Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አልማዝ ኃይለሥላሴ ወደርየለህ

Almaz H-Selassie

ዋና ዋና ስኬቶች:
የሴቶች ብልት ትልተላ በኢትዮጵያና በሌሎች 24 የአፍሪካ አገራት በአፋጣኝ እንዲቀረፍ አግዛለች፤ ለዚህም ሴቶችንና ሕፃናትን በሚጎዱ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ በተቋቋመው አፍሪካ አቀፍ ኮሚቴ (IAC) ውስጥ ለ18 አመታት ሰርታለች።
ወቅታዊ ሁኔታ የቦርድ ሊቀመንበር፣ DHENO የተቀናጀ የገጠል ልማት፣ ሰሜን ሸዋ፤ የአፍሪካ አቀፍ ኮሚቴ (IAC) በሴቶች ብልት ትልተላና በሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ በሚያዘጋጀው የሳይንስ ህትመት (ጆርናል) አስተባባሪ፣ የወሴክማ ኢትዮጵያ አማካሪ ምክርቤት አባል
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: 1939 (40) ዓ.ም.
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ:
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት

ኔቲቪቲ የሴቶች ትምህርት ቤት እና ኃይለሥላሴ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ለቀምት

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት

ዲፕሎማ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ትምህርት ተቋም፣ አዲስ አበባ፤ እንደ መጀመሪያ ዲግሪ የሚቆጠር ዲፕሎማ፣ በማህበራዊ አገልግሎት፣ አቴንስ የአሜሪካ ፒርስ ኮሌጅ፤ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በቢዝነስ አስተዳደር፣ ቢዝነስ ኮሌጅ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ

የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ

የሥነፆታ ተሟጋች


  የሕይወት ታሪክ
 

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍሪካ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ባከናወነችው ስራ የምትታወቀው አልማዝ ኃይለሥላሴ፣ የሙያ ህይወቷንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቷን በሙሉ አገሯ እንድትለማ እንዲሁም የሴቶችና የሕፃናት ሕይወት እንዲሻሻል በሚያደርጉ ስራዎች አውላለች። በማህበራዊ አገልግሎት ሙያ የሰለጠነች እንደመሆኗ፣ በንጉሡ ዘመንና በወታደራዊው የደርግ ዘመን በርካታ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርታለች። በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብና የሕፃናት ደህንነት ክፍል ኃላፊ የነበረችው አልማዝ፣ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የማህበራዊ ደህንነት ክፍል እንድትመራ ከመሾሟ በፊት፣ በዚሁ ክፍል ስር የሕፃናት ተቋም  ኃላፊ ነበረች። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን የእቅድ ክፍል ሃላፊ ሆና አገልግላለች። ከሁሉም በላይ እርካታ ያገኘችበት ግን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በተቋቋመው የመላ አፍሪካ ኮሚቴ ውስጥ የ25 አገራት አስተባባሪ በመሆን ለሰባት አመታት ያከናወነችው ስራ ነው። ዛሬ በሊቀመንበርነት በምትመራው DHENO የተቀናጀ የገጠር ልማት ማህበር፣ በሰሜን ሸዋ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙና፣ የገጠር ቤተሰቦች በተለይም ደግሞ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ዘላቂ ኑሮ እንዲገነቡ ታግዛለች። ከዩኒቨርስቲ ሶስት ዲግሪዎችን ለመያዝና ሉሊት የተሰኘ ልብወለድ ደርሳ ለማሳተም የበቃችው አልማዝ፣ ብዙ ሰርቻለሁ ብላ የምታርፍ ሴት አይደለችም፤ ከመስራትና ለማህበረሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠት ቦዝና አታውቅም።

ሁለት ልጆችን ላፈሩት ወላጆቿ የመጨረሻ ልጅ የሆነችው አልማዝ፣ በ1939 (40) ዓ.ም ተወልዳ ስድስት አመት እስኪያልፋት ድረስ ያደገችው በአዲስ አበባ ነው። አባቷ፣ በወለጋ ለቀምት ከተማ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የፖስታና የቴሌግራም ቢሮ ሃላፊ እንዲሆን ሲመደብ፣ ከቤተሰቧ ጋር ወደ ለቀምት ሄደች። በጀርመንና በፈረንሳይ የተማረው አባቷ ይቅርና፣ ከመሰረታዊ ትምህርት ያልተሻገረችው እናቷም ብትሆን፣ ለትምህርት ትልቅ ክብር ነበራት። ትምህርቷን አቋርጣ እንድትዳር ዘመድ አዝማድ ብዙ ቢወተውትም፣ ወላጆቿ ግን ጫናውን ተቋቁመው አልማዝ በትምህርቷ እንድገፋ ለማድረግ ችለዋል። ጥረታቸው መና አልቀረም። በትምህርት አያያዟና በውጤቷ የሚስተካከላት አልነበረም። እንዲያውም፣ በክፍሏ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሴት ተማሪዎችም ከወንዶች ጋር እየተፎካከሩ የላቀ ውጤት ሲያገኙ ማየት የተለመደ ነበር። ቅናት ያደረባቸው ወንዶች ችግር የፈጠሩ እንደሆነም አልማዝ በዝምታ አታልፍም ነበር። ላመነችበት ነገር በግልፅ መናገርና መሟገት የጀመረችው ገና በልጅነቷ ነው። ደግሞም፣ ብርታት የሚሰጥ አርአያ አላጣችም። እናቷ ወ/ሮ አሰገደች ኩምቢ ለህፃኗ አልማዝ ወደር የለሽ አርአያ ነበሩ። ለሰው አሳቢ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በሙያ አዋቂነታቸው ተወዳጅነትን ያተረፉት ወ/ሮ አሰገደች፣ የልምድ አዋላጅነትን ከዘመናዊነት ጋር በማጣመር ብዙ ድሃ ሴቶችን አዋልደዋል። በእፅዋት ባህላዊ ህክምና የሚታወቁ እንዲሁም፣ በጥልፍ ስራ፣ በእደ ጥበባትና በምግብ ዝግጅት ባለሙያነታቸው ስም ያተረፉት ወ/ሮ አሰገደች፣ በጣም ሃይማኖተኛ፣ ደግና ርህሩህ፣ የእርጋታንና የፈጠራ መንፈስ የተላበሱ ሴት እንደነበሩ ልጃቸው አልማዝ ትናገራለች።

አልማዝ በለቀምት የኃይለሥላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች፣ በወቅቱ በልዕልት ሂሩት ደስታ ወደሚተዳደረው እቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት ወደ አዲስ አበባ መጣች። እዚህ ነው፣ ዋና ዋና የሕይወት ቁም ነገሮችን እየቀሰመች፣ የራሷን ስብእና የቀረፀችው። የኪስ ገንዘብ በብልሃት መጠቀምን እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመጡ ልጃገረዶች ጋር ተቀራርቦ መኖርን ተማረች። ከማህበራዊ ግንኙነት ጀምሮ እስከ ስፖርት ክበብ፣ ከትያትር ጀምሮ እስከ ፒያኖና ሙዚቃ፣ ከለተያዩ የሕይወት ገፅታዎች ጋር ተዋወቀች።

አልማዝ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ትምህርታዊ ተቋም (በአበባ ዩኒቨርስቲ ስር ከመደረጉ በፊት) ውስጥ ገብታ ለመማር የወሰነችው ለስዊዲናዊቷ የተቋሙ መስራች ለአናማ ቶል በነበራት አድናቆት የተነሳ ነው። የሴት ተማሪዎች ቁጥር በዘመኑ አነስተኛ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ተቋም ግን የሴቶቹ ቁጥር ከወንዶቹ ይበልጥ ነበር። አልማዝን ጨምሮ አብረዋት በዲፕሎማ ከተመረቁት 15 ተማሪዎች መካከል ዘጠኙ ሴቶች ናቸው። እንደተመረቀች እዚህ አገር አልቆየችም። ወዲያውኑ፣ ወደ አቴንስ ግሪክ ሄዳ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ስመጥር  የሆነው የአሜሪካ ፒርስ ኮሌጅ ተመዘገበች። በማህበራዊ ጥናት ልዩ ሙያተኛ ለመሆን በኮሌጁ ለሁለት አመት ከተማረች በኋላ፣ አባቷ በጠና በመታመማቸው በ1958 (59) ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ግድ ሆነባት።

በ22 አመቷ፣ በብሄራዊ የማህበረሰብ ልማት ሚኒስቴር (በኋላ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳየ ሚኒስቴር በተሰኘው) መስሪያ ቤት ስራ አግኝታ ተቀጠረች። የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስተባባሪ በመሆን፣ የአቅም ግንባታና የስልጠና አቅርቦት ስትመራም ነው፣ ከልዕልት ሰብለ ጋር የመስራት እድል ያገኘችው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበር መሪ ከነበሩት ልዕልት ሰብለ ጋር በበርካታ ፕሮጀክቶች ዙሪያ አብራ የሰራችው አልማዝ፣ ከእነዚህም መካከል በካሳንችሽ የሕፃናት ተቋም በባህርይ ችግርና በስሜት መቋወስ ለሚሰቃዩ ሕፃናት የምክር አገልግሎት ለመስጠት በበጎ ፈቃድ ያከናወነችው ሥራ ይጠቀሳል። በሰለጠነችበት የሙያ መስክም፣ በ1960 (61) ዓ.ም. የሴቶችን ድርሻ ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበትና ከወንዶች ጋር እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተካሄደውን አለማቀፍ የሴቶች ጉዳይ ጉባኤ ለማስተናበር ከልዕልት ሰብለ ጋር  ሰርታለች። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስተባባሪ በመሆኗ፣ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የመሳተፍ እድል ያገኘችው አልማዝ፣ ከወደፊት የትዳር አጋሯ ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚም ፈጥሮላታል።

ግን በሥራዋ መቀጠል አልቻለችም። አልማዝ እንደምትለው፣ የቅርብ አለቃዋ የለየለት ፊውዳል ነው ቢባል ይሻላል። ለበታች ሠራተኞች በተለይ ደግሞ ለወጣት ሴቶች ቅንጣት ክብር አልነበረውም፡፡ ለዚህም ነው ሥራዋን በመልቀቅ፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብና ህፃናት ደህንነት ክፍል ሃላፊ በመሆን የተቀጠረችው፡፡ በእሷ የሚመራው ክፍል፣ በዝቅተኛ ገቢ የሚቸገሩ ቤተሰቦችን ለማገዝ እንዲሁም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ለመንከባከብ፣ በርካታ የህፃናት ማሳደጊያና ተቋማትን ለመመስረት ችሏል። ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ የሚታዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የጥናት ቅኝቶችንና የምርምር ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ አልማዝ  ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተዛወረችው አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የማዘጋጃ ቤቶች ረዳት ሚኒስትር ሳሉ ነው፡፡ ብዙም ሳትቆይ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ ለማህበራዊ ደህንነት ክፍል ሃላፊነት ተወዳደረች፡፡ የሃላፊነት ቦታውን የያዘችው በውድድር አሸናፊ ሆና በመውጣቷ ቢሆንም፣ ለአንዳንድ የሥራ ባልደረቦቿ ሊዋጥላቸው አልቻለም። የአልማዝን አመራር ላለመቀበል ያንገራገሩ በርካታ ወንድ ሠራተኞች፣ “እንዴ ተደርጎ ሴት አለቃ ይመራናል” የሚል አቤቱታ ለከንቲባው እስከማቅረብ ደርሰው ነበር። ተቃውሞውና አቤቱታው ግን አልማዝን  አጠነከራት እንጂ አላብረከረካትም፡፡ ሥራዋ ላይ እንድታተኩር አደረጋት አደረጋት እንጂ፣ በእንካ ሰላንቲያ አልተዘናጋችም። ግልፅ የሥራ መመሪያ በማውጣትና እያንዳንዱ ሠራተኛ በየፊናው የሥራ ድርሻውን መወጣት እንዳለበት ደጋግማ በመግለፅ፣ በአልበገር ባይነቷ ፀናች፡፡ ከሥራዋ ጎን ለጎን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨስቲ የቢዝነስ ኮሌጅ በማታው ክፍለጊዜ በቢዝነስ አስተዳደር የመጀመርያ ድግሪዋን አግኝታለች። ይሄን ጊዜ ነው የንጉሱ አገዛዝ ተገርስሶ፣ የደርግ ወታደራዊ መንግስት ሥልጣን የተቆናጠጠው፡፡

ከአዲስ መንግስት ጋር አነሰም በዛ ሹም ሹር መምጣቱ አይቀርምና፣ የቀድሞው ከንቲባ ወደ ሌላ የሃላፊነት ቦታ እንዲዛወር ተደርጎ፣ በምትኩ አዲስ ከንቲባ ተሾመ፡፡ አልማዝ ከአዲስ አለቃ ጋር ኮከቧ አልገጠመም፡፡ በሶሻሊዝም አቀንቃኝነቱ ከሚታወቀው ከንቲባ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ቀላል አልነበረም። በእርግጥ ከንቲባው ሥራዎቿን ያደንቅ ነበር፡፡ ትላልቅ የሃላፊነት ሥራዎችን የሚሰጧት፡፡ በአዲስ አበባ ጥንታዊ ቅርሶችን ከ ታሪካዊ ዳራቸው ጋር ለመቃኘትና ለመሰነድ የተነደፈውን የጥናት ፕሮጀክት እንድትመራ የተመደበችው በከንቲባው ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የህፃናት ዓመት በሚል ስያሜ በቶሪኖ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ለመሳተፍ የቡድን መሪ እንድትሆን የተመረጠችውም በከንቲባው ነው። እንዲያም ሆኖ ግን አልማዝ ከከንቲባው ጋር አብራ መሥራት አልቻሉም፡፡ በአስተሳሰብ፣ በመርህ እና ቅድሚያ በሚሰጧቸው ነገሮች ላይ የሚጣጣሙ ባለመሆናቸው፤ የማታ ማታ አልማዝ ማዘጋጃ ቤቱን ተሰናብታ ወደ ቱሪዝም ኮሚሽን ተዛወረች፡፡

በዚሁ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ፣ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር (አኢሴማ) ሊቀመንበር ሆና የተመረጠችው አልማዝ፣ በብሄራዊው ማህበር ስር ለከተማዋ ሴቶች በርካታ ሥራዎችን አከናውናለች። የሴቶች የህብረት ሥራ ማህበራትን አቋቁማለች፡፡ የጤና እና የህፃናት ክትባት ፕሮግራሞችን አስጀምራለች፡፡ ሴቶች  በመሠረተ ትምህርት ፕሮግራም እንዲጠቀሙ ከማድረጓም በተጨማሪ፣ በሴቶች መብትና እኩልነት ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሰርታለች። የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ያን ያህል የሚያወላዳ ሥልጣን ባይሰጠውም፣ ከከተማዋ የፖለቲካ ቢሮ በሚያገኙት ድጋፍ፣ የሴቶች ህይወት የሚያሻሽል አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደቻሉ አልማዝ ታስታውሳለች፡፡

በ1977 (76) ዓ.ም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ከተሾሙት ባለቤቷ ጋር ወደ ለንደን ስትሄድ ስራዋንና ሃላፊነቷን መልቀቅ ነበረባት። ነገር ግን፣ የራሷ እቅድ ነበራት። ያለሥራ መቀመጥ የማይሆንላት አልማዝ፣ አጋጣሚውን ተጠቅማ ትምህርቷን በመቀጠል፣ ከፒሲኤል/ ዌስትሚኒስተር ዩኒቨርስቲ በሰው ሃብት ልማት የማስተርስ ድግሪዋን ለማግኘት በቅታለች። በአራት ዓመት የእንግሊዝ ቆይታዋ፣ የአፍሪካ የዲፕሎማት ሚስቶች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር እንድትሆን ተመርጣ፣ በማህበሩ አላማ መሰረት ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ አሰባስባለች። ማህበሩ በሊቀመንበርነት እየመራች ከነበረችው ኖርማ (የናይጀሪያ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚስት) ጋር በመሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ያዘጋጀችው አልማዝ፣ በአፍሪካ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል የሚውል ገንዘብ ለዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት እንደተሰጠ ታስታውሳለች፡፡

አልማዝ በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ ከለንደን እንደተመለሰች፣ የሴቶችንና የህፃናትን ጤና የሚጎዱ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በተቋቋመው የመላ አፍሪካ ኮሚቴ (IAC) ውስጥ ስራ ጀመረች። በድርጅቱ ፕሬዚዳንት ብርሃኔ ራስወርቅ እንዲሁም የፕሮጀክት ሃላፊ ከነበረችው የድርጅቱ ተባባሪ መስራች ሚስ ማርጋሬታ ሊናንደር ስር፣ አልማዝ በአስር የአፍሪካ አገራት ዋና አስተባባሪ በመሆን እስከ 1987 (88) ዓ.ም ድረስ ለስድስት ዓመታት ሰርታለች፡፡ አልማዝ ድርጅቱን ለሁለተኛ ጊዜ ማገልገል የጀመረችው ከአምስት አመታት በኋላ ነው። ለአስራ ሁለት ተከታታይ አመታትም፣ ከሃያ አምስት በሚበልጡ የአፍሪካ አገራት ውስጥ፣ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን የማጥፋትና የሴቶችን አቅም የመገንባት አላማ ያነገቡ ብሔራዊ ኮሚቴዎች እንዲመሰረቱ ስልጠና ጭምር በመስጠት አስተባብራለች፡፡ አልማዝ፣ በሙያ ዘመኗ ከፍተኛ እርካታ የተጎናፀፈችው በዚህ ስራዋ ነው፡፡ እነዚህን ብሔራዊ ኮሚቴዎች ከመመስረትና ከመደገፍ ባሻገር፣ ምርምር በማካሄድና የሴቶች እኩልነት እንዲሰፍን እንዲሁም ያለዕድሜ ጋብቻና የሴቶች ብልት ትልተላን የመሰሉ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን የሚቀንስ ፕሮግራም በመቅረፅ የድርሻዋን አበርክታለች፡፡ በእርግጥ ማህበረሰቡ ከእነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶች እንዲላቀቅ ያደረገችው እንቅስቃሴ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ከማህበረሰቡና ከሃይማኖታዊ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቧም  ጭምር ጠንካራ ተቃውሞን ተጋፍጣለች፡፡ እንዲያም ሆኖ የማታ ማታ ማህበረሰቡ ባስመዘገበው ስኬት ከፍተኛ እርካታ ማግኘቷን ትናገራለች፡፡ ለዚህም የናይጀሪያ ፕሮጀክት እንደአብነት ይጠቀሳል፡፡ የሴት ብልት በመግረዝ ይተዳደሩ የነበሩ ሴቶች፣ ድርጊታቸው ስለሚያደርሰው ጉዳት  ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከተደረገና  አማራጭ የኑሮ መተዳደርያ እድሎች ከተፈጠረላቸው በኋላ፣ ለግርዛት የሚጠቀሙበትን ቢላ ለማስጣል ተችሏል፡፡  በኢትዮጵያ የጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ብሔራዊ  ኮሚቴ (የአሁኑ EGLDAM ማለት ነው) ባደረገው የማያቋርጥ ጥረትና ትጋት፣ በ1983 ዓ.ም 91 በመቶ የነበረው የሴቶች ብልት ትልተላ መጠን፣ በ2004 ዓ.ም ወደ 40 በመቶ መውረዱን የምትናገረው አልማዝ ፤ ትልቁ እርካታዋም ከዚህ እንደሚመነጭ ትገልፃለች፡፡ የሴቶች ብልት ትልተላ እንዲቀንስ በIAS አማካኝነት ያበረከተችውን አስተዋፅኦም የህይወቷ ትልቁ ስኬት አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ለንደን ሄዳ ከአጭር ቆይታ በኋላ የአማካሪነት ሥራ ለመጀመር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው አልማዝ፤ ከስራ ባልደረቦቿ ከሶስና ደምሴና ከዶ/ር ደምሴ ገ/ሚካኤል ጋር የሥነ ፆታ ጉዳዮችን በስፋት ለማስረፅ የሚሰራ DAS-EDS የተባለ ድርጅት አቋቋመች፡፡ በ2000 (01) ዓ.ም፣ በሴቶች ብልት ትልተላና በሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ በዶ/ር ያየህይራድ ዋና አዘጋጅነት የሚታተመውን የIAC ጆርናል በአስተባባሪነት መምራት የጀመረች ሲሆን፣ መፅሄቱ በየአገሩ የተቋቋሙ ብሔራዊ ኮሚቴዎች ከሚካሄዱት ጥናት የተገኙ ውጤቶችን ይዳስሳል። ADHENO የተቀናጀ የገጠር ልማት ማህበር ውስጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሆና በበጎ ፈቃደኝነት የሰራችው አልማዝ፣ በሰሜን ሸዋ የተገኘው የፕሮጀክት ስኬት በእጅጉ እንደሚያስደስታት ትገልፃለች፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተለይም ሴቶች፣ በእርከን ስራና በችግኝ ተከላ እንዲሳተፉ በመደረጉ፣ የተራቆቱ መሬቶች አገግመው እንደገና በአረንጓዴ ደን የተሸፈኑ ሆነዋል። በዶ/ር ፍስሃ የተቀረፀውና “ጉዲፈቻ” የሚል ስያሜ የወጣለት ይሄው የደን ልማት ፕሮጀክት፣ ገበሬዎችና የማህበሩ አባላት አንድ ወይም ከዚያ በላይ ዛፎችን እንደ ጉዲፈቻ ተረክበው እንዲያሳድጉ የሚያበረታታ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የብዙዎችን ቀልብ ከመሳቡም ባሻገር፣ ከዓለም ባንክና ከአየርላንድ ኤምባሲ ሽልማት ለማግኘት በቅቷል፡፡

አልማዝ፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሴቶች እኩልነትን ለማስፈን፣ ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ባደረገችው አስተዋፅኦና ቁርጠኛ ትግል መታወስ ትፈልጋለች፡፡

ሕልሟም፣ ኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር አርአያ ስትሆንና የሴቶች ኑሮ ሲሻሻል ማየት ነው። የማታ ማታ በፓርላማ ውስጥ የወንዶችና የሴቶች ተሳትፎ የተመጣጠነ ይሆናል የሚል ተስፋ የሰነቀችው አልማዝ፤ ያኔ የሴቶች ድምፅ ከትህትና ጋር ጎልቶ በብርቱ ይስተጋባል፤ መከራከሪያቸውም በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ይሆናል ብላ ታምናለች፡፡

አልማዝ ለልጃገረዶችና ለወጣት ሴቶች ስትመክር እንዲህ ትላለች፡ ገንዘብ የማከማቸት ሃሳብ ላይ ብቻ አታተኩሩ፤ የቤተሰባችሁንና የማህበረሰባችሁን ህይወት ለመቀየር እንዲሁም አገራችሁን ለማሻሻል ተግታችሁ ስሩ፡፡ የኢኮኖሚ ነፃነታችሁንና የገንዘብ አቅማችሁን ገንቡ።  ይሄ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ በውይይት፣ በድራማና በሥነጥበብ ሥራዎች አዕምሮአችሁን መገንባት አለባችሁ  ትላለች – አልማዝ፡፡


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከአልማዝ ኃይለሥላሴ ወደርየለህ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ በሐምሌ 2004 .
አጥኚ
ምንትዋብ አፈወርቅ፤ ሜሪ-ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>