Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አቻምየለሽ ክፍሌ፣ ኮሎኔል ዶ/ር

AlmazDj

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በጦር ኃይሉ ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩት ሴት ሐኪሞች መካከል አንዷ በመሆን ሥራ የጀመረችየኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያዋ ሴት ሐኪም ናት። ለመከላከያ ኃይል የሕክምና ተቋማትበሙሉ የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎቶች ዳሬክተር በመሆን፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሰው ኃይልቅጥርና ምደባ፣ የአሰራር መመሪያዎች መስፈርት ዝግጅትና አፈፃፀም፣ የሕክምና መሳርያዎችና ቁሳቁስአቅርቦት፣ መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥና ተመሳሳይ ሥራዎችን በሃላፊነት ትመራለች። በዚህምበጦር ኃይሉ ውስጥ የሥራ አመራርና የአገልግሎት እንዲሁም የአሰራር መስፈርቶችና ደረጃዎች ዙሪያበተተገበሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች የአመራር አስተዋፅኦ አበርክታለች። ባልቲሞር ሜሪላንድ ከሚገኘውከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ለተመረጡ ተመራቂዎች የሚበረከት የክብር ሽልማት አግኝታለች። ሁለትጊዜ የተፋጠነ የማዕረግ እድገት በማግኘት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የኮሎኔልነት ደረጃ ላይ ደርሳለች።
ወቅታዊ ሁኔታ በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በጤና ዋና ዳሬክቶሬት፣ የሕክምናና የድጋፍአገልግሎት ዳሬክተር
የትውልድ ቦታ: ጋምቤላ
የትውልድ ዘመን: ሐምሌ 22 ቀን 1957 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ጎሬ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት፣ ጎሬ፣ ኢሉባቦር
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጎሬ፣ ኢሉባቦር፤ ተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (12ኛ ክፍል)፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የሕክምና ዶክተር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ፖስትዶክቶራል ዲግሪ፣ በሕፃናት ሕክምናና ጤና፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በ1984 ዓ.ም፤ ማስተርስ ዲግሪ በጤና አጠባበቅ፣ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ፣ 1998 ዓ.ም
ዋና የስራ ዘርፍ
ሕክምና፣ የጦር ኃይል ሕክምና አገልግሎት አስተዳደር
የሕይወት ታሪክ
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያዋ ሴት ሐኪም የሆነችው ኮሎኔል ዶ/ር አቻምየለሽ ክፍሌ፤ ከደረጃ ደረጃ እያደገችና በበርካታ የሃላፊነት ቦታዎች እየሰራች፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የጤና ዋና ዳሬክቶሬት የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎት ዳሬክተር ለመሆን በቅታለች። የሠራችበትና ሃላፊነት የያዘችባቸውን ቦታዎች ዘርዝሮ ለመጨረስ ይከብዳል። በደብረ ዘይት የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተማሪና ዲን ሆና ሰርታለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ረዳት ፕሮፌሰር ናት። በጦር ኃይሎች የሪፈራልና የስልጠና ሆስፒታል፣ በሐኪምነት፣ በአስተማሪነት፣ በዲፓርትመንት ሃላፊነት እንዲሁም በሜዲካል ዳሬክተርነት አገልግላለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በሚካሄዱ ጥረቶች ያበረከተቻቸው የአመራር አስተዋፅኦዎች በርካታ ናቸው። ኤችአይቪን በሚመለከት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ያገለገለችው ኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፤ በብሄራዊ የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚከታተል ብሄራዊ ቦርድ ውስጥም ሰርታለች። ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በተመሰረተው ብሄራዊ የሴቶች ጥምረት ውስጥ የቦርድ አባል ናት። ለአገሪቱ ጦር ኃይል የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ የአምስት አመት የስትራቴጂ እቅድ፣  የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት አጠቃቀም መመሪያና ሌሎች የአሰራር ሰነዶችን አዘጋጅታለች፤ በዝግጅት ላይ ተሳትፋለች። በአገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ።

የነፃነት መንፈስ የተላበሰ ዘመናዊ ቤተሰብ ውስጥ የወላጆቿ ፍቅርና ድጋፍ ሳይለያት በጋምቤላ እንዲሁም በጎሬ ኢሉባቦር ያደገችው አቻምየለሽ፣ ሴትና ወንድ ልጆች በሙሉ በእኩል አይን ይታዩ እንደነበር ታስታውሳለች። ቤት ውስጥ እኩል ይሠራሉ፤ የጨዋታ ጊዜም ይፈቀድላቸዋል። በትምህርት ቤቷ የድራማ ክበብ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የክርክር ክበብ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቤተክርስትያን የፀሎት ቡድን አባል ነበረች። የወደፊት ሕይወቷን ለመምረጥ የቻለችው ታላቅ እህቷን በማየት ነው። ሆስፒታል በሌለባቸው አካባቢዎች ሐኪም ሆነው ሲያገለግሉ ከነበሩት ነርሶች መካከል የአቻምየለሽ ታላቅ እህት አንዷ ነች። የእህቷን ፈለግ በመከተል  በሕክምና ሙያ የተማረከችው አቻምየለሽ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታ ሕክምና ስታጠና ደግሞ ሌላ የሚማርክ ነገር አየች። ለተግባራዊ ስልጠና ወደተለያዩ ሆስፒታሎች ለመሄድና አሰራራቸውን ለመቃኘት እድል ነበራት። ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮችንም አስተውላለች። ከሁሉም በላይ ግን፣ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተመሰጠች። ምንም እንኳ ቤተሰቧ ውስጥ ውትድርናን የሚያውቅ ሰው ባይኖርም፣ በጦር ኃይሎች ያየቻቸው ነገሮች… የደንብ ልብሱ፣ ስነ ስርዓቱ፣ አደረጃጀቱ…  ነሸጧት። ተግባራዊ ስልጠናውንና የሕክምና ሃላፊነቷን እየተወጣች፤ ጎን ለጎን በሆስፒታሉ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መሳተፍ ጀመረች። ከሰዎች ጋር መግባባት ያስደስታታል። በዚያ ላይ ከታካሚዎቿ ጋር ቀረቤታ መፍጠርና ቤተሰብ መሆን የምትወድ ሐኪም ነች። ወደ ጦር ኃይል የመቀላቀል አዝማሚያዋ እየዋለ ሲያድር ስር ሰዶ የሕይወት አላማዋ ሆኖ ተተከለ። የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ለመሆን ፍላጎት እንዳደረባት ያወቁ አንዳንድ ጓደኞቿና የሥራ ባልደረቦቿ ሃሳቧን ለማስቀየር ቢሞክሩም የራሷን ፍላጎት ለመከተል ቆረጠች።

የትምህርቷ የመጨረሻ አመት ላይ የሙያ አቅጣጫዋን መርጣ የወሰነችው አቻምየለሽ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተመራቂዎችን በሚመለምልበት ወቅት ተመዘገበች። በእርግጥ የአየር ኃይል ሰዎች ወንድ ተመራቂዎችን ለመመልመል ነበር ያሰቡት። ቢሆንም እሷም ተቀባይነት አግኝታ በእጩ መኮንንነት ወደ ወታደራዊው የሙያ ሕይወት ገባች። የመኮንኖች ስልጠና ከወሰደች በኋላ በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ሥራ ጀመረች። በአየር ኃይል ውስጥ ብቸኛዋ ሴት ዶክተር እንደመሆኗ፣ ከጦሩ ቤተሰቦች ጋር ተቀራርባ በተለይም በሕፃናትና በእናቶች ጤና ላይ በልዩ ትኩረት ለመሥራት ጥራለች። ደብረዘይት በሚገኘው የአየር ኃይል ዋና የማዘዣ ካምፕ ውስጥ ከመደበኛው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ፣ በሰው ኃይል ቅጥር፣ በሕክምና ቦርድና በሌሎች ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ አገልግላለች።

ለአንድ አመት ያህል በሕክምና ከሰራች በኋላ፣ በ1979 ዓ.ም እንደገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመለሰች። በሕፃናት ሕክምና የድሕረ ምረቃ ትምህርቷን በ1984 ዓ.ም ያጠናቀቀችው አቻምየለሽ፣ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሕፃናት ሐኪም እንድትሆን ስትመደብ፣ በሆስፒታሉ የሕክምና ኮሌጅ በአስተማሪነት  ሰርታለች። ቀስ በቀስም ተጨማሪ ሃላፊነቶችን እየተረከበችና የአመራር ቦታዎችን እየያዘች የእድገት ጉዞዋን ጀመረች። የሆስፒታሉ የህፃናት ሕክምና ክፍል ሃላፊ፣ የሆስፒታሉ ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የስልጠናና የዶኩመንቴሽን ክፍል ሃላፊ በመሆን ስትሰራ ቆይታ፣ የጦር ኃይሎች የስልጠና ሆስፒታል ምክትል ዳሬክተር ከዚያም ዳሬክተር ሆናለች። ታዲያ ለጦር ሰራዊት ቤተሰቦች ሕክምና መስጠቷን ሳታቋርጥ ነው፣ የአመራር ድርሻዋን እንዲሁም ጥናትና ምርምሯን የምታካሄደው። ግን በዚህ አልተወሰነችም። ይበልጥ በስፋት መሥራት እንዳለባት ተገነዘበች። በ”ደ ቢርስ” የገንዘብ ድጋፍ በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የመማር እድል ያገኘችው አቻምየለሽ፣ በ1999 ዓ.ም በጤና አጠባበቅ የማስተርስ ዲግሪዋን የተቀበለችው ከከፍተኛ ማዕረግ ሽልማት ጋር ነው።

በጤና አጠባበቅ ከተመረቀች በኋላ፣ ደብረዘይት በሚገኘው የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እንድትሆን ተመርጣ ተመደበች። በተለያዩ ዘርፎች ኮሌጁ የሚያቀርባቸው ስልጠናዎች ከመከላከያ ኃይል ፍላጎቶች ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ፣ በሥርአተ ትምህርት ዝግጅቶችና ማሻሻያዎች ላይ ሰርታለች። በከፍተኛ መኮንንነትና በተቆጣጣሪነት ወደ መከላከያ ኃይል የሰላም አስከባሪ ማዕከል የተዛወረችው አቻምየለሽ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ተልእኮዎችን በሙሉ የሚያካትት ሃላፊነት ነበረባት። በዚህ ሃላፊነቷም፣ ጠቅላላ የጤና ሥርዓትና አሰራሮችን በበላይነት ከመቆጣጠርም በተጨማሪ የፖሊሲ አማካሪ በመሆንም ሰርታለች። ከዚያም እንደገና ወደ ሌላ ሃላፊነት ተዛወረች። ዩናሚድ በሚል ስያሜ ወደ ዳርፉር ሱዳን በተሰማራው የሰላም አስከባሪ ሃይል፣ ዋና ወታደራዊ የሕዝብ ግንኙነትና የመረጃ መኮንን እንድትሆን የተመደበችው አቻምየለሽ፣ ለአስር ወራት የሰላም አስከባሪው ዋና አዛዥ ቃል አቀባይ በመሆን አገልግላለች። አሁን በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና የጤና ዳሬክቶሬት፣ የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎቶች ዳሬክተር ሆና እየሰራች ነው። የፖሊሲና የአሰራር መስፈርቶችን ጨምሮ ጠቅላላ የሥራ አመራርና ሌሎች ተቋማዊ ሃላፊነቶችን ትወጣለች። በሐኪምነት የማማከር ስራዋን ግን አላቋረጠችም። በመከላከያ የጤና ኮሌጅም ታስተምራለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፋኩልቲ ደግሞ የክብር ረዳት ፕሮፌሰር ናት።

ዶ/ር አቻምየለሽ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ወታደራዊ የሙያ ሕይወቷን ያዋለችው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የጤና ተቋማትን አወቃቀር፣ የአገልገልግሎት ደረጃ እና አሰራርን ለመገንባት መሆኑ ያኮራታል። በአንድ ዘርፍ ብቻ የስፔሻላይዜሽን ስልጠና በመስጠት ሥራ የጀመረው የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ አሁን የሕክምና ዶክተሮችንና በማስተርስ ዲግሪ የሰለጠኑ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ በ12 የጤና ዘርፎች በርካታ ተመራቂዎችን እያፈራ ነው።

ኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፣ የሙያና የሕይወት አድማሳቸውን ለሚያስፋፉ እንዲሁም፣ የቤተሰብ ሕይወትንና የሙያ ሕይወትን አቻችለው ለሚመሩ ሰዎች ያላት ክብር እጅግ ትልቅ ነው። ተማሪ ሳለች የምታደንቃቸው ጄነራል ዶ/ር ኃይሉ ክፍሌ፤ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ከመሆናቸውም በላይ፣ ሐኪም፣ መሪ እና የሆስፒታሉ ዋና አዛዥ  ነበሩ። ለታካሚዎች ጊዜ ሰጥተው ከልብ የሚንከባከቡ ሴት ሐኪሞችም መንፈሷን ለሥራ ያነቃቁታል። ሌሎችን ለማገልገል ወደ ኋላ ሳይሉ በፅናት የሚሠሩ ሰዎች፣ አርአያዎቿ ናቸው።

በሙያ ሕይወቷ እንዳስተዋለችው፣ ሴቶች በትጋትና በሥራ ውጤት ብቃታቸውን ቢያስመሰክሩ እንኳ የአመራር ቦታ ለማግኘት ብዙ ፈተና ይገጥማቸዋል። ይሁን እንጂ በፈተናዎች አልተበገረችም። አስተዳደጓ፣ ፅኑ አቋሟ፣ አላማዋና በራስ የመተማመን ስሜቷ ፈተናዎችን ተጋፍጣ ለማሸነፍ ረድተዋታል። ትምህርት ላይ ፈጣን ነች፤ ነገሮችን በቅርበት አስተውላ ቶሎ ትገነዘባለች። በትኩረት ታዳምጣለች። እና ደግሞ፣ በቅን ልቦና ትሠራለች። በሙያ ሕይወት ላይ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በቁንፅል ሳይሆን ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር አስተሳስራ በትክክለኛ መነፅር እንደምትመለከት የምትገልፀው አቻምየለሽ፤ ትምህርቷ በዚህ በኩል እንደተቀማት ትጠቅሳለች።

ለኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፣ የሚሌኒየም የልማት ግቦች ከልብ አጓጊ ናቸው። ሰዎች ንፁሕ ውኃ፣ ምግብና ትምህርት የተሟላለት ሕይወት ሲያገኙ ማየት ሕልሟ ነው። በተለይም ሴቶች የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ትመኛለች። ማህበረሰቡም በሴቶች ሚና ላይም የማሕበረሰቡ አስተሳሰብ እንደሚለወጥ ተስፋ አላት። ለኢትዮጵያ ያላት ሕልም፣ ሕይወት የሞላላቸው ዜጎች የሚኖሩባት አገር እንድትሆንና ጠንካራ እድገት እንድትቀዳጅ ነው። የጦር ኃይል ሴት አባላት አስተዋፅኦም እውቅና እንደሚያገኝ ተስፋ ታደርጋለች።

ምንም እንኳ ጎልቶ የሚታይ አስተዋፅኦ በማበርከት ስኬቶችን ብታስመዘግብም፣ ገና እጅግ ብዙ ትሠራለች። የእናቶችና የሕፃናት ማዕከል ለመገንባት የጀመረችውን ውጥን ለማጠናቀቅ የምትፈልገው አቻምየለሽ፣ ወታደራዊ የሙያ ሥራዋን ስትጨርስ በማህበረሰብ ደረጃ ሴቶችን፣ ሕፃናትንና ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ታስባለች።

አቻምየለሽ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፣ ባለቤቷና ልጆቿ ሥራዋን  ያውቁላታል፤ የተሻለ ነገር እንድትሠራ አበረታች ድጋፍም ይሰጧታል።

ለወጣት ሴቶች ምክሯን ስታካፍል፤ ሳትዘናጉ በርትታችሁ ሥሩ በማለት ትጀምራለች። ሴቶችን የሚያደናቅፉ ልምዶችንና አስተሳሰቦችን እየታገላችሁ፤ የግልና የሙያ ብቃታችሁን ለማሳደግ ለአፍታ ሳትዘናጉ ሁልጊዜ ትጉ። በእኩል ደረጃ ከወንድ የሥራ ባልደረቦቻችሁ ጋር ተቀላቀሉ። ተጋፍጦና ታግሎ ለማሸነፍ፣ በራስ የመተማመንና በራስ የመኩራት መንፈሳችሁን ገንቡ። በሴቶች ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ዘይቤዎችንና አመለካከቶችን በዝምታ አትለፉ። በጋራ ትብብር ማህበረሰባችሁን ለማሻሻል የበኩላችሁን አበርክቱ።

 

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከኮሎኔል ዶ/ር አቻምየለሽ ክፍሌ፣ በነሀሴ 2004 ዓ.ም
አጥኚ
ሜላት ተክለጻዲቅ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>