Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ደስታ ገብሩ ደስታ

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
የጦር ሠራዊት ሚስቶች ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት በመሆን ወላጆቻቸውን ላጡ የወታደር ልጆች የማሳደጊያ ማዕከል አቋቁማለች። የሟች ወታደር ቤተሰቦች ማህበራዊ ደህንነት እንዲረጋገጥ አገራዊ ዘመቻ ከመምራቷም በተጨማሪ፤ የወታደር ሚስቶች ከቤት ውጭ ለሥራ እንዲሰማሩ በማበረታታትና ወጣት ሴቶችን በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች። ፀሐይ ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በማቋቋም በርዕሰ መምህርነት ሰርታለች – ትምህርት ቤቱ ወደ መንግስት ከተላለፈ በኋላም ጭምር። የኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበርና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ውስጥ የአማካሪ ኮሚቴ አባልና ድጋፍ አሰባሳቢ በመሆን አገልግላለች።
የትውልድ ቦታ: ፍልውሃ ሆስፒታል፣ አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: ህዳር 21 ቀን 1914 ዓ.ም
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
እቴጌ መነን ትምህርት ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
እቴጌ መነን ትምህርት ቤት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ሴክሬታሪያል ሰርቲፊኬት፣ በአዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት
ዋና የስራ ዘርፍ
ማህበራዊ ደህንነት
የሕይወት ታሪክ
ከከንቲባ ገብሩ ደስታ አምስት ሴት ልጆች መካከል አንዷ የሆነችውና የኮርያ ዘመቻ ዋና አዛዥ የካሳዬ የለምቱ ባለቤት የሆነችው ደስታ ገብሩ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ የተሰማሩ ወታደሮች ባቀረቡት አቤቱታ ልቧ ተነክቶ፣ ወላጅ ያጡ የወታደር ልጆችን ለመደገፍ በ1948(49) ዓ.ም የጦር ሠራዊት ሚስቶች ማህበርን ያቋቋመች ጠንካራ ሴት ናት። ያለ ወላጅ የቀሩ የወታደር ልጆችን ለመደገፍ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ከማቋቋም በተጨማሪ፣ ማዕከሉን ለማስፋፋት ሳታሰልስ ላይ ታች የታተረችው ደስታ ገብሩ፣ ሰዎችን አስተባብራ ድጋፍ የማሰባሰብ አስደናቂ ችሎታ ነበራት። ተውኔቶችን ፅፋ ለመድረክ በማብቃት፣ የሙዚቃ ፈጠራዎችን ሰርታ ለተመልካች በማቅረብ፣ የመዝናኛ ድግስ አዘጋጅታ እንግዶችን በመጋበዝ የገንዘብ ድጋፍ አሰባስባለች። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና የኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበር ውስጥም በአማካሪ ኮሚቴ አባልነቷ ሁለቱንም ማህበራት የሚያጠናክር የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰባሰብ ረድታለች። ታታሪነቷ፣ ፅናቷና ብርታቷ ተዳምረው፣ በማህበራዊ አገልግሎት በርካታ ስኬቶችን እንድታስመዘግብ አስተማማኝ ሃይል ሆነውላታል። ደስታ ገብሩ  ያልሆነችው ነገር የለም ማለት ይቻላል። ማህበራዊ ፕሮግራሞችን ፈጥራ እቅድ ከማውጣት ጀምራ፣ በፋይናንስ አስተዳደርና በሥራ አስኪያጅነት የተለያዩ ተቋማትን መርታለች። በበላይ ተቆጣጣሪነት የተለያዩ ስራዎችን ለስኬት የምታበቃ፣ በርካታ ወጣቶችን በሙያና በስነምግባር ኮትኩታ ለትልቅ ደረጃ የምታደርስ ብርቱ ሴት የነበረችው ደስታ ገብሩ፤ በአስተማሪነትና በርዕሰ መምህርነትም አገልግላለች። የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የማዘጋጀትና የመምራት ችሎታዋማ ልዩ ነው – አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በቲኬት ሻጭነትና በአስተናጋጅነት ጭምር ከመስራት ወደኋላ አትልም።አስራ ሁለት ልጆች በነበሩት ቤተሰብ ውስጥ ከአምስት እህትማማቾች መካከል አንዷ የሆነችው ደስታ፤ ከወንዶች እኩል ሆና እንድትኖር ነው አባቷ ከንቲባ ገብሩ ኮትኩተው ያሳደጓት። የተማሩና በርካታ ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉት ከንቲባ ገብሩ፤ የልጅ አስተዳደግ ሃሳባቸው ከዘመኑ ልማድ የተለየ ነበር። ሴት ልጆቻቸው ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ቤት ውስጥም ስልጡን አኗኗርን አስተምረዋቸዋል። ለሴት ልጆቻቸው በሚሰጡት የዘወትር ትምህርት፣ ከወንድ በምንም እንደማያንሱና በሴትነታቸው የሚያፍሩበት ምክንያት እንደሌለ አስረድተዋቸዋል። በስልጡን አስተዳደግ፣ እንደምርጫዋ ደፋርና ጎበዝ የመሆን እድል ያገኘችው ህፃኗ ደስታ፣ ነገረ ስራዋ በማህበረሰቡ ውስጥ ያልተለመደ አይነት በመሆኑ የብዙ ሰዎችን ትኩረት መሳቧ አልቀረም። የዚያን ዘመን ሴቶች፣ አንገታቸውን የደፉ ሽቁጥቁጦች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ስለነበር፤ ደስታ እንደ ሃይለኛ ሰው ትቆጠር ነበር። በወግ አጥባቂ ህብረተሰብ ውስጥ፣ አንገቷን ሳትደፋ የምታስበውን ነገር ሁሌም ፊት ለፊት እየተናገረች በተደጋጋሚ ብዙ ሰዎችን ታስደነብር ነበር።

ገና በ16 አመቷ ወደ ትዳር ገብታ በአመት ልዩነት ወንድ ልጅ የወለደችው ደስታ፤ ሌላ ልጅ በጨቅላነቱ ቢሞትባትም እስከ 36 ዓመቷ  ሁለት ሴት ልጆችን አፍርታለች። ልጆችን እንደ ነፍሷ ነበር የምትወደው። የሕይወት ዘመኗንም ያሳለፈችው ለሕፃናት ደህንነትና ትምህርት ሳትታክት በመስራት ነው። ትዳርና ቤተሰብ ስትመሰርት ትምህርቷን ለበርካታ አመታት አቋርጣ ብትቆይም፣ ተመልሳ ት/ቤት በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ፣ በንግድ ሥራ ፀሃፊነት ተመርቃለች። ያኔ የደስታ ባለቤት በኮርያ ዘመቻ የኢትዮጵያ ጦር አዛዥ እንደነበር ልጃቸው ታምራት ያስታውሳል። ከዚያ በኋላ በትምህርቷ ልትገፋበት አልቻለችም፤ ባለቤቷ በውትድርና ሥራው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወርና ሲመደብ፣ ቤተሰቡ በአንድ ቦታ ረግቶ ለመኖር አልቻለም ነበር። ለሥራ በሚመደብባቸው ቦታዎች ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አልነበሩም ማለት ይቻላል።

ደስታ ገብሩ በ1940ዎቹ መጨረሻ ገደማ ለተወሰነ ጊዜ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ብታስተምርም፣ የመጀመሪያዎቹን 12 የትዳር አመታት ቤት ውስጥ ሙሉ ጊዜዋን ለቤተሰቧ በመስጠት ነው ያሳለፈችው። በ1951 ዓ.ም ገደማ ነው፤ ሴት ተማሪዎችን ብቻ በሚያስተናግደው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት አጠገብ፣ ሴትና ወንድ በጋራ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመክፈት የወሰነችው። ስሙንም ፀሐይ ጮራ ብላ ሰየመችው። በየወሩ ከቆጠበቻት ገንዘብ በተጨማሪ፣ አባቷ ከሰጧት መሬት፣ በባሕር ዛፍ ሽያጭ አልፎ አልፎ የምታገኘውን ገንዘብ ጨምራ፣ ወደ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም አቅጣጫ፣ ከመንገድ ዳር አንድ ግቢ ተከራየች፤ የትምህርት ቤት ቁሳቁስና የመማሪያ መሳሪያዎችን ገዛች፤ አስተማሪዎችን ቀጥራም የአንደኛ ክፍል ትምህርት ጀመረች። በየአመቱ እያሳደገች እስከ 6ኛ ክፍል አድርሳ፣ ትምህርት ቤቱን ለመንግስት ለማስረከብ ያቀደችው ደስታ፤ ትምህርት ቤቱ ራሱን ችሎ እንዲቆም በማሰብ ተማሪዎች በየወሩ አንድ ብር እንዲከፍሉ ወሰነች። እንዳሰበችው አልሆነም። ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ብዙ ቤተሰቦች፣ በወር አንድ ብር የመክፈል አቅም እንደሌላቸው ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባትም። እናም መፍትሄ ማበጀት ነበረባት። አቅም ያላቸው ቤተሰቦች አንድ ብር እንዲከፍሉ፣ አቅም የሚያጥራቸው ሃምሳ ሳንቲም፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ ከክፍያ ነፃ እንዲሆኑ አደረገች። ብዙዎቹ ተማሪዎች የወታደር ልጆች ናቸው፤ አንዳንዶቹም በእናት ብቻ የሚያድጉ የሟች ወታደር ልጆች ናቸው። በየወሩ አንድ ብር ለመክፈል አቅም የሌላቸው ወላጆች በርካታ በመሆናቸው፣ ትምህርት ቤቱ ያን ያህልም የሚያወላዳ ገቢ አልነበረውም። በህመም፣ በቀብር ወይም በወሊድ ሳቢያ ከስራ የሚቀሩ አስተማሪዎችን ለመተካት ተጨማሪ መምህራንን መቅጠር ቢያስፈልግም፤ ደስታ ገብሩ ወጪ ለመቀነስ ብላ ከርዕሰ መምህርነት በተጨማሪ ምትክ አስተማሪ ሆና መሥራት ነበረባት። ፀሐይ ጮራ በትምህርት ሚኒስቴር ከተወሰደ በኋላም፣ በርዕሰ መምህርነት ደሞዝተኛ ሆና የቀጠለች ሲሆን ያለ ተጨማሪ ክፍያ በምትክ አስተማሪነት መሥራቷንም እንዳልተወች የመጨረሻ ልጇ ራሄል ታስታውሳለች።

ትምህርት ቤቱ እንዲህ በፈተናዎች ታጅቦ ቀስ በቀስ እየተስፋፋና እያደገ ሲሄድ፣ ሃላፊነቶቹም እየጨመሩ መጡ። ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን፣ የመረብ ኳስ፣ የጂምናስቲክስ እና ሌሎች የስፖርት ስልጠናዎችን በመስጠት በተማሪዎች መካከል ውድድር የሚካሄድበት አመታዊ በዓል ያዘጋጅ ነበር። ምንም እንኳ ትምህርት ቤቱን ለማስፋፋት ይቅርና በእግሩ እንዲቆም ለማድረግ ከባድ የገንዘብ ችግር ቢፈታተናትም ፤ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ በአስር አመት ውስጥ ያሰበችውን አሳክታ፣ በ1960 ዓ.ም ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክባለች።

በእርግጥ ፈተናው የገንዘብ እጥረትና የስራ መደራረብ ብቻ አልነበረም። ትምህርት ቤቱን ለመክፈትና ለማስፋፋት ላይ ታች ስትል፣ ብዙ ሰዎች ተችተዋታል – የትምህርት ቤቱን ግቢ ያከራይዋት ሴትዮ ሳይቀሩ፣ “የቤት እመቤትና የልጆች እናት እንዲህ አይነት ሥራዎች ውስጥ መግባት የለባትም” በማለት ገስፀዋታል። የደስታ ገብሩ ጠንካራ እምነት ግን መሰረቱን አልለቀቀም። ከችግረኛ ቤተሰብ የተወለዱ ሕፃናት ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ትልቅ ሥራ እንደሆነ ከልብ አምናበት ነው ወደ ሥራው የገባችው። ለትምህርት የነበራት ክብር ከአባቷ ከከንቲባ ገብሩ የወረሰችው እንደሆነም ልጇ ሃና ትመሰክራለች። ችግረኛ ሰዎችን አይታ ዝም ማለት የማያስችላት ደስታ ገብሩ፤ የመማር እድል ያልነበራቸው ችግረኛ ልጆችን ስታይ ለውጥ የማምጣት ፍላጎቷ ገፋፍቷት ወደ ሥራ ገባች።

ከዚሁ ጎን ለጎን፤ ደስታ ገብሩ ከእህቷ ከስንዱ ጋር ለቀይ መስቀል ማህበርና ለኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበር የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ብዙ ደክማለች። ቀይ መስቀልና የሴቶች ደህንነት ማህበር በጃንሆይ ሜዳ (በጃንሜዳ) የሚያዘጋጇቸው አመታዊ ባዛሮች ላይ፣ የምግብ ዝግጅትና የመስተንግዶ ሥራዎችን በመምራት የገንዘብ ድጋፍ አሰባስባለች። የቶምቦላ ቲኬቶችን በመሸጥ፣ እንዲሁም በወታደራዊ የሙዚቃ ባንድ የመዝናኛ ዝግጅቶችን በማሰናዳት የገንዘብ ድጋፍ ስታሰባስብ፣ ብዙውን ጊዜ እስከ ንጋት ድረስ ዝግጅቶቹን ራሷ ስትመራ ታድር ነበር።

በ1956 ዓ.ም በድርቅ ሳቢያ የከፋ ረሃብ በመከሰቱ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ደህንነት ማህበርና የቀይ መስቀል ማህበር በጋራ የእርዳታ እቅድ ሲያዘጋጁ፣ የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታውን ለማድረስ በበጎ ፈቃድ ለስራ የተነሱት ደስታ ገብሩና ሁለት ሴቶች ናቸው። የብዙዎችን የረሃብ ስቃይ ባየችበት ልብ የሚሰብር ጉዞ ላይ ነው፤ የሕይወት አቅጣጫዋን የሚቀይር ሌላ አሳዛኝ ነገር የገጠማት። የሶማሊያ ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል በጠረፋማው ቶጎ ውጫሌ የተሰሩ የጦር ሰፈሮችን ስትጎበኝ፣ ህሊናን የሚፈታተን መከራ ተመለከተች። የወታደሮቹ አኗኗር በእጅጉ ዘገነናት። ምሽግ ውስጥ እስከ ደረቱ ድረስ ጨቅይቶ ለጥበቃ የተሰማራ ወታደር አግኝታ አነጋገረችው። መከራውንና ስቃዩን እንችለዋለን፤ ምክንያቱም አውቀን የገባንበት ጉዳይ ነው አላት። የሚያስጨንቀው ነገር፣ የራሱ ስቃይ አይደለም። እኔ ብሞት ሚስቴንና ልጆቼን ዞር ብሎ የሚያያቸው እንደማይኖር ሳስብ እጨነቃለሁ ካለ በኋላ፤ ምን ልታደርጊልን ትችያለሽ በማለት ጠየቃት። በወታደሩ መከራና ጭንቀት ልቧ የተነካው ደስታ ገብሩ፤ የምትችለውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ቃል ገባች። የሕይወት አቅጣጫዋን ባስለወጣት በዚሁ አሳዛኝ አጋጣሚ መነሻነት፤ የሟች ወታደር ቤተሰቦችን ለመደገፍ በራሷ ላይ ሃላፊነት ጫነች።

ከጉብኝቷ እንደተመለሰች፣ በወቅቱ ሜጀር ጄነራል ለነበረው ባለቤቷና ለልጆቿ ምን እንዳጋጠማትና ምን ለማድረግ ቃል እንደገባች ነገረቻቸው። ቃሏን አክብራ ለሥራ ለመነሳት ጊዜ አላባከነችም። አምስት ሴቶችን (የጦር ሠራዊት ሚስቶችን) እቤቷ ድረስ ለሻይ ግብዣ ጠርታቸው ሲመጡ ነው፣ የጦር ኃይል ሚስቶች ማህበር የተጠነሰሰው። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላም ስራዬን ጨርሻለሁ ብላ አላቆመችም። ማህበሩ እንዲስፋፋና ጠንካራ አገር አቀፍ መሰረት እንዲይዝ፣ ጊዜና ቦታ ሳይገድባት  የወታደር ሚስቶችን በአባልነት ለመመልመል ዘመተች – ከባሎቻቸው ብርቱ ተቃውሞ ቢገጥማትም ወደ ኋላ አላለችም። ወላጅ ላጡ የወታደር ልጆች የማሳደጊያ ማዕከልና ትምህርት ቤት በማስገንባት ለዘለቄታው የማስተዳደር አላማ ይዞ የተነሳ ማህበር፣ ጠንካራ አቅም መገንባት አለበት። በዚህ በዚህ ደግሞ ደስታ ገብሩ፣ ማንም አይስተካከላትም። የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ በኩል፣ እጅግ የተዋጣላት ናት። በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል የፋሽን ትርዒቶችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ፤ “ምኞቴ” በሚል ርዕስ ተውኔት ፅፋ በብሔራዊ ትያትር ቤት (በቀድሞው ኃይለ ሥላሴ ትያትር ቤት) ለመድረክ በማብቃት ለማህበሩ ገንዘብ አሰባስባለች። የጦር ሠራዊት፣ የፖሊስና የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድኖችን በማስተባበር፤ እንዲሁም ከስፔን፣ ከጣልያን፣ ከራሺያ እና ከሌሎች አገራትም የተለያዩ የጥበብ ሰዎችን በመጋበዝ የአዲስ አመት ዋዜማ ትርዒቶችን በልደት አዳራሽ እና በገነት ሆቴል አቅርባለች። ይሄ ሁሉ፤ ዘመናዊ የሕፃናት ማሳደጊያ ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚበቃ አንድ ሚሊዮን ብር ገደማ ለማሟላት ነው።

ደስታ ገብሩ ካሰበችው አላማ ፍንክች እንደማትል ልጇ ሃና ስትመሰክር፣ የ12 አመት ሕፃን ሳለች ባለ አንድ ብር የቶምቦላ ትኬቶችን እንድትሸጥ ከተላከች በኋላ የተፈጠረውን ገጠመኝ ትጠቅሳለች። አንዱ ሚኒስትር ጋ እንድትሄድ ነው እናቷ የላከቻት። መቶ ትኬቶችን ይዛ የሄደችው ሃና፤ ሦስቱን ብቻ ሸጣ ተመለሰች። ደስታ ገብሩ ይህንን ማመን አልቻለችም። አንድ ሚኒስትር እንዴት የ3 ብር ትኬት ብቻ ይገዛል? በዚህ የተናደደችው እናት፤  እልህ እየተናነቃት፣ ልጇን ሃናን እየጎተተች ወደ ሚኒስትሩ ቢሮ ገሰገሰች። ሚኒስትሩ የደስታ ገብሩን የሰሙት ገና ቢሯቸው ሳትገባ ከፀሐፊያቸው ጋር ስትነጋገር ነው። ፊት ለፊት መጋፈጥ አሳፍሯቸው፤ ቢጨንቃቸው… ጠረጴዛ ስር ገብተው ተደበቁ። ደስታ ገብሩ ግን ያሰበችውን ሳታሳካ ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበረችም። የለበሰችው ጠባብ ቀሚስ ቢያስቸግራትም ተንበርክካ ጠረጴዛው ስር የነበሩትን ሚኒስትር አፋጠጠቻቸው። “ለመቶ ብር እንዲህ ራስዎን ሲያዋርዱ ያሳፍራል! ከፍለው ቢገላገሉ አይሻልም?” ብላ ጮኸች። ከቢሮው ተሰናብታ የወጣችው ትኬቶቹን አስረክባ መቶ ብር ከተቀበለች በኋላ ነው።

በመጨረሻ የደስታ ገብሩ እቅድና ጥረት ሰምሮ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከሉ ተገነባ። በአዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ (ቀድሞ አስመራ መንገድ በሚባለው) የተገነባው የሟች ወታደር ልጆች ማሳደጊያ ማዕከልና ትምህርት ቤት፣ 500 ሕፃናትን የማስተናገድ አቅም ነበረው። ደስታ ገብሩ በዚህ አላቆመችም። የጦር ኃይል ሚስቶች ማህበር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎችን እንዲያቋቁም በመላ አገሪቱ ከዳር ዳር ተሯሩጣለች። በሄደችበት ሁሉ፣ የወታደር ሚስቶችን እያነሳሳችና እያነጋገረች አስተባብራለች። በየጦር ካምፑ በምታቀርባቸው ንግግሮችም፤ ሁሉም ወታደሮች ከደሞዛቸው በየወሩ ሃምሳ ሳንቲም እንዲያዋጡ ሳትጠይቅ የቀረችበት ጊዜ የለም። የወታደር ቤተሰቦች ማህበራዊ ደህንነት ትኩረት እንዲያገኝ በየጊዜው ከቴሌቪዥንና ከሌሎች የዜና አውታሮች የማትጠፋ ሆነች። እንዲህ ማህበሩን ለማጠናከር በየሚዲያው ወጣ ወጣ ብላ መታየቷ ግን ከአንዳንድ የንጉሡ ቤተሰቦች ጋር የነበራትን ግንኙነት አሻክሮባታል።

እንዲያም ሆኖ የደስታ ገብሩ ጥረት ባለመቋረጡ፣ ማህበሩ በተለያዩ ከተሞች ጠንካራ ቅርንጫፎችን ለመመስረት በቅቷል። የጦር ሠራዊት ኮሎኔል ሚስት የሆነችው እህቷ ገነት ገብሩ በፕሬዚዳንትነት የምትመራው የአስመራ ቅርንጫፍ፤ እንዲሁም የድሬዳዋና የሀረር ቅርንጫፎች በጥንካሬያቸው ተጠቃሽ ናቸው። ተጨማሪ የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላትን ለማቋቋም፣ ቅርንጫፎቹ ራሳቸውን ችለው የገቢ ማሰባሰቢያ ልዩ ዝግጅቶችን ያሰናዱ ነበር። የሀረሩን ቅርንጫፍ ያቋቋመችው ራሷ ደስታ ገብሩ ነች – ባለቤቷ የአካባቢው አስተዳዳሪ በነበረበት ወቅት። ማህበሩን ከማጠናከርና የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላትን ከመመስረት ባሻገር፣ ከዚሁ ጋር የተሳሰረ ተጨማሪ አላማ ነበራት። ባላቸውንና ልጆቻቸውን ከመንከባከብ ያለፈ ሚና ያልነበራቸው የጦር ኃይል አባላት ሚስቶች፤ ቤት ውስጥ አንገታቸውን ደፍተው ከመቀመጥ ነፃ እንዲወጡ በነበራት አላማ ብዙ ጥራለች። ማህበሩን ለማጠናከር ከየካምፑ ስትዟዟርና በየሄደችበት ቦታ ሁሉ፣ ሴቶች በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ በፈቃደኝነት እንዲሳተፉና እንዲሰሩ ማግባባት የጀመረችውም በዚሁ አላማዋ ነው። በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሚሆኑ የወታደር ሚስቶች፤ ለሥራ ከቤት ውጭ ረዥም ጊዜ ማሳለፍ ስለሚኖርባቸው ከባሎቻቸው ተቃውሞ መሰንዘሩ አልቀረም። ምን ተቃውሞ ብቻ? ቤት ውስጥ አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል ትዕዛዝም ጭምር እንጂ። ደስታ ገብሩ አርፋ አልተቀመጠችም። ሚስቴ ከቤት አትወጣም የሚሉ ወታደሮችን፣ ቤት ድረስ ሄዳ ታነጋግረዋለች። ሚስት ማለት የቤት ሰራተኛ ማለት እንዳልሆነ ታስረዳቸዋለች። ምግብ ከማብሰልና ልብስ ከማጠብ፣ ቤት ከማፅዳትና ልጆችን ከመንከባከብ ባሻገር፣ ሚስቶች ትልልቅ ነገሮችን መስራት እንደሚችሉ በማሳየት ወታደሮችን ለማሳመን ትጥራለች። ሚስቶች እንደየዝንባሌያቸው እንዲሠሩና ተጨማሪ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ጠቅላላ የጦር ኃይል ቤተሰብንና ማህበረሰቡን እንደሚጠቅም በመግለፅ ትወተውታለች። ተሳክቶላታልም። የጦር ኃይል የአካል ብቃት ባለሙያዎችን በማግባባት ሴቶችን እንዲያሰለጥኑ አድርጋለች። በክብደት ማንሳት፣ በጦር ውርወራና በሌሎች የአካል ማጎልመሻ ስፖርቶች ላይ ሴቶች መሳተፋቸው ለጤንነት ጠቃሚ ከመሆኑም በተጨማሪ ጠቅላላ የሴቶችን ድርሻና አቅም ለማጠናከር እንደሚረዳ ተገንዝባለች። በርካታ ሴቶች በማህበሩ ውስጥ የተለያየ የሃላፊነት ቦታ ይዘው ከቤት ውጭ በሚያከናውኑት ሥራ፤ የነፃነት መንፈስና የሙያ ልምድ አዳብረዋል።

ንጉሡ የጦር ኃይል ሚስቶች ማህበር የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ ደስታ ገብሩ ጥያቄ ያቀረበችው ገና ከጅምሩ ነው። ንጉሡም ተስማምተው ድጋፋቸውን ገልፀው ነበር። ነገር ግን ድጋፋቸው አልዘለቀም። አላማዋን መጠራጠር ሲጀምሩ፣ ድጋፋቸው እየሳሳ መጣ። የጦር ኃይል ጄነራል የነበረው ባለቤቷ ጎልቶ እንዲታይ፣ የተወዳጅነት ዝና እንዲያገኝና የመሪነት ወንበር ላይ እንዲቀመጥ ትፈልጋለች የሚል እምነት ስላደረባቸው፤ ድጋፋቸውን ነፈጓት። አላማዋ ግን ጨርሶ ንጉሡ እንደጠረጠሩት አልነበረም። እንዲያውም፣ ንጉሡና ቤተሰባቸው ጥረቷን አይተው እንደሚደግፏት በማሰብ ነበር ተግታ የምትሠራው። ንጉሡ ፊታቸውን ቢያዞሩባትም፣ ደስታ ገብሩ ተስፋ አልቆረጠችም።  ድጋፉን ያልነፈጋት ባለቤቷም፣ ከጎኗ አልተለየም። እቅድ ስታወጣና ንግግር ስታዘጋጅ ባለቤቷ እንደ መሞከሪያ ያዳምጣት ነበር። የቤት ሥራዎች ላይም ምሽቱ እስኪጋመስ ድረስ ያግዛታል።

ማህበሩን ለማጠናከር በተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚገኙ የሴት ማህበራትና ተቋማት ጋር ትስስር የፈጠረችው ደስታ፤ በኬንያ፣ በጂቡቲና በግብፅ የተካሄዱ ጉባኤዎች ላይ ተሳትፋለች። የማህበሩን አላማዎችና ሥራዎች በተመለከተ በ1962 (63) ዓ.ም በእስራኤል በተካሄደው አለማቀፍ የሴቶች ጉባኤ ላይ ገለፃ አቅርባለች።

ከዚህ በኋላ ነው፣ የደስታ ገብሩንና የቤተሰቧን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአብዛኛውን ሰው ኑሮ የሚያናጋ ቀውስ እየተባባሰ መላ አገሪቱን ማዳረስ የጀመረው። የንጉሡን አገዛዝ በመቃወም የተቀሰቀሰው አብዮት እየተቀጣጠለ በመጣበት በ1966 ዓ.ም፣ የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው የደስታ ገብሩ ባለቤት ክስ ሳይቀርብበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎች የካቢኔ ሚኒስትሮች ጋር ታሰረ። ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ያለ ክስ የታሰረ ሰው፣ ነፃነቱ እንዲመለስለት አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው በአገሪቱ ሕገመንግስት ቢደነገግም ሕጉ አልተከበረም። ሚኒስትሮቹ ያለ ክስ ታስረው ሁለት ወር አለፋቸው። ፍትህ በአደባባይ ሲጣስ እያየች በዝምታ ለማለፍ ፈቃደኛ ያልሆነችው ደስታ ገብሩ፤ የሚኒስትሮቹን ሚስቶች አደራጅታ ወደ ንጉሡ ቤተመንግስት አቀናች። ሁሉንም በመወከልም በንጉሡ ፊት ተናገረች፤ ታሳሪዎቹ ሚኒስትሮች ያጠፉት ነገር ካለ ህግ በሚፈቅደው ሥርዓት መሰረት እንዲከሰሱ አልያም የሚያስከስስ ጥፋት ካልሰሩ ከእስር እንዲለቀቁ ጠየቀች። ሚኒስትሮቹ አልታሰሩም በሚል ንጉሡ የሰጧት ምላሽ ቅስሟን የሚሰብር ነበር። በየቀኑ ለባለቤቷ ምግብ ለማድረስ ወደ እስር ቤቱ መመላለሷን ብትቀጥልም፣ ከሳምንት በኋላ ደግሞ እሷም ታሰረች። በፖለቲካ ሰበብ ሴቶችን ማሰር ባልተለመደበት ዘመን፣ የደስታ ገብሩ እስር ለአብዛኛው ሰው አዲስ ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። ደስታ ገብሩ ታዋቂና የምትከበር ሴት መሆኗ ደርግ ለተሰኘው አዲሱ ወታደራዊ መንግስት አስፈሪ ሳይሆንበት እንዳልቀረ የምታምነው ሃና፤ እናቷ የወታደር ቤተሰቦችን ለመደገፍ በምታደርገው ጥረት ተወዳጅ እንደነበረች ታስታውሳለች። ሰፊ ድጋፍ አግኝታ ሚኒስትሮቹን ታስፈታለች ብሎ የፈራው ደርግ፤ ለሁለት አመት ተኩል አሰራት። ፀረ አብዮት ሴራ ፈፅማለች፤ ከመድፈኛ ጦር ድጋፍ ለማግኘትም ሞክራለች ተብላ ተከሰሰች። አንዴማ ልትገደል ሁሉ ነበር፤ ለጥቂት ተረፈች እንጂ። ባለቤቷ ግን አልተረፈም። እዚያው እስር ቤት እያለች ነው በ1967 ዓ.ም ባለቤቷ የተረሸነው። ሃዘኗን የሚጋራት ቤተሰብ ከአጠገቧ አልነበረም፤ እስር ቤት እየመጡ ከሚጠይቋት ቤተሰቦቿ ጋር እንዳትገናኝ ለሦስት ቀናት ተከልክላለች። ከእስር የተፈታችው በ1969 ዓ.ም ደርግ ለተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች ምህረት ሲያደርግ ነው።

በየጊዜው ከባባድና አደገኛ ፈተናዎች የተደራረቡባት ደስታ ገብሩ፤ የዚያኑ ያህል ችግሮችን የመጋፈጥ ጥንካሬዋ አስገራሚ ነበር። ወታደሮች ባሰኛቸው ሰዓት የትኛውንም መኖሪያ ቤት እየበረበሩ በዘፈቀደ በሚያስሩበትና በሚገድሉበት አስፈሪ ጊዜ፣ የደስታ ገብሩ ቤትም ከመንኳኳት አላመለጠም። መትረየስና ጠመንጃ የታጠቁ በርካታ ወታደሮች በውድቅት ሌሊት ወደ ቤቷ የመጡት፣ የመጨረሻ ልጇን ራሄልን ፍለጋ ነው – ይዘው ወደ ቀበሌ እስር ቤት ሊወስዷት። ደስታ ገብሩ ግን አሻፈረኝ አለች። በእንቢታዋ ወታደሮቹ ሊገድሏት እንደሚችሉ ብታውቅም፤  ልጄን በቀን ብርሃን እንጂ በውድቅት ሌሊት ልትይዟት አትችሉም ብላ ተጋፈጠች። ምናልባትም ወታደሮቹ ተሰናብተው የሄዱት በወኔዋ በመገረማቸው ሊሆን ይችላል።

ብዙም ሳይቆይ ሌላ አሳዛኝ ነገር ተጨመረበት። ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ የወታደር ልጆችን ለማሳደግ በስንት ጥረትና ድካም የተቋቋመው የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል በወታደራዊው መንግስት ተወርሶ የጦር ካምፕ እንዲሆን ተወሰነ። ህፃናቱ ያለማስጠንቀቂያ በአፋጣኝ ከማዕከሉ ስለተባረሩ መጠጊያ መውደቂያ አልነበራቸውም። ግን ተበትነውና ባክነው አልቀሩም። በማዕከሉ ከነበሩት ልጆች መካከል፣ ገነት የምትባል ልጃገረድን ጨምሮ በእድሜ ተለቅ የሚሉ አራት ልጆች፣ በእድሜ ገና ታዳጊ ቢሆኑም የሌሎቹን ህፃናት ችግር እያዩ በዝምታ ለማለፍ አልፈለጉም። በደስታ ገብሩ አርአያነትና በገነት መሪነት፣ በተራቸው ሃላፊነት ለመውሰድ የወሰኑት አራት ታዳጊዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለነበሩ፣ ስራ ማፈላለግ ጀመሩ። ሁለቱ ስራ አግኝተው ቤት ተከራይተው፣ ለሌሎቹ ሕፃናት መጠለያ በመስጠት አለኝታ ሆኑላቸው። አለኝታነታቸው ለአንድ ቀን ወይም ለአንድ ሳምንት ብልጭ ብሎ የሚጠፋ፤ ከአንድ ወር ወይም ከአንድ አመት �

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከሃና ከበደ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ ሃምሌ – ነሐሴ 2004 ዓ.ም፤ እንዲሁም የታምራትና የራሄል ከበደ ያዘጋጁት ፅሑፍ ዳሰሳ፣ መስከረም – ጥቅምት 2005 ዓ.ም (ሃና፣ ታምራትና ራሄል የወ/ሮ ደስታ ገብሩ ልጆች ናቸው)
አጥኚ
ሜሪ-ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>