Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሙሉመቤት ገብረሥላሴ

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የውበት ሳሎን እና የስፓ አገልግሎት ከፍታለች፤ የባዮጀኒክቢዩቲ ስፖት መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። የውበት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አቋቁማ ከ680በላይ ሙያተኞችን አስመርቃለች። ከጓደኞቿ ጋር “ሳራ ካኒዛሮ ቻይልድ ማይንደር” የተሰኘ ማኅበርበማቋቋም ችግረኛ ልጆችን የሚረዳ መዋዕለ ሕፃናት ከፍታለች።
ወቅታዊ ሁኔታ  የባዮጀኒክ ቢዩቲ ስፖት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ
የትውልድ ቦታ: ወንጂ፣ ኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: በ1950 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሰበታ ጌተ ሰማኒ አዳሪ ትምህርት ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
መድኃኔዓለም እና እቴጌ መነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዲፕሎማ፣ በሴክሬታሪያል ሳይንስ እና በአካውንቲንግ፣ አዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
 
ዋና የስራ ዘርፍ
የቢዝነስ ባለቤት
የሕይወት ታሪክ
በሙያዋ “ሙሉ ባዮጄኒክ” ተብላ የምትታወቀው ሙሉመቤት ገብረሥላሴ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የውበት ሳሎንና የስፓ አገልግሎት በፈር ቀዳጅነት ያስፋፋች ስኬታማ የቢዝነስ ሴት ናት። በአገሪቱ ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ የሥነ ውበት ትምህርት ቤት በማቋቋም ከ680 በላይ ሴቶችን አሰልጥናለች። “ባዮጀኒክ ቢዩቲ ስፖት” በተሰኘ የቢዝነስ ድርጅቷ በአዲስ አበባ ሦስት የውበት አገልግሎት ማዕከላትን ከመክፈቷም በተጨማሪ፤ በሽርክና የልብስ ፋብሪካ  መስርታለች። ማህበረሰብን የማገልገል ጠንካራ እምነት ያላት ሙሉመቤት፣ ሕፃናትንና አዛውንትን በልግስና ትደግፋለች፤ የውበት ማሰልጠኛ ተቋሟ ውስጥም ለችግረኛ ሴቶች የትምህርት ክፍያ ቅናሽ በማድረግ ትረዳለች።

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ መቶ ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ወንጂ ከተማ በ1950 ዓ.ም የተወለደችው ሙሉመቤት፤ የዘጠኝ አመት ሕፃን እያለች ነው ወላጆቿን ያጣችው። እናም አዲስ አበባ ትኖር ለነበረች አንዲት ሆላንዳዊት የጉዲፈቻ ልጅ ሆነች። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በሰበታ አዳሪ ትምህርት ቤት ከተከታተለች በኋላ፤ መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። ወደ እቴጌ መነን ተዛውራ በሴክሬታሪያል ሳይንስ ዲፕሎማ ያገኘችው ሙሉመቤት፤ ከአዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት በሂሳብ አያያዝ በዲፕሎማ ተመርቃለች። ከዚያማ ወደ ሥራ ዓለም ተቀላቀለች። በእርግጥ አንድ ቦታ ተቀጥራ አልረጋችም። ለጊዜው ያገኘችውን ሥራ እየሠራች፤ ሌሎች የሥራ እድሎችን ታፈላልጋለች። የሥራውን አይነትና ደሞዙን እያነፃፀረች፤ ሻል ወዳለው ለመሻገር ትወዳደራለች። በዚህም መንገድ ለበርካታ አመታት በመንግስት መሥሪያ ቤቶችና አትራፊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሥራ አስኪያጅ ፀሐፊ በመሆን ሠርታለች።

ጥሩ ደሞዝ ለማግኘት ብትችልም እርካታን አልሰጣትም። ሕልሟ ሌላ ነበራ። በውበት ሙያ ላይ መሰማራትና ለውጥ ማምጣት ነው የነፍሷ ጥሪ። በሕፃንነት እድሜዋም ሳይቀር፤ ትልቁ ምኞቷ በውበት ሙያ መሰማራት ነበር። ምኞት ብቻ ሆኖ አልቀረም። እድሜዋ ወደ 30ዎቹ ሲሻገር ወደ አሜሪካ የመሄድ እድል ያገኘችው ሙሉመቤት፤ በአንድ አመት ቆይታ በራሷ ወጪ የሥነ ውበት ትምህርቶችን ተከታተለች። ቢሆንም፣ አሜሪካ ውስጥ የመኖር እቅድ አልነበራትም። ዘመናዊ የውበት አገልግሎቶችን ወደ አገሯ አምጥታ የመሥራትና የማስፋፋት ሕልም ስለነበራት፤ ራዕይዋን እውን ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በ1985 ዓ.ም የመጀመሪያውን ባዮጀኒክ ቢዩቲ ስፖት ከፈተች። በእርግጥ፣ እንደተመኘቸው ዘመናዊ የውበት አገልግሎትን ማስተዋወቅ ቀላል አልሆነላትም። ደግነቱ ሙሉመቤት መፍትሄውን አላጣችውም፤ ለችግር ሳይበገሩ መጣጣር ነው መፍትሄው። የሕይወት አላማዋን የሙጢኝ እንደያዘች ለአመታት በትጋት ስለሠራችም ታዋቂነትን ለማግኘት በቃች። ታማኝ ደንበኞቿ እየበረከቱ ድርጅቷ ተመነደገ። ግን በቃኝ አላለችም። የሥነ ውበት ሙያን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ለመጀመር አሰበች። እሷ ራሷ ተጨማሪ አጫጭር ስልጠናዎችን ለማግኘት ወደ ሆላንድ የሄደችው ለምን ሆነና! ለሙያው ብቻ ሳይሆን ለትምህርትና ለስልጠና ከፍተኛ ክብር ስላላት ነው። እውቀቷንና ሙያዋን ለሌሎች ማድረስ የምትችለውም በስልጠና ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የውበት አገልግሎትን በሰፊው ለማስተዋወቅና ብቁ ሙያተኞችን ለመፍጠር በማሰብ፣ በ1997 ዓ.ም የውበት ማሰልጠኛ ተቋም ከፈተች። በርካታ ችግረኛ ሴቶችና ልጃገረዶች፣ ተቋሙ ውስጥ በቅናሽ ክፍያ እንዲማሩ ሙሉመቤት ስለፈቀደችላቸው ስልጠናውን ለማጠናቀቅ ችለዋል። ሌሎች ችግረኛ ሴቶች ደግሞ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ በተቋሙ ሰልጥነዋል። በተቋሙ የሰለጠኑ ከ680 በላይ ሴቶችና ልጃገረዶች ከሞላ ጎደል ሁሉም በተለያዩ የውበት አገልግሎት ማዕከላት ሥራ አግኝተዋል ማለት ይቻላል። አንዳንዶቹ የሙሉመቤት ድርጅት (ባዮጀኒክ ቢዩቲ ስፖት) ውስጥ ተቀጥረዋል። ቀስ በቀስ እያደገ በአዲስ አበባ ከተማ በሦስት ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ባዮጀኒክ፤ 60 ሰራተኞች አሉት። ሙሉመቤት ከዚህ ዋነኛ ሥራዋ በተጨማሪ የቢዝነስ እንቅስቃሴዋን ለማስፋፋት፤ በሽርክና ጂኤምኤም የልብስ ፋብሪካን መስርታለች። አልባሳትን እያመረተ ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ እየላከ የሚገኘው ጂኤምኤም ለመቶ ያህል ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች የሥራ እድል ፈጥሯል።

ሙሉመቤት የውበት አገልግሎት ቢዝነሷን የጀመረችው ከትንሽ ተነስታ ነው። ቢዝነሷን ቀስ በቀስ ለማሳደግም ለአመታት መጣጣርና ፈተናዎችን ማሸነፍ ነበረባት። በተለይ የባንክ ብድር ለማግኘት አለመቻሏ፣ በምትፈልገው መጠን አገልግሎቷን እንዳታስፋፋና በፍጥነት እንዳትገሰግስ እንቅፋት ሆኖባታል። የውበት አገልግሎት፣ ለበርካታ ሴቶች የሥራ እድልንና የኑሮ ዋስትናን የሚሰጥ ቢሆንም፤ ራሱን የቻለ ጠንካራ የሙያና የቢዝነስ ዘርፍ እንደሆነ ብዙዎች አልተገነዘቡትም። በዚህም ምክንያት የባንክ ብድር ለማስፈቀድ ከባድ ሆኗል። ሌላው ፈተና፤ ለስልጠና ማዕከሏ ቋሚ ቦታ ለማግኘት አለመቻሏ ነው።

ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን እየተቋቋመች ከመሥራት ወደኋላ የማትለው ሙሉመቤት፤ ታዋቂዋ የቢዝነስ ሴት የሺመቤት ተሰማ በአርአያነታቸው የብርታት ምንጭ እንደሆኑላት ትገልፃለች። በ1962 የሺ ቡና የተሰኘ የቡና ኤክስፖርት ቢዝነስ የመሰረቱት የሺመቤት ተሰማ፤ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት ነበሩ። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በርካታ ችግረኛ ሴቶች በአነስተኛ የንግድ ሥራ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩት የሺመቤት፤ የበርካታ ሴቶችን ሕይወት ለመቀየር በቅተዋል። ሙሉመቤትም ከባባድና ትልልቅ አላማዎችን ማሳካት እንደሚቻል፣ የሺመቤት በአርአያነት አሳይተውኛል ትላለች።

በእርግጥም ስኬትን መቀዳጀትንና ህልምን እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር አይታዋለች። አገሯ ውስጥ ዘመናዊ የውበት አገልግሎት ለማስፋፋት የነበራትን ህልም በበርካታ አመታት ጥረት እውን አድርጋዋለች። የተሟላ ዘመናዊ የውበት ማዕከልንና የስፓ አገልግሎትን ከሷ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፈተ ሰው አታውቅም። እሷ ከጀመረችው በኋላ ግን፣ በርካታ ሰዎች ፈለጓን እንዲከተሉ አርአያ ሆነችላቸው። ዛሬ በሺ የሚቆጠሩ የስፓ አገልግሎት ሰጪዎች ተፈጥረዋል። በርካታ ሺ ሴቶችም የሥራ እድል አግኝተዋል። በ20 አመታት ውስጥ ይህን የለውጥ እድገት ለማየት በመብቃቷም እርካታ ይሰማታል።

ከቢዝነስ ሥራዋ በተጨማሪ፤ በሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ አዘውትራ የምትሳተፈው ሙሉመቤት፤ ችግረኛ ሕፃናትን ለመርዳት ከጓደኞቿ ጋር፣ “ሳራ ካኒዛሮ ቻይልድ ማይንደር” የተሰኘ ማህበር መስርታለች። እንደ መዋዕለ ሕፃናት የሚያገለግለው የማህበሩ ማዕከል፣ በተለይ ለሕፃናት ተማሪዎች በጣም ጠቅሟቸዋል። ከትምህርት ቤት መልስ ወደ ማዕከሉ በመሄድ ገላቸውን ይታጠባሉ፤ ይመገባሉ፤ ያጠናሉ። የእነሙሉ ማኅበር የመዋዕለ ሕፃናት አገልግሎቱን ለማሻሻልና ለማስፋፋት፤ የራሱን ሕንፃ እየገነባ ነው። በካቶሊክ ቤተክርስትያን ስር ለአዛውንቶች የምግብና የመጠለያ አገልግሎት ለሚሰጥ የሳን ጁሴፒ ማዕከል እንዲሁም ለዓለም የሕፃናት ማዕከል በግሏ ድጋፍ የምታበረክተው ሙሉመቤት፤ በላየን ክለብ ኢንተርናሽናል አባልነቷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትሰጣለች።

ለስኬት የበቃችው በሥራ ትጋት እንደሆነ የምታምነው መሉመቤት፤ እድልን ብቻ የሚጠብቅ ምንም አያገኝም ትላለች። ለልጃገረዶችና ለወጣት ሴቶች ምክሯን ስትለግስ፤ ስኬት በአንድ ጀንበር አይገኝም ትላለች። ጊዜ ይወስዳል። ዛሬ ያለችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ሃያ አመት ፈጅቶባታል። ወጣቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለረዥም ጊዜ በትጋት መቀጠል ይኖርባቸዋል። ሠርተው ራሳቸውን መቻል አለባቸው። የምርጫ ብቻ ሳይሆን የሃላፊነት ጉዳይ ነው። ራሳቸውን ለመቻል ተግተው የመሥራት ሃላፊነት አለባቸው። ነገር ግን ዛሬ የሚያገኙትን ደመወዝና ገቢ ብቻ ማየት የለባቸውም። የወደፊት ራዕያቸውን አውቀው ከልብ የሚያፈቅሩትን የሥራ መስክ መርጠው እንዲሠሩ ታበረታታቸዋለች። ከልብ በሚያፈቅሩት ሥራ ላይ የሚተጉ ከሆነ፤ ስኬትና ገንዘብ ራሳቸው ይመጣሉ። በወጣትነት እድሜዋ በረድኤት ድርጅት በጥሩ ደሞዝ ተቀጥራ ብትሠራም እርካታ ልታገኝበት ያልቻለችው፤ ከልብ ከምትወደው የውበት አገልግሎት ሙያ ጋር ስላልተገናኘች ነው። ዛሬ ስኬታማ ሆናለች፤ ሕልሟ ስለሞላላትም እርካታን ተጎናፅፋለች።

 

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከሙሉመቤት ገብረሥላሴ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ሸዊት ወልደሚካኤል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>