Posted on October 7, 2014 By admin

አልፋ መለሰ ደመላሽ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ራይሲንግ ታይድ ካፒታል የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት የመሰረተች ሲሆን ድርጅቱ በሴቶች፣ በስደተኞች፣ በአናሳና በተዘነጉ ማህበረሰቦች ላይ በማተኮር የስራ ፈጠራ ፕሮግራሞችን እየቀረፀ እገዛ ይሰጣል፣ የድርጅቷን ስራ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበር እያሰበች ነው
ወቅታዊ ሁኔታ

የራይዚንግ ታይድ ካፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ

የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 2-3-1971
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: ኒው ጄርሲ፣ዩኤስኤ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ካቴድራል ት/ቤት፣ አዲስ አበባ /እስከ 6ኛ ክፍል/፤ሴንት አንድሪው ት/ቤት፣ ቦስተን፣ ማሳቹሴት፣ ዩኤስኤ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ቦስተን ላቲን ስኩል፣ ቦስተን፣ ማሳቹሴት፣ ዩኤስኤ /ከ9ኛ – 12ኛ ክፍል/

የዩኒቨርስቲ ትምህርት

ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ፣ ካምብሪጅ፣ ማሳቹሴት፣ ዩኤስኤ

ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
 

ኑሮዋን በአሜሪካ  ኒው ጀርሲ ያደረገችው አልፋ መለሰ ደመላሽ፤ በድሃ ማህበረሰቦች ውስጥ አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፍ ራይዚንግ ታይድ ካፒታል የተባለ ድርጅት ያቋቋመች የማህበረሰብ ስራ ፈጣሪ ናት፡፡ ድርጅቱ የንግድ ስራ ፈጣሪዎች፣ ስኬታማ የንግድ ተቋማትን እንዲፈጥሩና  የማህበረሰባቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲገነቡ ያግዛል፡፡ እሷና ድርጅቷ የሲኤንኤን ጀግና ተብለው በዓለም አቀፍ ቴሌቪዝን ቀርበዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደችው አልፋ፤ እስከ 12 ዓመቷ ድረስ በአብዛኛው ከአክስቷና ከአያቶቿ ጋር ነው ያደገችው – ምክንያቱም እናቷ ታላቅ እህቷን ከቀጠፈው የደርግ ቀይ ሽብር እልቂት ለማምለጥ ወደ ኬንያ ተሰዳ ነበር፡፡ እናቷ የሁለት ዓመት ልጇን ለታናሽ እህቷና ለአያቶቿ ጥላ ከመኮብለሏ በፊት ሁለት ፈታኝ ቅድመ ሁኔታዎችን ለወላጆቿ አቅርባ ነበር፡፡ አንደኛው ልጇን ሞንቶሶሪ ት/ቤት እንዲያስገቡላት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንዳያስገርዟት ነው ቃል ያስገባቻቸው፡፡ የልጇ ትምህርት በእጅጉ ያሳስባት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ከሞንቶሶሪ የህፃናት ት/ቤት ስትጨርስ፣ ስመ ጥር በነበረው ካቴድራል የሴቶች ት/ቤት እንድትገባላት የተማጠነችው፡፡ እናት፤ ለውድ ልጇ ገና ከጠዋቱ ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች፡፡ አልፋን ያረገዘችው ገና በለጋ እድሜዋ ሳትወድና ሳትፈቅድ ነበር – ያውም ደግሞ አፈ ቅቤና ሲያዩት ከሚማርክ ነውጠኛ ወንድ፡፡ አብራው እንደማትዘልቅ ብታውቅም ልጅዋን ህጋዊ ለማድረግ ስትል ብቻ አገባችው፡፡ ከሶስት ወር በኋላ ግን ተለያዩ – በፍቺ፡፡

አልፋ ያደገችው ዘመድ አዝማድ በበዛበት ቤተሰብ ውስጥ ነው – በአጎትና በአክስት ልጆች ተከብባ፡፡ በወቅቱ የፖለቲካ ምስቅልቅል የተነሳ አያቶቿ የማያስጠጉት ሰው አልነበረም፡፡ እናቷ አጠገቧ ባትኖርም አልፋ እድለኛ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ አክስቷ እንደ ስለት ልጇ በፍቅር ተንከባክባ ነው ያሳደገቻት፡፡ ስትጠራት እንኳን “ቦርስዬ“ እያለች ነበር፡፡ አልፋ በቅንጦት ነው ያደገችው፡፡ ብዙ ቅያሪ ጫማዎችና ደህና ደህና ልብሶች የነበራት ብቸኛ ልጅ ስትሆን እንደማንኛውም የሞንቶሶሪ ህፃናት ጠዋት ጠዋት ልብሷን የምትለብሰውና ጫማዋን የምትጫማው ራሷ ነበረች፡፡ የቤተሰቡ አባላት ተራ ገብተው ት/ቤቷ ያደርሷት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በተለይ ወንድ አያቷ ወደ ሞንቶሶሪ ሲሸኟት በእርጋታ እየተራመዱ ስለት/ቤቱ ውድ ክፍያና ለእናቷ ስለገቡት ቃል ያጉተመትሙ እንደነበረ አትዘነጋውም፡፡ ት/ቤት በእረፍት ሰዓት፣ አንድ ክፍል ውስጥ ተቀምጣ፣ ልዩ ልዩ አሻንጉሊቶችን፣ የሚገጣጠሙ መጫዎቻዎችንና ጌሞችን እንደልቧ  እያማረጠች ስትጫወትና በደስታ ስትቦርቅ ገነት የገባች ያህል ይሰማት እንደነበር ትዝ ይላታል፡፡ ከዓመታት በኋላ ከአሜሪካን ሃገር ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ስትመረቅ፣ በ70ዎቹ እድሜ ላይ የነበሩት አያቷ፣ ወደ እናቷ ፊታቸውን አዙረው የተናገሩትን ዛሬም ድረስ ታስታውሰዋለች \”ዛሬ ከሃርቫርድ ልትመረቅ የቻለችው እናቷ በልጅነቷ ሞንቶሶሪ ት/ቤት እንዳስገባት ስላደረገችኝ ነው\” ብለው ነበር፡፡

አያቷ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱ ጊዜ በቀጥታ የተጓዙት ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ ነበር፡፡ ከጥቂት ሰዓታት የመኪና ጉዞ በኋላም ቤተሰባቸው ለዘመናት ሲያርስ ከቆየበት ስፍራ ደረሱ – በቾ፡፡ የመጀመርያ ስራቸው በእናታቸው ጎጆ ውስጥ መሰረታዊ የንባብና የፅሁፍ ት/ቤት መክፈት ነበር፡፡ ት/ቤቱን ለማሳደግና ለማስፋፋት በማሰብም የአካባቢውን ገበሬዎች አሳምነው፣ በየዓመቱ 10 ብር እንዲያዋጡ አደረጓቸው፡፡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸውም የአካባቢው ሽማግሌዎች የተውጣጡበት ቦርድ አቋቋሙ – ዛፍ ስር የሚሰበሰብና የትምህርት ቤቱን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር፡፡ ዛሬ፣ ት/ቤቱ 416 ተማሪዎች ያሉት ሲሆን ከ1ኛ – 8ኛ ክፍል ድረስም ያስተምራል – በገበሬዎችና በአካባቢው መስተዳድር እገዛና በባህር ማዶ ለጋሾች ድጋፍ፡፡ የአያቷ ቀጣይ ህልም፣ አልፋ የተማረችው ዓይነት የህፃናት ትምህርት የሚሰጥ መዋዕለ ህፃናት ማቋቋም ነው፡፡

አልፋ ሴት አያቷንም የምታስታውሰው በፍቅር ነው፤ስለእሳቸው አውርታ አትጠግብም፡፡ በበርካታ ተሰጥኦዎች የተሞሉት አስገራሚ አያቷ፣ በፍቅር ምግባር የተደገፈ ፍትሃዊነትን፣ልግስናንና እምነትን በውስጥዋ አሳድረውባታል፡፡ የተራቡና የታረዙ ችግረኞችን፣ ህመምተኞችንና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሲያበሉና ሲያለብሱ እንዲሁም ያለቻቸውን በተትረፈረፈ ፍቅር ሲያካፍሉ እየተመለከተች ማደጓን ታስታውሳለች፡፡ የአልፋ አለመገረዝ በወደፊት ህይወቷ ላይ ችግር እንዳያመጣባት በሚል ይጨነቁ የነበሩት አያቷ፤ ታዳጊዋ የልጅ ልጃቸው እኔ ያልኩት ካልሆነ የምትል ሃሳበ ግትር የሆነችው ባለመገረዟ ይሆን እያሉ ያስቡ ነበር፡፡ ነገሩ ከዘመኑ ወግና ልማድ ያፈነገጠ ቢሆንባቸውም ለአልፋ እናት የገቡትን ቃላቸውን ሳያጓድሉ ጠብቀዋል – አያቶቿ፡፡

  የመዋዕለ ህፃናት ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ፣ ካቴድራል የሴቶች ት/ቤት ለመግባት ፈፅሞ አልተቸገረችም፡፡ ገና ከጠዋቱ በሞንቶሶሪ ት/ቤት ተቀርፃለቻ፡፡ በካቴድራል እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ የተማረችው አልፋ፤ ትምህርት ነፍሷ ነበረ፤ለዚህ ነው በውጤቷ ከሌሎች ተማሪዎች የላቀች የሆነችው፡፡

    ልጄ የት ደረሰች ብሎ የማያውቀው አባቷ፣ ድንገት ብቅ ያለው አልፋ የስምንት ዓመት ተኩል ልጅ ሳለች ነው፡፡ እንደወላጅ አባትነቴ ልጄን ወስጄ የማሳደግ ህጋዊ መብት አለኝ ብሎ እምቧ ከረዩ አለ፡፡ አክስቷና አያቶቿ አሻፈረን ብለው ተከላክለውላት ነበር፡፡ ከእናቷ ጋር በነበረ ጊዜ በነውጠኛነቱ ያውቁታላ፡፡ ሆኖም በዚያው ነውጠኛ ባህሪው፣ ቤተሰቧንና ጎረቤቱን በሃይል አስፈራርቶ ወሰዳት፡፡ ከዚያም እማታውቀው ሩቅ ስፍራ ካለ ቤቱ ወስዶ ከዓመት በላይ አስቀመጣት – እስረኛ አደረጋት ቢባል ይቀላል፡፡ ሆኖም ካቴድራል ት/ቤት መሄዷን አላቋረጠችም፡፡ አስተማሪዎቿና የአባቷ ጎረቤቶች በየቀኑ የሚደርስባትን ዱላና ስድብ፣ የእንቅልፍ እጦትና የስሜት ስብራት አላየንም አልሰማንም ሊሉ አይችሉም፡፡ ፊት ለፊት ይታይ ነበርና፡፡ ሆኖም ምንም የማድረግ አቅም አልነበራቸውም ወይም የለንም ብለው አስበዋል፡፡ አያቷም አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያዩዋት፡፡ በኋላ እንደሰማችው ግን እሷን ከአባቷ ላይ መልሰው ለመውሰድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በአገሪቱ ህግ መሰረት ጣልቃ የሚገቡበት አንዳችም ቀዳዳ ማግኘት ግን አልቻሉም፡፡

  በአባቷ ቤት ውስጥ የቆየችባቸው 12 ወራት፣ የ12 ዓመት ያህል ነበር የረዘመባት፡፡ መከራው ሲበዛባትና ከዱላና ከእስር የምትገላገልበት መላ ስታጣ፣ አባቷን ለመግደል አስባ ነበር፡፡ ባላሰበችው ቅፅበት ግን ይሄን ሃሳቧን የሚያስቀይር ነገር ገጠማት፡፡ ምን እንዳስቀየራት ግን እሷም አታውቀው – ተዓምር ነው ቢባል ይቀላል፡፡ አባቷን መግደል ነፃ እንደማያወጣትና ይልቁንም ይቅር ልትለው፣ ልትወደውና ልትረዳው እንደሚገባት  አሰበች – አውቃ አገናዝባ ሳይሆን የእምነቷ ሃይል ገፋፍቷት፡፡

 እሷ እንዲህ ታስብ እንጂ አባቷ አልተቀየረም፡፡ በመጨረሻ እንኳን የማታውቀው አገር ነው በመኪና ወስዶ የጣላት – በሃረር ክልል ከሚገኝ ራቅ ያለ ከተማ፡፡ ይሄኔ ነፃነት ተሰማት፡፡ አካሏ ነፃ ቢወጣም ስሜቷ ከስቃይ አላረፈም፡፡ የዘጠኝ ዓመት ህፃን የማታውቀው አገር ላይ ተጥላ ምን ይዋጣት? አዲስ አበባ ወደነበሩት አያቶቿ ቤት የተመለሰችው የከባድ መኪና ሹፌሮችን ለምና ነው – ሊፍት ሰጥተዋት፡፡

ከዚያ አስጨናቂ ጉዞ በህይወት የተረፈችው አልፋ፤ በአዲስ አበባ የ6ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ አሜሪካ በመጓዝ፣ የ2 ዓመት ህፃን ሳለች ከተለየቻት እናቷ ጋር ተገናኘች፡፡ ያኔ እናቷ ዓመለ ሸጋ የሆነ ግሩም ባል አግብታለች፡፡ አልፋም   በኋላ ላይ በእንጀራ አባቷ ስም /ደመላሽ/  ትጠራ ጀመር፡፡ ዛሬ በራይዚንግ ታይድ ካፒታል፣ የንግድ ስራ ፈጣሪ ሴቶችን ለመደገፍ በምታከናውነው ስራ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ጉዳይ ያሳስባታል፡፡ ጥቃቱን በጋራ ማስቆም ይቻል ዘንድ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ማስተማር እንደሚገባም ታምናለች፡፡

አልፋ ኢትዮጵያ ሳለች፣ እናቷ ቀን ቀን አስተናጋጅነት እየሰራች፣ ማታ ማታ ደግሞ በትንሿና ጠባቧ የመኖርያ ቤቷ ውስጥ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ልብሶችና ጋውኖችን ትሰፋ ነበር፡፡ እንዲህ ለዓመታት ሰርታና ትንሽ ትንሽ ቆጥባ ነው ልጇ ወደ አሜሪካ የምትመጣበትን የአውሮፕላን ጉዞ ወጪ የሸፈነችው፡፡ ልጇ በአሜሪካ የካቶሊክ ት/ቤት ለምትማርበት ክፍያ እንዲሁም ለልብሶቿ መግዣ የሚሆን በቂ ገንዘብ ማጠራቀምም ነበረባት፡፡ አልፋ በኋላ ላይ ለአነስተኛና ጥቃቅን ስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ስታስብ፣ የእናቷን ተመክሮ ታሰላስል ገባች፡፡ አብዛኞቹ የንግድ ሰዎች ቢዝነስ ለመጀመር ወይም ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ ሲያስቡ፣ ማንም የሚደግፋቸው እንደሌለ ተገነዘበች፡፡ ብዙ ጊዜም የገንዘብ ካፒታል ለማግኘት ወይም የደንበኛቸውን ቁጥር ለማሳደግ፣ ገንዘባቸውንም ሆነ ቢዝነሳቸውን እንዴት እንደሚያስተዳድሩና እንዴት እቅድ እንደሚያወጡ የሚያውቁት ነገር የለም፣ ድጋፍም አያገኙም፡፡

 አልፋ አሜሪካ እንደገባች ከአቅሟ በላይ ተጨናንቃ ነበር – ከአዲስ አገር፣ ከአዲስ ቋንቋና ከአዲስ ቤተሰብ ጋር ለመላመድ፡፡ ወንዶችና ሴቶች በሚማሩበት የቦስተኑ ሴይንት አንድሪው ት/ቤት ስትገባም ግራ መጋባቷ አልቀረም – እሷ የምታውቀው የሴቶች ት/ቤት ብቻ ነበር፡፡ 8ኛ ክፍል ስትገባ ግን አልተቻለችም፣ የክፍሉ ሰቃይ ተማሪ ሆና ዓመቱን  ጨረሰች፡፡ ከዚያም ሃይለኛ ፉክክር በነበረበት ዝነኛው ቦስተን ላቲን ስኩል ገባች፡፡ በዚህ ት/ቤት ንግግር ማቅረብና ጥንታዊ የግሪክና የሮም ስነፅሁፎችን ሸምድዶ ብዙ ታዳሚ ፊት በቃል መወጣት የትምህርቱ አካል ነበር፡፡ የመፅሃፍ ቀበኛ የነበረችው አልፋ፤ትምህርቷን ስትወድ ለጉድ ነበር፡፡ ሰው ፊት ወጥቶ መናገር ግን አይሆንላትም – አንደበቷ ይተሳሰራል፡፡ የእሳት እራት ወደ እሳት ነበልባል የምትሳበውን ያህል፣ እሷም ወደ ፈታኝ ሁኔታ ተስባ ገባች፡፡ ያ የማይሳካላትን፣ ሰው /ህዝብ/ ፊት የመናገር ኮርስ ለመውሰድ ተመዘገበችና ንግግር ማቅረብ ተማረች፡፡ ከዚያማ ማን ይቻላት!

ብዙ ታዳሚ ባለበት እንደልቧ መደስኮር ቻለች፡፡

ከቦስተን ላቲን ት/ቤት ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በአሜሪካ ምርጥ ከሚባሉት ት/ቤቶች አንዱ በሆነው ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ገብታ ፖለቲካ አጠናች – ስለመንግስት አወቃቀርና አሰራር ተማረች፡፡ ህጎች እንዴት እንደሚወጡ፣ በኢትዮጵያ ሳለች የተከሰተው የፖለቲካ ምስቅልቅል እንዴት እንደተፈጠረ፣ እንዴትስ ልትለውጠው እንደምትችል አሰበች፤ መረመረች፡፡ በሃርቫርድ ቆይታዋ፣ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን የተመለከተ ኮርስ በፕሮፌሰር ሮበርት ኤች ባትስ ተማረች፡፡ የሩዋንዳን የጅምላ ጭፍጨፋ ሲዝን ኦፍ ብለድ ከተሰኘው የፌርጋል ኪያን መፅሃፍ ላይ ያነበበችው አልፋ፤  የህግ የበላይነት ማንንም ከመቅሰፍት እንዳላዳነ ተረዳች፡፡ ከዚያም ታሪኩ እንደሷ የነዘራቸው የክፍል ጓደኞቿን በአንድ ቡድን በማደራጀት፤በሩዋንዳ የጥናት ጉዞ ለማድረግ በመጀመርያ ለራሷ፣ ከዛም ለአንድ የመጀመርያ ዓመት ተማሪና ለአምስት የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ አሰባስባለች – እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በሩዋንዳ ለተከሰተው የጅምላ ጭፍጨፋ መፍትሄ ለማበጀት፣ በስራ ላይ የዋለውን ጋካካ የተባለ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ለማጥናት፡፡ ከጥናቱ በኋላ በነበራት የማሰላሰያ ጊዜ፣ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ አቅም ከሌላቸውና ፍርሃት ካደረባቸው ህጎች ምንም ትርጉም እንደሌላቸው ተገነዘበች፡፡ ለምን ቢሉ — የስልጣን ጥመኞች እንዳሻቸው ለጥፋት ይነዷቸዋልና፡፡ ያኔ ነው በልማት ስራ ላይ በማተኮር፣ በመስኩ ከተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ጋር የተወያየችው፡፡ ለውጥ ማምጣት የምትሻ ከሆነ ለተጨማሪ ድግሪ ከመማር ይልቅ ትናንሽ ጥረቶች ማድረግ ብትጀምር የበለጠ ጠቃሚ እንደሚሆን  ስትሰማ፣ እንዴት የራስዋን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደምትችል ማሰብ ጀመረች፡፡

 የፖስት ሞደርን ፍልስፍናና ስነመለኮት ከተማረው ውድ ጓደኛዋ / በኋላ ባለቤቷ/ አሌክስ ፎርስተር ጋር በመሆን ብዙ አወጣች አወረደች፡፡ ከዚያም ዓላማዋን ለመተግበር የሚያግዟትን ወሳኝ ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመረች፡፡ ሳያሰልስ የሚደጋገመውን ድህነት ለማጥፋትና ለችግረኞች ኢኮኖሚያዊ እድል ለመፍጠር የተደረጉ ያለፉ ጥረቶችን መመርመር ያዘች፡፡ በጠና የታመመችውን የፎርስተር እህት ለመንከባከብ ወደ ኒው ጀርሲ ባቀኑ ጊዜ ነው በግዛቷ ባሉ ከተሞች የተንሰራፋውን ጥልቅ ድህነትና የኢኮኖሚ ኢ – ፍትሃዊነት የተገነዘበችው፡፡

አልፋና ባለቤቷ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ከጓደኞቻቸውና ባልደረቦቻቸው እርዳታ በማሰባሰብ ራይዚንግ ታይድ ካፒታል የተባለውን ድርጅት መሰረቱ – የተራውን  ህዝብ   የስራ ፈጠራ አቅም በመገንባት ለማገዝ፡፡ የቀድሞ ሃሳባቸው ኒው ጀርሲ  ትክክለኛውን ጎዳና እንድትይዝ የአቅማቸውን ካደረጉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና የቀረው ዓለም መሻገር ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፍም ሆነ የአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት ብድር ማነቆ ችግር እንዳልነበር በመገንዘባቸው፣ ህብረተሰቡን በማሰልጠን ስራ ላይ ለማተኮር ወሰኑ – ስለቢዝነስ እንዴት እንደሚያስቡ፣ የቢዝነስ እቅዶች እንዴት እንደሚነድፉ፣ ገበያ እንዴት እንደሚያፈላልጉ፣ እንዴት በራስ መተማመንን እንደሚገነቡ፣ የገንዘብ ድጋፍ ካገኙ በኋላ እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ያሰለጥኑ ገቡ፡፡ ይሄ ብቻ ግን በቂ አልነበረም፡፡ ሰዋዊ ጉዳዮችንም ማካተት ነበረባቸው – ከሰዎች ስሜትና ስነልቦና ጋር የተገናኙ፡፡ ለምሳሌ የግል ሰብዕናና ባህርይ፣ የእርስ በርስ መተማመን እንዲሁም ለዕለት ተዕለት የቢዝነስ አመራር የሚያስፈልግ ጥልቅ ክህሎትን ማሰልጠን ነበረባቸው፡፡ የገንዘብ ድጋፍና ብድሩንም አልዘነጉትም፡፡ ለአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት የብድር አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ድርጅቶችን በመቅረብ  በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሽርክናን  ገነቡ፡፡ ራይዚንግ ታይድ ካፒታልን የመሰረቱት፣ አነስተኛ ስራ ፈጣሪዎች  እንዴት ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲያስቡና ካሉት የገንዘብ ምንጮች /ሃብቶች/ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለማመላከትና ለማገዝ ነው፡፡ ስራ ፈጣሪዎች በቀጥታ ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት መምረጥና መወሰን ያለባቸው ጉዳይ አለ፡፡ አንድን የንግድ ስራ  ስኬታማ ለማድረግ በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት 7 ቀን ተግቶ መስራት የግድ ይላል፡፡ እንዲህ ያለው ልባዊ ቁርጠኝነት አላቸው የላቸውም? ወይስ ሌላ የሚፈልጉት ነገር አለ?

 እነዚህ ጥያቄዎች በትክክል ከተመለሱ በኋላ፣ የመረጡትን ስራስ እንዴት ነው የሚተገብሩት? የሚለውን በቅጡ እንዲያስቡበት እነአልፋ እገዛ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ፣ ቢዝነሳቸውን አሳድገው በሺ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን የሚቀጥሩ ትልልቅ የንግድ ተቋማት የሚፈጥሩ በጣት የሚቆጠሩ ስራ ፈጣሪዎች ብቻ እንደሆኑ ተገንዝበዋል፡፡ ሆኖም ትናንሾቹም የንግድ ተቋማት አስፈላጊና ባሉበት መቀጠላቸው በራሱ ስኬት እንደሆነ አልጠፋቸውም፡፡ ዛሬ ራይዚንግ ታይድ ካፒታል፤ ከ600 በላይ አዳዲስ አነስተኛ ስራ ፈጣሪዎችን ከማሰልጠኑም በላይ፣ በስራ ላይ ለነበሩ 254 የንግድ ተቋማት ድጋፍ በመስጠት አጠናክሯል፡፡ ሌሎች 242 የሚሆኑ ደግሞ በእቅድ ደረጃ ተይዘዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም አልፋና ራይዚንግ ታይድ ካፒታል፣ የሲኤንኤን ጀግና ድርጅት በሚል ለመመረጥ በቅተዋል፡፡  በሲኤንኤን ቴሌቪዝን ሊቀርብ የተቀረፀው የእነአልፋ ፕሮግራም መጀመርያ ላይ በፋራህ ፋውሴት፣ ከዚያም በማይክል ጃክሰን ሞት የተነሳ ለሌላ ጊዜ ተላልፎ ነበር፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ፣ የማይክል ጃክሰን ዘገባ ሽፋን ሲሰጠው የእነአልፋ ፕሮግራምም በመቅረቡ፣ በመላው ዓለም በርካታ ተመልካቾች ሊታደሙት ችለዋል፡፡ እንደአጋጣሚ ደግሞ ፕሮግራሙ በተላለፈበት ዕለት፣ የአልፋ ሴት አያት አምስተኛ ሙት ዓመት ስለነበር፣ አልፋ የዛሬ ማንነቴን ቀርፀውልኛል ከምትላቸው ሶስቱ ሴቶች – አያቷ፣ እናቷና አክስቷ ጋር በልጅነቷ የተነሳችው ፎቶግራፍም አብሮ ታይቷል፡፡ ፕሮግራሙ ልቧን በእጅጉ እንደነካውም አልፋ ታስታውሳለች፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ አልፋና አሌክስ ከዋይት ሃውስ ጥሪ ሲቀርብላቸው ፈፅሞ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡ ግን እውነት ነበር፡፡ የጠሯቸውም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሲሆኑ ላከናወኑት በጎ ተግባር እውቅናና ምስጋና ለመስጠት አስበው ነው፡፡ ኦባማ ፤ በዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፊት ባደረጉት ንግግር፤ \”እስካሁን ራይዚንግ ታይድ ካፒታል፣ በኒው ጀርሲ ግዛት ለ250 የንግድ ድርጅት ባለቤቶች እገዛ አድርጓል፤ እስቲ በመላው አሜሪካ ተጨማሪ 500 ወይም 1000 ሰዎችን ማገዝ ቢችሉ ብላችሁ አስቡ- –  እንዲህ ያሉትን ድርጅቶች አቅም ብንገነባ፣ ህይወታቸውን የምንለውጥላቸውን ሰዎች፣ ገቢያቸውን የምናሳድግላቸውን ቤተሰቦች እንዲሁም ከደነዘዘ ህይወት የምናነቃቸውን  ማህበረሰቦች ብዛት ልታስቡት ትችላላችሁ\” ብለዋል፡፡

አልፋ በህይወቷ ላይ ትልቅ ለውጥ የፈጠሩላት መልካም እድሎችና አጋጣሚዎች  የማይሆን ነገር የለም ብላ እንድታምን አድርገዋታል – \”ቁርስህን በልተህ ሳትነሳ ስድስት ሊሆኑ የማይችሉ ዓምራዊ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ\” እንደሚለው የአሊስ  ዎንደር ላንድ ታሪክ፡፡ አሁን አልፋ የራይዚንግ ታይድ ካፒታልና የራሷ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን፣ሩዋንዳንና የቀረውን ዓለም እንዲጨምሩ ምን ማድረግ እንዳለባት በእጅጉ እያሰበችበት ትገኛለች፡፡ የሚንቀሳቀሱበትን ክልል ማስፋት ይኖርባታል፡፡ እሷም ይሄ አልጠፋትም፡፡ አንድ አገር በቀል ድርጅት እነሱ የሰሯቸውን ስራዎች ሁሉ እንዲሰራና ፕሮግራሞችን እንዲሁም የውጤትና የኢንቨስትመንት ትርፍ መለኪያ መንገዶችን ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ /አውድ/ ጋር በማጣጣም እንዲተገብር የሚያስችል የስራ ፈቃድ ለማበጀት እየጣረች ነው፡፡ የአልፋ ህልም፣ መጀመርያ 100 እጅግ በኑሮ የተጎዱና  የተቸገሩ ማህበረሰቦች ጋ መድረስ ነው፡፡ ከዛም ከእያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ 1ሺ ስራ ፈጣሪዎችን በመለየት ድጋፍ መስጠት – የማታ ማታ 100 ሺ የማህበረሰባቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚገነቡና ጉልህ ለውጥ የሚያመጡ ስራ ፈጣሪዎች አቅም ይጎለብታል ማለት ነው፡፡

አልፋ በኢትዮጵያ ላሉ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች እንዲህ ስትል ትመክራለች – ምናባችሁን አትፍሩት፤ እንዳሻችሁ በነፃነት ተጠቀሙበት፡፡ ምክንያቱም በወንዶች፣ በመንግስት ወይም በማንም ሰው ሊገደብ የማይችል ብቸኛ ግዛታችሁ እሱ ነው፡፡ ይሄ ግዛት ሙሉ በሙሉ በናንተ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ ስለዚህም በቅጡ ተጠቀሙበት፡፡ ህልሞቻችሁን እውን ለማድረግ በማገዝ ረገድ ትልቅ ጉልበት ሊሆናችሁ ይችላል፡፡ ገና ሲያዩዋችሁ አይሆንም ወይም አይቻልም የሚሏችሁን ሁሉ በጄ አትበሉ፡፡ እምቢ መባልን እንደግል ችግራችሁ አትቁጠሩት፡፡ በእርግጥ ይሄ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ እጅግ በርካታ ��


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከአልፋ ደመላሽ ጋር እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ
ሌላ ምንጮች
  http://www.tadias.com/01/27/2011/alfa-demmelash-transforming-lives-and-communities-through-entrepreneurship/
አጥኚ
ሜሪ ጄን – ዋግል፣ ሸዊት ወልደሚካኤል