Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

የምወድሽ በቀለ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
 

የራሷን የአጭር ልብወለዶች መድበል በማሳተም የመጀመርያይቱ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት የመጀመርያዋ ሴት የፖሊስ ፕሬስ ክፍል ሃላፊ ሆና አገልግላለች የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ናት ከሰባት በላይ መፃህፍት የፃፈችና ያሳተመች ናት

 

ወቅታዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: ነሀሴ 1952 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አፍሪካ አንድነት አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት

ካምብሪጅ ቱቶርያል ኮሌጅ /ቱቶርያል/ የመጀመርያ ድግሪ /ቢኤ/ በአድቨርታይዚንግ እና ኮሙኒኬሽን ለንደን ዩኬ

ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
 

ከሰባት በላይ መፃህፍት ያሳተመች ታዋቂ ገጣሚና የአጭር ልብወለድ ደራሲ የሆነችው የምወድሽ በቀለ፤ ለ26 ዓመታት ባገለገለችበት የፖሊስ ፕሬስ ክፍል ሃላፊ በመሆን የሰራች የመጀመርያዋ ሴት ናት።  በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች ደራስያን ማህበርን በፕሬዚዳንትነት እየመራች ሲሆን የሴቶች መብት ቁርጠኛ ተሟጋች በመሆንም ትታወቃለች  ለሴቶች እድገትና መሻሻል በሚተጉ  ቦርዶችና ድርጅቶች ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለች ነው

 በ1952 ዓ.ም ክረምት ላይ በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አካባቢ የተወለደችው የምወድሽ  ለወላጆቿ ብቸኛ ልጅ ስለነበረች ትንሽ የመሞላቀቅ እድል አግኝታለች – በልጅነቷ። ከጥበቡ ዓለም ጋር የመጀመርያ የፍቅር ግንኙነት የመሰረተችው  በህንድ ፊልሞች አማካኝነት ነው። የህንድ ፊልም ነፍሷ ነበር።

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የክፍል ጓደኞቿ የሚሰነዝሯቸውን  ቀልዶች በግጥም  በመመለስ  ትታወቃለች። የፖሊስ መኮንን ልጅ የሆነችው  የምወድሽ ከልጅነቷ አንስታ የፖሊስ ጋዜጦችንና ህትመቶችን ታነብ ነበር።  በምታነባቸው ታሪኮች ከመደነቅም ባሻገር አንድ ቀን የፖሊስ ዘጋቢ መሆኔ አይቀርም እያለች ማለም ጀመረች።

ነፍስ እንዳወቀች ነበር በግጥም ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረችው። በ19 ዓመቷ በባህልና ስፖርት ሚ/ር ድጋፍ በተዘጋጀ የግጥም ውድድር ላይ ተካፍላ አሸነፈች – በ1971 ዓ.ም። በዚህም የተነሳ 12 ግጥሞቿ በስዕል በተደገፈ መድበል አብዮታዊ ግጥሞች በሚል ርዕስ ታተመላት።  ከግጥሞቿ አንዱ ከማጀት እስከ ከተማ የሚል ሲሆን  ጭብጡ በሴቶች ትግል ዙሪያ ያጠነጥናል። በ1982 ዓ.ም በ27 ዓመቷ የመጀመርያዋ የሆነውን ሙሉ የአጭር ልብወለድ መድበል “የባከነ ጊዜ በሚል ርዕስ  አሳተመች።  በ1990 ዓ.ምያላፈራ ፍሬ የተሰኘ መፅሃፏን ካሳተመች በኋላ ዘጠኝ ሴት ደራስያን በሴቶች ዙሪያ በፃፉት ዕጣ የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። ቀጣዩ ስራዋእብዷ በለጠች የተባለው ቤሳ ልብወለድ ነው።  ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር 42 ሴት ደራስያንን አወዳድሮ በአሸናፊነት ከመረጣቸው  ዘጠኝ ሴት ደራስያን አንዷ በመሆንም  ያልተናበቡ ልቦች በሚል መድበል ውስጥ ስራዋ ተካቶላታል። ከዚያም ፍቅር የጠማቸው ነፍሶች የተሰኘ ጭብጡን  በወንጀል ላይ ያደረገ  ረዥም ልብወለድ ያሳተመች ሲሆን በመቀጠል ዋጊኖስ በሚል ርዕስ የግጥም መድበል አሳትማለች። የበርካታ ደራስያንን ስራዎች ባካተተው የዋርካ ስር ጉባኤ የአጭር ልብወለድ መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። የበርካታ ሴት ደራስያን ግጥሞችን ባሰባሰበው እኛ2 የግጥም መድበል ውስጥም ተካትታለች።  የአጫጭር እውነተኛ ታሪኮች ስብስብ ለማሳተም በተዘጋጀው ውድድር ካሸናፊዎቹ አንዷ በመሆንም  የእኔ ዓለም በሚል መድበል ስራዋ ተካትቷል። በ2004 ዓ.ም በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ድጋፍ በተዘጋጀው ውድድር በማሸነፍአዙሪት በተሰኘው መድበል ውስጥ ስራዋ ታትሞላታል። በዚሁ ዓመት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነዋዡ ምሁር የተሰኘ ረዥም ልብወለድ አሳትማለች።

 ፀሃፊ ገጣሚና የፖሊስ ጋዜጣ ዘጋቢ የመሆን  ህልሟን  እውን እንድታደርግ  እድል የፈጠረላት አንደኛው መፅሃፏ ነው። መፅሃፉ እንደታተመ የተወሰኑ  ቅጂዎችን  ለመሸጥ ወደ ፖሊስ ቢሮ ጎራ ብላ ነበር።  በመፅሃፉ ታሪኮች  የተደመመው የፖሊስ ክፍል ሃላፊ በፖሊስ ጋዜጣ ላይ በተለማማጅነት እንድትሰራ ጠየቃት። ዓይኗን አላሸችም። ስራውን የወደደችው የምወድሽበተለማማጅነት ብቻ አልቀረችም የማታ ማታ በዘጋቢነት ተቀጠረች።  በኋላ ላይም የፕሬስ ክፍል ሃላፊ ለመሆን በቅታለች።

በዚህ የሃላፊነት ቦታ ላይ ሳለች የመጀመርያዋ ሲቪል ብቻ ሳይሆን የመጀመርያዋ ሴት የፕሬስ ሃላፊ በመሆኗም ጭምር ትላልቅ ፈተናዎች ገጥመዋታል።  በፖሊስ ሃይል ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች በየአጋጣሚው ይቃወሟትና ይገዳደሯት እንደነበር ታስታውሳለች። የምወድሽ ግን በችሎታዋና  በጥንካሬዋ  ትተማመን  ነበር።  ለስራው ባላት ልባዊ ፍቅርም  በስራዋ ለመግፋት ችላለች። የማታ ማታ ሌሎችም  ይሄንን ሃቅ ተረድተውታል። በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ በዘጋቢነት ስትሰራ ከቆየች በኋላ ዋና አዘጋጅ ለመሆን የቻለችው የምወድሽ ለስድስት ዓመትም በፕሬስ ክፍል ስራ አስኪያጅነት አገልግላለች።  በዚህ ሃላፊነቷም ብቃት ያላቸው ድጋፍ የሚሰጡ ሰራተኞችን  አፍርታለች።

 ዝነኛው  ደራሲ በዓሉ ግርማ  አርአያዋ እንደሆነ ትናገራለች።  ጥልቀት ያላቸው አጫጭር  ዓረፍተነገሮች እንዴት እምቅ ትርጉምና ሰፊ ሃሳብ እንደሚያስተላልፉ ስራዎቹ  አሳይተዋታል። በኋላ ላይ ካወቀቻት ዝነኛዋ ገጣሚ ፊርማዬ ዓለሙ ደግሞ  መድረክ ላይ ስትወጣ የነበራትን በራስ መተማመንና የእርጋታ መንፈስ  አስተውላለች።

በብዙ ሁኔታዎች ሴትነቴ ለፈተናዎች አልዳረገኝም ማለት እችላለሁ። አንዳንዴ ግን እንደሴትም  እንደእናትም  መሆኔ አይቀርም የሌሎች ህመምና ስቃይ በጥልቀት ይሰማኛል። በፖሊስ ፕሬስ የስራ ዘመኔ ትልቁ ፈተናዬ ይሄ ነበር። ለምሳሌ የትንሽ ሴት ልጇን መደፈር ልታመለክት የመጣች እናት ስመለከት ራሴን መቆጣጠር የሚያቅተኝ ጊዜ ነበርብላለች – የምወድሽ።

 በአንድ በኩል ልጆቿን እያሳደገች በሌላ በኩል ከሰባት በላይ መፃህፍትን ለማሳተም የቻለችው በሌላ ተዓምር ሳይሆን  ውስጣዊ ጥንካሬዋንና ቁርጠኝነቷን  በመገንዘቧ እንደሆነ ታምናለች። የህይወትን ውጣ ውረዶች ያለፈችውና  ድል ያደረገችውም  በፅናትና በፍቅር ነው – እግዚአብሄርን ከጎኗ አድርጋ።

ከፖሊስ ፕሬስ ብትወጣም ዛሬም መፃፏን አልተወችም። ለሴቶች እድገትና መሻሻል በሚሰሩ በርካታ ድርጅቶች ውስጥም እያገለገለች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ከመሆኗም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሴቶች ቅንጅት ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር ናት።

 ለወጣት ልጃገረዶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – መሪዎችና እንስት ጀግኖች ለመሆን ራሳችሁን አለማምዱ። ህልማችሁን እንዳታሳኩ ደንቃራ የሚሆንባችሁን አሉታዊ ተፅእኖ ሁሉ አሻፈረኝ በሉ። ትችት ሲሰነዘርባችሁ በአንክሮ አዳምጡ። ምክንያቱም ለማደግ ያግዛችኋል።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከወ/ሮ የምወድሽ በቀለ ጋር በሚያዝያ 2004 
አጥኚ
ሰምሃል ኪሮስ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>