Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አበበች ወልዴ ተበጀ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ከፍተኛ ሪፖርተርና አዘጋጅ፤ ለስድስት ዓመት የኢትዮጵያ ሴት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር
ወቅታዊ ሁኔታ የግል አማካሪ
የትውልድ ቦታ: አዘዞ፣ ጎንደር፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: እ.ኤ.አ በ1969 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አፄ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጎንደር
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
አፄ ፋሲል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጎንደር
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመርያ ድግሪ (ቢኤ)፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነፅሁፍ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
የሥነፆታ ጥናት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ
ጋዜጠኝነት
የሕይወት ታሪክ
የተዋጣላት ጋዜጠኛና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆነችው አበበች  ወልዴ፤ በሥነፆታ፣ በኮሙኒኬሽንና በመገናኛ ብዙኃን ጉዳዮችም አማካሪ ናት። በኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የሰባት ዓመት ቆይታዋ የዋና አዘጋጅ ደረጃ ላይ ደርሳለች። ለሴቶች ሙያዊ እድገትና ግስጋሴ ልባዊ ፍቅር ያላት አበበች፤ በኢትዮጵያ ሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ውስጥ ለስድስት ዓመት ገደማ በዋና ዳይሬክተርነት አገልግላለች።

ከአባቷ ከሃምሳ አለቃ ወልዴ ተበጀና ከእናቷ ወይዘሮ እልፍነሽ ሃይለሚካኤል የተወለደችው አበበች፤ ወላጆቿ ካፈሯቸው አምስት ልጆች አንዷ ናት። አበበች 4ኛ ክፍል እስክትደርስ፣ ቤተሰቦቿ በጎንደር አዘዞ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ነው የኖሩት። በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ መኖር ጥቅምም ጉዳትም አለው ትላለች አበበች። በአንድ በኩል በትምህርት ላይ የነበረው ግንዛቤና ድጋፍ ከሌሎቹ የጎንደር አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር የላቀ ነው። በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ቦታዎች እጅጉን የከፋ የፆታ ጥቃት ይታይበታል። አበበች፤ ሴት አስተማሪዎቿና   በትምህርታቸው የተሳካላቸው ጥቂት የአካባቢዋ ልጃገረዶች፣ በትምህርት እንድትጎብዝ  ነሽጠዋታል።

እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ሴቶች ቁጥር ጥቂት ከመሆናቸው አንፃር፤ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣቷ ለእሷም ሆነ ለቤተሰቧ ልዩ እርካታ የሚያቀዳጅ  ነበር። በአስመራ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና በሥነ ፅሁፍ ክፍል የተመደበችው አበበች፤ በዩኒቨርስቲው ለሶስት ዓመት ብትማርም፣ አገሪቱ ሰላም አጥታ የታመሰችበት ወቅት ስለነበር ትምህርቷም ተስተጓጎለ። በአስመራ ጦርነቱ እየተባባሰ ሲመጣ፤ የዩኒቨርስቲው የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ወደ አጋርፋ የእርሻ ማሰልጠኛ ማዕከል ተዛወረ። እሷና ሌሎች ተማሪዎችም ወደ ዚያው ሄዱ። ሆኖም ከአንድ ሴሚስተር በኋላ፣ እንደገና ከትምህርት የሚያስተጓጉል ሌላ ጣጣ መጣ። ሁሉም የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ትምህርት ተቋረጠ። አበበችም፤ ከመላው አገሪቱ ከተውጣጡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር፣ ለውትድርና ተመልምላ ብላቴ ማሰልጠኛ ማዕከል ለመግባት ተገደደች።

ያቺ ቅፅበት ለአበበች አስፈሪ ነበረች። ህይወቷ አስባውም አልማውም ወደማታውቀው አቅጣጫ ዞሯል። ሆኖም ወዲያው ራሷን ከአዲሱ ሁኔታ ጋር በማለማመድ፣ የውትድርና ስልጠናውን ኮስተር ብላ ትከታተል ገባች። በብላቴው የስልጠና ወራት ለህይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን እንደቀሰመች የምታስታውሰው አበበች፤ አሁንም ድረስ እንደዋና ጉዳይ የምታየው የእህትማማችነትን ፋይዳ በተግባር የተገነዘበችበት ጊዜ እንደሆነ ትናገራለች። የፆታ ጥቃት አሰቃቂ ገፅታን ጨምሮ በውትድርናው አለም ያሉ የፆታ ጉዳዮችንም አይታበታለች። በመሃል መንግስት ተለወጠና፣ የውትድርና ስልጠናው ላይ ከነበሩት በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ወደ ኬንያ ሞያሌ በስደት ሄደች። እንደብዙዎቹም ከወር ገደማ በኋላ ወደ አገሯ በመመለስ ያቋረጠችውን ትምህርት ለማጠናቀቅ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባች። የድግሪ ትምህርቷን አጠናቅቃ እንደተመረቀች፣ በውሃ ሃብት ሚኒስቴር እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በህዝብ ግንኙነት ክፍል ተቀጥራ ሰርታለች – እ.ኤ.አ እስከ 1979 ዓ.ም።

የጋዜጠኝነት ስራዋን በእንግሊዝኛው ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ፣ በከፍተኛ ሪፖርተርነት የጀመረችው አበበች፣ በሰባት ዓመት አገልግሎቷ እስከ ኤክስኪዩቲቭ አዘጋጅነት ደረጃ  ለመድረስ ችላለች። እ.ኤ.አ በ2005 አጋማሽ የኢትዮጵያ ሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ሆና ስትመረጥ፣ የሴት ጋዜጠኞችን ጥቅም ለማስከበር ከመቻሏም በተጨማሪ፣ የሴቶች መብትና የሥነ ፆታ ጉዳይ በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን እንዲያገኝ ከፍተኛ ግፊት አድርጋለች። ጎን ለጎንም፣ ስለኢትዮጵያ ሴቶች ከተፃፉ በጣም ጥቂት መፃህፍት አንዱ ለሆነው ህንዳኬ፡ ጥኑዎቹ የኢትዮጵያ ሴቶች (Candace: Invincible Women of Ethiopia) የተሰኘ መፅሃፍ መረጃ በማሰባሰብ ቁልፍ ተባባሪ ነበረች። በWACC በተካሄደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ክትትል ፕሮጀክት (Global Media Monitoring Project (GMMP) 2009/10) ላይ የኢትዮጵያ አስተባባሪ በመሆን ሰርታለች። ፕሮጀክቱ በሥነ ፆታ ዙሪያ በመላው ዓለም የዜና ማሰራጫ ተቋማት ላይ ከተካሄዱ የረዥም ጊዜ ክትትሎች ሁሉ በስፋቱ የላቀ ነው። የኢትዮጵያ ሴት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበርን በዋና ዳሬክተርነት ለ6 ዓመት ገደማ ካገለገለች በኋላ፣ በኦክስፋም ካናዳ ተቀጥራ፣ የፆታ ፍትሃዊነት የፕሮግራም ኦፊሰር በመሆን ሰርታለች። የኢትዮጵያ ሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ማህበርን ከመሰረቱት ጋዜጠኞች አንዷ የሆነችው አበበች፣ የማህበሩ የዳሬክተሮች ቦርድ ፕሬዚዳንትና ሊቀመንበር እንድትሆን ተመርጣ ሰርታለች። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅትንም በቦርድ አባልነት አገልግላለች። በአገር ውስጥና በክፍለ አህጉር ደረጃ በተለያዩ ሴት- ተኮር ድርጅቶችም ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ናት። በአሁኑ ወቅት በሥነ ፆታ፣ በኮሚኒኬሽን እና በመገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ላይ በግል አማካሪነት ትሰራለች።

አሁን የአበበች ዋና ትኩረት፤ ከልማት ጋር አስተሳስሮ የሥነ ፆታ ግንዛቤን ማስፋት ነው። በሴቶች ህይወት ላይ አንዳንድ የመሻሻል ለውጦች መፈጠራቸውን ባትክድም፤ በአብዛኛው የታይታ ነው ትላለች። በሥነ ፆታ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማበርከት ተስፋ የምታደርገው አበበች፤ የሴትነትን አቅም ሙሉ ለሙሉ በመቀበል፤ የሴቶች ጠንካራ ድርጅቶችንና የድጋፍ ስርአት ለመገንባት መሳተፍ ትፈልጋለች።

ለዘመናች የኢትዮጵያ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች የምትሰጠው ምክር፡

  • ያሉትን አማራጮች ተጠቀሙ፤ ወይም አዳዲሶችን ፍጠሩ
  • በማንነታችሁና በእምቅ አቅማችሁ እምነት ይኑራችሁ
  • ግባችሁን ለማሳካት ታገሉ
  • ለሥነ ፆታ ትኩረት ስጡ

እውቀታችሁንና ክህሎታችሁን በየጊዜው ሳታቋርጡ አሻሽሉ

  • ጥንካሬያችሁን አሳዩ
ዋና የመረጃ ምንጮች
ከአበበች ወልዴ ጋር እ.ኤ.አ በ2012 ተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ቤተል በቀለ ብርሃኑ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>