Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ማጂ-ዳ አብዲ

MajiDa Small

ዋና ዋና ስኬቶች:
ሽልማት ያሸነፈ “The River that Divides” የተሰኘ ዶክመንታሪ ፊልም በፀሃፊነት፣ በፕሮዱዩሰርነትና በዳይሬክተርነት ሰርታለች፡፡ ፊልሙ በኢትየ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከመኖርያቸው ተገደው ስለተፈናቀሉ ሴቶችና ህፃናት ታሪክ የሚናገር ነው፡፡ ስኬታማ የፊልም ፕሮዱሰር ናት፡፡ በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተዘጋጀ “Images That Matter” የተሰኘ የፊልም ፌስቲቫል አዘጋጅ ስትሆን በፌስቲቫሉ ላይ ለወጣት የምስራቅ አፍሪካ ፊልም ሰሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ የፊልም ፕሮዱዩሰር፣ ኖማድስ ፊልም
የትውልድ ቦታ: ድሬዳዋ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ጥቅምት 15 ቀን 1963
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: ዳካር፣ ሴኔጋልና ፓሪስ፣ ፈረንሳይ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ናይሮቢ፣ ኬንያ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት

የመጀመርያ ድግሪ፣ /ቢኤ/፣በቢዝነስ፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስተርን ኦንታርዮ፣ለንደን፣ ኦንታርዮ፣ ካናዳ

ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
 

የህይወት ጎዳናዋ በበርካታ አቅጣጫዎች የወሰዳት ማጂ-ዳ አብዲ እጅግ ሰፊ ተመክሮዋን ለፊልም ፕሮዱዩሰርነትና ለተሟጋችነት ስራዋ ያዋለች ትጉህ የፊልም ባለሙያ ናት፡፡  እጣፈንታ ያመጣውን ለመቀበል ክፍት መሆኗና  የማወቅ ጉጉነቷ ህይወቷን አበልፅጎላታል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በመጀመርያ በጋዜጠኝነት፣ ከዚያም የሌሎችን ቪዲዮና ፊልም ፕሮዱዩስ በማድረግ ከሰራች በኋላ “The River that Divides” የተሰኘውን የራሷን የመጀመርያ ፊልም ፅፋ በዳይሬክተርነት ሰርታለች፡፡ ይሄ ዶክመንታሪ ፊልም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ስለተፈናቀሉ ሴቶችና ህፃናት የሚተርክ ሲሆን ፊልሙ የካናዳ ሰብዓዊ መብት ሽልማትን ሊያሸንፍ በቅቷል፡፡ ኤርምያስ ወልደአምላክ ዳይሬክት ያደረገውንና የቀይ ሽብርን ዘመን የሚያሳየውን አባትየው የተሰኘ ፊቸር ፊልም ፕሮዱዩስ አድርጋለች፡፡ ሌሎች ሃሳባቸውን እንዲያሰሙ ለማገዝ በቁርጠኝነት የምትተጋው ማጂ“Images That Matter” የተሰኘ የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል  በአዲስ አበባ አዘጋጅታለች፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከመላው ዓለም የመጡ 100 ፊልሞች ለእይታ የበቁ ሲሆን ከምስራቅ አፍሪካ ለመጡ 137 ወጣቶችም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 1963 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለደችው ማጂ እስከ 4 ዓመቷ ድረስ በአዲስ አበባ ነው ያደገችው፡፡ ያኔ ከአባቷ ጋር በፍቺ የተለያዩት እናቷ እሷንና ወንድሟን ይዘው ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሸሹ- በ1966 ዓ.ም የፈነዳው አብዮት ካስከተለው አደገኛ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ለማምለጥ፡፡ የመጀመርያ ደረጃና አብዛኛውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን  በናይሮቢ ከተከታተለች በኋላ ወደ ካናዳ የተሻገረችው ማጂ በሞንትርያል 12ኛ ክፍልን በቶሮንቶ ደግሞ 13ኛ ክፍልን  አጠናቀቀች፡፡ ከዚያም በለንደን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዌስተርን ኦንታርዮ ገባች- ቢዝነስና ስነፅሁፍ ለማጥናት፡፡ በእርግጥ ትምህርቱን ትወደው ነበር፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የክፍሏ ተማሪዎች በዎልስትሪት የኢንቨስትመንት ቢዝነስ ውስጥ ለመቀጠር ያለሙ እንደነበሩ አልጠፋትም፡፡ የእሷ ፍላጎት ግን ሌላ ነበር፡፡ ሆኖም ትምህርቷን አጠናቃ በቢዝነስ ድግሪዋን ያዘች፡፡ በፈረንሳይ ስነፅሁፍም የኦነርስ ፕሮግራም የተከታተለች ሲሆን ፕሮግራሙን እንደወደደችው ታስታውሳለች፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል የክፍል ጓደኛዋ የነበረው የቦስተን ማሳቹሴት የፊልም ተማሪ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ፊልም እየተመለከተ ስለፊልም ሲፅፍ እንደሚውል ስትሰማ ህልም ነገር ነበር የመሰላት፡፡ እንዲህ ዓይነት እድል ፈፅሞ ይገኛል ብላ አስባ አታውቅም፡፡ ልጆች ይሄን ሲያደርጉ ወላጆች ሳይቆጡ ዝም ይላሉ የሚለው ነገርም አልተዋጠላትም፡፡ የማታ ማታ ግን የሰማችው ሁሉ እውነት እንደሆነ ተገንዝባለች፡፡ ያኔ ነው ፊልሞች ላይ የመስራት እድል እንዳለ ለመጀመርያ ጊዜ ጭንቅላቷ ውስጥ የተተከለው፡፡

የድግሪ ትምህርቷን በካናዳ ካጠናቀቀች በኋላ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ለዓመት ያህል በጃፓን፣ በኔፓልና በታይላንድ እየተዟዟረች በየቦታው ትንሽ ትንሽ ሰራች፡፡ በጃፓን እንግሊዝኛ ያስተማረች ሲሆን በኔፓል ደግሞ በደን አስጎቢኝነት ሰርታለች፡፡ በምስራቃውያን ፍልስፍናና መንፈሳዊ አስተሳሰብ የተማረከችው ማጂበታይላንድና ኔፓል የቡዲስት ቅዱስ ስፍራዎችን ጎብኝታለች፡፡ ወደፊልም ዓለም የመሳቡ ሁለተኛ አጋጣሚ የተፈጠረው ያኔ ነበር፡፡ ኔፓል ከገባች በኋላ ባረፈችበት መንደር ውስጥ ፊልም ሲቀረፅ አጋጠማት፡፡ እሷም በካሜራዋ ቀረፃውን ማንሳት ጀመረች፡፡ The Little Buddah የተሰኘውን ፊልም ሲቀርፅ ከነበረው ዳይሬክተር ጋር እንዲህ በአጋጣሚ ተገናኘች፡፡ ዳይሬክተሩም በፊልሙ ቡድን ውስጥ ካሉት ተለማማጆች ጋር እንድትቀላቀል ጋበዛት፡፡ ማጂ ዓይኗን አላሸችም፡፡ የፊልም አሰራር ሂደት ምን እንደሚመስል ያወቀችው ይሄኔ ነው፡፡

ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በእናቷ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ መስራት ጀመረች፡፡ መጀመርያ የሰራችው በጂጂጋ የንግድና የጭነት ማመላለሻ ኩባንያ ውስጥ ነበር፡፡ ስራው በጎዴ ለሚሰራው ግድብ ከጂጂጋ ሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ አቅርቦቶችን ማመላለስ ነበር፡፡ የጭነት ማመላለሻ ኩባንያውን የመምራት ተመክሮዋ አስደናቂ ነበር፡፡ እናቷ የጭነት መኪኖቹ በመንገዱ እንዲያልፉ የሶማሌ የጎሳ አለቆችን አግባብተዋቸው ነበር፡፡ ማጂ መጀመርያ ላይ ስራዋን በቅጡ ለማከናወን ተቸግራ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ጓደኞች ማፍራት ቻለች፡፡ አንድ ቡድን በመመስረትም ስራውን ለማሰራት በቃች፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የእናቷን ሱፐርማርኬት መምራት ጀመረች፡፡ በሱፐርማርኬቱ ስራ ደስተኛ እንዳልነበረች የሚያውቀው ጓደኛዋ አንድርያስ እሸቴ ከደች የፊልም ሰሪ ቡድን ጋር አገናኛት፡፡ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ዶኩመንታሪ ፊልም ለመስራት የመጣ ሲሆን ፕሮዳክሽን ማናጀር እያፈላለገ ነበር፡፡ በዘርፉ ምንም የስራ ልምድ ባይኖራትም በከፍተኛ ጉጉት ዘላ ገባችበት፡፡ ማጂ ለስራው አዲስ እንደነበረች የደች ፊልም ሰሪዎች ለማወቅ ብዙ ጊዜ አላስፈለጋቸውም፡፡ ነገር ግን ጥንካሬዋንና የስራ ጉጉቷን ወደዱላት፡፡ የማታ ማታ ከደች ባልደረቦቿ በተደረገላት እገዛ ከፍተኛ ልምድ ገብይታ ስራዋን ለማጠናቀቅ ቻለች፡፡ ከዚያ በኋላማ ማጂ ውድ ሆነች፡፡ ከፍተኛ ተፈላጊነት አገኘች፡፡ ከውጭ መጥተው በፊልም ስራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች በፕሮዱዩሰርነት መስራቱን ተያያዘችው፡፡ በዚሁ ወቅት ለሲኤንኤን በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ትሰራ የነበረችው ማጂ ለረዥም ጊዜ በዘርፉ ብታገለግልም በኋላ ጋዜጠኝነት ዘላቂ እንጀራዋ እንዳልሆነ ወሰነች፡፡

በ1992 ዓ.ም ለፊልም ፕሮዱዩሰሮች በተዘጋጀ ውድድር አሸንፋ አባትየው የተሰኘውን የመጀመርያዋን ፊቸር ፊልም ለመስራት በቃች፡፡ የፊልሙ ታሪክ በ1960ዎቹ በቀይ ሽብር ዘመን የነበሩትን ምርጫዎችና ያስከተሉትን ውጤቶች ያሳያል፡፡ በ1993 ዓ.ም ራሷ በዳይሬክተርነትና በፕሮዱዩሰርነት የሰራችውን “The River that Divides” የተሰኘ ዶኩመንታሪ ፊልም ያወጣች ሲሆን ፊልሙ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከመኖርያቸው ያለፍላጎታቸው ተገደው ስለተፈናቀሉ ሴቶችና ህፃናት ታሪክ የሚናገር ነው፡፡ይሄ  ዶኩመንታሪ ፊልም የካናዳ ሰብዓዊ መብት ሽልማትን አሸንፏል፡፡

ማጂ የወደፊት ባለቤቷን ሞሪታኒያዊ/ማሊያዊ የፊልም ዳይሬክተሩን አብደርሃማኒ ሲሳኮን የተዋወቀችው በ2000 ዓ.ም የሮተርዳም ፊልም ፌስቲቫል ላይ ነበር፡፡ ከዚያም በፊልም ስራ ላይ አብረው ተሰማሩ፡፡ በኔዘርላንድ በቴሌቪዥን የካሜራ ባለሙያነት ይሰራ የነበረውን አብርሃም ሃይሌ ብሩን ያስተዋወቃት አብደርሃማኒ ነበር፡፡ ከዚያም ማጂ ይሄ ባለሙያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ አባትየው የተባለውን ፊልም እንዲቀርፅ አግባባችው፡፡ በእርግጥ የአብርሃም ወደኢትዮጵያ መመለስ ለኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ በተለይ ደግሞ ፊልም ለሚያጠኑ ወጣት ኢትዮጵያውያን እንደትልቅ በረከት የሚቆጠር ነበር፡፡ ማጂም ይሄ ባለሙያ ወደ አገሩ እንዲመለስ በማድረግ ረገድ በነበራት ሚና መደሰቷ አልቀረም፡፡ የማታ ማታ ማጂና አብደርሃማኒ በትዳር ተሳሰሩ፡፡ ከዚያም ማጂ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ እየተመላለሰች የባለቤቷንና የሌሎችን ፊልሞች ፕሮዱዩስ ማድረግ ቀጠለች፡፡ በቅርቡ  በ2000 ዓ.ም የጥዬ ህልም የሚል ስለአንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት ሴት የሚተርክ ፊልም የሰሩ ሲሆን ፊልሙ የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማሳየት የሚሰሩ ተከታታይ ፊልሞች አካል ነው፡፡

በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የፊልም እድገትን ለማስፋፋት በቁርጠኝነት የምትታትረው ማጂ በ2002 ዓ.ም ክረምት ላይ “Images That Matter” በሚል ርዕስ የፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ አዘጋጅታለች – ከዘላለም ፕሮዳክሽን ባለቤት ከዘላለም ወልደማርያም ጋር በመተባበር፡፡ ፌስቲቫሉ ልማትን ለማስፋፋት ፊልምን እንደግልና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ልማት መሳሪያ መጠቀምን የማበረታታት ዓላማን ያነገበ ነበር፡፡ ከ130 በላይ ለሆኑ ወጣቶች ዎርክሾፕና ስልጠና በተሰጠበት በዚህ ፌስቲቫል ላይ በ25 የምስራቅ አፍሪካ ወጣት የፊልም ባለሙያዎች መካከል ውድድር ተካሂዷል፡፡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ 100 ፊልሞችም ለተመልካች ቀርበዋል፡፡ ከፌስቲቫሉ ስኬቶች መካከል ደዘርት ፍላወር የተባለው ፊልም መቅረቡ ተጠቃሽ ነው፡፡ ፊልሙ ሶማሊያዊቷ ሞዴል ዋሪስ ዲሪስ የሴቶች ብልት ትልተላ ልማድ ከሆነበት አስከፊ ባህል እንዴት እንዳመለጠች የሚያሳይ ነው፡፡ ከፊልሙ እይታ በኋላ የሴቶች ብልት ትልተላ ስለሚያስከትለው አደጋና የአካል ጉዳት የተጋጋለና አነቃቂ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከመላው አፍሪካ የመጡ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ፌስቲቫሉ ይሄን አሰቃቂ ድርጊት በማጥፋት አስፈላጊነት ዙሪያ  ትኩረት መስጠት በመቻሉ አስደስቷታል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ወደፊትም እንደሚቀጥል ተስፋ የምታደርገው ማጂ የምስራቅ አፍሪካ ወጣቶች ሃሳባቸውን በፊልም የመግለፅ አቅማቸውን ለማዳበር ያግዛቸዋል ብላ ታስባለች፡፡

ዛሬ ነፍስ የሆኑ ታዳጊ ልጆች እናት የሆነችው ማጂ በሴኔጋል መኖርያ ቤት ሰርታ ለማጠናቀቅ እየተጋች ሲሆን ባለቤቷ ለቀጣይ ፊቸር ፊልሙ እንዲዘጋጅ እያገዘችው ነው፡፡ በልጅነቷ ዳሌ ከማውጣቷ በፊት የባሌት ዳንሰኛ እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ አሁን ስለሃይማኖታዊ ውዝዋዜ ለማጥናትና ለመፃፍ ፍላጎት አላት፡፡ ምናልባት ወደ ዩኒቨርስቲ ተመልሳም ፒኤችዲዋን ትሰራ ይሆናል፡፡ በታዳጊነቷ ስቃይን ከዓለም ላይ የማጥፋትና ዓለምን የተሻለች የመኖርያ ስፍራ የማድረግ ምኞት ነበራት፡፡ ይሄ ህልሟ አሁንም አብሮአት አለ፡፡ ማህትማ ጋንዲ ኬንያዊቷ የአካባቢ ጥበቃ ተሸላሚ ዋንጋሪ ማታይና የቺ ኮንግ መምህሯ ጀግናዎቼ ናቸው ትላለች፡፡ ድሮም አሁንም ስራቸውን በተከበረ መንገድ የሚያከናውኑ ተራ ሰዎች መነቃቃትን ይፈጥሩላታል፡፡ ችግርን እንደችግር አትቀበልም፡፡ ይልቁንም እንደመልካም አጋጣሚዎችና ጀብዱ እንደመፈፀም ትቆጥረዋለች፡፡ በእምነትና በትዕግስት መጠበቅ ከቻልን ህይወት መንገዱን ታሳየናለች፡፡ ለመስጠትና ለመካፈል እንዲሁም ከራሷ ጋር ሰላም ለመፍጠር  የጥሞናና ወደ ውስጥ የመመልከቻ ጊዜ ትወስዳለች፡፡

የወደፊት ህልሟ የበለጠ ሰላምና መግባባት እንዲፈጠር የራሷን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው፡፡ ብሄርተኛ አይደለችም፡፡ በዓለምአቀፍ የሰው ልጅ አንድነት ታምናለች ይሄንንም እምነቷን የማሳደግ ሃሳብ አላት፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአቸው የፈጠራ ክህሎት የታደሉ እንደሆኑ የምትናገረው ማጂእንደ እናትነታቸው ለፍቅር የተፈጠሩ ናቸውየተሻለች ዓለም እንድትፈጠርም ያልማሉ ባይ ናት፡፡ የአመራር ቦታዎችን ሁሉ ሴቶች ቢይዙት ኖሮ እንዳሁኑ ብዙ ጦርነቶች አይከሰቱም ነበር ትላለች፡፡ በተለይ ደግሞ የዓለም የውሃ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ያሳስባታል፡፡

ለወጣት ሴቶች የምትለግሰው ምክር “ውስጣችሁን በጥልቀት ተመልከቱ ልበሙሉና ትእግስተኛ ሁኑ ሁሉን ነገር ይቻላል ብላችሁ እመኑ፡፡ ቁርጠኝነት አይለያችሁ፡፡ ችግሮችና እንደ አበሳ ሳይሆን ራሳችሁን ለማሻሻል እንደተፈጠረ መልካም አጋጣሚ እና እንደጀብዱ ከቆጠራችሁት፣ ጨርሶ የተለየ ሃይልና ጉልበት ትታጠቃላችሁ፡፡ ምንም ነገር አያሸንፋችሁም፡፡ ከዛሬው ዘመን እጅግ የላቁ ፈተናዎችን ተጋፍጠው ስኬት ካስመዘገቡ ሴቶችና ከታሪክ ጀግንነትንና ቁርጠኝነትን ተማሩ፡፡ ሁኔታዎች የከፉ በሚመስሉበት ሁኔታም እንኳን ቢሆን (ለምሳሌ በቲምቡክቱ ማሊ በሴቶች ላይ እንደሚደርሰው ችግር) ተስፋችሁና ውስጣዊ ፈገግታችሁ ይብራ፣ ለሽንፈት እጅ አትስጡ”


ዋና የመረጃ ምንጮች
   ሰኔ 2004 ዓ.ም ከማጂ- ዳ አብዲ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ሜሪ ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>