Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አይዳ አሸናፊ ተሰማ

Aida Ashenafi from Sammy - Copy

ዋና ዋና ስኬቶች:
በአሜሪካና በኢትዮጵያ ለ15 ዓመታት የሙያ ልምድ ያካበተች ፊልም ሠሪ ናት፤ የኮሙኒኬሽን ቢዝነስ ላይ የተሰማራ ማንጎ ፕሮዳክሽንስ የተሰኘ ኩባንያ በሽርክና መስርታለች። በማንጎ ፕሮዳክሽንስ ስር፣ የገጠርን ኑሮ የሚቀምሱ የከተማ ወጣቶች ዙሪያ ጉዞ በሚል ርዕስ የሠራችው ፊልም፣ በሦስተኛው አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል አንደኛ ተሸላሚ ሆኗል። በአሜሪካ፣ የኦስካር ተሸላሚ ኢታን ኮኢን በፃፈው የፊልም ድርሰት፣ ‘ኔክድ ማን’ የተሰኘውን ፊልም ሠርታለች። በሁለት የጆኒ ራጋ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ለሽልማት ለመታጨት የበቃችና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮ ሥራ ላይ በፈርቀዳጅ አስተዋፅኦዋ የምትጠቀስ ባለሙያ ናት።
ወቅታዊ ሁኔታ ማኔጂንግ ዳሬክተር፣ ማንጎ ፕሮዳክሽንስ ኃ.የተ.የግ.ማ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣
የትውልድ ዘመን: መጋቢት 21 ቀን 1963 ዓ.ም.
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሳንፎርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ኮኖ ስኩል፣ አየዋ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ኖርዝፊልድ ማውንት ሄርሞን፣ ማሰቹሴትስ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ)፣ በፊልምና በፎቶግራፍ ሙያ እንዲሁም በሥነጥበብ፣ አይተክ ኮሌጅ፣ አይተክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩኤስኤ
ዋና የስራ ዘርፍ
ፊልም ሠሪ
የሕይወት ታሪክ
በፊልም ሙያ ውስጥ ከ15 ዓመት በላይ ስትሠራ የቆየችው አይዳ አሸናፊ፣ የታዋቂ ዘፋኞች የሙዚቃ ቪዲዮ እንዲሁም የማስታወቂያ ሥራዎችን በመምራት፣ እንዲሁም የሙሉ ሰዓት ፊልሞችን በማዘጋጀት ሰፊና ረዥም የሙያ ታሪክ የፈጠረች ባለሙያ ናት። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ስትመጣ፣ በፊልም የሙያ መስክ በአሜሪካ የጀመረችውን ስኬታማ ጉዞ አላቋረጠችውም።  በማንጎ ፕሮዳክሽንስ መሥራችነቷና በኩባንያው መሪነቷ ለአገሬው የፊልምና የኮሙኒኬሽን ሙያ ልዩ የፈጠራና የመነቃቃት ሃይል ይዛ መጥታለች።

አይዳ እዚሁ በተወለደችበት በአዲስ አበባ ከተማ ነው ከሁለት ወንድሞቿ ጋር ያደገችው። አባትና እናት ልጆቻቸውን ኮትኩተው ያሳደጉት፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አርአያነታቸውን በማሳየት  ጭምር ነው። ተግተው እየሠሩና ባገኙትም ነገር እየተደሰቱ፣ ዘወትር በሚከተሉት አኗኗራቸው አማካኝነት፣ የታታሪነትና የደስታ ክቡርነትን ለልጆቻቸው አስተምረዋል። አይዳ፣ በሳንፎርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት ለጥቂት ዓመታት ከተማረች በኋላ፣ ከወንድሟ ጋር ወደ አሜሪካ የተላከቸው፣ አዳሪ ትምህርት ቤት እንድትገባ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት፣ በጥሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር እድል ማግኘቷ፣ ለእድገቷና ለሙያ ጉዞዋ በጣም እንደረዳት ታምናለች። እንዲያውም፣ ጥሩ የትምህርት እድል፣ ከሁሉም የላቀ የወላጆች ስጦታ ነው ትላለች።

አይዳ፣ ያላሰበችውና ያልጠበቀችው የሕይወት አቅጣጫ ያጋጠማት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች ነው። ለተመራቂ ተማሪዎች በሚዘጋጅ የቪዲዮ ሥራ ላይ ስትሳተፍ፣ አይን የበራላትና ከአዲስ ዓለም ጋር የተዋወቀች ያህል ሆኖ ተሰማት። ለፊልም ሙያ በተከፈተው አይኗ ተመርታም፣ በኒው ዮርክ አይተክ ዩኒቨርስቲ ገብታ በሶስት ዘርፎች፣ በፊልም፣ በፎቶግራፍ እና በሥነጥበብ የዲግሪ ትምህርት ለመከታተል ወሰነች። ምንም እንኳ የፊልም ሙያ በዚያን ዘመን፣ ገና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ክብር ለማግኘት ባይበቃም፣ ወላጆቿ ግን የሙያ ምርጫዋን ከልብ ደግፈውላታል። በዩኒቨርሲቲው ለምትሰራቸው ፊልሞች ሙሉ ወጪዎቿን እየሸፈኑላት፣ ፊልሞቿንም ሄደው እያዩላትና እያበረታቷት፣ በ1991 (92) ዓ.ም ተመረቀች።

እንደተመረቀች ወዲህ ወዲያ እያለች ጊዜ አላባከነችም። “አይ ላይክ ኢት ላይክ ዛት” በተሰኘው ፊልም ላይ፣ ያለ ክፍያ በተለማማጅነት ገብታ ለአንድ ዓመት ሠራች። የሙያ ሕይወቷ መባቻ የሆነላት የመጀመሪያው ዓመት ሲጠናቀቅ ነው፣ ለፊልም ሥራው ዋና መሪ (ፕሮዲዩሰር) ረዳት ሆና የተመደበችው። ከዚያም በስኬታማነቱ ስመጥር እየሆነ ወደ መጣው የኒው ዮርኩ ‘ጂቭ ሪከርድስ’ በማምራት፣ የታዋቂ ዘፋኞች የሙዚቃ ቪዲዮ ሥራዎችን በተቆጣጣሪነት መርታለች። ከዓመት በኋላ ደግሞ፣ የፊልም ሥራዎችንና ቅንብሮችን የሚያከናውን ሶስ ኢንተርቴይንመንት የተሰኘ ኩባንያ እዚያው ኒው ዮርክ በሽርክና መሰረተች። የሙያ ድንበሯን እያሰፋች የመጣችው አይዳ፣ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ለሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ሠርታለች። ከእነዚህም መካከል ናይኪ፣ ፓናሶኒክ፣ ኮካ ኮላ፣ ዳርክ ኤንድ ላቭሊ እንዲሁም ቶይስ ‘አር’ አስ ይጠቀሳሉ። አር ኬሊ፣ ባክ ስትሪት ቦይስ፣ ‘ኤ ትራይብ ኮልድ ኩዌስት’፣ ብሪትኒ ስፒርስ፣ ጆ እና የሌሎች በርካታ ታዋቂ ዘፋኞች በየጊዜው የሚያቀርቧቸውን የሙዚቃ ቪዲዮዎች በተቆጣጣሪነት አሠርታለች። በሙያ ሕይወቷ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረችው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙሉ ሰዓት ፊልም በፕሮዲዩሰርነት የመሥራት እድል አገኘች። እንደ ሙያ አባቷ የምትቆጥረው የፊልም ሥራ ባለሙያ ቤን ባሬንሆልዝ፣ በፊልም ሥራ ዝናን ካተረፉት የ‘ኮኢን’ ወንድማማቾች ጋር ሲያስተዋውቃት ነው፣ አስደናቂው እድል የተከፈተላት። በኦስካር ተሸላሚው በኢታን ኮኢን የተፃፈውና ኔክድ ማን የተሰኘውን የፊልም ድርሰት በፕሮዲዩሰርነት ሠራች። ፊልሙ በዩኒቨርሳል ፒክቸርስ አማካይነት ለእይታ ቀርቧል። አይ ቲንክ አይ ዱ የተሰኘው የሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልምን ጨምሮ በርካታ ፊልሞችን የሠራችው አይዳ፣  ሜዲያ ኖቼ የተሰኘ ጥናታዊ ፊልምም ሠርታለች።

በጠና ከታመሙት አባቷ አጠገብ ለመሆን በበ1992 (93) ዓ.ም ወደ አገር ቤት የተመለሰችው አይዳ፣ አባቷ ከሞቱ በኋላ፣ ካክተስ በተሰኘው የማርኬቲንግና የማስታወቂያ ኩባንያ ውስጥ በፈጠራ ዳሬክተርነትና በኦፐሬሽን ማኔጀርነት ኩባንያው እግር ተክሎ እንዲራመድ ረድታለች።

ከካክተስ ወጥታ ለተወሰነ ጊዜ እረፍት ከወሰደች በኋላ ነው፣ እንደገና የሙያ ጉዞዋን እንደአዲስ የጀመረችው። ‘ማንጎ ፕሮዳክሽንስ’ በሚል ስያሜ በ1995 (96) ዓ.ም አዲስ ኩባንያ መሰረተች – በሽርክና ከፈለቀ ደነቀ ጋር።  ሁሉን አቀፍ የኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ለተለያዩ ተቋማት ለማቅረብ አልሞ የተነሳው ማንጎ ፕሮዳክሽንስ፣ ትልልቅ ኩባንያዎችንና ለትርፍ ያልተመሰረቱ ድርጅቶቾችን ጨምሮ፣ ተስማሚ የሥራ ባህልና ባህሪ የተላበሱ ደንበኞችን በመምረጥ አብሯቸው ይሰራል። ከፊልም ሥራ እስከ ማስታወቂያ ቅንብር፣ በህትመት ከሚካሄዱ የህዝብ ግንኙነት ስርጭቶች እስከ ሬዲዮ ፕሮግራም ዝግጅት አገልግሎቶችን ያቀርባል። በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን ስትራቴጂን፣ ማስታወቂያንና የምርት ብራንድን ጨምሮ፣ የደንበኞችን የኮሙኒኬሽን ፍላጎቶች ሁሉ ማሟላት የአይዳ ሥራ ሆነ። አይዳ በማኔጂንግ ዳሬክተርነት የምትመራው ማንጎ ፕሮዳክሽንስ፣ ጉዞ በሚል ርዕስ የመጀመሪያ ጥናታዊ ፊልሙን ሰርቶ ለእይታ ያበቃው የካቲት 29 ቀን 2001 ዓ.ም ነው። 138 ደቂቃ የሚፈጀውን ፊልም በአዘጋጅነት ያሰናዳችው አይዳ፣ የፊልም ሥራውን ከሌላ የሙያ ባልደረባ ጋር በጣምራ መርታለች። የፊልሙ አቀናባሪም (ኤዲተርም) እሷ ነች። 1.2 ሚሊዮን ብር ገደማ የወጣበት ይሄው ፊልም፣ የከተማ ወጣቶች ወደ አገሪቱ የገጠር አካባቢ የሚያደርጉትን ጉዞ ይተርካል። ከተሜዎቹ ወጣቶች የገጠርን ሕይወት በአይናቸው በብረቱ አይተውትና ኖረውበት፣ ችግርና መከራውን እንዲሁም የህዝቡን የጋራ ሰብአዊነት፣ ብልህነትና አዋቂነት ተገንዝበው ትምህርት ሲቀስሙ የሚያሳይ ፊልም ነው። ለፊልሙ ከተበረከቱለት ሽልማቶች መካከል፣ በ2001 (02) ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው አዲስ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በአሸናፊነት የተቀበለው ሽልማት ይጠቀሳል።

አይዳ አሸናፊ፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮ ቢዝነስ ውስጥ ፈር ቀዳጅ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ሐበሻዊ እና ቁልፉን ስጪኝ በተሰኙት የጆኒ ራጋ ሁለት የሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ የመሪነት ሚና ነበራት። በእርግጥም ሐበሻዊ የተሰኘው የሙዚቃ ቪዲዮ በአፍሪካ ደረጃ፣ ሁለተኛው የሙዚቃ ቪዲዮ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በሬጌ ስልት ለምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ሽልማቶች ለመታጨት በቅተዋል። አሁን አሁን፣ ኩባንያው የሙዚቃ ቪዲዮዎችን የሚያዘጋጀው፣ ከሥራው እርካታን ለማግኘት ያህል እንደሆነ አይዳ ትናገራለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሴት በመሆኗ ብቻ የፊልም ባለሙያነቷን ለመቀበል የሚያንገራግሩና በጥርጣሬ የሚያዩዋት በርካታ ሰዎች አጋጥመዋለታል። ነገር ግን፣  በራስ የመተማመን መንፈሷንና ብርታቷን ለአፍታ ያህል ሲያዩ፣ ስሜታቸው ይለወጣል። በአድናቆት አብረዋት ለመሥራት ይጓጓሉ። በሙያዋ ውስጥ ከገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ በጣሙን ያስቸገራት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ዝቅተኛ የሥራ ባህል ጋር የተያያዘው ሠራተኞችን የማስተዳደር ጣጣ ነው። ግን፣ የማይታለፍ ፈተና አይደለም። ሠራተኞች በጥራትና በቅልጥፍና እንዲሠሩ ማበረታታት ይቻላል የምትለው አይዳ፣ ሁነኛ መፍትሄ ሠራተኞችን በአክብሮት ማስተናገድና ትክክለኛውን ማነቃቂያ ማቅረብ እንደሆነ ትገልፃለች። ማንጎ ፕሮዳክሽንስ፣ ለሠራተኞች የረዥም ጊዜ አገልግሎት ቦነስ፣ የሕክምና ወጪ ሽፋንና የአልባሳት አበል ይሰጣል። በትላልቅ ስኬታማ ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ፣ ለሰራተኞቹ ትርፍ ያጋራል። በሠራተኞቹ ላይ እምነት በማሳደርም፣ በስልክና በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ ሰፊ ምርጫ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በእርግጥ ወጪው ቀላል አይደለም። ከኩባንያው ዓመታዊ ወጪ፣ 8 በመቶ ያህሉ ለእነዚህ ተጨማሪ ክፍያዎችና ጥቅማጥቅሞች የሚውል ነው። ቢሆንም፣ ወጪው በአግባቡ ጥቅም ላይ የዋለ ውጤታማ ወጪ ነው የምትለው አይዳ፣ የድርጅቱ ሠራተኞች በአብዛኛው ከስምንት ዓመት በላይ አብረዋት የቆዩ መሆናቸውን ትናገራለች።

አይዳ ለማንጎ ፕሮዳክሽንስ ያላት ህልም፣ ለሥራ እና ለሙያ መርሆች ክብር የሚሰጥ ተቋማዊ ባህልና ስርዓትን ይበልጥ የተጎናፀፈ ኩባንያ ሆኖ ማየት ነው። ጊዜ የማይሽረው ጥሩ የፊልም ታሪክ ለማግኘት እያፈላለገች ያለችው አይዳ፣ የሙሉ ሰዓት ፊልሞችን እንደምትሰራ ታምናለች። እንደስካሁኑ አዳዲስ የሥራ አይነቶችን እየሞከረች የሥራ አድማሷን ለማስፋትም ትመኛለች።

ለወጣት ሴቶች ምክር ስትሰጥ እንዲህ ትላለች፡ ትምህርት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ግን የሥራ ልምድም የዚያኑ ያህል ዋጋ አለው። ወላጆች እና ሌሎች ሰዎች በናንተ ላይ እምነት እንዲያድርባቸው ካደረጋችሁ በኋላ፣ ለወደፊት ሕይወታችሁና ለሙያችሁ መደላድል የሚፈጥር ልምድ የምትቀስሙበትን መንገድ ፈልጋችሁ አግኙ። አንዱ መንገድ፣ ያለ ክፍያ በተለማማጅነት መሥራት ነው፤ በሙያተኞች መሃል የመሥራት እድል ታገኙበታላችሁ። ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለማየት የሚያስችል ዘዴ ይኑራችሁ። የተለያዩ አይነት ነገሮችን ከመሞከር አትቆጠቡ፤ ለህልውናችሁ አስፈላጊ ነው። ከሰዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያገለግሉ ጠቃሚ ጥበቦችን እንድታዳብሩ ያግዛችኋልና።

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከአይዳ አሸናፊ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ ሐምሌ 2004
ሌላ ምንጮች
http://www.ethiopianfilminitiative.org/component/content/article/36-ethiopian-filmmakers/230-aida-ashenafi?directory=60;

http://www.tmcnet.com/usubmit/2006/09/12/1881070.htm;

http://africanwomenincinema.blogspot.com/2010/02/glance-at-ethiopian-women-in-cinema.html

አጥኚ
ሃና አርአያሥላሴ፣ ሸዊት ወልደሚካኤል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>