተገደለባት ባሏ የ13ሺ ብር ካሳ የተቀበለች አንዲት ሴት አገኘሁ ብሎ፤ እናናን ጥሏት እብስ አለ። ትዳሯ ፈርሶ ህይወቷ ተናጋ። በዚያ ላይ ጋለሞታ መባልም አለ። አዲስ የትዳር ህይወትና ተስፋ እንደማይኖራት አስባ በእንባ ጎርፍ ታጠበች።
ወዲያው ወደ ኢንፍራንዝ ተመልሳ እናቷ ቤት የገባችው እናና፤ ያልሞከረችው የስራ አይነት የለም። ጠላ ከመጥመቅ መጥረጊያ እስከ መሸጥ በርካታ የተለያዩ ስራዎችን እየተሯሯጠች በመስራት 900 ብር ለማጠራቀም ቻለች። ያኔ ዘጠኝ መቶ ብር ቀላል ገንዘብ አልነበረም፤ ቤት ገዛችበት። ቤቷ ከዋናው መንገድ ዳር ስለነበር፤ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ‘የሚሸጥ ምግብ አለ ወይ?’ እያለ ሲወተውታት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለላት። ያኔ ነው እጇ ላይ በነበረችው መቶ ብር በማትሞላ መነሻ ገንዘብ፣ ትንሽዬ ምግብ ቤት ለመክፈት የወሰነችው። እንዳሰበችው ሆነላትና ምግብ ቤቷ በጣም ዝነኛ ሆነች። በከተማዋ የሚያልፉ የአውቶቡስ ሾፌሮች፣ ተሳፋሪዎችና መንገደኞች፤ ቁርስና ምሳ ፍለጋ ወደ ምግብ ቤቷ ጎራ ማለት ያዘወትሩ ጀመር። እሷም ከሾፌሮች ጋር ቅርበቷ እየጨመረ በመምጣቱ፣ በየአውቶብሱ ውስጥ እየገባች፤ የተለያዩ ምግቦችና ሻይ-ቡና ለተሳፋሪዎች መሸጥ ያዘች። ገበያው ሞቀላት፤ ስራው ሰመረላት። ራሷ ለመንቀሳቀስም ሆነ እቃዎቿን ለማመላለስ የትራንስፖርት ችግር አልነበረባትም – ሾፌሮች የት ሄደው! እንዲያውም፤ እናና በሾፌሮች ዘንድ ዝናዋ እጅግ ከመናኘቱ የተነሳ፤ ዘፈን ሁሉ አውጥተውላታል። ክፋቱ ግን፤ ያኔ ሰላም አልነበረም። አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ የምትታመስበት ወቅት ነበር። እናም አንድ ቀን፤ “ትሃህት” በመባል የሚታወቁ የኢህአዴግ ተዋጊዎች ይመጡና ጨው እንደጫነ እቤቷ በር ላይ ቆሞ የነበረውን መኪና ያቃጥላሉ። ይህን ተከትሎ፤ የእናና ምግብ ቤት ኦና ሆነ። አብዛኞቹ ደንበኞቿ ሸሿት፤ ከፍተኛ ኪሳራም ደረሰባት።

በኪሳራው ወድቃ አልቀረችም። ተመልሳ ወደ ጎንደር በመሄድ፤ አንድ ስራ ፈትቶ የተቀመጠ ትንሽዬ ሱቅ አግኝታ፤ የንግድ ስራ ማጧጧፍ ጀመረች። ጎንደርን ከዳር ዳር ለማዳረስ ጊዜ ያልፈጀበት የእናና ስም፤ ከሁሉም አንደበት የማይጠፋ ቃል ሆነ። ሆኖም ዝና ሳያታልላት፣ ወጪና ገቢዋን በጥንቃቄ በመቆጣጠር በቂ ገንዘብ ለማጠራቀም በመቻሏ፤ 22ሺ ብር የሚያወጣ ቤት ገዛች። ከቀድሞው የበለጠ አዲስ ምግብ ቤትም ከፈተችበት። ምግብ ቤቷን ‘አንድነት’ ብላ የሰየመችው አለምክንያት አይደለም። የፆም ምግቦችን ብቻ በማሰናዳት ክርስትያኖችንና ሙስሊሞችን በአንድነት ስለምታስተናግድበት ነው። ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ምግብ ቤቷ፤ በተለይ ጣት በሚያስቆረጥሙ የአሳ ምግቦች ይታወቃል።

ስኬት ስኬትን ይወልዳልና፣ ከመኖሪያ ቤቷ በተጨማሪ፣ ሁለት ለንግድ የሚውሉ ህንፃዎች ባለቤት ለመሆን በቃች። የንግድ ስራዎቿን እያስፋፋች የመጣችው እናና፤ 30 ለሚጠጉ ሰዎች ‘ህይወትን የሚቀይር’ የስራ እድል ፈጥራለች። ደግሞም የሰራተኛ አያያዝ ታውቅበታለች። የሰራተኞችን የእለት ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ፤ ለቤተሰቦቻቸው የህክምና ወጪ ትሸፍናለች። እንዲያውም ለአንድ ሰራተኛ መኪና ገዝታ እስከመስጠት ደርሳለች – ለበርካታ አመታት ላበረከተው ታማኝ አገልግሎቱ። ከሁሉም በላይ ግን፤ እናና በቁጠባ ላይ ባላት የማይናወጥ እምነት ትታወቃለች። “ዛሬ መቶ ብር ያገኘ ሰው ከ25 ብር በላይ ማጥፋት የለበትም፤ ቀሪውን 75 ብር ለነገ ቆጥቦ ማስቀመጥ አለበት” የምትለው እናና፤ ለእያንዳንዱ ሰራተኛ የባንክ ሂሳብ በመክፈት ገንዘብ እንዲቆጥቡ ታበረታታለች። በዚህም መንገድ፤ ብዙዎቹ የቀድሞ ሰራተኞቿ የራሳቸውን ሱቅ ለመክፈት በቅተዋል።

እናና ሶስት ልጆችን አድርሳለች። ሁለት ሴት ልጆቿ የሚኖሩት በአውሮፓ ሲሆን ወንድ ልጇ ጎንደር ነው። በኤችአይቪ ኤድስ ወላጆቻቸውን የተነጠቁ ሦስት ህፃናትንም በግል ትምህርት ቤት እያስተማረች አሳድጋለች – የግል አስጠኚ በመቅጠር ጭምር።

እናና ፈፅሞ ሰርታ አትደክምም። በስራ ጉዳይ ላይ፤ የወንድና የሴት የሚባለው የዘልማድ ክፍፍል አይዋጥላትም። ለምሳሌ ህንፃዎቿን ስታስገነባ፣ ከቀን ሰራተኞቿ ጎን ሳትጠፋ፤ አሸዋና ሲሚንቶ፣ ምስማርና ጣውላ አቀብላለች። ታትሮ በመስራት ህይወታችንን መለወጥ እንችላለን የምትለው እናና፤ ስራ መቀጠር ካልቻልን ስራ በመፍጠር የጥገኝነትን ባህል ማስወገድ አለብን ብላ ታምናለች። ቢሆንም ግን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የእለት ምግባቸውን ማግኘት ያቃታቸው ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ስለሚያሳስባት፤ ከአገራችን ከርሰ ምድር ነዳጅና ሌሎች ማዕድናት ቢገኙ ምኞቷ ነው። ሰዎች የተሻለ ገቢ የሚያገኙበት፤ የግድቡ ግንባታ የሚጠናቀቅበት፣ ልጆች በተሻለ ትምህርት ቤት ውስጥ ጥራት ያለው ትምህርት የሚያገኙበት ጊዜ እንዲመጣ ታልማለች። የነገዋ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን ማድረግም ምኞቷ ነው።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከእናና ውበት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
አጥኚ
ወደር አበበ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>