Posted on October 6, 2014 By admin

ነፃነት መንግስቱ አልማው

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በትምህርት፣ በጤናና ሳኒቴሽን ላይ በማተኮር የሴቶችንና የህፃናትን ህይወት ለማሻሻልና የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚሰራውን ፕሮጂኒስት የተባለ ድርጅት መስርታ እየመራች  ትገኛለች፡፡  የመክሊት አነስተኛ የብድር ተቋምም መስራችና ስራ አስኪያጅ ናት፡፡ ተቋሙ ላለፉት አስር አመታት በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች የብድርና የስልጠና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ የፕሮጂኒስት ዋና ዳይሬክተር
የትውልድ ቦታ: አሶሳ፣ ወለጋ
የትውልድ ዘመን: ሚያዝያ 6 ቀን 1943 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አሶሳ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
እቴጌ መነን ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመርያ ድግሪ፣  (ቢኤ)፣ በቢዝነስ አስተዳደር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ
የሴቶች ተቆርቋሪ
የሕይወት ታሪክ
ነፃነት መንግስቱ የሴቶችን ህይወትና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በቁርጠኝነት የሚሰራ ፕሮጂኒስት የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመና  መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ስትሆን ከፕሮጂኒስት ጋር ጥምረት በመፍጠርም መክሊት አነስተኛ የብድር ተቋምን መስርታለች፡፡ ይሄ አገር በቀል አነስተኛ የብድር ባንክ በዋናነት ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚሰራ ነው፡፡ ስራ ከጀመረ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ድርጅቱ፤ሴቶችና ልጃገረዶች የትምህርት፣ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲጎለብትና ማህበራዊ ልማት እንዲስፋፋ በትጋት እየሰራ ነው፡፡ ድርጅቱ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የጉራጌ ዞን እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በወሊሶ፣ ቀርሳና ማሊማ ወረዳዎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል፡፡  በ1997 ዓ.ም ለኖቤል የሰላም ሽልማት ከታጩት 1ሺ ሴቶች መካከል አንዷ የነበረችው ነፃነት፤ አገሯን ለማሻሻል በቁርጠኝነት መታተር የህይወት ዘመን ስራዋ በመሆን ቀጥሏል፡፡በቀድሞ የወለጋ ክልል አሶሳ ከተማ የተወለደችው ነፃነት፤ በአዲስ አበባ እቴጌ መነን ት/ቤት ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስ ስኩል ገብታ፣ በቢዝነስ አስተዳደር የመጀመርያ ድግሪዋን አግኝታለች፡፡ መጀመርያ ላይ ገበሬ የመሆን ህልሟን እውን ለማድረግ በማሰብ አለማያ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ፈልጋ ነበር፡፡ ሆኖም ዩኒቨርስቲው ያኔ ለሴቶች ከባልትና ሳይንስ በስተቀር የድግሪ ፕሮግራም ስላልነበረው ህልሟ እውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ነፃነት ዩኒቨርስቲ ስትገባ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተጋጋለበት ወቅት ስለነበር እሷም የለውጥ እንቅስቃሴው ንቁ ተሳታፊ ልትሆን በቃች፡፡ በዚህም ሳቢያ በ1966 ዓ.ም በንጉሱ ከዩኒቨርስቲው ከታገዱ ተማሪዎች አንዷ ሆናለች፡፡ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተቀጥራ በማዘጋጃቤቶች ዲፓርትመንት ስራ የጀመረችው ነፃነት፤ በመላው አገሪቱ በስፋት የተጓዘች ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ባለ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በቅርበት መገንዘብ ቻለች፡፡ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደምትሰራም ቁርጠኝነቷን አረጋገጠች፡፡ የደርግ መንግስት ጨቋኝነት እያደር እየጨመረ ሲመጣ፣ ደርግን ለመቃወም በተቋቋመው የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ውስጥ አባል በመሆን ለአራት ዓመት ( ከ1968 – 1972 ዓ.ም) በህቡዕ የሰራችው ነፃነት፤ በደርግ ተይዛ ለስድስት ዓመት ታስራለች፡፡ የወህኒ ቤት ህይወት በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም መገደልም ስለነበረ በእስር ብቻ መገላገሌን እንደ እድለኛነት እቆጥረዋለሁ ትላለች- ነፃነት፡፡ ከእስር ቤት ተመክሮዋ የተሻለ ነገር ለማውጣት በመወሰንም እንደሰው ልጅ ያደግሁት እዚያ ነው ብላ ታምናለች፡፡ ከተለያዩ የህይወት ዘርፎች ከመጡና በአዕምሮ ከበሰሉ ሰዎች እጅግ ብዙ ትምህርት ቀስማለች፡፡ በወህኒ ቤት ውስጥ ት/ቤት የመግባት እድል ያገኘችው ነፃነት፤ለራሷ ከመማሯም ባሻገር ማስተማሯንም ትናገራለች፡፡ በወቅቱ ወህኒቤቱ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሰፊ የመፃህፍት ስብስብ ነበረው፡፡ ለዚህም ነው የስድስት ዓመት እስሯን ምርጥ ትምህርት የተከታተለችበት ጊዜ አድርጋ የምትቆጥረው፡፡ የዛሬ ህይወቷንና ስራዋን በመቅረፅ ረገድም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ትገልፃለች፡፡በ1978 ዓ.ም ከወህኒ ቤት ከወጣች በኋላም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ መስራት ጀመረች፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶችም ውስጥ ስዊዲሽ ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ይገኝበታል፡፡ ጨቋኙ የደርግ መንግስት እንዲገረሰስ በነበራት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ፣ በኢህአዴግ ድል መቀዳጀት መደሰቷ አልቀረም፡፡ በመጪው ዘመን ከሽግግር መንግስቱ ጋር ተመሳሳይ ራዕይ እንደምትጋራ በማመንም፣ የውጭ ንግድ  ምክትል ሚኒስትር ሆና ስትሾም ሳታንገራግር ሹመቱን ተቀብላ ለሁለት ዓመት ሰርታለች፡፡ ሆኖም  የሽግግር መንግስቱ ከሚከተላቸው አቅጣጫዎች በአንዳንዶቹ ላይ ልዩነት እንዳላት ይፋ ሲወጣ አለቆቿ ተበሳጩ፡፡ ከዚያም መንግስት ምክንያቱን ሳይገልፅላት ከሃላፊነቷ አነሳት፡፡ ይሄን ተከትሎም የሽግግር መንግስቱ ይፋ መልቀቂያ እንዲሰጣት ጥያቄ አቀረበች፡፡ ከመንግስት አስፈላጊውን መረጃ እጇ ካስገባች በኋላ፣ በምን ዘርፍ ላይ ብትሰማራ ለአገሯ ውጤታማ አገልግሎት ልትሰጥ እንደምትችል ማሰብ ማሰላሰል ያዘች፡፡ በመጨረሻም የህይወቷን ጥሪ ለትርፍ ባልተቋቋመ ዘርፍ ውስጥ አገኘችና በሴቶች ጉዳይ ላይ ለመስራት ተነሳች፡፡ ድርጅት ለመመስረት ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ ያልነበራት ቢሆንም ህልሟንና ልቧን ይዛ ፕሮጂኒስት የተባለውን ድርጅት መሰረተች – በ1971 ዓ.ም ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በሚል በማስመዝገብ፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴና በኋላም በኢህአፓ ውስጥ በነበረች ጊዜ፣ ሴቶችን በተመለከተ አያሌ ትንተናዎች መሰራታቸውን፣ ነገር ግን ያለጥቅም በመፃህፍት መደርደርያ ላይ መቅረታቸውን ታውቃለች፡፡ እነዛ ትንተናዎች የሴቶችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ወይም ለሴቶች የአመራር ቦታዎችን በመስጠት ረገድ ምንም የረባ ውጤት እንዳላመጡም ተገንዝባለች፡፡ ከእስር በተለቀቀች ጊዜ የሴቶች ወደ ህዝብ መድረክ የመግባት እሳቤና አቅም እየተዳከመ መምጣቱ ተሰምቷታል፡፡ ደርግ የሴቶችን ችግሮች ለመፍታት አንዳንድ ስራዎችን ቢሰራም ጥረቱ የብዙሃኑ ህዝብ ህይወት ላይ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ሴቶች የተጋረጠባቸውን ማህበራዊና ባህላዊ እንቅፋቶች  ተጋፍጠው እንዲያሸንፉ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲያጎለብቱ ዘላቂ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመነች፡፡አራቱ የትምህርት፣ ጤና፣ ንፁህ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም የቢዝነስ ልማት ምሰሶዎች ላይ ለማተኮር በመወሰን፣ ነፃነትና ፕሮጂኒስት የተባለውን ድርጅት አብረዋት የጀመሩ ሌሎች ሴቶች ለመጀመርያ ስራቸው በአዲስ አበባ አንድ ወረዳን መረጡ – ልደታ ተብሎ የሚጠራውን የቀድሞ ወረዳ 26፡፡ ወደ ማህበረሰቡ ዘልቀው ሲመለከቱ ግን ችግሮቹ ካሰቡት በላይ የከፉ መሆናቸውን ተገነዘቡ፡፡ እናም በቁጠባና በብድር ፕሮግራም የእናቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከማጎልበት በተጨማሪ፣ ሴቶችን ከመሃይምነት ማላቀቅና የልጃገረዶች ትምህርት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልጋቸው አሰቡ፡፡ የውሃ እጥረትና የንፅህና አጠባበቅ ችግርም ከገመቱት የበለጠ አስከፊ ነበር፡፡ ውሃ፣  ሳኒቴሽን፣ የህፃናት ትምህርትና ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት የቅድምያ ትኩረታቸው አድርገው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ዛሬ ፕሮጂኒስት በሶስት ክልሎች እየሰራ ይገኛል – በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጉራጌ ዞን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በርካታ ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት በመገንባት ላይ ነው፡፡

ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሚታዩትን ሴቶችና ህፃናትን የመጨቆን ጎጂ ልማዶችን ለመከላከል የፆታ ፍትህ ማዕከላትን ያቋቋመ ሲሆን ሴት የህግ ባለሙያ ረዳቶችን በማሰልጠን ችግሮቹ ላይ አተኩረው ለመፍትሄ እንዲሰሩ ጥረት አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማህበረሰቡን በማደራጀት ችግሮቹን እንዲገነዘብና ጥቃትን እንዲከላከል በትጋት ሰርቷል፡፡ በአዲስ አበባ፣ ወሊሶ፣ እንድብርና ቡታጅራ የጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ህፃናት የጉዳት ማገገሚያ ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን ህዝቡን በማስተማር እንዲሁም ጥቃቶችን በመከላከል ጥረት ላይ ፖሊስንና የፍትህ ስርዓቱን በማሳተፍ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ድርጅቱ በአዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግ መሰረት በእነዚህ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራውን የቅስቀሳ እንዲሁም ከፖሊስና ፍትህ ስርዓቱ ጋር ሲያከናውናቸው የነበሩትን ተጓዳኝ ስራዎች ለማቆም ተገዷል፡፡ ሆኖም ለጥቃት ተጎጂዎች የምክርና የህክምና ድጋፍ መስጠቱን ቀጥሏል፡፡  በ2004 ዓ.ም አስራ አምስተኛ ዓመቱን ያከበረው ድርጅቱ፤ አገልግሎቱን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ማዳረስ የቻለ ሲሆን ከ8ሺ በላይ ህፃናትንም በአማራጭ የመሰረታዊ ትምህርት ማዕከላቱ ውስጥ አስተምሯል፡፡

ድርጅቱ በተለይ በትምህርት ላይ በሰራቸው ስራዎች እንደምትኮራ ነፃነት ትናገራለች፡፡ በፕሮጂኒስት ት/ቤቶች ትምህርታቸውን አሃዱ ብለው የጀመሩ ብዙዎቹ የገጠር አካባቢ ህፃናት በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከመከታተል ደርሰዋል፡፡ ፕሮጂኒስት በቡታጅራ ከተማ በሆስቴልነት የሚያገለግል ባለሁለት ፎቅ ህንፃ በማስገንባት ሂደት ላይ ሲሆን ሆስቴሉ ከት/ቤታቸው ርቀው የሚኖሩ የከተማና የገጠር ችግረኛ ልጃገረዶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በመኖርያነት የሚያገለግል ይሆናል፡፡ ድርጅቱ በት/ቤቶች ውስጥ ክለቦችን ከማቋቋምም ባሻገር፣ ክለቦቹ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ድጋፍ ለሚያደርጉ መምህራን ስልጠና ይሰጣል፡፡ ህፃናት ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ራሳቸውን በነፃነት እንዲገልፁ፣ በራሳቸው እንዲተማመኑና ለመብታቸው እንዲቆሙ በማስተማርም በመላው ህይወታቸው ሁሉ የሚያገለግላቸው ትምህርት እንዲያገኙ ይተጋል – ፕሮጂኒስት፡፡ ድርጅቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ወንድና ሴት የፆታና የአካል ጥቃት ተጎጂዎችንም ያስተምራል – ስለመብታቸው፣ ከቤተሰብ ጋር መወያየት ስላለው ጥቅም፣ እርዳታ የት እንደሚያገኙና ተቋማት ስለተጣለባቸው ድጋፍ የመስጠት ሃላፊነቶች እና የመሳሰሉት፡፡ ብዙውን ጊዜም እኒህ ተጎጂዎች ከጉዳታቸው ካገገሙ በኋላም ሌሎች ተጎጂዎችን መርዳትና መደገፍ ይጀምራሉ፡፡ አሁንም እንዳለመታደል ሆኖ ግን ፕሮጂኒስት በእነዚህ ዘርፎች የሚያከናውናቸው ስራዎቹ በአዲሱ ህግ ታግዷል፡፡

ለሴቶች ከወንዶች እኩል መብት ለማጎናፀፍ የሚደረገው ትግል በአንድ ጀንበር ውጤት የሚያመጣ ሳይሆን የረዥም ጊዜ ሂደት መሆኑን ነፃነት ታምናለች፡፡ በየትኛውም ክልልና የኑሮ መደብ ውስጥ ሴቶች ለጥቃት ተጋላጮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም አካባቢ ሴቶች የበታች ናቸው የሚል አመለካከት በመስፈኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለሴቶች እኩልነትና ፍትሃዊ አያያዝ መወያየት እንኳን አስቸጋሪ ነው፡፡ ስር የሰደዱ አመለካከቶችና ልማዶችን በአንድ ጊዜ መለወጥ አይቻልም፡፡ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ግን ትግሉ መቀጠሉ ወሳኝ ነው፡፡ ከፍተኛ ስራና አቅምም ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው ህግ መሰረት፣ ፕሮጂኒስት አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት በመሆኑ ትግሉን የመምራት ሚና ሊጫወት አይችልም፡፡ ሆኖም ትግሉ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሴቶች በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በዝምታ መመልከት የለባቸውም የምትለው ነፃነት፤ ይልቁንም እርስ በርስ በመመካከርና በመተጋገዝ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መቃወምና መከላለል እንዳለባቸው ታምናለች፡፡ ሴቶች በቤተሰብ ክበብ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ በመንፈሳዊና ማህበራዊ ማህበራት ውስጥም ይታቀፋሉ፡፡ ለምሳሌ ሲሞቱ የሚተጋገዙበት እድር አላቸው፡፡ ነገር ግን በህይወት ሳሉ አይተጋገዙም፡፡ ሴቶች ስለራሳቸው ጉዳዮች የሚወያዩበት መድረክ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሄ ጉዳይ አስፈላጊ ነው ብለው መወሰን ብቻ ሳይሆን  ለውጥ ለማምጣት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን መሰዋት አለባቸው፡፡

ለወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች የነፃነት ምክር እንዲህ የሚል ነው- “ሴትነት ክብርና ኩራት መሆኑን እወቁ፡፡ ሴቶች የበታች አይደሉም፡፡ በመብቶቻችሁ ጉዳይ ላይ አትደራደሩ፡፡ ለትዳራችሁ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ባላችሁን አክብሩ፡፡ ነገር ግን ጥቃትን አትቀበሉ፡፡ ገና በትዳራችሁ መጀመርያ ላይ ጥቃትን አሻፈረኝ ካላላችሁ ጥቃቱ እየተባባሰ ይመጣል፡፡ ለሌሎች የመስጠትና የማካፈል ባህልን ተግብሩ፡፡ እያንዳንዳችን ለሌሎች የመስጠት ሞራላዊና መንፈሳዊ ሃላፊነት አለብን፡፡ በትንሽ ድጋፍ ሰዎች ትላልቅ ስኬቶችን ሊቀዳጁ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትንሽ ድጋፍ ወይም ማበረታቻ ባለማግኘታቸው ብቻ የትም ሳይደርሱ ባክነው የቀሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እናም ሌሎችን ለመደገፍ የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡”

ዋና የመረጃ ምንጮች
ሀምሌ 2004 ዓ.ም ከነፃነት መንግስቱ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፤
ሌላ ምንጮች
www.progynist.org.et ;http://word.world-citizenship.org/wp-archive/447
አጥኚ
ናሁሰናይ ግርማ