Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሂሩት በፈቃዱ ወልደሚካኤል

Hirut Befecadu

ዋና ዋና ስኬቶች:
የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ ኮንፈረንስ በቤጂንግ በሚካሄድበት ወቅት፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ውስጥ የሴቶች ክፍል አቋቁማለች። የአፍሪካ የተግባር አቋም (African Platform for Action) የተሰኘውን ሰነድ ለማዘጋጀትና በቤጂንግ ጉባኤ 10ሺ የሚጠጉ የአፍሪካ ሴት ልዑካን ለማሳተፍ አስተባብራለች። አአድ በመላ አፍሪካና በተቀረው አለም ተአማኒነትን እንዲያገኝ ለ17 አመታት የመረጃ አገልግሎት ሃላፊ ሆና ሰርታለች። በሴራሊዮን በተሰማራው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል፣ ለስድስት አመታት ቃል አቀባይና የፖሊሲ አማካሪ ሆና አገልግላለች።
ወቅታዊ ሁኔታ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ከተባበሩት መንግስታት በጡረታ የወጣች የማህበረሰብ በጎ ፈቃደኛ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: ታህሳስ 1934 ዓ.ም.
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሳንፎርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት፣ አዲስ አባባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አስመራ (9ኛ እና 10ኛ ክፍል)፤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት (ኮከበ ፅባህ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል – በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ምሩቃን ከነበሩት ሁለት ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ)
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
በሶሻልና በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ)፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ (ከዩኒቨርስቲ ኮሌጅነት ወደ ዩኒቨርስቲነት እንዲያድግ ከተደረገ በኋላ፣ ከመጀመሪያዎቹ ምሩቃን መካከል አንዷ)
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
በዓለማቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ)፣ ፍሎረንስ ዩኒቨርስቲ፣ ጣልያን
ዋና የስራ ዘርፍ
ዓለማቀፍ ግንኙነት
የሕይወት ታሪክ
የአፍሪካ ህብረት፣ ከሃምሳ አመት ገደማ በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በሚል ስያሜ ሲመሰረት፣ ደፋ ቀና ብለው እግሩን እንዲተክል ከደከሙለት ቀደምት ሰራተኞቹ መካከል አንዷ ሂሩት በፈቃዱ ነች። ለ34 አመት በዘለቀው የስራ ዘመኗ በርካታ የሃላፊነት ቦታዎችን ብትይዝም፣ በስፋት የምትታወቀው ግን አአድን ከተቀረው አለም ጋር በሚያስተዋውቅና በሚያስተሳስር የመረጃ ክፍል ሃላፊነቷ ነው። ከዚህ በኋላ ነው፣ በድርጅቱ ውስጥ የሴቶች ክፍል እንድታቋቁም ብቻ ሳይሆን እንድትመራውም ጭምር የተሾመችው። ከመላ አፍሪካ በተሰባሰበ የሴቶች ሃሳብ መነሻነት፣ በ1987 ዓ.ም በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ዓለማቀፍ ጉባኤ የቀረበው ‘የአፍሪካ የተግባር አቋም’ የተሰኘ ሰነድ ሲዘጋጅ ዋና አስተባባሪ ሆና የሰራችውም ሂሩት ናት።

የበኩር ልጃቸው ሂሩትን ጨምሮ ስድስት ልጆች ያፈሩት ወላጆቿ፤ የምዕራቡን አለም ባህል በወጉ የሚያውቁና በአውሮፓ የኖሩ ናቸው። በጀርመን የተማሩት አባቷ፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል። እናቷም የተማሩት እዚያው እንግሊዝ ነው። የአባቷ ሥራ ለሰከነ ኑሮ የሚያመች አልነበረም። አገረ ገዢ ሆነው ሲሾሙ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ዋና ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ፣ ከዚያም ዲፕሎማትና አምባሳደር እንዲሆኑ ሲመረጡ፣ ከከተማ ከተማ፣ ከአገር አገር ዞረዋል። ሂሩትም በልጅነት እድሜዋ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ እየሄደች የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን አዳርሳለች። አንዳንዴ ግን ከወላጆቿ ጋር አብራ መጓዝ አትችልም ነበር። የአመቱን ትምህርት እንዳታቋርጥ ወይም ወላጆቿ እስኪመለሱ ድረስ፣ ከአክስቷ ጋር እየኖረች ትማራለች። ነገር ግን፣ ትምህርት የምታገኘው ከትምህርት ቤት ብቻ አልነበረም። በህይወትዋ ውስጥ በአርአያነታቸው ጎልተው ከሚታዩዋት ከአባቷ እንዲሁም በእናቷ ወገን ከሴት አያቷ ቀፀላወርቅ ቱሉ ብዙ ተምራለች። ዝርክርክነትን ቀርቶ ትንሽ ቸልተኝነትን እንኳን  የማይታገሱት አባቷ፣ ከላይ እስከታች እንደሙሽራ መሽቀርቀር ይወዱ ነበሩ። ሽክ ባለው አለባበሳቸው ላይ፣ ስልጣኔ ያልተለየው ጨዋ አቀራረባቸው እንዲሁም ለሥነስርዓት ያላቸው ጥንቃቄ ሲታከልበት ግርማ ሞገሳቸውን ያጎላዋል። ሂሩት ከአባቷ የወረሰችው፣ ለውበት ትኩረት የመስጠት ዝንባሌን ብቻ ሳይሆን አንደበ ርቱዕነትን የማድነቅ ልምድም ጭምር ነው። ለሴት አያቷ የነበራት ፍቅር ደግሞ ልዩ ነው። ብልህነታቸው፣ ወደር የለሽ ጥንካሬያቸውና ፅናታቸው ያስገርማታል። ምንም እንኳ የተጨናነቀ ባህላዊ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ቢሆኑም፤ አንገታቸውን ሳይደፉ ላመኑበት ሃሳብ በድፍረት የመሟገት ችሎታቸው ሂሩትን ያስደንቃታል። ልብ ብለው በእርጋታ የማዳመጥ ትእግስት የታደሉት አያቷ፤ በሃሳብና በተግባር ኮትኩተው የማሳደግ ጥበብ ነበራቸው። በወጣትነታቸው እንግሊዝ የተማረና በእድሜ የገፋ ሃኪም አግብተው ትዳር የመሰረቱት ቀፀላወርቅ፣ እንግሊዝኛ ብቻ የሚናገር ባለቤታቸውን ተከትለው ወደ ህንድ ከሄዱ በኋላ በርካታ ልጆችን ወልደውለታል። የነርስ ባለሙያ ሆነውም ከባለቤታቸው ጋር በህክምና አገልግሎቱ ሰርተዋል።

የአባቷና የአያቷ አርአያነት ባይለያትም ሂሩት በልጅነቷ ሲበዛ አይናፋር ነበረች። ድራማ ውስጥ በተዋናይነት እየሰራችና በመድረክ ውይይት በመሳተፍም ነው ከአይናፋርነት የተገላገለችው። በኋላማ፣ በዩኒቨርስቲ የክርክር ክበብ ውስጥ አባል ለመሆን በቃች። አይናፋርነቷን ታግላ ማሸነፏ አይገርምም። በባህሪዋ፣ አቅምን የሚገዳደሩ ፈተናዎችንና ከባባድ ስራዎችን በጣም ትወዳለች፤ በዚያው ልክ ደግሞ መሸነፍን ትጠላለች። የተማሪዎች ምክርቤት አባል ለመሆን በምርጫ መወዳደር እጅግ የሚያስደስታት፣ ከወንድ የክፍል ጓደኞቿ ጋር የምታደርገው ፉክክር ፈታኝ እንደሚሆን ስለምታውቅ ነበር። እናማ፣ ከሰው አይን ትሸሽ የነበረችው ሂሩት፣ የኋላ ኋላ የሰው አይን ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት መኮርኮር የዘወትር ስራዋ ሆነ። አእምሮዋን የሚፈታተኑ አስተያየቶችንና ጠንካራ መከራከሪያዎችን በአድናቆት ማስተናገድ የለመደችው ሂሩት፤ ከእያንዳንዱ ሰው ብዙ የምማረው ነገር አለ የሚል ስሜት ለማዳበር በቃች።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ እንደ አዲስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተብሎ ከተቋቋመ በኋላ፤ በመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎቹ ውስጥ የነበሩት ሴቶች ሰባት ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም አንዷ በሶሻልና በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘችው ሂሩት ናት። በኋላ ላይም ወደ ጣልያን ሄዳ፣ ከፍሎረንስ ዩኒቨርስቲ በዓለማቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪዋን አግኝታለች።

አዲስ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ውስጥ በ1955(56) ዓ.ም የተቀጠረችው ሂሩት፣ ለአንድ አመት እንደሰራች ነው ገና እግር እየተከለ ወደ ነበረው ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ስራ የቀየረችው። አህጉራዊ ሃላፊነትን የተሸከመና ብዙ የሚጠበቅበት ድርጅት ውስጥ፣ ለዚያውም በጨቅላነቱ ጊዜ፣ የስራ ወከባው ፋታ አይሰጥም። በአአድ ጊዚያዊ ፅህፈት ቤት የተቀጠረችው ሂሩት፤ በአዲስ አበባ የድርጅቱን ቢሮዎች የማዋቀር ስራ ላይ ተጠመደች። በመረጃና በፕሮቶኮል ክፍል ውስጥ፣ የመረጃ አገልግሎት ሃላፊ ሆና ተመደበች። የአፍሪካ አገራትን በማካተትና ሁሉንም በአንድነት በመወከል እንዲሰራ የተመሰረተው አዲስ አህጉራዊ ደርጅት፤ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የአህጉሪቱን ጉዞ የሚቀርፁ አዳዲስ እቅዶችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ነበር። የመረጃ አገልግሎት ሃላፊ ሆና የሰራችባቸው በርካታ አመታት፣ እጅጉን ፈታኝ እንደነበሩ አያጠራጥርም። በማራኪና በአሳማኝ አቀራረብ የአዲሱን ድርጅት አላማዎችና የጉዞ አቅጣጫዎቹን በሰፊው የማስተዋወቅ ሃላፊነት፣ ለማንም ሰው ቀላል ሊሆን አይችልም። ከአገር ውስጥና ከሌሎች አገራት የሚመጡ ዓለማቀፍ ጋዜጠኞች በጭራሽ እረፍት አይሰጡም፣ በጥያቄ ብዛት ልብ ያወልቃሉ። በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ተመራማሪዎችም ያለ ፋታ በየጊዜው መረጃ ይጠይቃሉ። ከጋዜጠኞችና ከተመራማሪዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ ሁሌም የሚያጠግብ መልስ መስጠት ይኖርባታል። መረጃና የሚያጠግብ መልስ ለመስጠት ግን፣ በቅድሚያ እሷ ራሷ ጠንቅቃና አብጠርጥራ ማወቅ ያስፈልጋታል። ዘወትር፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰነዶችንና መጻሕፍትን እያነበበች መዘጋጀት ነበረባት። እለት በእለት ያለ ማቋረጥ ጥናት ማካሄድን የሚጠይቅ ፈታኝ ስራ ነው። ደግነቱ፣ በሙያዋ እንድታድግ ብርታትና ድጋፍ የሚሆኑ ሰዎችን አላጣችም። ከፍተኛ ክብር ለመጎናፀፍ ከበቁት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ገዳሙ አብርሃ፣ ከስር ከስር እየተከታተለ ሙያውን እንድትካነው አግዟታል።

በአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ ከመጀመሪዎቹ ሴት የስራ ሃላፊዎች መካከል አንዷ የሆነችው ሂሩት፤ በኮንፈረንሶች፣ በአውደጥናቶችና በስብሰባዎች ላይ ለመካፈል አህጉሪቱን ከጫፍ ጫፍ ስትዞር፣ ያልረገጠችው አገር የለም ማለት ይቻላል። ሁሌም ታዲያ፤ በሄደችበት ቦታ ሁሉ የዘወትር ስራዋ አአድን የሚመለከቱ መረጃዎችን ማካፈል ነው፤ ድርጅቱ ለአፍሪካ እንዲሁም ለመላው አለም ትልቅ ፋይዳ የሚያስገኝ ዓለማቀፍ ተቋም መሆኑን ታስተዋውቃለች። አአድን በመወከል፣ ለመንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድኖችና ለሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች ገለፃ የማቅረብ ሃላፊነት የተሸከመችው ሂሩት፣ ገና ‘ሀ’ ብላ ስትጀምረው በፍርሃት የሚያብረከርክ ሆኖባት ነበር። ግን ፈተናዎችን መጋፈጥና ማሸነፍ እንጂ መሸሽ አታውቅም። በየትኛውም አገርና መድረክ፣ በአዳራሽም ሆነ በአደባባይ ውጤታማ ለመሆን የንግግርና የአቀራረብ ችሎታዋን ለማሳደግ ቆረጠች። ይህም ብቻ አይደለም። እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ብቻዋን ወደ ተለያዩ የውጭ አገራት የመጓዝ ልምድ አልነበራትም። መሄጃና መመለሻ ትራንስፖርት ማማረጥ፣ ማረፊያ ሆቴል ማፈላለግ፣ የጉዞ ጣጣዎችን ሁሉ መጨረስና ማሰናዳት ለሂሩት እንግዳ ነገር ነበር። በምትካፈልባቸው ጉባኤዎች ውስጥ፣ ብዙውን ጊዜ ከሷ ሌላ ሴት ተፈልጎ አይገኝም። ቢገኙም በጣም የሚቆጠሩ ናቸው። በየአገሩ እየሄደች በጉባኤ ላይ መሳተፍና መመለስ ብዙም ፈታኝ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፣ የአአድ መሪዎችን የመወከልና የልዑካን ቡድን የመምራት ሃላፊነት ተሰጥቷት ነው ወደ ጉባኤዎች የምትጓዘው። የሚያስፈራ ፈተና ነው። ነገር ግን፣ በተማሪነት እድሜዋ በተውኔትና በድራማ ስራዎች መሳተፏ ጠቀማት። ፍርሃቷን ከማስወገድ አልፋ፣ በሄደችበት ጉባኤ ሁሉ፣ ከሰዎች ጋር መገናኘትና መነጋገር፣ እውቀት መቅሰምና ሙያ ማዳበር አስደሳች እየሆነላት መጣ። ሂሩት በአአድ ውስጥ በነበራት የሃላፊነት ቦታ፣ የአፍሪካ መሪዎች አመታዊ ጉባኤ፣ የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ የተባበሩት መንግስታት መድረኮች ላይ ለመሳተፍ በየጊዜው ወደ በርካታ የአህጉሪቱ መዲናዎች ስትጓዝ፤ ከመላው አለም እየተሰባሰበ የሚንጋጋ የጋዜጠኛ መንጋ ይከተላታል። እንደ እሳት የሚፋጁ የአፍሪካ አጨቃጫቂ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሱ በጥያቄ ሲያጣድፏት በብልሃት ማስተናገድ ይጠበቅባታል።

በዚህ መሃል ነው፤ የድርጅቱን የመረጃ ክፍል በዋና ሃላፊነት የመምራት ህልሟ የተጨናገፈው። የያኔው የአአድ ዋና ጸሐፊ፣ አንድ ካሜሮናዊ የመረጃ ክፍሉን በሃላፊነት እንዲመራ ሲመድቡ፣ ለአመታት የገነባችውን ህንፃ ከእግሯ ስር የናዱባት ያህል ተሰማት። ዋና ጸሐፊው፣ ላንቺ ደህንነት በመጨነቅ ያሳለፍኩት ውሳኔ ነው ሲሏትም፣ ፈፅሞ ሊያሳምናት አልቻለም። በእርግጥ፣ ወቅቱ ስልጣን ይዞ የነበረው የደርግ ወታደራዊ መንግስት የሰዓት እላፊ ያወጀበት ጊዜ ነበር። የአአድ የመረጃ አገልግሎት ክፍልን በበላይነት መምራት ደግሞ፣ 24 ሰዓት መሉ ዝግጁ ሆኖ መገኘትን የሚጠይቅ ስራ ነው። በውድቅት ሌሊት ለስራ ጉዳይ ትፈለጊያለሽ ብትባል፣ ወዲያው ተነስታ ከመኖሪያ ቤት ወደ መስሪያ ቤት ልሂድ ብትል ለአደጋ እንደምትጋለጥ ዋና ጸሐፊው ሊያስረዷት ሞክረዋል። የስራ ሃላፊነቴን ሙሉ ለሙሉ መወጣት እችላለሁ በማለት ሂሩት አጥብቃ ብትከራከርም ዋና ጸሐፊው በጄ የሚሉ አልሆኑም። ሴት በመሆኔ ምክንያት በደል ደረሰብኝ የሚል  ስሜት ሸነቆጣት። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ እንዲህ አይነት የተጠቂነት ስሜት አጋጥሟት አያውቅም። ነገሩ ካለፈ በኋላ ስታስበው ግን የዋና ጸሐፊው  ውሳኔ፣ ምክንያት የለሽ  እንዳልሆነ ታይቷታል።

እናም በመረጃ ክፍል ለ17 አመታት ስትሰራ የቆየችው ሂሩት፣ በ1973(74) ዓ.ም. የአፍሪካ የእርስበርስ የቴክኒክ ትብብር ወደ ተባለው ክፍል ተዛወረች። ከዚህ ክፍል ዋና ዋና ሃላፊነቶች መካከል፣ ለምሁራን ፍልሰት መፍትሄ ማግኘት አንዱ ነው። ከአፍሪካ ወደ ምዕራብ አገራት የሚጎርፈው የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ አንዳች መላ ማበጀት የሂሩትና የባልደረቦቿ ሃላፊነት ሆነ። ከዚሁ ጎን ለጎን፣ በደቡብ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች ጋር የትብብር ግንኙነት ማጠናከርም የእነ ሂሩት ስራ ነበር። የቴክኒክ ትብብር ክፍል፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በርካታ ዘርፎችን የሚያካትት ትልቅ መዋቅር እየሆነ ሲመጣ፣ ሂሩት የአለማቀፍ ትብብር ዘርፍን በበላይነት እንድትመራ ተመደበች። በዚህ ሃላፊነቷም፣ ከተባበሩት መንግስታት፣ ከጋራ ብልፅግና አገራትና ከአሜሪካ መንግስታት ድርጅት፣ እንዲሁም ከኤስያ መንግስታት የጋራ ድርጅት፣ የካሪቢያን መንግስታትን ካካተው ድርጅትና ከሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት ማድረግ የእለት ተእለት ስራዋ ሆነ። በአለማቀፍ ድርጅቶች ዘንድ ተአማኒነትን እያተረፈች፣ በጋራ እቅዶች ላይ ያተኮረ የአጋርነት ስምምነትና ጠቅላላ የትብብር ግንኙነት ለመመስረት ጥረት ከማድረጓም በተጨማሪ፣ አአድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውና አህጉሪቱን የሚወክል ድምፅ መሆኑ በሰፊው እንዲታወቅ ሳታሰልስ ሰርታለች።

በቤጂንግ ከተማ በ1987 ዓ.ም የተካሄደው የሴቶች ጉዳይ ጉባኤ እየተቃረበ ሲመጣ፣ እንደገና የሂሩትን የሃላፊነት ስራ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ። በወቅቱ የአአድ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዶ/ር ሳሊም አህመድ ሳሊም፣ በቤጂንግ ጉባኤ የአፍሪካ ተሳትፎ ውጤታማ እንዲሆን ሂሩት በአስተባባሪነት እንድትመራና በአአድ ውስጥ የሴቶች ክፍል እንድታደራጅ ሃላፊነት ሰጧት። ለቤጂንግ ጉባኤ የሚቀርብ፣ የአፍሪካ ሴቶች የተግባር አቋም ለማዘጋጀት የአፍሪካ ሴቶችን ማስተባበር ስትጀምር ነው፤ መንፈስን የሚያነቃንቅ ድንቅ ስራ ውስጥ እንደገባች ያወቀችው። የአህጉሪቱን ሴቶች ከዳር ዳር፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ በየጓዳው ካሉት ሴቶች ጀምሮ፣ በየቤተመንግስቱ እስካሉት የአገር መሪ ሚስቶች ድረስ ለማስተባበር ስትሰራ፣ ሴቶች እጅግ አስደናቂ ሃይል እንዳላቸው በግላጭ የሚያሳይ ትምህርት አገኘች። ታዋቂዋ ሜሪ ታደሰ ከምትመራው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሴቶች ክፍል ጋር በአጋርነት መስራት ጀመረች። በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ ሆና ከተሾመችው ታደለች ኃይለሚካኤል ጋርም የትብብር ግንኙነት ፈጠረች። በአጭሩ፤የተሰጣትን ሃላፊነት ለመወጣት የሚጠቅሙ ሃሳቦችንና መረጃዎችን፣ ድጋፎችንና ትብብሮች ለማግኘት አህጉሪቱን አስሳለች ማለት ይቻላል። ያላነጋገረችው የሴቶች ማህበርና ቡድን የለም ቢባል ይቀላል። በሴቶች ጉዳይ ላይ ያተኮሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የማህበረሰብ ድርጅቶችን በስፋት አወያይታለች። ከዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ተጨምቆ የወጣውና የአህጉሪቱን የጋራ አቋም ያንፀባርቃል ተብሎ በሂሩት መሪነት የተዘጋጀው  ሰነድ፣ “የአፍሪካ የተግባር አቋም” “African Platform for Action” በሚል ርዕስ ለቤጂንጉ ጉባኤ ቀረበ። አድናቆትም ተችሮታል። ሂሩት የደከመችለት የአፍሪካ ሰነድ፣ በቤጂንግ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ “የቤጂንግ የተግባር እቅድ” ተብሎ ለፀደቀው አለማቀፍ ሰነድ ሁነኛ ግብአት በማበርከት ተጠቃሽ ሆኗል። ከመንግስት አካላትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከማህበረሰብ ድርጅቶችና ከተለያዩ ማህበራት የተውጣጡ፣ ወደ 10 ሺ የሚጠጉ አፍሪካዊያን ሴቶች በቤጂንጉ ጉባኤ ተሳትፈዋል። እንዲያ በሴቶች ጉዳይና በችግሮቻቸው ዙሪያ ትኩረት መሰጠቱ፣ ለአፍሪካ ሴቶች በአጠቃላይም በመላው አለም ለሚገኙ ሴቶች ሁሉ፣ ትልቅ ትርጉም ያለው የግስጋሴ እርምጃ ነው። ከተለያዩ አገራት የተሰባሰቡ ልዑካን ተቀላቅለው የተወያዩበትና ግንኙነት የመሰረቱበት፣ በጋራ አቋም ዙሪያ ጠንካራ ጥምረትና የእርስ በርስ ትስስር የተፈጠረበት የቤጂንግ ጉባኤ፣ ለሂሩት በህይወቷ የማይረሳ ተሞክሮ ሆኖ አለፈ።

ከ34 አመታት የስራ ዘመን በኋላ ከአአድ በጡረታ የወጣችው ሂሩት፤ በሴራሊዮን የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ውስጥ በመግባት የሃላፊነት ቦታ አገኘች። በሲቪል ጉዳዮች ክፍል ውስጥ በአስፈፃሚነት በመመደቧ፣ በሴራሊዮን የእርስበርስ ጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት፣ ፖሊስ ጣቢያዎችና ሌሎች መሰረታዊ የአገልግሎት ተቋማት እንደገና ተገንብተው ማህበረሰቡ ነፍስ እንዲዘራ ማገዝ የእለት ተእለት ስራዋ ሆነ። በ10 አመታት የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሰው እንዲያንሰራሩ ከመርዳት በተጨማሪ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ በመረጃ አገልግሎት ዘርፍ ከነበራት ልምድ በመነሳት፣ የሰላም አስከባሪው ኃይል ቃል አቀባይ እንድትሆን ተመድባ ሰርታለች። በመጨረሻም፣ በሴራሊዮን ከፍተኛ ጥፋት ባደረሰው በኤችአይቪ ኤድስ ጉዳይ የሰላም አስከባሪው ኃይል ዋና አዛዥ የፖሊሲ አማካሪ ሆነች። ገና ከጦርነት እፎይ ብላ ማገገም የጀመረችው አገር፣ ብዙም ሳትቆይ የኤድስ በሽታ አዲስ የጥፋት በትር ሆኖባት ነበር። ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱ በግልፅ በመታየቱም ነው፤ ሂሩት ሰላም አስከባሪው ኃይል በተሰማራባቸው አካባቢዎች፤ በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በሰፈሩት 18 ሺ ወታደሮች ዘንድ ኤድስን የመከላከል ዘመቻ እንድታካሂድ የተመደበችው።

በሴራሊዮን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪው ኃይል ከ6 ዓመታት በኋላ የስምሪት ጊዜውን ሲያጠናቅቅ፣ ሂሩት ከስራ ዓለም ለመሰናበትና ወደ አገሯ ለመመለስ ወሰነች። ግን ያለ ስራ ለመቀመጥ አላሰበችም። ለበርካታ አመታት ያካበተችውን እውቀትና ልምድ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቿ በተለይም ለወጣቶች ለማካፈል እያሰበች ወደ አገሯ መጣች። ያኔ ልጆቿ አድገዋል። በአሜሪካ ስራ ይዘው መኖር ጀምረዋል። እናም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰከነ ኑሮ ለማጣጣም ፈለገች። ከዘመድ ወዳጅ ጋር የምትጫወትበትና የምታወጋበት ሰፊ ጊዜ ከማግኘቷም በተጨማሪ፣ እንደ ሮታሪና ወሴክማ በመሳሰሉ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ አባልነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታበረክታለች። በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር በማድረግም ሃሳቧን ለሰዎች ታካፍላለች። በተለይ ለሴቶችና ለወጣት ልጃገረዶች የራሷን ተመክሮ በማካፈል፣ መንፈሳቸውን የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ንግግር ለማቅረብ የሚያስችል መድረክና ዝግጅት ካገኘች እንዲያልፋት አትፈልግም።

ሂሩት የዘመኑ ወጣቶችን ውስጣዊ ኃይልና በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን ስትመለከት፣ ልብ የሚያሞቅ የእርካታና የተስፋ ስሜት ይፈጠርባታል። ወጣት ሴቶች፣ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ትልልቅ ነገሮችን እያሳኩ  ነው። ብዙ ሴቶች በቢዝነስና በሌሎች መስኮች ስኬታማ ስራ ፈጣሪና መሪ እየወጣቸው ነው። የዛሬ ወላጆች፣ የገጠሮቹ ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ለማስተማር ባላቸው ቁርጠኝነት ታደንቃቸዋለች።

ለልጃገረዶችና ለወጣት ሴቶች የምትሰጠው ምክር፡ በራሳችሁ አቅምና ብቃት እምነት ይኑራችሁ፤ ወደ ኋላ አትበሉ፤ የማይቻልና የማይሳካ ነገር የለም። የምታልሙትንና የምትፈልጉትን ነገር መቀዳጀት ትችላላችሁ። ከስራ ስራ አታበላልጡ። እያንዳንዱ ስራ አስፈላጊ ነው፤ ልቅም ጥንቅቅ ተደርጎ መሰራት ይገባዋል። ሁሉም ስራና ሁሉም ተሳትፎ ዋጋ አለው። ከሰዎች ጋር ግንኙነት ፍጠሩ፤ ከእያንዳንዱ ሰውም የምትቀስሙት ትምህርት እንዳለ እወቁ። በዚያው መጠን ደግሞ፣ ሰውን የሚያንጓጥጥና የሚያጎሳቁል ጥፋተኛ ሲያጋጥማችሁ አይታችሁ እንዳላያችሁ አትሁኑ። በአደባባይ ዘግናኝ ድርጊት ሲፈፅም፣ በዝምታ አትለፉ። በማን አለብኝነት እንዲፈነጭ አትፈቀዱለት። ሃሳባችሁን ተናገሩ፤ ነገሬ ብሎ አይሰማችሁ ይሆናል። ግን ያ አይደለም ቁም ነገሩ። ጥፋት ሲፈፅም ማየታችሁን ንገሩት። ውጤት ሊመጣ የሚችለውም በዚሁ መንገድ ነው።

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከሂሩት በፈቃዱ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ መጋቢት 2004 ዓ.ም
አጥኚ
ሜሪ-ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>