Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሂሩት ወልደማርያም

AlmazDj

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በሥነ ልሳን ፈጣን የተባባሪ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኘች፣ የመጀመርያዋ ሴት የአካዳሚ ጉዳዮች ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ከዚያም የውጭ ግንኙነቶችና ትብብር ክፍል የመጀመርያዋ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ከ20 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች የታተሙላት፣ በስነምህዳር ጥበቃ የምትሳተፍ
ወቅታዊ ሁኔታ
የትውልድ ቦታ: ደብረማርቆስ፣ ጎጃም፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1968
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ጣይቱ ብጡል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ውስጥ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የተሾመች የመጀመርያዋ ሴት ናት፡፡ መጀመርያ ላይ የአካዳሚ ጉዳዮች ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን፣ ከዚያም በውጭ ግንኙነቶችና ትብብር ክፍል በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግላለች፡፡  ከ20 በላይ የአካዳሚ ፅሁፎች የታተሙላት ዶ/ር ሂሩት፤ በአካዳሚ ሙያዋ ባስመዘገበችው የላቀ ውጤት ትታወቃለች፡፡ በዜግነቷም፣ የስነምህዳር ጥበቃ ላይ ትሳተፋለች፡፡

ታሪኳ እነሆ፡
የተወለድኩት እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም በጎጃም ደብረማርቆስ ነው፡፡  በቀድሞው የሃረር መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ምሩቅ የነበረው አባቴ፤ በጎጃም በመምህርነት ተመድቦ አስተምሯል፡፡ እናቴን አግኝቶ ያገባትም  እዚያ ነው፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ ፤ እኔ የበኩር ልጅ ነኝ፡፡ ዕድሜዬ አራት ዓመት ሲሆን አባቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዲግሪ መርሀግብር የመማር እድል አገኘና ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ እኔም የአራተኛ ዓመት ልደቴን ካከበርኩ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው አንደኛ ክፍል ገባሁት፡፡ ከዚያ በፊት እቤት ውስጥ ማንበብና መፃፍ ተምሬ ነበር፡፡ እንደ አባቴ አስተማሪ የነበረው የምወደው አጎቴ፣ ከፅሁፍና ከንባብ ጋር አስተዋውቆኛ፡፡ ተጀምሮ እስኪያልቅ ትምህርቴን በሙሉ የተከታተልኩት በመንግስት ትምህርት ቤት ነው – መጀመርያ በጣይቱ ብጡል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም በእንጦጦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት። የመጀመርያና ሁለተኛ ድግሪዬን በሥነ ልሳን (ሳይንሳዊ የቋንቋዎች ጥናት) የሰራሁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው። እናም እዚያው ዩኒቨርስቲ ተቀጥሬ በስነልሳን የትምህርት ክፍል አስተምሬአለሁ፡፡ ዶክትሬቴን የሰራሁት በጀርመን ኮሎኝ ዩኒቨርስቲ፣ በአፍሪካ ጥናቶች ተቋም ነው፡፡ የተከታተልኩት ፕሮግራም በኮሎኝና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትብብር የተዘጋጀ “ሳንድዊች” ፕሮግራም ነበር።

እንደ አብዛኞቹ ህፃናት፣ ለእኔም የመጀመርያው አርአያዬ አባቴ ነው፡፡ ገና በህፃንነቴ የነበረኝ ምኞትም እንደ አባቴ አስተማሪ መሆን ነበር፡፡ እቤት ውስጥ አባቴ የሚያደርገውን እያየሁ፣ አስተማሪ ለመምሰል ስጣጣር ትዝ ይለኛል፡፡ አባቴ የሚያስተምረው ነገር ሲዘጋጅና  የፈተና ወረቀት ሲያርም ከአጠገቡ አልጠፋም ነበር – ሁሉን ነገር አጠገቡ ቁጭ ብዬ እመለከታለሁ፡፡ በእደም ከፍ ስልማ የተማሪዎችን ውጤት በመደመር አግዘው ጀመር (ፈተና አርሜ ግን አላውቅም)። ቤተሰባችን ወዲህ ወዲያ የመፈናፈኛ ጊዜ አይሰጥም። እያነበብን ወይም እየፃፍን አልያም እያጠናን መሆናችንን አባቴ ሁልጊዜ ይከታተለናል። መዝናኛ የሚባል ነገር እምብዛም አልነበረም፡፡ ቴሌቪዥን እንኳ ከተወሰነች ሰዓት በላይ ማየት አንችልም፡፡ ከጓደኞቻችን ጋር ልንውል ቀርቶ ዘመድ ጥየቃም ቢሆን እንድንወጣ አይፈቀድልንም፡፡ ከግቢ ውልፊት ማለት የለም። ከኛ የሚጠበቀው ትምህርታችን ላይ አተኩረን ማጥናት ብቻ ነው፡፡ ቤታችን ቤተመፃህፍት ነበር ማለት ይቻላል። ጓደኞቻችሁ መፃሕፍት ናቸው እንባል ነበር። ቤተሰቡ በትምህርት ጉዳይ እጅጉን ከመጠመዱ የተነሳ፣ የቤት እመቤቷ እናቴ ሳትቀር ትምህርት ቤት ለመግባት ተገዳለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ በአንድ ድርጅት ውስጥ በስልክ ኦፕሬተርነት ተቀጥራ ነበር።
በአጭሩ፣ ማህበራዊ ህይወት የሚባል ነገር ሳላውቅ ወይም ብዙም ቀርቤ ሳላየው ነው ነፍስ ያወቅሁት፡፡ ከማህበራዊ ህይወት ይልቅ ስራዬ ላይ የበለጠ ማተኮሬም፣ ከአስተዳደጌ የመነጨ ባህርይ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ደግሞ፣ ቤተሰቤ በትምህርት ላይ ብቻ የሙጢኝ በማለቱ ሳቢያ  የመጣ ጉድለት ነው፡፡

በስነልሳን የመጀመሪያ ድግሪዬን እንዳገኘሁ፣ ሀ ብዬ ስራ የተቀጠርኩት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ነበር፡፡ በሚኒስቴትር መስሪያ ቤቱ ስር በነበረው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ለአንድ ዓመት በጀማሪ ኤክስፐርትነት ሰርቻለሁ፡፡ የማስተርስ ድግሪ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ ደግሞ፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስነልሳን ትምህርት ክፍል በአስተማሪነት ተቀጠርኩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለዩኒቨርስቲው እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ወዲህና ወዲያ ሳልል ስራዬ ላይ ረግቼ የቆየሁበት አንዱ ምክንያት፣ በህፃንነቴ ወቅት ቤተሰቤ በውስጤ ያሳደረው የትምህርት ዝንባሌ፣ የአካዳሚ (የምሁር) ሙያን እንደ ህይወቴ ጥሪ እንድቆጥረው ስላደረገኝ ነው ማለት ይቻላል።

ፈጣሪዬ ምስጋና ይግባውና በርካታ የምኮራባቸው ስኬቶች አሉኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ምሁር ጥሩ ግስጋሴ አሳይቻለሁ –  ያውም በጣም ፈጣን ግስጋሴ፡፡ የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠባቸው ቋንቋዎችና ባህሎች ልዩ ትኩረት የምሰጥ የሥነ ልሳን ባለሙያ እንደመሆኔ፤ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሬ ጥናትና ምርምር አድርጌአለሁ – ብዙውን ጊዜ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፍኩ፡፡ የመስክ ስራ የት ያልወሰደኝ ቦታ አለ! በደቡብ ወደ ሱርማ ወረዳና ወደ አባያ ደሴት፤ በሰሜን ወደ ኩናማና ወደ ኢሮብን የመሳሰሉ ስፍራዎች ወስዶኛል፡፡ በብዙዎቹ ስፍራዎች አስቸጋሪ አቀበትና ቁልቁለት ለበርካታ ሰዓታት እየወጣሁና እየወረድኩ መጓዝ ነበረብኝ፡፡ የኤሌክትሪክ መብራትና የሆቴል አልገልግሎት ባልደረሰባቸው እልም ያሉ ገጠራማ አካባቢዎችም አድሬያለሁ፡፡ በርካታ የጥናትና የምርምር ውጤቶቼን ፅፌ አሳትሜያለሁ፤ በመላው ዓለም ከ20 በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችም ላይ ተሳትፌአለሁ። የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጠኝ በተፋጠነ እድገት ነው። ምክንያቱም ዕድገቱን ለማግኘት ከሚያስፈልጉ የጥናትና የምርምር ፅሁፎች፣ እጥፍ ያህል አዘጋጅቼ ማሳተም በመቻሌ ነው፡፡ እስካሁን ከ20 በላይ የጥናት ፅሁፎች በስሜ የተመዘቡልኝ ሲሆን፣ አብዛኞቹም በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ታትመውልኛል፡፡ በሂደት ላይ ያሉ የምርምር ፕሮጀክቶችም አሉኝ፡፡ አንዳንዶቹን ከዓለም አቀፍ የሙያ ባልደረቦቼ ጋር በመተባበር ነው የምሰራቸው፡፡ የመፅሃፍ ዝግጅትና ህትመት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ፣ ብዙዎቹ  በቅርቡ የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚ ጉዳዮች አስተዳደር ውስጥ ሰርቻለሁ – ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ተመድቤ። የሥነ ልሳን ትምህርት ክፍል የመጀመርያዋ ሴት ሃላፊ ነበርኩ፡፡  የመጀመርያዋ ሴት  የአካዳሚ ጉዳዮች ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን አገልግያለሁ። ከሁለት ዓመት ወዲህም የመጀመርያዋ ሴት  የውጭ ግንኙነቶችና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡ በዕውቀትና በሙያ ኮትኩቶ ያበለፀገኝን ተቋም ማገልገሌ ብቻ አይደለም የሚያረካኝ። ለወጣት ሴት ምሁራን ፈርቀዳጅና አርአያ የመሆን እድል ማግኘትም እጅጉን ያረካል።
በማህበረሰብ አገልግሎት ውስጥም እሳተፋለሁ። ለምሳሌ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከሥነ ምህዳርና በአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክቶች ላይ እሰራለሁ፡፡ በእነዚህን ፕሮጀክቶች የማከናውነው ከቤተሰቦቼና ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ባለትዳር ነኝ፤ ነፍስ የሆኑ ሦስት ልጆችንም ባርኮ ሰጥቶኛል። ከሚወደኝና ከሚረዳኝ ቤተሰቤ ከወላጆቼ የተትረፈረፈ ፍቅር ይፈስልኛል። ገና ወጣት ነኝ፤ ጤናና ብርታት ያደለኝ። ከፊቴ ገና ብዙ መልካም ነገር እንደሚጠብቀኝ አምናለሁ። ከዚህ በላይ ምን እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ!

በህይወቴና በሙያዬ ጉዞ ሁሉ፣ በጎ በጎ ሰዎችን በማግኘት በኩል በጣም ዕድለኛ ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ሰው ይዋጣልኛል። ከትምህርት ቤት ህይወቴ እስከ ዩኒቨርስቲ ስራዬ የገጠሙኝ አስተማሪችና  የስራ ባልደረቦች፣  አይዞሽ የሚሉኝና የሚያደፋፍሩኝ ነበሩ። እኒህ ምሳሌ የሆኑኝ ቀና ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ዛሬ ወዳለሁበት ደረጃ ለመገስገስ ባልቻልኩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ ነገሮች አልጋ ባልጋ ነበሩ ማለት አይደለም፤ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ፡፡

ትልቁ ፈተናና መሰናክል ደግሞ፣ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የአመራር ቦታ መውጣቸው፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር ክፉኛ በጥርጣሬ አይን መታየቱ ነው። በመንግስት መስሪያ ቤቶች አካባቢ የሚታየው ጥርጣሬ ብዙም አይገርምም። ካለፈው ዘመን የወረስነው የፊውዳል ስርዓት ቅሪትና በአባወራ ፈላጭ ቆራጭነት የተቃኘው የኑሮ ዘይቤ በህብረተሰባችን ውስጥ ስር የሰደደ ነውና፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም እንደተጣበቀ መዝለቁ ግን ያሳዝናል። ይሄን የምለው ዝም ብዬ አይደለም። በተቀረው ዓለም በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በምሁርነትም ሆነ በሃላፊነት ደረጃ ሴቶች ቁልፍ ቦታ ይይዛሉ፤ አንዳንዴም አብዛኞቹን ቦታዎች ተቆጣጥረው ይታያሉ። ከኢትዮጵያ ውጭ ትምህርታችንን የተከታተልን ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሴት መምህራን ድርሻ ቀላል አይደለም። በበርካታዎቹ ተቋማትም ብዙዎቹ መምህራን ሴቶች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ፣ የአስተዳደር ሃላፊነቱን ሴቶች በበላይነት ይዘውታል። በእኛ አገር የሚታየው እውነታ ግን፣ የተገላቢጦሽ ነው። የውጭው አለም ኖረውና አይተው የመጡ ምሁራን ሳይቀሩ አንዷ ባልደረባቸው ከአጠገባቸው ተነስታ፣ በሃላፊነት መስላሉ ላይ አንድ ወይም ሁለት ደረጃ ስትወጣ፣  እንደ አንዳች ነገር ያደርጋቸዋል። በሃላፊነት ላይ የተቀመጥሽው ሴት መሆንሽን ሲያዩ፣ ደካማና ብቃት እንደሌለሽ አድርገው ይቆጥሩሻል። “እስቲ እናያለን፣ እስቲ ጉዷን እንልያት” ብለው እንኳ እድል አይሰጡሽም። ቅንጣት ስህተት ብትፈፅሚ፣ ጉድሽ ነው። ነገር ግን፣ እኔ ለመሆን እንደምሞክረው ያለማወላወል በግልፅ አካፋን አካፋ የምትይ ጠንካራ ሴት ከሆንሽ፣ አንቺ ላይ የሚዘንብብሽ የጥቃት ውርጅብኝ ጨርሶ አያባራም። ተከብሮ የቆየ የምሁርነት ስምሽና የሙያ ታሪክሽ ከያለበት ተፈልፍሎ ለግምገማ እየወጣ፤ ክፋትና ጥላቻ በተሞላበት መሰሪነት ይብጠለጠላል።

ሰርተሽ ፈግተሽ ያገኘሻቸው እድገቶችና ሃላፊነቶች ሁሉ፣ በገልፅ መስፈትና መመሪያ የሚፈፀሙ የሙያ እድገቶችና ሃላፊነቶች ጭምር፣ በጥርጣሬ አይን እንዲታዩ አሉባልታ እየተነዛ ተንኮል ይሸረብብሻል። አንዳንዴ፣ ጥቃቱ በሴትነሽ ላይ ያነጣጥርና፣ ከወንዶች ጋር ከስራ ባልደረቦች ጋር ያለሽ ግንኙነት ጭምር የቡና ቁርስ ይሆናል። ምናለፋሽ! ጥቃቱ የማይገባበት የለም። የጓዳና የአደባባይ፣ የስራና የግል ህይወትን አይለይም። እንዲህ አይነቱን ጥቃት ከድርሻዬ በላይ አስናግጃለሁ። ስቃይ ነው ብለው ይሻላል።

ደግነቱ፣ በእንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቶች የምረታ ሰው አይደለሁም፡፡ ችግርና ፈተናን ፊት ለፊት ተጋፍጬ በራሴ ጥረት ራሴን ሰው ያደረግኩ ሴት ነኝ። ከእያንዳንዷ ጥቃት ውስጥ ጥንካሬን ተጎናፅፌ እወጣለሁ እንጂ አልዳከምም፡፡ ይህን የሰብዕናዬ ዋልታና ማገር የሚያፈርስ ነገር ጨርሶ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

“ውሾቹም መጮሃቸውን አላቋረጡም፤ ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል” የምትለዋ አባባል ከአንደበቱ የማትጠፋ አንድ ጥሩ ወዳጄ አለ፡፡ የእኔ የምወዳት ግን እንቁራሪቶች ተራራ ለመውጣት ስላ ደረጉት ውድድር የምትተርክ ተረት ነች፡፡ ተወዳዳሪዎቹ እንቁራሪቶች በብዙ ተመልካች ተከበዋል፡፡ እያንዳንዷ እንቁራሪት ተራራውን ለመውጣት ስትታገል፣ ተመልካቹ ጩኸቱን ያቀልጠዋል፤ ትችትና ስድብ ያዥጎደጉዳል። “ወደኋላ ቀረሽ፤ ጥለውሽ ሄዱ” እያለ ተመልካቹ ሲያንባርቅ፤ አንዷ እንቁራሪት “እኔ ነኝ ወደ ኋላ የቀረሁት” ብላ ውድድሩን አቋርጣ ወጣች። የተመልካቾቹ ጩኸት ግን አላቋረጠም፤ “ወደ ኋላ ቀረሽ” ማለታቸውን ቀጠወለዋል። በርካታ እንቁራሪቶች፤ “ውራ ሆነሻል የሚሉት እኔን ነው” በሚል ግምት ተስፋ ቆርጠው ውድድሩን ሲያቋርጡ፤ አንዷ ብቻ ቀረች፡፡ የማታ ማታም ውድድሩን አጠናቅቃ አሸናፊ ሆነች፡፡ ለካ እንቁራሪቷ ጆሮዋ አይሰማም። የተመልካቹን ተስፋ አስቆራጭ ጩኸት ስለማትሰማ ነው፤ ውድድሩን ያላቋረጠችው። በጩኸትና በመሰሪ ተግባራቸው ሊያሰናክሏቸሁ ለሚሞክሩ ክፉ ሰዎች  ጆሮ መስጠት አያስፈልግም ብዬ አስባለሁ።

የእያንዳንዱ ሰው ህይወት በሆነ መንገድ መለያየቱ አይቀርም። ስለዚህ፣ ለኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች የህይወት መመሪያ እንዲሆን ከኔ ህይወት ውስጥ ተቀድቶ ሊወሰድ የሚችል ነገር የለም፡፡ ግን ጥቂት ዘለላ ምክሮችን አላጣም፡፡ ምንም ነገር ስትሰሩ፣ በፅኑ እምነት፣ በልባዊ ፍቅርና በወኔ ይሁን፡፡ በየቦታው በሚያጋጥማችሁ ነገር ተስፋ ቆርጣችሁ ከጉዟችሁ አታፈግፍጉ። ለችግርና ለፈተና ተሸንፋችሁ የህይወት ግባችሁንና ተልእኮአችሁን አትበርዙ፡፡

ያለማቋረጥ አዳዲስ ዘዴዎችን፣ ብልሃቶችንና የህይወት ክህሎቶችን ተማሩ፡፡ ፅኑ እምነት ይኑራችሁ። ውድቀትን እንደ ዓለም መጨረሻ አትቁጠሩት፤ ይልቁንም ከስህተታችሁ ለመማርና ጠንካራ ሰው ሆኖ ለመውጣት ተጠቀሙበት፡፡

ምኞቴ ብልፅግናና እድገት እንዲፈጠር ነው – በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎች ሰብአዊ ልማትም ጭምር። የዜጎች ሰብአዊ ልማት ስል፤ ብዙ ዲግሪና ሰርተፊኬት የያዙ ሰዎችን ማፍራት ብቻ አይደለም። አንዱ ለሌላው፤ እንዲሁም በአጠቃላይ ለህይወት በጎ አመለካከት ያላቸውን ማፍራት ማለቴ ነው፡፡ ይህች አገር፣ አንዱ የሌላውን በጎ ነገር ለማየትና እዚያ በጎነት ላይም እየገነባ ለማደግ የሚጣጣር ሰው የሞላባት አገር ተብላ ስትጠራ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ እውን ይሆን ዘንድ አንድዬ ይርዳን!

 


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ላቀረብነው መጠይቅ በምላሹ በወ/ሮ ሂሩት ወልደማርያም የተፃፈ
አጥኚ
ወደር

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>