Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

መዓዛ ከበደ መካ

Meaza-Kebede

ዋና ዋና ስኬቶች:
በተለይ ለሴቶችና ለህፃናት የውሃ እና የአካባቢ ንፅህና አገልግሎትን የማሻሻል ጥልቅ ልባዊ ፍቅር ሰንቃ፣ በከፍተኛ ሙያዊ ቁርጠኝነት ሰርታለች።  በቤተመፃህፍት ባለሙያነቷ፣ በወጣቱ ዘንድ የማንበብ ፍላጎትና ፍቅርን ለማስረፅ  ትተጋለች።
ወቅታዊ ሁኔታ በተባበሩት መንግስታት ዓለምአቀፍ የህፃናት ፈንድ /ዩኒሴፍ/ የውሃ፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ዘርፍ፣ የአቅም ግንባታ ልዩ ባለሙያ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣
የትውልድ ዘመን: ታህሳስ 9 1957 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አጋዝያን ት/ቤት እና ቅዱስ ዮሐንስ ት/ቤት፣አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ባይብል አካዳሚ፣ ናዝሬት (የአሁኑ አዳማ)
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ዲፕሎማ፣ በላይብረሪ ሳይንስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ የመጀመርያ ድግሪ፣ /ቢኤ/ ፣ በማህበረሰብ ጥናት እና በማህበረሰብ አስተዳደር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ሁለተኛ ድግሪ፣ /ኤምኤ/ በሴቶችና በልማት ላይ ያተኮረ የሥነ ልማት ጥናቶች፣ የማሕበረሰብ ጥናቶች ተቋም፣ ኔዘርላንድስ
ዋና የስራ ዘርፍ
ዓለም አቀፍ ልማት
የሕይወት ታሪክ
በስርዓተ- ጾታ እና በልማት ላይ በማተኮር በዘርፉ የካበተ ልምድ  ያላት መዓዛ ከበደ፤  በአሁኑ ወቅት  በዩኒሴፍ የውሃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና  /WASH/ ዘርፍ ውስጥ  በአቅም ግንባታ ልዩ ባለሙያነት እየሰራች ትገኛለች። በኢትዮጵያ  በ WASH ዘርፍ የሚሰሩ የፌደራልና የክልል ቢሮዎችን አቅም ለመገንባት የተቀረፀውን  ፕሮጀክት የምትመራው መዓዛ፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ ለህብረተሰቡ  የተሻለ የውሃ፣ የሳኒቴሽንና የሃይጂን አገልግሎት ማቅረብ መሆኑን ትናገራለች። ይሄንንም ለማሳካት ዩኒሴፍ  የፖሊሲ ጉዳዮች ጨምሮ የሚሰጠውን  የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍም ትመራለች።

በ1958/59 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደችው መዓዛ ፤መካከለኛ ገቢ በነበረው ሰፊ ቤተሰብ  ውስጥ ነው ያደገችው – ከአምስት እህቶቿና ከበርካታ የዘመድ ልጆች ጋር በመሆን። መሃንዲስ  አባቷ የቤተሰቡን የዕለት ጉርስ ሲያቀርቡ፤ እናቷ ደግሞ ቤተሰቡንና የቤት ውስጥ ጉዳዮችን ጥንቅቅ አድርገው  ይመሩ ነበር። በትምህርት ጉዳይ ዋዛና ፈዛዛ የማያውቁት አባቷ፤ ትምህርትና ጥናትን በተመለከተ በሁሉም ልጆቻቸው  ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ጥብቅ ደንብና ሥርዓት ነበራቸው። የአባቷን  የማያፈናፍን ህግ የሚያለዝበው  የእናቷ የርህሩነትና የቸርነት ባህርይ ነው። የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ የጨረሰችው መዓዛ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ናዝሬት ተልካ የአዳሪ ት/ቤት በነበረው  የባይብል አካዳሚ አጠናቃለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታም  ላይብረሪ ሳይንስ በማጥናት  በ1976 ዓ.ም በዲፕሎም ተመርቃለች። (ያኔ በላይብረሪ ሳይንስ የድግሪ ፕሮግራም አልተጀመረም ነበር)

በጋለ ልባዊ ፍቅር የምትተጋበትን የሙያ መንገድ ወዲያው አልነበረም ያገኘችው። ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቀች በያኔው የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ሚኒስቴር ተቀጠረች። በደቡብ ምዕራባዊ ኢትዮጵያ በምትገኘው የጂማ ከተማ፣ የህዝብ ቤተመፃህፍት ሃላፊ ሆና ለሁለት ዓመት የሰራችው መዓዛ፤ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ በሥነጥበብ ት/ቤት (አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር ነው) በቤተመፃህፍት ባለሙያነት ለስምንት ዓመት አገልግላለች። የሥነጥበብ ት/ቤት አገልግሎቷን ልታጠናቅቅ ገደማ፣ በ1985ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታ፣ የማህበረሰብ ጥናትና የማህበረሰብ  አስተዳደር በመማር የመጀመርያ ድግሪዋን አገኘች። ከተመረቀች በኋላ በሁለት ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ በበርካታ የሥራ መደቦች ላይ  አገልግላለች።  የመጀመርያው  ዓለም አቀፉ “የካናዳ ሃኪሞች የረድኤት ድርጅት” (CPAR) ሲሆን  በጎሃ ፅዮን ፕሮጀክቱ  የሥርዓተ- ፆታ አማካሪ ሆና ሰራች። ከዚያም በአዲስ አበባ  “የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ፎረም” በተባለ ድርጅት የተቀጠረችው መዓዛ ፤ በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች ላይ ስትሰራ ቆይታ  የክልል ቢሮ አስተባባሪ እስከመሆን ደርሳለች – የደሴ፣ ናዝሬትና ድሬዳዋ ቢሮዎች። ከዚህ በኋላ ነው መዓዛ በቀጣይ የሙያ ዘመኗ በጋለ ፍቅር ከምትተጋለት  የሥራ ዘርፍ  ጋር የተገናኘችው። “ወተር አክሽን” ውስጥ  ገብታ በተለይ ለገጠር ሴቶችና ህፃናት ትልቅ ፋይዳ ባለው የውሃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና አገልግሎት ዘርፍ ላይ መሥራት ጀመረች።  ትዳር ከመሠረተችና  በ1993 ዓ.ም ከኔዘርላንድስ  የማህበረሰብ  ጥናቶች ተቋም፣ በሴቶችና ልማት የትምህርት ዘርፍ  ሁለተኛ ድግሪዋን ካገኘች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው መዓዛ ፤ ከውሃና የአካባቢ ንፅህና ወይም ሥርዓተ ጾታ አሊያም ከሁለቱም ጋር በተገናኙ  የሥራ ዘርፎች  አገልግላለች።  “ወተር አክሽን” ውስጥ ተመልሳ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየች  በኋላ  “አግሪሰርቪስ ኢትዮጵያ” የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ  አገር በቀል ድርጅት ውስጥ የተቀጠረች ሲሆን  የሥርዓተ- ፆታና የማህበራዊ ጉዳይ ክፍል ሃላፊ በመሆን ሰርታለች። ቀጣዩ ሥራዋ ወደ ባህርዳር ወሰዳት። የኢትዮጵያና የፊንላንድ መንግስታት የሁለትዮሽ  ትብብር ፕሮግራም በሆነው “የገጠር ውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም” ( RWSEP)  ውስጥ የተቀጠረችው መዓዛ ፤ የሕብረተሰብ እሴት ልማት አማካሪ በመሆን መሥራት ጀመረች። በዚህ ሃላፊነት ላይ እያለች እጅግ አስደሳችና እርካታ የሚያጎናፅፍ ጊዜ እንደገጠማት ታስታውሳለች። ከሥራዋ ጎን ለጎን የመሥሪያ ቤቱ ህትመቶች ኤዲቶርያል ኮሚቴ አባል ሆና ስትሰራ ፤ የፕሮጀክቱ  ተጠቃሚ በሆኑና ባልሆኑ ቀበሌዎች  መካከል ያለውን የኑሮ  ልዩነት የሚያሳይ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርባ  ነበር። ለዚህ ፅሁፍ ግብአት የሚሆን ጥናት ባካሄደች ወቅት፣ የቀበሌ አስተዳደር አባላትንና ከሁለቱም ቀበሌዎች የተውጣጡ ሴቶችን  አነጋግራ ነበር – በኑሮአቸው ሁኔታ ዙርያ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም  የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ያልነበረው ቀበሌ፣ የፕሮጀክት ናሙና ሆኖ በመመረጥ ማህበረሰቡ  የንጹህ ውሃ አቅርቦት እንዲያገኝ ተደረገ – በመዓዛ ጥረት።  ማህበረሰቡም ይሄን ጥረቷን  እንደቀልድ አላየውም። የውሃና ተያያዥ ችግራቸው ትኩረት እንዲያገኝ በማድረጓ ፣ አዲሱን የውሃ አቅርቦት  በስሟ በመሰየም፣ ለሷ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ገልፀውላታል።

ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ የተመለሰችው  መዓዛ ፤የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባልደረባ በመሆን በስርዓተ- ፆታ አማካሪነት አገልግላለች – የአነስተኛ ብድር ፕሮግራማቸው  ሴቶችን የበለጠ በሚጠቅም መልኩ እንዲያገለግል በማገዝ። “ኬር ኢንተርናሽናል” በተባለው ድርጅት ውስጥ በመቀጠር  ወደ አለም አቀፍ የውሃ መድረክ የመጣችው  መዓዛ፤ በድርጅቱ  ዓለም አቀፍ የውሃ ኢንሽየቲቭ ፕሮግራም ፣ የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት፣ የአቅም ግንባታ አስተባባሪ ሆና ሰርታለች። በአሁኑ ወቅት  መዓዛ በዩኒሴፍ የውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ፣ የአቅም ግንባታ ልዩ ባለሙያ ናት።

በሙያ ዘመኗ ሁሉ የሴቶችንና  የህፃናትን ህይወት ለሚያሻሽሉ ነገሮች እየተማረከች  ስትሰራ ኖራለች – ለንፁህ የመጠጥ ውሃና የአካባቢ ንፅህና ጥበቃ  አገልግሎት  ልዩ ትኩረት በመስጠት። በእስካሁኑ የሙያ ጉዞዋ፣ ያከናወነቻቸው ሥራዎች ቀስ በቀስ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳመጡ ታምናለች። መዓዛ በውሃ ፕሮጀክቶች ሥራዋ ከፍተኛ እርካታ ይሰማታል። ማህበረሰቡ በውሃ እጥረት ሳቢያ የሚጋፈጣቸውን ችግሮች ለይቶ የማወቅ እንዲሁም በትክክል የመግለፅ ፣ ከዚያም ከውሃ ጋር የተያያዘ ችግሩን ለመፍታት የማገዝ፣ በመጨረሻም ከአካባቢው ነዋሪ ፊት ላይ የሚፈነጥቀውን የደስታ ብርሃን  የማየት — አጠቃላይ ሂደቱ እንደሚያስደስታት ትናገራለች። ማህበረሰቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በአካባቢው ሲያገኝ፣ በህይወቱ ላይ የሚታየው ለውጥ በእርካታ የሚያጥለቀልቅ ነው – የንፅህና አጠባበቅ ይሻሻላል፣ የበሽታና የሞት መጠንም ይቀንሳል፣ ህፃናት ት/ቤት ከመሄድ አይናጠቡም።

በሙያ ዘመኗ የተለያዩ ፈተናዎችን አሳልፋለች። ወጣት የቤተመፃህፍት ባለሙያ ሆና በምትሰራ ወቅት፣ ሰዎች ብዙ ጊዜ፣ “ሃላፊውን ጥሪልን” እያሉ ያስቸግሯት ነበር።  ምክንያቱም ብዙዎቹ  እሷ  የቤተመፅሃፍቱ ሃላፊ ትሆናለች ብለው አይገምቱም – በዕድሜዋና በሴትነቷ የተነሳ። በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ስትሰራ ያሳለፈችውን  ፈተናም አትዘነጋውም። ጋራ ሸንተረሩን መውጣት መውረድ፣ እንዲሁም ረዥም ርቀት በእግሯ መጓዝ ነበረባት። ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሳ ስታስበው፣ እንዴት እንደተቋቋመችው  ግርም ይልታል።

በሥራዋ ለተቀዳጀችው ስኬት የወላጆቿ፣ የባለቤቷና የሥራ አለቆቿ አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች። በርካታ የሥራ ባልደረቦቿና ጓደኞቿም አበረታችና  አይዞሽ ባይ እንደነበሩ ታስታውሳለች።  ትኩረቷን ወደ ሥርዓተ- ፆታ እንድታደርግ ዓይኗን የገለጡላት  ወ/ሮ ዘውዴ አበጋዝ  የዕድሜ ልክ አርአያዋ ናቸው።  በሚሰሩት ሥራ ላይ ያላቸውን ልበሙሉነት እንዲሁም በሥርዓተ- ፆታ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶችና ክርክሮችን  የሚመሩበት ሙያዊ ብቃት በእጅጉ እንደሚያስደምማት ትናገራለች። በሥርዓተ – ፆታ ላይ ለመስራት ያነሳሳኝ ወ/ሮ ዘውዴን ማወቄ ነው  የምትለው መዓዛ፤  በሥርዓተ ፆታ እና በልማት የትምህርት መስክ ለማስተርስ ድግሪዋ እንድታጠና ትጋትና ብርታት የሆኗትም እሳቸው እንደሆኑ አትዘነጋም።

መዓዛ በሥራዋም ሆነ ከሥራዋ ውጭ የማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል ትሰራለች። “ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ፎረም” ውስጥ ስትሰራ በአዲስ አበባ ቂርቆስ አካባቢ፣  ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች የጥናት  ክፍል ከፍታለች – ትርፍ ጊዜያቸውን በንባብ ክፍል እንዲያሳልፉና የህይወት ዘመን የንባብ ልምድ  እንዲያዳብሩ ለማበረታታት። ወደፊት ቀላል ክህሎትን የሚጠይቁ ቁሳቁሶችን የሚያመርት ፋብሪካ የማቋቋም እቅድ አላት – ልጆቻቸውን ይዘው በጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሴቶች የሥራ ዕድል ለመክፈት። እነዚህ ሴቶች ከጎዳና ላይ እንዲነሱና ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው የተሻለ ህይወት እንዲገነቡ ልታግዛቸው ትመኛለች።

መዓዛ በቅርቡ ከሙያዋ የመለየት ሃሳብ የላትም። በውሃና በአካባቢ ንፅህና ዘርፍ የያዘችውን ሥራ ለመቀጠል  አቅዳለች። ሁሉም ሰው የንፁህ ውሃ አቅርቦት የሚያገኝበትን ጊዜ ትናፍቃለች። አብዛኛውን ጊዜያቸውን ውሃ በመቅዳት የሚያጠፉ ሴቶችም በአቅራቢያቸው ንፁህ ውሃ አግኝተው፣ጊዜያቸውን በሌሎች ትርፋማ ሥራዎች ላይ ሲያውሉት ማየት ትሻለች። የበለፀገች፣  አረጓንዴ ኢትዮጵያን የምታልመው  መዓዛ፤ በሃብታምና በድሃ መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ ትመኛለች።

መዓዛ ልጃገረዶችንና ወጣት ሴቶችን ስትመክር እንዲህ ትላለች –  በሥራችሁ ውጤታማ ለመሆን  ጊዜያችሁን አንጠፍጥፋችሁ ተጠቀሙ። መልካም  እድሎችንና አጋጣሚዎችን  በአግባቡ ጥቅም ላይ አውሉት። ችግርና ውጣ ውረድ ሲገጥማችሁ አትማረሩ። ይልቁንም እንደ መረማመጃ ድልድይ ተጠቀሙበት –  ለወደፊት ስኬት መማሪያ በማድረግ። ራሳችሁን ማስተማር ላይ አተኩሩ። ስለአገራችሁ እወቁ፤ የአገራችሁም ተቆርቋሪ ሁኑ።

ዋና የመረጃ ምንጮች
በ21/7/2004 ዓ.ም ከመዓዛ ከበደ መካ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ሊዲያ ቱጁባ አቶምሳ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>