Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ብርሃኔ ዳባ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ከአካል ጉዳተኝነት ጋር የተያያዙ ልማዳዊ ፍረጃዎችን  ተጋፍጣ በማሸነፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ለመሆን በቅታለች ፤አካል ጉዳተኞች የገቢ ማስገኛ ክህሎት ስልጠናና ከሌሎች እኩል ስራ የመቀጠር  እድል እንዲያገኙ ልዩ ትኩረቱ አድርጎ የሚሰራውን  የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ከሌሎች ጋር በመመስረት፣  በፕሬዚዳንትነት ትመራለች
ወቅታዊ ሁኔታ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ፣ ብሄራዊ ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ፣ ኢትዮጵያ፤የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት
የትውልድ ቦታ: ሆለታ፣ ኦሮምያ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ሠኔ 15 ቀን 1957 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ቼሻየር ሰርቪስ፤ መናገሻ፤  ቀጨኔ ወላጅ አልባ ህፃናት፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዲፕሎማ ፣በሴክሬተርያል ሳይንስ፣ የንግድ ት/ቤት፤ ቢኤ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ አድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ አዲስ አበባ
ዋና የስራ ዘርፍ
የአካል ጉዳተኝነት ተሟጋች
የሕይወት ታሪክ
ብርሃኔ ዳባ  የአካል ጉዳተኛ ሴቶችን  መብት ለማስከበርና ከሌሎች እኩል ስራ የመቀጠር  እድል እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሟገተው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር  መስራች ስትሆን ፤ይሄን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት  በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ትገኛለች። ከአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ  በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የመጀመርያ ድግሪዋን ያገኘችው ብርሃኔ ፤ በብሄራዊ  ቤተመፃህፍት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል በሲስተም አድሚኒስትሬተርነት እየሰራች ነው። አካል ጉዳተኞች ስለራሳቸው፣ ህብረተሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች አቅምና  ችሎታ ያለው ምስልና ግምት እንዲሻሻል በልባዊ ፍቅር የምትተጋው  ብርሃኔ፤ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች እንደ ስሟ ብሩህ ተስፋ  ናት።

በኦሮምያ ሆለታ፣ አሁንም ድረስ መብራትና  ውሃ ባልገባላት ጉቱታ በምትባል የገጠር መንደር የተወለደችው ብርሃኔ ፤ የሶስት ወይም የአራት ዓመት ህፃን ሳለች ነው  በሰውነት ልምሻ /ፖሊዮ/ አካል ጉዳተኛ የሆነችው። በቤት ውስጥ ስራ እንደምትረዳቸውና ትዳር ከያዘች በኋላም እንደምትደግፋቸው ለተማመኑት ቤተሰቦቿ ነገሩ  አስደንጋጭ ነበር።  እናቷን ገና ወጣት ሳለች በሞት ብትነጠቅም ገበሬ የነበሩት አባቷ አለ የተባለ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መፈወሻ ቦታ  አልቀራቸውም። በወቅቱ ዘመናዊ የህክምና ማዕከል በአካባቢው ለዓመል ያህል እንኳን አልነበረም።ሴት አያቷ እንደአብዛኛው ማህበረሰብ  አካል ጉዳቷ አንድም ቡዳ በልቷት አሊያም  ከእግዚአብሄር ቁጣ የመጣ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ስለዚህም ጠበል ለማስጠመቅ ቤ/ክርስትያን ይወስዷት ነበር። በዚህ ጉዳቷ የተነሳም ከእድሜ እኩዮቿ ጋር ት/ቤት ለመሄድ አልታደለችም።

አባቷ  በባህላዊ ህክምና አለመፈወሷን ሲመለከቱና  እሷን ከሁለት ወንድሞቿ ጋ  ለማስተዳደር  አቅም ሲያጥራቸው፣  ቼሻየር ሰርቪስ የተባለ የአካል ጉዳተኞች ማገገሚያ ማዕከል ላኳት። በማዕከሉ ህክምና ካገኘችና በመራመጃ ሽመሎች መራመድ ከተለማመደች በኋላ በሚሽኖች የገንዘብ ድጋፍ  አዳሪ ት/ቤት ገባች – የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል። ነገር ግን ከቤተሰብ ርቆ መኖሩን አልቻለችውም። ይባስ ብሎ ቤተሰብሽ ጠፍተዋል የሚል መረጃ ደረሳት። ይኼኔ ተስፋ መቁረጥ ጀመረች። በእርግጥ ሚሽኖቹ ደጋፊዎቿ ያበረታቷት ነበር – ራሷን  መቻል የምትፈልግ  ከሆነ  ትምህርቷ በርትታ እንድትገፋ በማነቃቃት። ሆኖም በዙሪያዋ ያሉ  በሙሉ ተስፋ እንደሌላትና በትምህርቷም መግፋት እንደማትችል በማሰብ  ከንፈራቸውን ይመጡላት ነበር። ይሄ ነው የቀረች ተስፋዋን ያሟጠጠባትና የእለት ተዕለት ህይወቷን  ፈተና ያደረገባት። ሴት አያቷ ምንም እንኳን በትምህርት ግስጋሴዋ ቢደመሙም ብዙ ርቀት ትጓዛለች የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበራቸውም።ትምህርቷን ብትጨርስስ — ምን ልትሰራበት ነው እያሉ ይጠይቁ ነበር። ብርሃኔ  ግን ራሷን ሰው የምታደርግበት አንድ እድል ይሄ ብቻ መሆኑን አውቃለች፤  እናም ስራዬ ብላ ትምህርቷን ከልቧ መከታተል ያዘች – ስኬታማ እንደምትሆን በመተማመን። በእርግጥ የመማር ዕድል እንድታገኝ ሳይታክቱ የጣሩት አባቷ ባለውለታዋ  መሆናቸውን አትዘነጋም።

ከቼሻየር ሰርቪስ ህክምናዋ  በኋላ በአዲስ አበባ  ወላጅ አልባ ህፃናት ማዕከል የገባችው ብርሃኔ፤ በማዕከሉ ውስጥ  ስነስርዓትን ተምራለች። ይሄን ብቻ ግን አይደለም የተማረችው። የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሄርን መፍራት መሆኑንና እግዚአብሄርን በልብ ውስጥ  ከያዙ ሁሉም ነገር እንደሚሳካ የተማረችውም በዚሁ ማዕከል ውስጥ ነው። በት/ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሚሽኖች፣ ተማሪዎች በመርህ የሚመሩና ለዓላማቸው የሚሞቱ ሰዎች እንዲሆኑ ቀርፀዋቸዋል።  ለደረሰችበት ስኬትና ሌሎችን ለመርዳት ላላት ቁርጠኝነት በማዕከሉ የነበራት እድገት መሰረት እንደሆናት ብርሃኔ ታምናለች።መፃህፍት እንድታነብ፣ በራስ የመተማመን ስሜት እንድታዳብር፣ ጊዜዋን በብልሃት እንድትጠቀምና ያላትን ለሌሎች እንድታካፍል እየተበረታታች ማደጓን  ታስታውሳለች። እንደክፍል ጓደኞቿ፣  እሷም በሄደችበት ሁሉ እግዚአብሄር እንደሚከተላት ተምራለች። እነዚህ ሁሉ ነገሮች  ለዛሬ ማንነቷ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ፣ በአዲስ አበባ ንግድ ት/ቤት ገብታ በፀሃፊነት ሙያ /ሴክሬቴርያል ሳይንስ/ በዲፕሎም ተመረቀች። ስራ ፈልጎ መቀጠር ግን የማትወጣው አቀበት  ሆነባት። ማመልከቻ ያላስገባችበት መ/ቤት የለም፣ የጠየቁትን መስፈርት ሁሉ ታሟላለች፣ የቅጥር መመዘኛ ፈተናዎች ስለሚቀሏት ያለጭንቀት ነው የምትሰራው። ግን ማንም ሊቀጥራት ፍላጎት የለውም። ገና ሲያዩዋት አሁን እቺ እንዴት አድርጋ ልትሰራ ነው የሚል ጥርጣሬ ያድርባቸዋል – ለእሷ ባይገባትም።  እንቆቅሎሹ የተፈታላት ከሌሎች አካል ጉዳተኞች ጋር በጉዳዩ ላይ ከተወያየች በኋላ ነበር። ስራ የመቀጠር እድል የተነፈገችው በአካል ጉዳተኝነቷ መሆኑን ስትሰማ ተስፋዋ ነጠፈ።የአካል ጉዳተኝነቷ የህፃንነት ህይወቷን ያቃወሰባት ሳያንስ በቀሪ ህይወቷም ፈተናው እንደሚቀጥል ተገነዘበች። ደግነቱ ተስፋ አልቆረጠችም፤ ይልቁንም ራሷን አጠንክራ በመንገዷ የሚገጥማትን ሁሉ  ለመጋፈጥ ቆርጣ ተነሳች።

ከረጅም ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ በብሄራዊ ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ የተቀጠረችው ብርሃኔ፤  የቤተመፃህፍቱን ካታሎግ  በታይፕ የመተየብ ስራ ላይ ተመደበች። በዚህ ተመስጌን ብላ ከመቀመጥ ይልቅ ክህሎቷን ለማሻሻል በማሰብ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማጥናት ወሰነች። ጊዜ ሳታባክን ወዲያው በአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገብታ፣ በማታው መርሃ ግብር ትምህርቷን  ጀመረች። ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተሟጋች በመሆን  በበጎ ፈቃደኝነት ትሰራ ነበር። ከቦታ ቦታ በታክሲ መጓጓዝ  አስቸጋሪ ቢሆንባትም ለችግሮች ሳትፈታ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ  የመጀመርያ ድግሪዋን ለመያዝ በቃች። ዛሬ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆነችው ብርሃኔ፤ እዚያው ብሄራዊ ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ ውስጥ በሲስተም አድሚኒስትሬተርነት ትሰራለች።

ብርሃኔ፤ እየሰራች ስትማር በነበረ ጊዜ ነው ከሰባት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበርን የመሰረተችው። ማህበሩ፤ አካል ጉዳተኛ ሴቶች በአካል ጉዳተኝነታቸው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተጋፍጠው ለማሸነፍና ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲገነዘቡ ለመርዳት የተቋቋመ ድርጅት ነው። በእርግጥ የመጀመርያ ሃሳቡ የመነጨው በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ትሰራ ከነበረችው ወ/ሮ መቅደስ ነበር። በኡጋንዳ ጉዞዋ  አካል ጉዳተኛ ሴቶች እንዴት ራሳቸውን እንዳደራጁ አይታ የተመለሰችው ወ/ሮ መቅደስ፤ ራሷ አካል ጉዳተኛ ባለመሆኗ እንዴት አድርጋ ተመሳሳይ ድርጅት ለመመስረት እንደምትችል እርግጠኛ አልነበረችም። እናም ይሄን ሃሳቧን ማየት ለተሳናት የዩኒቨርስቲ የክፍል ጓደኛዋ አማከረቻት። እሷ ደግሞ ለብርሃኔ ነገረቻት። ከዚያም ብርሃኔና ሰባት ጓደኞቿ፣ በመቅደስ እገዛ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበርን አቋቋሙ – በ1994 ዓ.ም። ከእነሱ ቀድሞ የተመሰረተ የሴቶች ክንፍ ያለው የአካል ጉዳተኞች ማህበር ስለነበር የእነብርሃኔ ማህበር ተቃውሞ ገጠመው ።  ብዙዎች  ለሴቶች ብቻ ተብሎ አዲስ ማህበር    መቋቋሙን አልወደዱትም ነበር። ብርሃኔና ባልደረቦቿ ግን የሚፈለገውን ያህል እንዳልተሰራ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ልባዊ ፍቅርና ቁርጠኝነትም ነበራቸው። ለበርካታ ወራት በበጎፈቃደኝነት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ለማህበሩ የመጀመርያውን  ድጋፍ ከማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አገኙና ዎርክሾፕ መስጠት ጀመሩ። በዎርክሾፑ ላይ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ግለሰባዊና ማህበራዊ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች፣ ማብራሪያዎችና ገለፃዎች ያቀርባሉ  – የራሳቸውን ተመክሮ በማካፈልና ሌሎች አካል ጉዳተኛ ሴቶች እንዲናገሩ በማነሳሳት። በክልሎች በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰነዘረው አጉል ማህበራዊ  ፍረጃ ከአዲስ አበባም የከፋ ነው። በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ጥቂት አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብቻ ናቸው የሚገኙት። ለምን ቢባል አብዛኞቹ ከቤት ለመውጣት  በሃፍረት ስለሚሸማቀቁ ነው።

አንዳንድ አካል ጉዳተኞች የተረጂነት ስሜት እንዲያዳብሩ በመደረጋቸው ከማህበሩ ችሮታ የሚፈልጉ ቢሆንም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ግን ተረጂነትን አያበረታታም- ራሳቸውን እንዲችሉ ያግዛል እንጂ። አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ለማብቃትም የገቢ ማስገኛ ክህሎቶች ስልጠና ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ አካል ጉዳተኝነት በተለይ ሴቶችን ለጥቃት  ስለሚያጋልጥ ማህበሩ እንዴት ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል።  ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንም አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ይሰራል። ዛሬ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ቢሮው ከ800 በላይ አባላት ሲኖሩት፤ በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ /ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ መቀሌና ናዝሬት/ ከ1ሺ200 በላይ አባላት አሉት።ማህበሩ በአዲሱ አዋጅ መሰረት እንደአገር በቀል የኢትዮጵያ ድርጅት ዳግም ከተመዘገበ ወዲህ፣ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንጮች መቀበል የሚችለው 10 በመቶ ብቻ ሲሆን የቀረውን ከአገር ውስጥ ማሰባሰብ ይጠበቅበታል። ለዚህም ነው  ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች የስራ እድል፣ ለማህበሩ ደግሞ መጠነኛ ገቢ የሚሰጥ ዳቦ ቤት የከፈተው። ብርሃኔ ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት እያገለገለች ነው።

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰነዘረው አጉል ልማዳዊ ፍረጃ አሁንም ቀጥሏል – በተለይ በሴቶች ላይ – በተለይም በክልሎች። ማህበሩን የመሰረቱት ብርሃኔና ሰባት ጓደኞቿ አስቸጋሪ ፈተናዎችን አሸንፈው የተሳካላቸው ጠንካራ ሴቶች ስለነበሩ ነው። አንዱ የጥንካሬያቸው ምንጭ ደግሞ ትምህርት እንዳይማሩ ተስፋ ያስቆርጧቸው  ከነበሩ ቤተሰብና ማህበረሰብ እንዲሁም ከተወለዱበት  ከባቢ ማምለጥ መቻላቸው ነው። ህፃናት ከቤታቸው ሳይርቁ በመደበኛ ት/ቤት ትምህርታቸውን መከታተል የሚያስችላቸው ሁኔታና ንቃተ ህሊናው የዳበረ ማህበረሰብ ያለበት ከባቢ መፍጠር ተመራጭ ነው። ልማዳዊ ፍረጃው በከፋበትና በቂና ተገቢ አገልግሎት መስጪያዎች እንዲሁም የሰለጠኑ ባለሙያዎች በሌሉበት ሁኔታ የአካል ጉዳተኞች  አዳሪ ት/ቤቶችንና የወላጅ አልባ ህፃናት ማዕከላትን መዝጋት እንደማይገባ ብርሃኔ ታስጠነቅቃለች። ድህነት የአካል ጉዳተኞችን ፈተና አክብዶባቸዋል። አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ  የህክምና፣ የማገገምያና የትምህርት ድጋፎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ፈተና ሆነው የሚጋረጡባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አሌ የሚባል አይደለም። ለምሳሌ እርግዝና፣ የታክሲዎች አመቺነት፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የመሳሰሉት። ነገር ግን ህብረተሰቡ እነዚህን ነገሮች ጨርሶ የማይወጡ ተራሮች አድርጎ በመሳል የበለጠ ያከብደዋል። ብርሃኔ ግን ነገሮች ሰዎች እንደሚሉት ጨርሶ የማይቻሉ አይደሉም – ትላለች። እሷ ለምሳሌ ቤቷን በቅጡ ታስተዳድራለች፤ ዋና ዋና የሚባሉትን የቤት ውስጥ ስራዎችን ታከናውናለች –  ልብስ ማጠብና እንጀራ መጋገር የመሳሰሉትን ። የተለያየ የአካል ጉዳት ላሉባቸው ከ800 በላይ የማህበሩ አባላትም ነገሩ ተመሳሳይ ነው።

ብርሃኔ፤ በማህበሩ ስራዎች አማካኝነት በጭለማ ውስጥ ተጋርደው ለነበሩ ወገኖች የብርሃን ተስፋ መፈንጠቅ  መጀመሩ ያኮራታል። ግን ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉና  ይሄን እንደስራው መነሻ እንደምትቆጥረው ትናገራለች። አካል ጉዳተኞች ሌሎች የሚያገኙት እድል እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ፣ እንዲሁም እነሱም እንደሌሎች ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ማህበረሰቡን ለማስተማር እየሰራች ነው። እሷ ራሷ በልጅነቷ የትም አትደርስም ተብላ ተስፋ ተቆርጦባት እንደነበር ታስታውሳለች። የማታ ማታ ግን ከታላቅ ወንድሞቿ የላቀ ስኬት ለመቀዳጀት በቅታለች። ቁርጠኝነቱ ካላችሁና ወኔያችሁ እንዳይሞት ካደረጋችሁ በህይወት ውስጥ ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ማሳካት ትችላላችሁ ትላለች – ብርሃኔ። አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ለማገዝ ለሚፈልጉ ወላጆች ተስፋ መሆን በመቻሏና ሌሎች ችግራቸውን እንዲፈቱ በማገዟ ወደርየለሽ ደስታ ይሰማታል።በማንነቷ ትኮራለች። አካል ጉዳተኝነቷ ፈፅሞ አያሸማቅቃትም፤ በራሷ ደስተኛ ናት። ልበሙሉዋ ብርሃኔ፤ ግልፅና ቀጥተኛ ስትሆን ሁሌም ትኩረቷ ልታሳካው የምትሻው ዓላማዋ ላይ ነው። እነዚህን ባህርያት ያላበሳት ደግሞ ትምህርቷን የተከታተለችበት ሂደት እንደሆነ ትናገራለች። አሁንም ክህሎቷን ለማዳበር የማትቦዝነው ብርሃኔ፤በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማስተርስ ድግሪዋን ለማግኘት ትምህርቷን የመቀጠል ሃሳብ አላት። አሁን ግን በታክሲ እየተመላለሰች ሳይሆን በርቀት ትምህርትመርሃግብር ነው።  መርሃግብሩ ለሌሎች በርካታ አካልጉዳተኞችም የተለየ ጠቀሜታ አለው።

ብርሃኔ ለወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – የንባብ ልማድ አዳብሩ፤  ራሳችሁን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አስተዋውቁ። ሴት እንደመሆናችሁ መጠን  የማንም ጥገኛ ልትሆኑ አይገባም፤  ራሳችሁን መቻል አለባችሁ። በንባብ ራሳችሁን ልታስተምሩ ይገባል፤ መፅሃፍ ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው።  /ብርሃኔ ቤተመፃህፍት የሚጠቀሙ ሴቶች  ከወንዶች በእጅጉ ያነሱ እንደሆኑ በስራዋ አጋጣሚዋ  አስተውላለች/ ቅድምያ የምትሰጧቸውን ጉዳዮች በግልፅ አስቀምጡ።በማይረቡ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ራሳችሁን በማበልፀግ ላይ አተኩሩ። በራስ መተማመንን አዳብሩ፤  የራሳችሁን ግቦችም ቅረፁ። ትርጉም ያለው ህይወት ይኑራችሁ። ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገውን መስዋእትነት  ለመክፈል ፈቃደኛ ሁኑ። አንዴ ግባችሁን ከቀረፃችሁ በኋላ በቁርጠኝነት ለማሳካት ትጉ፤  ሌሎች መጥተው ህልማችሁን እንዲያሳኩላችሁ አትጠብቁ። በጓደኛ ምርጫ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ፤ በአካባቢያችሁ ከምታዩት እውነታ ትምህርት ውሰዱ። ዛሬ ዛሬ ብዙ ልጃገረዶች ፊልም ያዩና የዚያን ዓይነት ህይወት መኖር ይሻሉ። ያ ግን ፊልም እንጂ ተጨባጩ እውነታ አይደለም። በህልም ዓለም መኖር እንደማይቻል እወቁ።

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከብርሃኔ ዳባ ጋር በ2004 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ፤ ኢትዮጵያ ሬዲዮ «የሴቶች መድረክ» ፕሮግራም – የግል ቃለምልልስ፤ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ29/01/2003 ዓ.ም የተላለፈ
አጥኚ
ናሁ ሰናይ ግርማ፤ ሸዊት ወልደሚካኤል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>