Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አልማዝ ደጀኔ ገብረማርያም

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከቀደምት ሴት ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት (ሮማንወርቅ ካሳሁንና እሌኒ መኩሪያ በሰሩበት ዘመን) መጀመርያ ላይ የሴቶች የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነበረች፤ በኋላም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት፣ እንዲሁም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በህዝብ ግንኙነት ክፍል ሰርታለች፤ በንጉሱና በደርግ ዘመን
ወቅታዊ ሁኔታ ጡረታ
የትውልድ ቦታ: ሃረር፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1940
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሸኖ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (በአዲስ አበባ ደሴ መስመር 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ)
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  አልማዝ ደጀኔ፣ ሴቶች ወደ ሙያው ደፍረው በማይገቡበት ዘመን ፣የሮማነወርቅ ካሳሁንን ፈር ቀዳጅነት በመከተል፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ከተሰማሩት ቀደምት ሴቶች አንዷ ናት፡፡ እንዲያውም ገና ተማሪ ሳለች ዘወትር የሮማነወርቅን ድምፅ በሬዲዮ መስማት ያስደስታት ነበር፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የተሳበችውም በእሷ የተነሳ ነው፡፡

አልማዝ፤ በሐረር ከተማ ብትወለድም እድገቷ ግን ከአዲስ አበባ በ80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሸኖ፣ ከአያቷ ጋር ነበር – ወላጆቿ በፍቺ በመለያየታቸው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በሸኖ ከተከታተለች በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡ እንደሌሎቹ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሁሉ፣ ጥሩ ነጥብ አምጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (የያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ) የገባችው አልማዝ፣ በቢዝነስ አስተዳደር የባችለር ድግሪዋን አግኝታለች፡፡ የእሷ ምኞት ጋዜጠኝነት ብትማር ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ዩኒቨርስቲው በጋዜጠኝነት መስክ የድግሪ መርሃ ግብር አልነበረውም፡፡ ሆኖም የጋዜጠኝነት ነገር ከአእምሮዋ ጠፍቶ አያውቅም። ዩኒቨርስቲ ሳለች በትርፍ ጊዜዋ በሬዲዮ ድራማዎች ላይ ትሳተፍ ስለነበር፣ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ለመቀጠር ያመለከተችው በድፍረት ነው፡፡

በ1963 ዓ.ም.  ከዩኒቨርስቲ የተመረቀችው አልማዝ፣ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥራ በኢትዮጵያ ሬዲዮ መሥራት ጀመረች፡፡ እናም ከቀደምቶቹ ፈርቀዳጅ ሴት ጋዜጠኞች ጋር ተቀላቀለች። በጣት ከሚቆጠሩት ሴት የሬዲዮ ጋዜጠኞች መካከል፣ ያቺ ድምፅዋን የምትወድላት ሮማንወርቅ ካሳሁን  የሙያ ዘመኗን ለማጠናቀቅ ተቃርባ ነበር፡፡ ሌላዋ የሬዲዮ ሴት ጋዜጠኛ እሌኒ መኩርያ፣ በሙያዋ የስኬት ማማ ላይ የወጣችበት ጊዜ ነው፡፡ አሰገደች ይበርታ ደግሞ፣ የአልማዝ የቅርብ የስራ ባልደረባና የሙያ እናቷ ነበረች፡፡ አልማዝ የሬዲዮ ሥራዋን ሀ ብላ የጀመረችው፣ በባልትና ሙያ፣ በልጆች አስተዳደግና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረውን የሴቶች ፕሮግራም በማዘጋጀትና  በማቅረብ ነው፡፡ ንጉሱን ከስልጣን ለማውረድ ከተካሄደው አብዮት በኋላ ለሁለት ዓመት የሰራችውን ጨምሮ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመት በሬዲዮ ውስጥ አገልግላለች፡፡  በ1968 ዓ.ም.  በማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ተዛውራም በዶክመንቴሽንና የመረጃ ክምችት በማደራጀት ሰርታለች፡፡ በዚያን ወቅት ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ ጥቂት ሴቶች ተቀጥረው ቢገቡም፣ በአብዛኛው ወንዶች የገነኑበት ግዛት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እንዲያም ሆኖ እነዚያ ጥቂት ሴቶች በእኩል ዓይን ይታዩ እንደነበር የምታምነው አልማዝ፤ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በሚፈቅደው ደንብና አሠራር መሰረት ከወንዶች እኩል ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

አብዛኞቹ የሬዲዮና የቴሌቪዝን ፕሮግራሞች፣ ስለሶሻሊስት አብዮት የሚቀሰቅሱ፣ የሴቶች ጭቆናንና የለውጥ አስፈላጊነትን የሚያቀነቅኑ ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ፣ የደሞዝ ጭማሪና የሥራ እድገት የሚገኘው በሙያ ብቃት ሳይሆን በፓለቲካ ፓርቲ አባልነት እየሆነ ቢመጣም፣ አልማዝ ግን ‘ሞቼ እገኛለሁ’ ብላ ፓርቲውን ሳትቀላቀል ቀረች፡፡ በደርግ ስርዓት በአብዛኛው ደስተኛ አልነበረችም፤ በዘመኑ የሚፈፀሙ ግድያዎች ያሳዝናትና ይሰቀጥጣት ነበር። ሆኖም ሥራዋን ለቅቃ መውጣት አልቻለችም –  የቤተሰቧን ህይወት ማቆየት ነበረባት፡፡ በበጎ ጎኑ ደግሞ፣ ደርግ “መሬት ላራሹ” ያወጀበትን ዕለት ታስታውሳለች፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በከተማ ቀመስ የገጠር አካባቢ ያደገችው አልማዝ፤ እንዲያ የሚለፉ ገበሬዎች ምንኛ ያጡ የነጡ ድሆች እንደሆኑ ታውቃለች – በወሬ ሳይሆን በዓይኗ አይታለች፡፡ አዲሱ የመሬት አዋጅ የገበሬዎችን ህይወት ያሻሽላል የሚል ፅኑ እምነት ስለነበራትም ነው፤ አዋጁን ስትሰማ በደስታ የቦረቀችው፡፡ በእርግጥ አዋጁ ምን ያህል በትክክል እንደሚተገበር በእርግጠኛነት ለማወቅ አዳጋች ነበር፡፡

በህዝብ ግንኙነት ክፍል ለሶስት ዓመት ከሰራች በኋላ በ1971 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ጣቢያ የተዛወረች ሲሆን፣ ከውጭ አገር የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር የፕሮግራም ልውውጥ የማካሄድ፣ እንዲሁም ፊልሞችንና የቴሌቪዝን ተከታታይ ድራማዎችን የማስመጣት ሃላፊነት ላይ ተመድባ ሰርታለች፡፡ ከሶሻሊስት አገራት የሚመጡት አብዛኞቹ ፊልሞች፣ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን የሚሰብኩና የሚያወድሱ ነበሩ፡፡ ሆኖም ስልጣኑን ያደላደለው የደርግ መንግስት የሚነቀንቀው እንደሌለ እየተሰማው ሲሄድ፣  በ1976 ዓ.ም ገደማ የቁጥጥር ሰንሰለቱን እያላላ መጣ። አልማዝ ይሄን አጋጣሚ ተጠቅማ፣ የምዕራብ አገራትን ለማሰስ ተነሳች፡፡ ወደ እንግሊዝ አገር በመጓዝ፣ ከፕሮፓጋንዳ የፀዱ አዝናኝ ፊልሞችና አስቂኝ ድራማዎችን እንዳመጣች ታስታውሳለች፡፡ ከአሜሪካ “ሜሪ ታይለር ሙር ሾው”፣ “ጀነራል ሆስፒታል” እና “ሆም ስዊት ሆም”፣ እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚማሩ የውጭ አገር ዜጎችን የሚያሳይ “ማይንድ ዩር ላንጉጅ” የተሰኘ አስቂኝ ተከታታይ ድራማና ሌሎች ፊልሞችን  ከእንግሊዝ አገር አስመጥታለች።

ደርግ በ1983 ዓ.ም በኢህአዴግ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ፣ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ይሠሩ የነበሩት በርካታ ሠራተኞች ተባረዋል፡፡ አልማዝ ግን ሥራዋ ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ስላልነበረ (ለደርግ ወይም ለሽምጥ ተዋጊው ሃይል፣ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ባለማሳየቷ) ከሥራዋ አልተፈናቀለችም፡፡ ሆኖም ወደ ሽያጭ ክፍል መዛወር አልቀረላትም፡፡ እዚያም የቴሌቪዝን የማስታወቂያ ገቢዎችን በመሰብሰብ፣ እንዲሁም የአዲስ ዘመንና የሄራልድ ጋዜጦችን ስርጭት በማስፋት ሰርታለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን አዲስ ፓሊሲ ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት አልማዝ ከስራዋ ተባረረች፡፡ ፖሊሲው የተለያዩ ባህሎችን የሚያገናኝ መስተጋብር ከማጠናከር ይልቅ ሠራተኞችን በብሄር (በጎሳ) የሚያቧድን መሆኑ እንዳልተስማማት ትገልፃለች፡፡

ለጥቂት ጊዜ እቤቷ በመቀመጥ እረፍት ከወሰደች በኋላ፣ የሴቶች ልማት ማህበር (ሴልማ) በሚል የተደራጁ 17 ሴቶችን ተቀላቀለች – በበጎ ፈቃድ አገልጋይነት ለሴቶች ጉዳይ ለመሥራት። ማህበሩ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከአባላት መዋጮ፣ ከጥናትና ምርምር፣ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ከሚያከናውናቸው የቅስቀሳ ዘመቻዎች፣ እንዲሁም በሳምንት ሶስቴ ከሚካሄዱ የአካል እንቅስቃሴ ፕሮግራሞች ነበር፡፡ አልማዝና የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋ አሰገደች ይበርታ ሙሉ ጊዜያቸውን ለድርጅቱ አገልግሎት ሲያውሉ፣ ሌሎች አባላት  በትርፍ ጊዜያቸው ነበር የሚያገለግሉት፡፡ ድርጅቱ በዚህ መልኩ በማያጠግብ ድጎማ  ለስድስት ዓመታት ሰርቷል፡፡ አልማዝን ከሚያኮሯት ስኬታማ ስራዎቿ መካከል፣ ለ100ኛው የአድዋ ጦርነት በዓል የሰራችው ንግስት ጣይቱን የተመለከተ ጥናታዊ ፊልም አንዱ ሲሆን ሌላው የልምሻ (ፖሊዮ) በሽታን ለማጥፋት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዝንና በህትመት ያካሄደችው የቅስቀሳ ዘመቻ ሌላው ነው፡፡

ሴልማ የተባለው የሴቶች ማህበር ከተዘጋ በኋላ፣  በ1991 ዓ.ም አጥቢያ ኮከብ የህትመትና ማስታወቂያ ኩባንያን ተቀላቀለች፡፡  በ1984 ዓ.ም የተቋቋመው ይሄው ኩባንያ፤ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ “ጦቢያ” መፅሄትንና ጋዜጣን ያሳትም ነበር፡፡ አልማዝ በድርጅቱ ውስጥ መሥራት ስትጀምር የሥራ ድባቡ እንግዳ አልሆነባትም፡፡ ኩባንያውን በጋራ ያቋቋሙት ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር የተባረሩ ጋዜጠኞች፣ የመምሪያ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ በድርጅቱ የሽያጭና ስርጭት ክፍል እንዲሁም በቪዲዮ ስቱዲዮው ውስጥ የሠራችው አልማዝ፤ በተለይ በጋሞጎፋ ጨንጫ ወረዳ ፣በአነስተኛ ነጋዴዎች ሕይወትና ቤተሰቦቻቸው ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ቪዲዮ ለመሥራት ባበረከተቸው አስተዋፅኦ ትኮራለች፡፡ በመጨረሻ ግን ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የተፈጠረውን ረብሻ ተከትሎ ኩባንያው ተዘጋ፡፡

አልማዝ ለወጣት ሴቶች ምክሯን ስታካፍል፣ “መሥራት የምትወዱትን ሥሩ” ትላለች፡፡ ብዙ ወጣቶች ትምህርታቸውን ከዳር እንደሚያደርሱ ተስፋ የምታደርገው አልማዝ፤ ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ ታምናለች፡፡ የሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ መስራች ለሆነችው መዓዛ ብሩ ልዩ  አክብሮት ያላት አልማዝ፣ የዛሬዎቹንም ወጣት ሴቶች ከልቧ ታደንቃለች – በሬዲዮና በቴሌቪዝን የምትሰማቸውና የምታያቸው ሴቶች በፈጠራ የተካኑ ብርቱ ወጣቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>