Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)

Elizabeth WoldeGiorgis Small

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም የመጀመሪያ ሴት ዳሬክተር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትዕይንተ ጥበባትና የስነ ጥበብ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዳሬክተር
ወቅታዊ ሁኔታ የትዕይንተ ጥበባትና የስነ ጥበባት ኮሌጅ ዳሬክተር፣ አዲስ አበባ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1948
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ናዝሬት ስኩል፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ተመራማሪ ምሁር፣ ደራሲ፣ የትምህርት ባለሙያ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርትና የጥናት ተቋም ሃላፊ ነች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም የመጀመሪያዋ ሴት ዳሬክተር ነበረች። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተቋቋመው የትዕይንተ ጥበባትና የስነ ጥበባት ኮሌጅም የመጀመሪያ ዳሬክተር በመሆን አገልግላለች።

በ17 አመቷ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አልማ ወደ አሜሪካ የሄደችው ኤልሳቤጥ፣ ቀጣዮቹን 27 አመታት እዚያው አገር አሳልፋለች። በባልቲሞር ሜሪላንድ ከሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪዋን አግኝታ ከተመረቀች በኋላ፤ በሳንፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያም ከጎልደን ጌት ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪዋን ተቀብላለች። በባንክ ዘርፍ የስራ ህይወቷን የጀመረችው ኤልሳቤጥ፣ አነሳሷ ከዝቅተኛ የስራ ደረጃ ቢሆንም፤ በየጊዜው ራሷን እያሳደገች በአሜሪካ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁት ባንኮች አንዱ በሆነው በባንክ ኦፍ አሜሪካ የኦፕሬሽን ማኔጀር ለመሆን በቅታለች። ከዚህ በኋላ ነው ኑሮዋን ዋናዋ የንግድ እምብርት ወደሆነችው ኒው ዮርክ በማዛወር፤ በጃፓናዊያን በተመሰረተው ሚዙሆ ኮርፖሬት ባንክ የብድር ኦፊሰር እና የንግድ ወኪል ሆና መስራት የጀመረችው። ቢሮዋ በኒው ዮርክ የአለም ንግድ ማዕከል ሕንፃ ላይ ነበር። መስከረም 1 ቀን 1993 ዓ.ም በህንፃው ላይ የአሸባሪዎች ጥቃት ሲደርስም በቢሮዋ ውስጥ ነበረች። ኤልሳቤጥ ከአደጋው በህይወት ተርፋለች። ነገር ግን ክስተቱ ህይወቷን የሚያናውጥ ድንጋጤን ፈጥሮባታል። አለምን ካስደነገጠው የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ የሙያ አቅጣጫዋን ለመቀየር ብትወስንም፤ በስነ ጥበብ መስክና በስነ ጥበብ ታሪክ ላይ ለማተኮር የመረጠችው ግን በአጋጣሚ አይደለም፤ ከልጅነት እስከ እውቀት የምታፈቅረውና የሚመስጣት ስለነበር እንጂ።

በባንክ የሙያ መስክ የነበራትን የ17 አመታት የስራ ህይወት እንደ ዘበት ጥላ በመውጣት፤ በሙዝዬም ጥናቶች የመጀመሪያ ዲግሪ ለማግኘት በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ተመዘገበች።

የዲግሪ ትምህርቷን ልትጨርስ ስትል ነው፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፤ ወደ አገር ቤት እንድትመለስና የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም ዳሬክተር እንድትሆን የጋበዟት። እሷም ግብዣውን ተቀበለች። ከ27 አመታት የአሜሪካ ኑሮ በኋላ ወደ አገሯ የተመለሰችው ኤልሳቤጥ፤ በተቋሙ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዳሬክተር ለመሆን በቃች። ነገሩ አልጋ ባልጋ አልሆነላትም። የመጀመሪያ ሴት ዳሬክተር መሆኗን ተከትሎ፤ ከባባድ ፈተናዎች ተደቀኑባት። በአንድ በኩል ሴት በመሆኗ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የትምህርት ብቃት ማስተርስ ዲግሪ ብቻ መሆኑን ሰበብ በማድረግ፣ ከየአቅጣጫው ተቃውሞና ንቀት ተደራረቡባት። አሜሪካ ውስጥ በፆታና በቆዳ ቀለም የሚያጋጥሙ የአድልዎ አሰራሮችንና ፈተናዎችን ተቋቁሞ የማሸነፍ የረዥም ጊዜ ፅናትና ተሞክሮ ባታዳብር ኖሮ፤ በኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም ውስጥ ለአንዲት ቀን እንኳን መቆየት ፈተና ይሆንባት እንደነበር ኤልሣቤጥ ትናገራለች። ተቋሙን ለሦስት አመታት ከመራች በኋላ በኪነጥበብ ታሪክ እና በትዕይንተ ጥበባት የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመቀጠል ወደ አሜሪካ የተመለሰችው ኤልሣቤጥ፤ ኢታካ ኒው ዮርክ ወደ ሚገኘው ኮርነል ዩኒቨርሲቲ ገባች። የሄደችበትን አላማ ጨርሳ ስትመለስም፣ ተቋሙን ለአመት ያህል እንደገና መርታለች። ከተቋሙ የለቀቀችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚቃን፣ ስዕልን፣ ትያትርን እና የሞደርን አርት ሙዚዬምን ያካተተ አዲስ የትምህርት ማዕከል ሲከፈትና ማዕከሉን እንድትመራ ስትመረጥ ነው። እናም የትዕይንተ ጥበባትና የስነ ጥበባት ኮሌጅ የመጀመሪያዋ ዳሬክተር ሆነች።

ኤልሣቤጥ የተማረና አይዞህ ባይ ቤተሰብ ውስጥ ማደጓ፣ የራሷን የትምህርት ፈለግ እንድትከተልና እንደ አለት የፀና የስብእና መሰረት እንዲኖራት ጠንካራ ድጋፍ ሆኗታል። በአርአያነት የምታያቸው በንጉሡ ዘመን ታዋቂ የስነፅሁፍ ሰውና የአዲስ ዘመን የመጀመሪያ አዘጋጅ የነበሩትን አባቷ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስን ነው። ለቤተሰቧ የመጨረሻ ልጅ የሆነችው ኤልሣቤጥ፤ ታላላቅ ወንድሞቿ በየተሰማሩበት መስክ ስኬትን ሲቀዳጁ አይታለች። ብቸኛ የሆነችው ታላቅ እህቷም በኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ ተመራቂ ነርሶች መካከል አንዷ ነች።

ዛሬ ሃሳብና ህልሟ፤ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ እድገትን የሚዳስስ መፅሐፍ በማሳተም፣ ለዘርፉ መመንደግ የበኩሏን አስተዋፅኦ ማበርከት ነው። በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ታሪክና በዛሬው የኪነ ጥበብ ፍካት ዙሪያ፣ የግንዛቤ አድማስ እንዲሰፋ፤ በዚህም ንቁ ተመልካችነትና ውይይት እንዲያብብ ለማገዝ እችላለሁ ብላ ተስፋ አድርጋለች።

ማንነታችሁን እወቁ በማለት ለኢትዮጵያ ታዳጊ ሴቶች ምክሯን የምትለግሰው ኤልሣቤጥ፣ በዙርያችሁ ካሉት ወንዶች ጋር በእኩል ደረጃ ራሳችሁን ለማቆም ታገሉ ትላለች። ፆታዊ ተዋረድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ተደራጁ፤ የሴቶችን ማዕረግና ክብር ለማሳደግ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳተፉ ስትልም ትመክራለች። እናም ነባሩን ስርዓት ለመጋፈጥ መሰረታዊ ጥቄዎችን አንሱ ትላለች፤ ለምሳሌ በአገራችን ታሪክ እና በመጪው ዘመን የሴቶች ሚና ምንድነው የሚለውን ጥያቄ።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከዶ/ር ኤልሣቤጥ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ቤተል በቀለ ብርሃን

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>