Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ብሩክታዊት ጥጋቡ ታደሰ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
ከሰባት አመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ጠቃሚ መልዕክቶችን የሚያስተላልፍ “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የተሰኘየቴሌቪዥን ፕሮግራም በመፍጠር ተሸላሚ ሆናለች። አራተኛ አመቱን የያዘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሚሊዮንሕፃናት ታይቷል። እድሜያቸው 10 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ልጆች የሚሳተፉበትና ስለራሳቸው ሕይወት የአንድደቂቃ ቪዲዮ የሚያዘጋጁበት ፕሮግራምም ጀምራለች – “ኢንቮልቭ ” በሚል ሥያሜ። 13 አመትና ከዚያበላይ ለሆኑ ልጆች የሚዘጋጅ “ትንንሽ መርማሪዎች” የተሰኘ ፕሮግራምም ፈጥራለች – የፈጠራ ጉጉትን እያነሳሳሳይንስን በማራኪ መንገድ ለማስተዋወቅ። ብሩክታዊትና ያቋቋመችው ድርጅት (ህዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕበርካታዓለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ወቅታዊ ሁኔታ የዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤ “ፀሐይ መማርትወዳለች “ኢንቮልቭ ” እና “ትናንሽ ተማራማሪዎች የተሰኙ ፕሮግራሞችፕሮዲዩሰር
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: ሀምሌ13 ቀን 1973 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ገርጂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የሚል አዝናኝና አስተማሪ የሕፃናት የቴሌቪዥን ፕሮግራም በማሰናዳት የምትታወቀው ብሩክታዊት ጥጋቡ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ከመሆኗም በላይ ከባለቤቷና ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ተጨማሪ የሕፃናት ፕሮግራሞችን በመፍጠር ለእይታ አብቅታለች።  የኢትዮጵያ ሕፃናት ለወደፊት ሕይወታቸው ጥሩ መነሻ አግኝተው በፍቅር ትምህርት ቤት እንዲገቡ የሚያዘጋጃቸው ፕሮግራም ለማሰናዳት በማሰብ፣ ሥራውን በ1997 ዓ.ም የጀመረችው፤ ከባለቤቷ ከሼን ኢዘንሀውሰር ጋር የምትኖርበት ቤት ህዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ የተሰኘ ትንሽ ስቱዲዮ በመፍጠር ነው። ከባለቤቷ፤ ከሰባት ታታሪ የሥራ ባልደረቦቿና ከበጎ ፈቃደኞች ትብብር ጋር የብሩክታዊት ጥረት ተሳክቶ፤ በ1998 ዓ.ም “ፀሐይ መማር ትወዳለች” የተሰኘው የአሻንጉሊት ትርዒት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መቅረብ ጀመረ። በ2002 ዓ.ም ደግሞ፤ ከችግረኛ ማህበረሰብ የመጡና ከ10 እስከ 15 ዓመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ስልጠና ወስደው በራሳቸው ሕይወት ዙሪያ የአንድ ደቂቃ ቪዲዮ የሚያዘጋጁበት “ኢንቮልቭ ሚ” የተሰኘ ፕሮግራም ተጨመረበት። ከዚያም ከተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ13 እስከ 18 አመት እድሜ ያላቸው ተማሪዎች የሚሳተፉበት፣  “ትናንሽ መርማሪዎች” የሚል አዲስ ፕሮግራም ታከለበት። ተማሪዎቹ በየእለቱ ሕይወታቸውን የሚነኩ የአካባቢ ጥበቃና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ ጉዳዮችን በሳይንሳዊ መንገድ ይመረምራሉ።

በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ ድህነት ጎልቶ በሚታይበት ሰፈር በ1973 ዓ.ም ከችግረኛ ቤተሰብ የተወለደችው ብሩክታዊት፣ አስር አመት እስክትደፍን ድረስ የቤታቸው  ብቸኛ ልጅ ነበረች። ያኔ ነው ታናሽ ወንድሟ የተወለደው። ከሦስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ቤታቸውን ገርጂ አካባቢ ሠርተው ሲገቡ፣ ከአያቷ ጋር የነበረችው ታላቅ እህቷ አብራቸው ልትኖር መጣች።

በተፋፈገ የሳሪስ ሰፈር ተወልዳ ያደገችው ብሩክታዊት፤ በጠባብ ግቢ ውስጥ አስር ቤተሰቦች ተጣብበው ኑሯቸውን ሲገፉና ከግቢው ልጆች ጋር ቆሻሻ ላይ ስትጫወት ታስታውሳለች። አንዳንዴም ከሌሎቹ ልጆች ጋር የአከራይ ቤት ውስጥ ቴሌቪዥን ታይ ነበር። የብሩክታዊት አባት ትልቅ ትልቁን የሚያስብ የትጋት ሰው ስለሆነ፤ ምንም መሀይም ቢሆንም ተፈጥሯዊ የንግድ ችሎታ ነበረው። የቡልዶዘር ሠራተኛ ሆኖ እረፍት ሳያምረው እየሰራ የተወሰነ ያህል ገንዘብ ካጠራቀመ በኋላ፤ ቤት መግዛትና መሸጥ ጀመረ። የኋላ ኋላም የተዋጣለት ሥራ ፈጣሪ የቢዝነስ ሰው ሆኗል። ደግሞም ሌሎች ሰዎች ከድህነት ሲወጡ ማየትና መደገፍ የሚወድ ለጋስ ነበር። የብሩክታዊት እናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቀች ብትሆንም፤ ከጓዳ እንድትወጣና እንድትሠራ የሚያበረታታ ነገር አላገኘችም፤ የመሥራት እድል ባለማግኘቷም ሁሌም ይቆጫት ነበር። ይህን የእናቷን ቁጭት እያየች ያደገችው ብሩክታዊት፤ ተመሳሳይ እጣ እንዲደርሳት አልፈለገችም። እናቷም የልጄ ሕይወት ከኔ የተሻለ መሆን አለበት ብላ ስለቆረጠች፤ ህልሟን ለማሳካት እንድትተጋ፤ አላማና ምኞቷን በግልፅ እንድትናገር ታበረታታት ነበር። ብሩክታዊት ትምህርቷ ላይ እንድትበረታ በማሰብም፤ የቤት ሥራ መሥራቷን፤ በደንብ እያነበበችና እያጠናች መሆኗን እናቷ ሳትከታተላት የቀረችበት ጊዜ የለም።
በገርጂ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን እንዲሁም በቦሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ብሩክታዊት፤ ፓይለት ወይም ዶክተር የመሆን ህልም ነበራት፤ አስተማሪነትን በጭራሽ አስባው አታውቅም። እናቷ እንደሚሉት ከሆነ ግን፤ አስተማሪነት ለብሩክታዊት እንግዳ አይደለም፤ ከልጅነቷ አንስቶ አብሯት አድጓል። የሰፈር ልጆችን ሰብስባ ፊደልና ንባብ ታስተምር አልነበር? የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ደግሞ አስተማሪነትን የገቢ ምንጭ  ሆኖላታል – እያስከፈለች ተማሪዎችን አስጠንታለች። ያም ሆነ ይህ፤ ብሩክታዊት እንዳሰበችው ፓይለት ወይም ዶክተር የምትሆንበት እድል አልነበራትም። አብዛኛው ወጣት እንደ ምርጫው በሚፈልገው የሙያ መስክ ትምህርት ወይም ስልጠና የማግኘት እድል የለውም። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ላይ በሚያመጡት ውጤት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ኮታ እየታየ ነው ተማሪዎች ለስልጠና የሚመደቡት። የሙያ መስክ መምረጥ በቀላሉ የማይገኝ ቅንጦት ሆነና፣ ብሩክታዊት ያለፍላጎቷ ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተመደበች። መንፈሷ በቅሬታ ደበዘዘ። የከበባት ደመና ከላይዋ ላይ የተገፈፈው፤ ትምህርቷን ለማጠናቀቅ የተቃረበች ጊዜ ለልምምድ ተመድባ አስተማሪነትን ስትቀምሰው ነው። ከገመተችው በላይ ወደደችው። እንዲያውም አስተማሪነት እንከን የለሽ ተስማሚ ሙያ ሆኖ ተሰማት። ተመርቃ ሙሉ ጊዜዋን በአስተማሪነት ላይ ለማዋል ጓጓች። ከዚያ ወዲህ በተለይ ሕፃናትን ማስተማር ከሁሉም የላቀ ቅዱስ ሙያ እንደሆነ ማመን የጀመረችው ብሩክታዊት፣ በ1993 ዓ.ም ከተመረቀች በኋላ በተለያዩ የግል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተምራለች። እጅጉን የረካችው ደግሞ በመዋዕለ ሕፃናት ውስጥ ስታስተምር ነው። በዚህ መሀል የሕይወቷን አቅጣጫ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ። ከፍተኛ ፈጠራ የሚታይበት “ቱ ዊንግስ አካዳሚ” ውስጥ የመዋዕለ ሕፃናት አስተማሪና ሃላፊ ሆና በምትሰራበት ወቅት ሼን ኢዘንሀውሰር የተባለ ወጣት አሜሪካዊ በበጎ ፈቃደኝነት የእንግሊዝኛ አስተማሪ ሆኖ መጣ። ገና ከመምጣቱም፤ ለሕፃናት የቴሌቪዥን ትዕይንት እንፍጠር በማለት ሌሎቹን አስተማሪዎች ተፈታተናቸው። ምንም አይነት የሕፃናት የቴሌቪዥን ትዕይንት በሌለበት አገር አዲስ የመፍጠር ሃሳብ ብሩክታዊትን ነሸጣት። ብሩክታዊትንና ሼንን ጨምሮ የተወሰኑ አስተማሪዎች የዘወትር ሥራቸውን ሳያጓድሉ፤ በበጎ ፈቃደኝነት ጥረታቸውን ጀመሩ። ነገር ግን አንዳቸውም ቢሆኑ፤ ስለቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘገጃጀት ምንም እውቀት አልነበራቸውም። ለዚህም ነው፤ ምን ያህል ጥረት እንደሚጠይቅ ለመገንዘብ ጊዜ የወሰደባቸው። ለካ በበጎ ፈቃድ የትርፍ ሰዓት ጥረት ብቻ የሚነቃነቅ ሥራ አይደለም። ግን ተስፋ ሰጪ ቡቃያ መታየቱ አልቀረም። ቀስ በቀስ እየተዋወቁና እየተቀራረቡ የመጡት ሼን እና ብሩክታዊት በፍቅር ተማርከው በጋብቻ ተሳሰሩ። ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ተለያዩ አገራት ሲዘዋወሩ፤ የትምህርት ነገር የማይሆንላት ብሩክታዊት በሄዱበት ቦታ ሁሉ ትምህርት ቤቶችን ሳትጎበኝ አታልፍም ነበር። በየትምህርት ቤቱ ያየችው ከፍተኛ አቅምና የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎች አስደንቋታል። ሙሽሮቹ በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ አስተማሪ ሆነው የመሥራትና የመኖር እድል የነበራቸው ቢሆንም፤ ልባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነና ተመልሰው መጡ። ለኢትዮጵያውያን ሕፃናት ጥሩ የትምህርት መነሻ የሚሆን የቴሌቪዥን ትዕይንት ለመፍጠር የወጠኑት ሃሳብ በእንጥልጥል ሲቀር ማየት አልፈለጉም።

የ24 አመቷ ብሩክታዊትና ባለቤቷ በ1997 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እንደመጡ ከመደበኛው የአስተማሪነት ሥራቸው ለቀቁ። ነገር ግን ከትምህርት አልተላቀቁም። የቴሌቪዥን ትርዒት እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል  ራሳቸውን ማስተማር ጀመሩ። ስልጠና የሚያገኙበት ተቋም ስላላገኙ፤ መፃህፍትን በማንበብ፣ መረጃ በማሰባሰብ እንዲሁም ብዙ ትዕይንቶችን በመመልከት እውቀታቸውን አዳበሩ። ሼን የድምፅና የቪዲዮ ማቀናበሪያ ሶፍትዌር ያዘጋጀ የኮምፒዩተር መሃንዲስ ቢሆንም፤ የቴሌቪዥን ትዕይንት ለመፍጠር ግን ከብሩክታዊት የተሻለ እውቀት አልነበረውም። በንባብና በጥናት ራሳቸውን እያስተማሩ፣ በምርምርና በሙከራ ልምድ እያካበቱ ለአንድ አመት ያህል ያለማቋረጥ ሠሩ። መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አረንጓዴ የአልጋ ልብስ ግድግዳ ላይ እየዘረጉና ቪዲዮ እየቀረፁ፣ በአሻንጉሊትና በአኒሜሽን እየሞካከሩ፣ ድምፅና ቪዲዮ እያቀናበሩ፣ ከበርካታ ወራት ጥረት በኋላ የ15 ደቂቃ ትዕይንት አጠናቅቀው አሰናዱ። በቱ ዊንግስ አካዳሚ የ15 ደቂቃውን ትዕይንት ለመመልከት እድል ያገኙ ሕፃናት ፈነደቁ። የአገራቸውን መንፈስ የተላበሰና በሚያውቁት ቋንቋ የቀረበ በመሆኑ አስተማሪነቱ ማረካቸው። አዝናኝነቱ አስደሰታቸው። የሕፃናቱ ደስታ ደግሞ፤ ብሩክቲንና ሼንን መልሶ አስፈነደቃቸው።
ይሄኔ ነው ብሩክታዊት ቆም ብላ ለማሰብ እረፍት የወሰደችው። ምን መሥራት እንዳለባት ለመወሰን መጀመሪያ ለሕፃናት ትምህርት ምን ምን እንደሚያስፈልግና ምን ምን እንደጎደለ በግልፅ ማወቅ ይኖርባታል። የችግረኞች ሰፈር ውስጥ ያደገችው ብሩክታዊት፤ ብዙ ልጆች መዋዕለ ሕፃናት ገብተው ከንባብና ከትምህርት ጋር የመተዋወቅ እድል እንደማያገኙ ታውቃለች። በእርግጥ እናቷ የተማሩ ስለነበሩ፣ ቤት ውስጥ ከንባብና ከትምህርት ጋር እንድትተዋወቅ እያገዙ ያበረታቷት ነበር። ብዙ ሕፃናት ግን ይህንን እድል አያገኙም።

መንግስት ሁሉንም ሕፃናት ወደ ትምህርት ለማስገባት ብዙ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን እየገነባ ቢሆንም፤ ሕፃናቱ ለትምህርት ቤት ዝግጁ እንዲሆኑ ከቁጥር የሚገባ ጥረት ሲደረግ አይታይም። የትምህርት ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ ሕፃናት 7 አመት ሳይሞላቸውና ትምህርት ቤት ሳይገቡ ዋና ዋና የትምህርት መሰረቶችን (ለምሳሌ የጤንነት፣ የሥነ ዜጋ፣ የሥነ ምግባርና የመርማሪነት መሰረቶችን) መጣል አለባቸው። አለበለዚያ ጊዜው ሊረፍድ ይችላል። ለዚህም ነው ብሩክታዊት ከ3 እስከ 6 አመት እድሜ ላይ ባሉት ሕፃናት ላይ ለማተኮር የወሰነችው፤ ለወደፊት ሕይወታቸው ጥሩ መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን የሚዳስስ የቴሌቪዠን ፕሮግራም ለመፍጠርና ለማሰናዳት የወሰነችው ብሩክታዊት፤ በቀጭኔ አሻንጉሊት ፀሐይ የተሰኘች የስድስት አመት ሕፃን ገፀባህሪ ዙሪያ ያጠነጠነ ትዕይንት ፈጠረች። ለሕፃናት ሊተላለፉ የሚገቡ መልእክቶችን፤ ነገሮችን የመመርመር፤ በአካባቢያችን ካሉ ነገሮች ግንዛቤ የመጨበጥ፤ ንባብን የማፍቀር፣ እየተጫወቱ የመማር አስፈላጊነትን ያሳያል።  በሁለተኛ ደረጃ በወላጆች ላይ ያተኮረ መልእክት ለማስተላለፍ የዘፈቀደ ልማዳዊ አስተሳሰብን የሚያስተካክሉ አርአያዎች በትርዒቱ ይቀርባሉ። በኮንስትራክሽን ሙያ ላይ የተሰማራች እናት እንዲሁም ቤት ውስጥ ለልጆች ምግብ እያዘጋጀና ከመተኛታቸው በፊት ታሪክ እያነበበላቸው የሚንከባከብ አባት በትርዒቱ ውስት ተካተዋል። ጎረቤቶችን የሚረዳና ብልህ ሽማግሌን ጨምሮ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን በክብር የሚያዩት ለሕፃናት የሚያስቡ ሰዎች የተሰባሰቡበት ሰፈር የትርዒቱ አካል ነው። ትርዒቱ ለሕፃናት ትምህርት የሚያስተላልፈው በሙዚቃና በዳንስ፤ በምስሎችና በቃላት ነው። በብሩክታዊት ድምፅ የሚቀርበው የፀሐይ ንግግርን ጨምሮ በትዕይንቱ ውስጥ የሚነገሩ ቃላት በአማርኛ የሚቀርቡ ናቸው – በእንግሊዝኛ የፅሁፍ ትርጉም ታጅበው። በእርግጥ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለማሰራጨት አማርኛው በበርካታ ቋንቋዎች ይተረጎማል። እስካሁንም፤ በመላ አገሪቱ ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ትርዒቱን ተመልክተዋል። ኤችአይቪና ወባን ጨምሮ ጤናን፤ እንዲሁም የትምህርትና የግብረ ገብነት ጥቅምን የሚዳስስ ትርዒት ሕፃናትን በሚማርክ መንገድ ለማሰናዳት ብሩክታዊትና የስራ ባልደረቦቿ የተለያዩ የፈጠራ መንገዶችን አዳብረዋል። በአንድ ትምህርታዊ ርዕሰ ጉዳይ (ለምሳሌ በእውነተኛነት) ዙሪያ መነሻ ፅሁፍ የሚያዘጋጁ በጎ ፈቃደኞችን ታሰባስባለች። በየሁለት ሳምንቱ እየተገናኙ ከሚያዘጋጁት አፅመ ታሪክ በመነሳት፤ ብሩክታዊት፤ ባለቤቷ ወይም ከስራ ባልደረቦቿ አንዱ የሙሉ ዝግጅት ታሪክ ይፅፋል።

የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ቀስ በቀስ መልክ እየያዘ ሲመጣ፣ ትርዒቶቹን የሚያዘጋጅና የሚያሰናዳ ህዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ የተሰኘ ለትርፍ የሚሠራ ማህበራዊ የቢዝነስ ድርጅት ያቋቋመችው ብሩክታዊት፤ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋርም የትብብር ግንኙነት ፈጠረች። ፕሮግራሙ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ገንዘብ የሚያሟላ የገቢ ምንጭ መፍጠር ግን ትልቅ ፈተና ሆነባት። ትርዒቶቹን እየተቀበለ የሚያሰራጨው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ገንዘብ አይከፍልም። ህዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ ፈተና ላይ ወደቀ። በጎ ፈቃደኞችንም እያሳተፈ በአነስተኛ ወጪ የሚሠራ ቢሆንም፤ የቁሳቁስ፣ የቅንብር፣ የዝግጅት ወጪዎችን መሸፈን ትግል ሆነባት። ስፖንሰር ለመሆን ብቅ ያለ የቢዝነስ ተቋም የለም። የቢዝነስ ተቋማት ትኩረት ያልሰጡበት አንዱ ምክንያት፤ የሕፃናት ትምህርታዊ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደ ትልቅ ነገር ስለማይታይ ሊሆን ይችላል ብላ ታምናለች – ብሩክታዊት።

እንዲያም ሆኖ ከጀመረችው ሥራ ወደኋላ አላለችም። እንዲያውም ታዳጊ ልጆች ራሳቸውን የሚገልፁበት መድረክ እንዲያገኙ በማሰብ “ኢንቮልቭ ሚ” የተሰኘ አዲስ የልጆች ፕሮግራም ፈጠረች። ከ10 እስከ 15 ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች ለአራት ቀናት የፊልም አሰራር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ፣ በራሳቸው ሕይወት ዙሪያ የአንድ ደቂቃ ቪዲዮ ያዘጋጃሉ። ይህንን የቪዲዮ ትርዒት ለማዘጋጀት ሲጣጣሩ የሚታዩት ልጆች፣ የራሳቸው የኑሮ ሁኔታዎችንና ፈተናዎችን ለተመልካቾች ያካፍላሉ። ከዚያም የልጆቹ የአንድ ደቂቃ ቪዲዮዎች ለተመልካች ይቀርባሉ። በሁለት ዙር ለሁለት አመታት በዘለቀው ፕሮግራም በባህርዳር፣ በወልዲያ፣ በገብረ ገጫር፣ በሻሸመኔና በአዲስ አበባ ከሚገኙ ችግረኛ ሰፈሮች 120 ገደማ ታዳጊዎች ስልጠናውን በመውሰድ ተሳታፊ ሆነዋል። አይናፋር የነበሩ ተማሪዎች በአራት ቀን ስልጠና ወደ ልበሙሉነት ተሸጋግረው በራሳቸው ህይወት ዙሪያ የቪዲዮ ትዕይንት ሲያዘጋጁ ማየት በእጅጉ አስገራሚ እንደሆነ ብሩክታዊት ትናገራለች። የልጆቹ ታሪክ ልብን በጥልቀት ይነካል። በ”ሪያሊቲ ሾው” አይነት አቀራረብ በሚዘጋጀው የ”ኢንቮልቭ ሚ” ፕሮግራም የልጆቹ የቪዲዮ ትዕይንት በዳኞች ፊት ለውድድር ይቀርባል። አሸናፊው ልጅ፣ የአመቱ የታዳጊዎች ምርጥ ፊልም ሠሪ ተብሎ ይሸለማል።

ብሩክታዊት በዚህ አላበቃችም። በቅርቡም “ትናንሽ መርማሪዎች” የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም ፈጥራ ስርጭቱ ተጀምሯል።  ከ13 እስከ 18 ዓመት እድሜ ክልል የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ይሄው ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ሳይንሳዊ ዘዴዎችንና ስልቶችን በመጠቀም ለችግሮች መፍትሄ የማመንጨትና የመፍጠር ችሎታ እንዲያዳብሩ ያበረታታል። ፕሮግራሙን በአስተናጋጅነት የሚያቀርቡት የ13፣ የ14 እና የ15 አመት እድሜ ያላቸው ተማሪዎች ናቸው (ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ)። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጥናት ርዕሰ ጉዳዮችን እየዳሰሱ፣ ሳይንሳዊ ሙከራ ያካሂዳሉ፤ በየአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በማሳተፍና ሰዎችን በማነጋገር መረጃ ያሰባስባሉ፤ መፍትሄዎችን ያበጃሉ። ተማሪዎቹ ከዳሰሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፣ የደን ጭፍጨፋና የውሃ ብክለት ይገኙበታል።

ሦስቱን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መፍጠሯ፣ መምራቷና ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ማድረጓ ለብሩክታዊት ትልቅ ኩራት ነው። ፀሐይ መማር ትወዳለች የተሰኘው ፕሮግራም፣ በርካታ አለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል። በተለይ ደግሞ ብዙዎች በሚመኙትና በጃፓን በሚካሄደው አለማቀፍ የትምህርታዊ ስርጭት ውድድር  ላይ በ2000 ዓ.ም በአንደኝነት ተሸልሟል –  ለትንንሽ ሕፃናት የሚሰራጭ ምርጥ ፕሮግራም ተብሎ። በ2003ዓ.ም በማይክሮሶፍት የትምህርት ሽልማት ዘርፍ፣ የብሩክታዊት ህዊዝ ኪድስ ዎርክሾፕ “የቴክ አዋርድ ሎሬት” ተብሎ ተሰይማል። ብሩክታዊትም በ2002 ዓ.ም “የሮሌክስ ወጣት ሎሬት” የሚል የክብር ስም አግኝታለች። ከሁሉም በላይ የምትመኘው ግን፣ ስሟ ከመጪው ዘመን ስኬታማ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር አብሮ እንዲነሳ ነው። ስኬታማዎቹ ባለሙያዎች በልጅነታቸው ከብሩክታዊት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጥሩ የትምህርት መነሻና የመንፈስ ብርታት አግኝተዋል በሚል ታሪኳ እንዲጠቀስ ትመኛለች።

የአንድ አመትና የአራት አመት ልጆቿን ቤት ውስጥ እያስተማረች የምታሳድጋቸው፤ የወትሮው ሥራዋን ሳታቋርጥ ነው – ቤትዋ ውስጥ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞቿን ታሰናዳለች። ልጆቿን ስታሳድግና ሥራዋን ስታከናውን በየእለቱ ከፈተናዎች ጋር ትጋፈጣለች። አንዳንዴማ ፈተናዎቹ መውጫ መፈናፈኛ የሚያሳጡ ይሆኑባታል። ግን እጅ አትሰጥም። የስኬት ተስፋዋንና ልባዊ የሙያ ፍቅሯን አጥብቃ ይዛ በአይበገሬነት ውጥኖቿን እውን ለማድረግ ራሷን ታበረታታለች። ውስጣዊ ሃይል የምታገኘው ለመጪው ዘመን ካላት ብሩህ ራዕይ ነው – ሙሉ አቅማቸውን ለመጠቀምና በራሳቸው ውሳኔ ሕይወታቸውን ለመምራት በቂ መነሻ የሰነቁ ብልህ ሕፃናት የምናይበት ብሩህ ራዕይ። የመገናኛ ብዙሃን ስርጭት ትልቅ ሃይል እንደሆነ የምታምነው ብሩክታዊት፤ ሕፃናት እምቅ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ የሚረዳ መረጃና ማበረታቻ ለብዙ ሕፃናት ለማድረስ እንችላለን ትላለች። ከአስተዳደጓና ከሃይማኖት እምነት የመነጨ የሰው ልጅን የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት ያላት ብሩክታዊት፣ “አይሆንም” ለሚል ምላሽ ጆሮ የማይሰጥ አይበገሬነትና ለፈተናዎች የማይንበረከክ በትጋት የመሥራት ባህርይ ለእስካሁን ጉዞዋ ጠቅመዋታል።

ብሩክታዊት ለኢትዮጵያ ያላት ሕልም ትልቅ ነው። ታዳጊዎችን በትምህርት እያነፅን በሚመለከታቸው ጉዳይ ሁሉ እንዲሳተፉና በውሳኔ አሰጣጥ ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው ካደረግን፤ የተሻለ ዓለም እንደምናይ አያጠራጥርም። እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው ሰዎች እምቅ አቅማቸውን ተገንዝበው፣ለቤተሰባቸውና ለህብረተሰባቸው መልካም ነገር ለመስራት በራሳቸው ውሳኔ የመመራት ብቃት ሲጎናፀፉ ነው። በተለይ ሴቶች እጅግ ቁልፍ ናቸው። ምክንያቱም፣ ሴቶች ብቃት ሲጎናፀፉ፣ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ብቃት እንዲጎናፀፍ ያደርጋሉ። የማህበረሰቡ የልብ ትርታ፣ ሴቶች ናቸውና። ደግሞም ችግር ፈቺ የፈጠራ ክህሎት እንዲስፋፋና እንዲከበር ማድረግ ትፈልጋለች። ለምን ቢሉ፣ ኢትዮጵያ የሌሎችን ምፅዋት ሳትጠብቅ የራሷን ችግሮች ራሷ መፍታት ትችላለች።
ብሩክታዊት ለኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች እንዲህ ስትል ምክሯን ታካፍላለች፡ “ሁላችሁም፣ በተለይ ከፍተኛ ፈተና የተጋፈጣችሁ ወጣቶች በሙሉ ድንቅ ሰዎች መሆናችሁን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ችግሮችን ተቋቁማችሁ ስታሸንፉ የላቀ ክህሎት ይኖራችኋል። ባህላዊውን አኗኗር ተከትላችሁ በለጋ እድሜያችሁ ማግባትንና መውለድን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ነገሮችን ለመስራት መፈጠራችሁን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ልባችሁ ውስጥ ጠልቃችሁ ተመልከቱ። በባህልና በአኗኗር ሳቢያ ከታጠረው ክልል ውጭ አስፍታችሁ አስቡ። ‘በህይወቴ፣ ከጉድም ጉድ የሚያሰኝ ምን መስራት እችላለሁ?’ ብላችሁ  ራሳችሁን ጠይቁ፤ እናም በተግባር ፈፅሙት። አንዳች የሚረብሽና የሚገድብ ነገር ካጋጠማችሁ፤ ጣጣው ቢወገድ ምንኛ መልካም እንደሚሆን በምናባችሁ እዩት፤ ታዲያ እኔስ ምን አስተዋፅኦ ማበርከት እችላለሁ ብላችሁ አስቡ። እኛ ሴቶች በራሳችን ብንተማመን፤ የፈለግነውን ነገር መሆን እንችላለን። አካባቢያችሁን ስትመለከቱ፣ ሴቶች የማይሰሩት ነገር ካያችሁ፣ ‘ለምን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁና፤ ‘እኔ ልስራዋ’ ብላችሁ ተነሱ። ልማዳዊውን አኗኗር ተጋፍጣችሁ ስሩት። እርካታ ታገኙበታላችሁ፤ ማህበረሰባችሁን ለዘለቄታው ትቀይሩበታላችሁ። እኛ ሴቶች፣ ሁላችንም ከሚጠበቅብን በላይ ከሰራን ኢትዮጵያን እንለውጣታለን።


ዋና የመረጃ ምንጮች
 

ከብሩክታዊት ጥጋቡ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ ነሀ 2004 .ም፤ በአዲስ ላይፍ መፅሄት ቃለምልልስ: ቁጥር 4 መከረም 2003 .

ሌላ ምንጮች
 
አጥኚ
ሜሪ-ጄን ዋግል፣ ቤተል በቀለ፣ ወደርየለሽ አበበ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>