Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሀረገወይን ቸርነት ወልደማርያም

Haregewoin Cherenet

ዋና ዋና ስኬቶች:
የሴቶች ልማት የምርምርና ሥልጠና ማዕከል (CERTIUDE) (አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስርዓተ – ፆታ ጥናቶች ተቋም) ቀደምት ዳሬክተሮች ከነበሩት አንዷ ናት፡፡ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የምትሟገት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሃይማኖት መሰረት አላቸው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለማጥፋት የሃይማኖት መሪዎችን በማስተባበር  የፈርቀዳጅነቱን ሚና የተጫወተች፤ ለፈሪ ተለማማጅ መምህራን ድፍረትን የሚያስተምር “Assertiveness for shy Teacher Trainess” የተሰኘ ማንዋል በአማርኛ፣ ኦሮሚፋና ትግርኛ አዘጋጅታ፤ በአማራ፣ ኦሮምያና ትግራይ ክልሎች ላሉ ተለማማጅ አስተማሪዎች ተከፋፍሏል፡፡ በአዋሳ እርሻ ኮሌጅ የሰራችውን ጥናት መሠረት አድርጋ፣ ለእንጀራ የሚሆን የተለያዩ ዱቄቶች አመጣጠንና  አዘገጃጀትን  የሚያስተምር ማኑዋል የፃፈች ሲሆን በግብርና ሚ/ር በኩል ለገጠር የቤት እመቤቶች ተሰራጭቷል፡፡ በአገሪቱ የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ (1998-2002)ውስጥ የተካተተውን “ብሔራዊ የፆታ እኩልነት የትግበራ ዕቅድ” ሰነድ ያዘጋጀ ቡድን መርታለች፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ የሥነፆታ እና የጤና አማካሪ፤ የሥርዓተ- ፆታ እና የክርስትና ሃይማኖት  ተመራማሪ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ሰኔ 18 1938 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አበራ እና አስፋው ወሰን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ፍቼ (ሰላሌ)
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
እቴጌ መነን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት (እስከ 10ኛ ክፍል)፤ ካቶሊክ ካቴድራል ት/ቤት (12ኛ ክፍል)፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመርያ ድግሪ፣ (ቢኤስ ሲ)  በምግብና በአመራር ሳይንስ፣ ከንግስት ኤልዛቤት ኮሌጅ፣ የለንደን ዩኒቨርስቲ፤ ኦርዲናሪ ናሽናል ዲፕሎማ (OND) በምግብ ቴክኖሎጂ፣ ደቡብ ለንደን ኮሌጅ፣ ለንደን፣ ዩ ኤል
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
                          ሁለተኛ ድግሪ፣(MSC) በማህበረሰብ ጤና፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤  ዲፕሎማ፣ ከዚያ የመጀመርያ  ዲግሪ (BTH)፣ በሥነመለኮት፣ ከቅድስት  ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ አዲስ አበባ
ዋና የስራ ዘርፍ
የስርዓተ- ፆታ እና የጤና አማካሪ፤ የሴቶች መብት ተሟጋች
የሕይወት ታሪክ
የሐረገወይን ቸርነት የህይወት ዓላማ እውቀት መቅሰምና ለሌሎች በጎ መሥራት ነው፡፡ የሙያ ህይወቷም እነዚህን መንታ ዓላማዎች  ያንፀባርቃል፡፡ በህይወት ዘመኗ ደጋግማ ወደ ት/ቤት  በመመለስ የተማረችው ሃረገወይን፤ የነርስነት ሙያዋ፣  የዩኒቨርስቲ መምህርነቷ፣  የምርምር ሥራዋ፣ የሥርዓተ – ፆታ አማካሪነቷ፣ በቅርቡ ደግሞ የሥነ መለኮት ተመራማሪነቷ  ሁሉ   የሰዎችን ህይወት ለማሻሻል ያለመ ነው- በተለይ ደግሞ የሴቶችን ህይወት፡፡ የሴቶች ልማት የምርምርና ሥልጠና ማዕከል “CERTWID” (ለአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ    የሥርዓተ- ፆታ ጥናቶች ተቋም መነሻ ነው) ቀደምት ሠራተኞች መካከል አንዷ ስትሆን በኋላም የማዕከሉ ዳይሬክተር ለመሆን በቅታለች፡፡ የሴቶችን ጭቆና ለመፋለም በጋለ ልባዊ ፍቅር የታተረችው ሐረገወይን ፤ ሙያዋንና እውቀቷን  ያዋለችው ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡

ወላጆችዋ  አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ሐረገወይንም ሆነች የቀሩት ልጆቻቸው ምርጥ ትምህርት እንዲያገኙ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ በ1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብትወለድም የቄስ ትምህርቷን እንደጨረሰች  እናቷ  ወደ ፊቼ ገጠማራ አካባቢ ይዛት የሄደችው ለሌላ ሳይሆን ጥሩ ት/ቤት አለ መባሉን ስለሰማች ነው፡፡ ያኔ በአካባቢው ት/ቤት የገባች ብቸኛዋ ልጃገረድ ሐረገወይን ስለነበረች ጎረቤቶች በእናቷ መሳቃቸው አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ሴቶችን ማስተማር ብክነት ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው፡፡ ሀረገወይን የቱንም ያህል ብትማር ሥራ የማግኘት ዕድል የላትም የሚሉት የእናቷ ጎረቤቶች፤ “ብታገኝም እንኳ ከፍርድ ቤት ራፖር ፀሃፊነት አያልፍም፣ እሱም ቢሆን ለሴት ልጅ ላም አለኝ በሰማይ ነው” እያሉ ይሳለቁባቸው  ነበር፡፡ የሀረገወይን እናት ግን ለማንም ጆሮዋን አልሰጠችም፡፡ ልጇ ት/ቤት እንድትገባና ጎበዝ ተማሪ እንድትሆንላት ወገቧን ታጥቃ ተነሳች፡፡ ሐረገወይን የቤት ሥራና ጥናት እያላት በቤት ውስጥ ሥራ እንድታግዛት አትፈቅድላትም ነበር፡፡ እናቷ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም  የልጇን ደብተሮች ከማየትና ከመፈተሽ ግን አላገዳትም፡፡ ዝቅተኛ ውጤት ስታይም በዝምታ አታልፋትም፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ በዝቶባት እንደሆነ ትጠይቃታለች፡፡ ሀረገወይን ሙዚቃና ዳንስ እንደ ነፍሷ ብትወድም  በንባብ ፍቅርም  ተኮትኩታ ነው ያደገችው፡፡ ንባብ ወደ ዕድሜ ልክ የእውቀት ዓለም የሚያስገባ  በር ነው የምትለው ሀረገወይን፤ ወጣቶች በለጋ እድሜያቸው የማንበብ ልማድን እንዲያዳብሩ ትመክራለች፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፍቼ አበራ እና አስፋው ወሰን ት/ቤት ያጠናቀቀችው        ሃረገወይን፤ አዲስ አበባ በመምጣት የሴቶች አዳሪ ት/ቤት በነበረው የእቴጌ መነን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገባች፡፡ 10ኛ ክፍል የመጨረሻ ዓመት ላይ የቀለም ትምህርቷን አቋርጣ፣ በልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል የነርስ ት/ቤት ለመግባት የወሰነችው የነርስ ትምህርትን ለማስተዋወቅ ወደ ት/ቤቷ በመጡ ነርሶች ተማርካ  ነው፡፡  በዚያ ላይ የጓደኞቿ ውትወታ ቀላል አልነበረም ፡፡ የነርስነት ትምህርቷን ተከታትላም ዲፕሎማዋን አገኘች፡፡ በኦፕራሲዮን ክፍል  በነርስነት እየሰራች ደሞዝ ማግኘቷ ለአቻዎቿ የሚያስቀና ቢሆንም እሷን ግን አንድ ነገር  እረፍት ነሳት – የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አለማጠናቀቋ፡፡ ይሄኔ ነው በካቶሊክ ካቴድራል ት/ቤት የማታ ትምህርት ክፍል ገብታ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በመከታተል ማጠናቀቅ የቻለችው፡፡ በእርግጥ ጓደኞቿና የሥራ ባልደረቦቿ ለምን መማር እንዳስፈለጋት ፈፅሞ አልገባቸውም፡፡ ለሐረገወይን ግን ትምህርት ትልቅ ጉዳይዋ ነበር፡፡ እንደ እሷ ያለ ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠማቸው ወጣት ሴቶችም፣ ት/ቤት ተመልሰው በመግባት ያቋረጡትን ትምህርት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ የምትመክረው ሀረገወይን ፤ በክፍል ውስጥ ካሉት ተማሪዎች  በዕድሜ ትልቅ ብትሆኑም ችግር የለውም ባይ ናት፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ብዙም ሳትቆይ ነበር ለተጨማሪ ትምህርት እንግሊዝ  የመሄድ ዕድል የገጠማት፡፡ የመጀመሪያ ዓመት የትምህርቷን ክፍያ ራሷ መሸፈን ነበረባት፡፡ ደግነቷ ውጤቷ ጥሩ ስለነበር ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘች፡፡ በአምስት ዓመት የእንግሊዝ ቆይታዋ በምግብ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ ያገኘች ሲሆን በምግብና በአመራር ሳይንስ የመጀመሪያ ድግሪዋን ተቀብላለች፡፡ ከትምህርቷ ጐን ለጐን በነርስነት ትሰራ የነበረችው ሃረገወይን ፤ የሙያ ክህሎቷ ከተገመገመ በኋላ State Registered Nurse (SRN) የሚል እውቅና አግኝታለች   – ከተጨማሪ ዲፕሎማ ጋር፡፡

ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰች  ያኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በነበረው አዋሳ እርሻ  ኮሌጅ (አሁን  በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ሥር ነው) ገብታ በመምህርነትና በዲፓርትመንት ሃላፊነት ሰርታለች፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመመለስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ ጤና አጥንታ  የማስተርስ ድግሪዋን ወሰደች፡፡ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት በእርሻ  ፋኩሊቲ ካስተማረች በኋላ የሴቶች ልማት የምርምርና የስልጠና ማዕከል (CERTWID) ውስጥ ተቀጥራ በተመራማሪነትና በሥልጠና ባለሙያነት  መስራት ጀመረች፡፡ (በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነፆታ ጥናቶች ተቋም ማለት ነው) የማታ ማታም የማዕከሉ ዳሬክተር ለመሆን በቅታለች፡፡ በምርምር አሰራር ዙርያ ሥልጠናም ከመስጠቷም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፋኩልቲ የህዝብ ጤና ክፍል ውስጥም አስተምራለች፡፡ በሴቶች ልማት የምርምርና ስልጠና ማዕከል ሳለች፣ በስርዓተ- ፆታ ጉዳዮች ላይ የጥናት ፕሮጀክቶችን ከማካሄድ ጎን ለጎን በመስኩ የመመረቂያ ጥናታቸውን ለሚሰሩ ተማሪዎች የድጋፍ ክትትልና ሥልጠና ትሰጥ ነበር፡፡  በማዕከሉ በተደረገላት ድጋፍም በኢትዮጵያና በውጭ አገራት በስርዓተ- ፆታ  ልማት ዘርፍ በርካታ አጫጭር ሥልጠናዎችን  የወሰደች ሲሆን ይሄም በተለይ በስርዓተ ፆታ አማካሪነት ላይ አተኩራ ለመስራት የሚያስችላትን ክህሎት እንዳስጨበጣት ሐረገወይን ትናገራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ካዘጋጀቻቸው የህትመት ሥራዎች አንዱ የሚፈሩ መምህራን ደፋር የሚሆኑበትን መንገዶች የሚጠቁም መመሪያ (Manual) አንዱ ሲሆን ማኑዋሉ በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በክልሎች  ተሰራጭቷል፡፡

ለአምስት ዓመት ብቻ አገልግላ ማዕከሉን በጊዜ የለቀቀችው ሀረገወይን፤ ለትርፍ ባልተቋቋመው ዓለም አቀፍ ድርጅት “CARE” የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ  ተቀጠረች፡፡ እዚያ ሳለችም የፕሮጀክት አስተባባሪ በመሆን በቤተሰብ ምጣኔና በኤችአይቪ መከላከል ላይ ሰርታለች፡፡ ከዚሁ ሥራዋ ጐን ለጐን የሴቶች ብልት ትልተላና የመሳሰሉ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም በሚሰራው EGLDAM የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ትሰጥ ነበር – በምክትል ፕሬዚዳንትነት እየሰራች፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ መስራቷ ነው ትኩረቷን ከስርዓተ- ፆታ ጥናቶች ወደ ሴቶች ጥቃት እንድታዞር ሰበብ የሆናት፡፡ ሆኖም በተለመደው መንገድ እየሰራች ለመቀጠል አልፈለገችም፡፡  አዲስ ውጤታማ መንገድ እንድትፈትሽና እንድትመረምር የሚገፋፋ ነገር ገጠማት፡፡

አንድ ቀን ዶክመንታሪ ፊልም ስትመለከት ክርስትያንና ሙስሊም የሃይማኖት መሪዎች፤ ቅዱስ መጽሐፋቸው የሴቶች ብልት ትላተላን እንደማያዝ ሲናገሩ ሰማች፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሙሉ በተሳሳተ መንገድ የሃይማኖት ድጋፍ እየተሰጣቸው ይፈፀሙ እንደሆነ ለማወቅ በጉጉት የተሞላ ፍላጎት አደረባት፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማንበብና መጠየቅ ስትጀምር፤ ባህልና ሃይማኖት እነዚህን ልማዳዊ ድርጊቶች መፈፀም እንደሚያስገድዱ በተደጋጋሚ ተነገራት፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ሃይማኖት ስለዚህ ጉዳይ በትክክል ምን እንደሚያስተምር መጠየቅ የጀመረችው፡፡ የጥያቄውን መልስ ራሷ ለማግኘት በማሰብም በ1997 ዓ.ም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገባች  – በ61 ዓመቷ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ዲፕሎማዋን ያገኘችው ሐረገወይን የበለጠ ለማወቅና ለማጥናት  ትምህርቷን በመቀጠል በ2004 ዓ.ም የባችለር ድግሪዋን አገኘች፡፡ ሁለቱንም ጊዜ የተመረቀችው ደግሞ በማዕረግ  ነው፡፡ ትምህርቷን ስትከታተል በክፍሏ ውስጥ በዕድሜ ከሁሉም ትልቋ እሷ ብትሆንም መሳቂያና መሳለቂያ አልነበረችም፡፡ እንደውም ዕድሜዋ በተቃራኒው ክብርና ሞገስ አቀዳጅቷታል – ከአስተማሪዎቿም ሆነ ከክፍል ጓደኞቿ፡፡ ይሄን ፅሁፍ የሚያነቡም ከእሷ ምሳሌ እንዲማሩ ትፈልጋለች – ት/ቤት ለመግባት ወይም ለመማር ፈፅሞ ጊዜው እንደማይረፍድ፡

የሁለተኛ ዓመት የኮሌጁ ተማሪ ሳለች የመመረቂያ ጥናቷን የጀመረችው ሐረገወይን፤የጥናቷም ትኩረት “ቤተክርስትያንና መፅሐፍ ቅዱስ ስለሴቶች ምን ይላሉ?” ፣ “ህብረተሰቡ ስለሴቶች ያለው አመለካከት ምንድነው” በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ያጠነጠነ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ከጥናቱ ያገኘችው ውጤት ግን አስደንግጧታል፡፡ ከቤተክርስትያን ይልቅ ህብረተሰቡ ሴቶች ያላቸውን ሚና በእጅጉ ዝቅ አድርጎ እንደሚገምት እንዲሁም ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ የቱን ያህል ከቁጥር እንደማይገቡ ጥናቷ ይጠቁማል፡፡ ለመመረቂያ ፅሁፏ ለመከራከር በቀረበችበት ወቅት የጥናቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ተጠይቃ ስትመልስ፤

ህብረተሰቡና ቤተክርስትያን ሴቶችን በተመሳሳይ መነጽር ይመለከቱ እንደሆነ ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁማ ፤ የሁለቱ ዕይታ በጣም የተለያየ መሆኑን ከጥናቱ ውጤት መገንዘቧን ገልፃለች፡፡ እንደውም የሃይማኖት መሪዎች ሴቶች ከወንድ እኩል መሆናቸውን  እንደሚያምኑ፣ ያነጋገረቻቸው የሃይማኖት መሪዎችም  መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ምን እንደሚልና ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌላቸው ለህብረተሰቡ ለማስተማር ፈቃደኞች መሆናቸውንና ይሄንንም ለማድረግ ቃል እንደገቡላት ለመምህራኖቿ ተናግራለች፡፡

ይሄን ጥናት መሠረት ያደረገ መጽሐፍ የማሳተም ዕቅድ ያላት ሲሆን እስከዚያው ግን የግጥም ስብስቦችን የያዘ መድበል አሳትማለች፡፡ ግጥሞቹም ቢሆኑ ከጥናቷ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት አላቸው፡፡ በማሕበረሰቡ ውስጥ ከሚታየው እውነታ በተለየ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሴቶች የሚላቸውን ነገሮች የሚያንፀባርቁ የግጥም ስብስቦች እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመስራትና በመወያየት፣ ሃይማኖታዊ  ትምህርቶች ስለሴቶች በሚሰጡት ትምህርት ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ እምነት ለማስወገድ በምታደርገው ጥረት፣ የቤተክርስትያን መሪዎች እንደሚተባበሯት ሃረገወይን ተስፋ ታደርጋለች፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ጉልህ ሚና የተነሳ  አያሌ ሰዎች ጋ ስለሚደርሱ ያሰበችው ግቡን ይመታል ብላ ታስባለች፡፡ ሃረገወይን ከክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ጋር እንደምትሰራው ሁሉ የሙስሊም ሴቶችም ከሙስሊም ሃይማኖት መሪዎች ጋር ይሰራሉ የሚል ተስፋ አላት፡፡ እነዚህ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮችን በምታነሳ ወቅት በስነመለኮት ዘርፍ ያገኘችው ድግሪ ተዓማኒነቷን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ሀረገወይን ታምናለች፡፡ ለምን ቢሉ ለመቀየር  የተነሳችው ቀላል ነገር ሳይሆን ለረዥም ጊዜ የዘለቀና ሥር የሰደደ (በወንዶችም ሆነ በሴቶች)  ማህበረሰባዊ አመለካከት ነውና፡፡

በህይወቷ ትልቅ አርአያ የሆኗት እናቷ፤ መሠረታዊ የህይወት መርሆችን አስጨብጠዋታል፡፡  ተግቶ የመስራትን፣ የሃቀኝነትንና የሃይማኖትን ፋይዳ የተማረችው ከእናቷ ነው፡፡ ከባለገንዘቦች ይልቅ ለሰው አክብሮት ላላቸውና ሃቀኛ ለሆኑ ሰዎች ትልቅ ዋጋ እንድትሰጥ እየነገሩ ያሳደጓት እናቷ፤ ምንም ዓይነት መድልዎና መገለል ቢደርስባት ትኩረት እንዳትሰጠው ወይም ነገሬ እንዳትለው መክረዋታል፡፡

ሃረገወይን ሌሎች አርአያዎችም አሏት፡፡ አንደኛው ታላቁ የቀዶ ህክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ናቸው፡፡ በልዕልት ፀሐይ ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ በነርስነት አብራቸው ስትሰራ፣ የቱን ያህል ራሳቸውን ለሥራቸው እንደሚሰጡ፤ እንዲሁም ትጋታቸውንና ሙያዊ ልቀታቸውን አስተውላለች፡፡ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሚያንፀባርቁትን ሃሳቦችም የመስማት ዕድል ነበራት፡፡ ለሥራ ትጋትና ለሃቀኝነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጡት የአዋሳ እርሻ ኮሌጅ ዲን የነበሩት አለቃዋ ዶ/ር ገረመው ሃይሌም  አርአያዋ ናቸው፡፡ ከሦስቱም አርአያዎቿ የተማረችው እሷም ራሷ እንደ እንቁ የምታከብራቸውን  የሥነምግባር እሴቶች ነው – ትጋት፣ ሃቀኝነትና የአገር ፍቅር፡፡

ለኢትዮጵያ የምታልመው ሰዎች ከየትም ይምጡ ከየት፤ በእኩል ዓይን የሚታዩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ ሰውን ማክበር ሃብትና ገንዘቡን አይቶ ሳይሆን በፈሪሃ እግዚአብሔር የፈጣሪን መንገድ ከመከተል እንዲመነጭ ትሻለች፡፡ ቤተክርስትያን ወንዶችና ሴቶች እኩል መሆናቸውን በአደባባይ የምታውጅበትንና  ሃይማኖት ሴቶች ላይ ጉዳት ማድረስ እንደማይፈቅድ ትክክለኛውን ትምህርት በይፋ የምትናገርበትን ጊዜ ትናፍቃለች፡፡

በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች ሃረገወይን ስትመክር እንዲህ ትላለች– ራሳችሁን ሁኑ – ልዩ ማንነት አላችሁ፤ ሌላውን ሰው ለመምሰል አትሞክሩ፡፡ እንደ ወንዶች ለመሆን አታልሙ ወይም የወንዶችን ስኬት፤ የስኬታችሁ መለኪያ አታደርጉ፡፡ እንዲያ ማድረግ መድረሻችሁን ከመገደብ በቀር ፋይዳ የለውም፡፡

የራሳችሁ ልዩ ማንነት ባለቤት ስለሆናችሁ የራሳችሁን አቅምና ችሎታ አዳብሩ፡፡ በየዕለቱ የምትሰሩትን በመገምገም የቱን ያህል እንዳሻሻላችሁ፤ነገ ከነገ ወዲያ እንዴት የበለጠ ስኬታማ ልትሆኑ እንደምትችሉ …የምታሰላስሉበት የጥሞና ጊዜ በየምሽቱ ይኑራችሁ፡፡

ራስን አሻሽሎ የተሻለ ሰው ለመሆን ፈጽሞ ጊዜው አይረፍድም፡፡ ዋናው ነገር ጽናትና በራሳችሁ ላይ እምነት ማሳደር ነው፡፡ እኔ ያቋረጥኩትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመቀጠል የማታ ትምህርት ስጀምር ሁሉም ሰው ስቆብኝ ነበር – አልፎብሻል ሚል፡፡ ያኔ እኮ ገና 20 ዓመቴ ነበር፡፡ በ61 ዓመቴ መንፈሳዊ  ኮሌጅ ስገባማ ብዙዎች ያበድኩ ነበር የመሰላቸው፡፡ እኔ ግን ነገሬ አላልኳቸውም፡፡ እናንተም የምትፈልጉትን እንዳታደርጉ የሚያደናቅፏችሁን መንገድ አትስጧቸው፡፡ ራሳችሁን ሌሎች በሚናገሩት አትለኩ፡፡ የራሳችሁ መለኪያና መስፈሪያ ይኑራችሁ፡፡

ዋና የመረጃ ምንጮች
በነሐሴ 2004 ዓ.ም ከሃረገወይን ቸርነት ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ማርያማዊት እንግዳ ወርቅ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>