Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

መስከረም አሰግድ ባንቲዋሉ

Meskerem Assegued 1

ዋና ዋና ስኬቶች:
በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ አቅራቢያ ሀርላ በምትባል መንደር፣ ዞማ የዘመነኛ ሥነ ጥበብ ማዕከል (ZCAC) የመሠረተች የማዕከሉ ዳሬክተር ነች። በዓለማቀፍ ደረጃ የምትታወቅ የሥነ ጥበብ አሰባሳቢ፤ የሥነ ጥበብና የአንትሮፖሎጂ ኤግዚቢሽን አዘጋጅ
ወቅታዊ ሁኔታ የዞማ ዘመነኛ ሥነ ጥበብ ማዕከል (ZCAC) ዳሬክተር
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አዲስ አበባ ውስጥ በናዝሬት ስኩል፣ በካቴድራል፣ በኒው ኢራ፣ በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ደብረዘይት ውስጥ በሞዴል ትምህርት ቤት ተምራለች።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ከሥነ ጥበብ ኤግዚቢሽን አዘጋጅነቷ በተጨማሪ፣ በሙያዋ አንትሮፖሎጂስት የሆነችው መስከረም አሰግድ ባንቲዋሉ፣ ከተፈጥሮ ጋር ህብር በሚፈጥር መንገድ ሥነጥበብን የማበረታታት እና ባሕልን የመጠበቅ ፍቅር አላት። በኢትዮጵያና በውጭ አገራት በርካታ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ከመታወቋም በላይ፤ በትልልቅ ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ በመራጭ ኮሚቴዎች ውስጥ ተሳትፋለች። ስለ ኪነ ጥበብና ባሕል ጽሑፎችን የማቅረብ ልምድ ያላት መስከረም፤ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አቅራቢያ በምትገኘው ሀርላ መንደር፣ “ዞማ የዘመነኛ ሥነ ጥበብ ማዕከል” (ZCAC) አቋቁማ በዳሬክተርነት እየመራችው ትገኛለች።

ወላጆቿ፣ በኑሮ ደረጃ እጅጉን ከሚራራቁ ቤተሰቦች የመጡ ቢሆኑም፤ መስከረም ግን “የባላባት ቤተሰብ” ከሚባሉት የአባቷ ዘመዶችና፣ መካከለኛ ገቢ ከነበራቸው የእናቷ ቤተሰቦች ጋር እኩል ለመቀራረብ አልቸገራትም። ከዘመናቸው አስተሳሰብና አኗኗር በማፈንገጥ የሚታወቁት አባቷ፤ በራሷ ምርጫና መንገድ ለመኖር የነበራትን የነፃነት መንፈስ ይደግፉላት ነበር። እናቷም ሴት ልጆቻቸውን ለማስተማር የነበራቸው ቁርጠኝነት የዋዛ አይደለም። መስከረም እና እህቶቿ የየራሳቸውን ማንነት መቅረፅና የሙያ ህይወታቸውን መገንባት እንዳለባቸው፣ ገና በጥዋቱ ከእናታቸው የዘወትር ምክር ተምረዋል። የእናት እና የአባቷ ቤተሰቦች፣ በኑሮ ደረጃና በአኗኗር ዘይቤ ሰፊ ልዩነት ቢኖራቸውም፤ ሁለቱም ይህ ቀረሽ የማይባል ፍቅር እየሰጡ በነፃነት መንፈስ እንድታድግ ለማድረግ ችለዋል። በግል ነፃነቷ የምትደሰተው ታዳጊዋ መስከረም፤ የመሰላትን የምታደርግ ናት የምትባል አይነት ልጃገረድ ነበረች። ከወንዶች ጋር ኳስ ትጫወታለች፤ ባሰኛት አቅጣጫ ለዙረት ትወጣለች። ከእንሰሳት አስገራሚ ባህርያት በተጨማሪ ተራራውና ወንዙ፣ ደኑና መስኩ ያስደንቃታል። አራዊቱና እጽዋቱ ሕብር ፈጥረው የሚኖሩበት የተፈጥሮ ፀጋ ያስደምማታል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል በአዲስ አበባ እና በደብረ ዘይት ከተሞች በርካታ ትምህርት ቤቶችን ካዳረሰች በኋላ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አዲስ አበባ በሚገኘው ሊሴ ገብረማርያም አጠናቀቀች። በ17 አመቷ፣ በአሜሪካ ኮሙኒቲ ስኩል (አሁን ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ስኩል በሚባለው) ተቀጥራ ፈረንሳይኛ አስተምራለች። ከዚያ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ አቀናች። ከኮሌጅ እንደተመረቀችም ትዳር ይዛ ሁለት ልጆችን ወልዳለች። ግን የከፍተኛ ትምህርት ፍላጎቷ አልቀነሰም። ሁሌም በኪነ ጥበብ የምትማረከው መስከረም፤ ኮሌጅ ውስጥ ባሳለፈቻቸው ዓመታት በርካታ የኪነ ጥበብ ኮርሶችንና ተዛማጅ ትምህርቶችን ተከታትላለች – ዘመነኛ ዳንስ እና የጃዝ ዳንስ ጭምር። ነገር ግን በያኔው ዘመን፣ ብዙ ሰዎች ኪነ ጥበብን እንደ ተጓዳኝ ዝንባሌ ይቆጥሩት እንደሆነ እንጂ፣ ራሱን የቻለ የምሁር ሙያ ነው ብለው አያስቡም ነበር። ምሁር ባለሙያ ማለት፤ በከበሬታ በሚታይ የህክምና ወይም የምህንድስና ዘርፍ ተመርቆ መሥራት ማለት ነው ብለው ያምኑ ነበር። መስከረምም፤ በአሜሪካ ኦሀዮ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ፓርክ ኮሌጅ (አሁን ፓርክ ዩኒቨርስቲ በሚባለው) ክሊኒካል ሳይኮሎጂ ተምራ በዲግሪ ተመርቃለች። ታዲያ፣ ከኮሌጁ የሳይንስ ላብራቶሪ አጠገብ ተለይታ አታውቅም ነበር። መደርደሪያዎቹን ሞልተው በሚታዩት፣ አፈ ሰፊ የፕላስቲክ ጣሳዎች ላይ የባክቴሪያ አይነቶች ተፈልፍለው እንዲባዙ ታደርጋለች። ባክቴሪያዎቹ ተራብተው፣ በተለያየ ቅርፅና ቀለም እየተሰባጠሩ የሚፈጥሩትን ልዩ መልክ ማየት በጣም ያስደስታት ነበር።

የአገሯን ባሕልና ባሕላዊ ማንነቷን የማፈላለግ አሰሳ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። ነገር ግን፤  በኦሃዮ ግዛት በሚገኘው ማክግሪጎር ስኩል ኦፍ አንቲኦክ ዩኒቨርስቲ፣ የማስተርስ ትምህርት በጀመረችበት ወቅት ነው፤ የማንነት ፍለጋዋ ቅርፅ እየያዘ የመጣው። ጉዞዋም ወደ አገሯ አቅጣጫ ሊዞር ተቃርቧል – እትብቷ ወደ ተቀበረበት ምድር። ማክግሪጎር ስኩል ኦፍ አንቲኦክ ዩኒቨርስቲ እና አዲስ አዲስ ዩኒቨርስቲ ጋር በፈጠሩት የሥራ ትብብር አማካኝነት፤ በካልቸራል አንትሮፖሊጂ የማስተርስ ዲግሪዋን  ለማጠናቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች። ለጥናት ፅሁፏና ለመስክ ጥናቷ የመረጠችው ርዕሰ ጉዳይ፤  በኦሮሞ ህዝብ የሚከበረውና በደብረ ዘይት የሚከናወነው የእሬቻ በዓል ላይ ያተኮረ ነው። እሬቻ ላይ ለማተኮር የመረጠችው በዘፈቀደ አይደለም፤ የቀደምት እናቶቿና አባቶቿን አኗኗር ለማወቅ ጉጉት ስለነበራት እንጂ። ነገር ግን ስለቀድሞው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ መጪው ጊዜም የዚያኑ ያህል ታስባለች። ልጆቿን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማሳደግ የቆረጠችውም በዚሁ ምክንያት ነው።

ኪነ ጥበብ፣ ለመስከረም ልዩ ትርጉም አለው።  ከምትማረውና ከምትሠራው ነገር ጋር ሁሉ የተቆራኘ ነው – ኪነጥበብ። አሜሪካ ውስጥ በኦሃዮ ግዛት ውስጥ በየሎው ስፕሪንግስ ከተማ የመሰረተችው የቤተሰብ ኑሮ፤ በኪነ ጥበብ የታጀበ ነበር። ለምን ቢባል፤ የምትኖርበት መንደር ከሌሎች ለየት ይላል። አማራጭ የኪነ ጥበብ ሕይወት ለመፍጠር የተሰባሰበ ማህበረሰብ ነው፤ የአካባቢው ነዋሪ። በዚሁ ማሕበረሰብ ውስጥ፣ መስከረም የሥነ ጥበብ ስራዎችን በመፍጠር፣ ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት እንዲሁም የዳንስና የሙዚቃ ትርዒቶችን በማሰናዳት ተሳትፋለች። ከዚህም በተጨማሪ፣ “ኤ ሚድሰመር ናይትስ ድሪም” እና “ትዌልፍዝ ናይት” የተሰኙ የሼክስፒር ድርሰቶችን ጨምሮ በርካታ ድራማዎችን በመድረክ እንዲቀርቡ በአስተባባሪነትና በተዋናይነት እየሰራች፣ የማህበረሰቡን የኪነ ጥበብ ሕይወት አሟሙቃለች። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የምትመለስበት ምክንያት አልነበረም። ውስጣዊ የኪነጥበብ ዝንባሌዋን ከልብ ተቀብላ፤ የኪነ ጥበብ ፍቅሯን ተከትላ መጓዝ እንዳለባት ተገንዝባለች። በቃ፤ ኪነ ጥበብ ለመስከረም ሙያዋና ሕይወቷ ሆነ። የምታደንቃቸው ጀግኖች እንዳደረጉት ነው ያደረገችው። የኔ ጀግኖች፣ ህልማቸውን ተከትለው ለመጓዝ የሚደፍሩ፤ ሥራቸውንና ሙያቸውንም የሚያፈቅሩ ሰዎች ናቸው ትላለች መስከረም።

በኦሃዮ የተወለደው የኪነጥበብ ሙያዋ፣ አደባባይ ወጥቶ የታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። አርቲስቶች ድንኳን ውስጥ ሥዕል እየሰሩ ለተመልካቾች የሚታዩበት፤ “ጊዜያዊ ቁ.1” የተሰኘ “ላይቭ” ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ እምብርት በመስቀል አደባባይ አቀረበች። “ዞማ የዘመነኛ ሥነ ጥበብ ማዕከል” በሚል ስያሜ የተቋቋመው የመስከረም ድርጅትም፤ ለሰው ጆሮ የበቃው ያኔ ነው። መስከረም ያሰባሰበቻቸው አምስት የውጭ አገርና አስር ኢትዮጵያዊ አርቲስቶች በኤግዚቢሽኙ የተካፈሉ ሲሆን፤ ድንኳን ውስጥ በተመልካች ፊት ሥዕል እየሰሩ አሳይተዋል። በ”ጊዜያዊ ቁ.1″ ኤግዚቢሽን የተበረታታችው መስከረም፤ ከኢትዮጵያም ሆነ ከውጭ አገራት አርቲስቶችን ለተለያዩ የኪነ ጥበብ ፕሮግራሞች በእንግድነት የሚያስተናግድ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ተዛማጅ የሆኑ ስልጠናዎችን የሚያካሂድ ማዕክል ለመገንባት ተነሳች። ቁሳዊና መንፈሳዊ የኪነ ጥበብ አሻራዎችን ለመጪው ዘመን ማስተላለፍ የሚለውን ዓላማ ሰንቆ የተቋቋመው ይሄው ማዕከል፤ የወደፊቱን ትውልድ ለመፍጠር ከዛሬው ትውልድ ጋር እንሥራ፤ ከዛሬው ትውልድ ጋር ለመሥራትም የቀድሞውን ታሪክ እናጥና ይላል። መስከረም አስባ አልቀረችም፤ የአዲስ አበባው የሥነ ጥበብ ማዕከል ግንባታ ተጀመረ። በኪነ ጥበብ ስራዎቻቸው ብዛት ከሚታወቁት የኢትዮጵያ አርቲስቶች መካከል አንዱ የሆነው ኤሊያስ ስሜ፣ የማዕከሉን ግንባታ እንዲያከናውን ሲመረጥ ምን እንደሚጠበቅበት አልጠፋውም። የመስከረምን ሃሳብ በመረዳት፤ ለአካባቢ ጥበቃ የሚስማሙ ባሕላዊ ቁሳቁሶችና ዘዴዎችን በመጠቀም ማዕከሉን ገንብቶ አጠናቋል። ሁለተኛው የሥነ ጥበብ ማዕከል ደግሞ፤ ድሬዳዋ አቅራቢያ ሀርላ በምትባል አነስተኛ መንደር ውስጥ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ በተውጣጡ የሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በአካባቢው አርቲስቶችና በነዋሪው ህዝብ ትብብር እየተገነባ ነው።

መስከረም ካዘጋጀቻቸው በርካታ ኤግዚቢሽኖች መካከል፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚዬም  በ1994 እና በ1995 ዓ.ሣ. የቀረቡት፣ የዓለም ፕሬስ ፎቶ ኤግዚቢሽኖች፣ እንዲሁም Arts and Ceramicists የተሰኘው የኤልያስ ስሜ ኤግዚቢሽን ይጠቀሳሉ። ኦስትሪያ አገር በቬና ከተማ በተካሄደው New Crowned Hope Festival፣ ግሪን ፍሌም የተሰኘ የትዕይንተ ጥበባት ኤግዚቢሽን የተዘጋጀው በመስከረም ነው። በካሊፎርኒያ ለሳንታ ሞኒካ የኪነ ጥበብ ሙዚዬምም፤ “አይ ኦፍ ዘ ኒድል፣ አይ ኦፍ ዘ ኸርት” የተሰኘ ኤግዚቢሽን አሰናድታለች። “2004 Dak’Art Biennale” እና “52nd Venice Biennale’s African Pavilion” በተሰኙ ዝግጅቶችም፤ በኤግዚቢሽን የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለመምረጥ በኮሚቴ አባልነት ተሳትፋለች። መስከረም ካዘጋጀቻቸው ጥናታዊ ስልጠናዎች መካከል፤  በ1997 ዓ.ም ዓለማቀፍ የኪነ ጥበብ ሃያስያን ማህበር (AICA) በኢትዮጵያ ያካሄደው ስልጠና ተጠቃሽ ነው። በ2003 ዓ.ም. ያዘጋጀችውና “Where Do We Go From Here?” የተሰኘው ስልጠና ደግሞ፤ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ፤ የሙዚዬም አስተዳደርና የኤግዚቢሽን አዘገጃጀት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦችን የሚዳስስ ነበር። በኪነ ጥበብና በባሕል ዙሪያ፤ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ካታሎጎች ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን በማቅረብ የምትታወቀው መስከረም፤ የኢትዮጵያ ተረቶችን የያዘ የሕጻናት መጽሐፍ “Diving for Honey” በሚል ርዕስ አሳትማለች። ከአንትሮፖሎጂ ኤግዚቢሽኖቿ መካከል አንዱ፤  በ1997 ዓ.ም “ምን ነበር?” በሚል ስያሜ የቀረበ ሲሆን፤ በጉራጌ አገር የሚከናወን ዓመታዊ የነጎድጓድ በዓል ላይ የሚያተኩር ነው። እየጠፋ ባለው በዚህ አገር በቀል ባሕል ላይ፣ ከኤልያስ ስሜ ጋር በመሆን የመስክ ጥናት ያካሄደችው መስከረም፤ የበዓል አከባበሩንና ታሪካዊ ሂደቱን በኤግዚቢሽኗ ተርካለች – ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት ጭምር በማሳየት።

የሰው ልጅና የተቀረው ተፈጥሯዊ ዓለም ተጣጥመው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንችላለን ብላ ታምናለች – መስከረም። ለዚህ ግን ትብብር ያስፈልጋል ባይ ነች። ለኪነ ጥበብ፣ ለባሕልና ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ፍቅር፤ በተቻላት አቅም ለብዙ ወጣቶች ለማካፈል የምትጣጣረው፤ ለቀጣዩ ትውልድ ባላት ተቆርቋሪነት ነው። ሥራዎቿን ለመጪው ዘመን በማስተላለፍም፣ የዛሬውን ትውልድ ከቀጣዩ ትውልድ ጋር የምታገናኝ ድልድይ ለመሆን ተስፋ ታደርጋለች። ከእርስ በርስ ፉክክር ይልቅ፤ እርስ በርስ ተግባብተውና ተረዳድተው፣ ተደጋግፈውና ተባብረው በሚሰሩ ሰዎች የታነፀ ማህበረሰብ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አደርጋለሁ የሚል ህልም አላት።

የኪነ ጥበብ ሥራዋ የተወሰኑ ሰዎችን በመማረኩና ዓለማቀፍ ትኩረትን በመሳቡ ደስተኛ እንደሆነች መስከረም ትገልጻለች። ነገር ግን፤ ከቤተሰቧ፣ ከጓደኞቿ፣ ከሥራ ባልደረቦቿና ከወዳጆቿ ጋር የምትካፈለው ፍቅር፤ ከሁሉም የላቀ ትልቁ ስኬቷ እንደሆነ ትናገራለች። በሕይወቷ በርካታ እንቅፋቶች እንደገጠሟት አትክድም። ነገር ግን፤ እንቅፋቶቹ ሁሉ፣ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የሚጠቅሙ ትምህርቶችና የጥንካሬ ምንጮች ናቸው ብላ ታስባለች። በጣም የምትወደው የአፍሪካ አሜሪካዊያን አንድ አባባል አለ – “አይኖችህን ከሽልማቱ ላይ አታንሳ” የሚለውን አባባል ትወደዋለች። ፈተናዎች ቢገጥሟትም ትምህርት እየቀሰመችባቸው፣ ቀና ቀናውን የሚያስኬድ ውስጣዊ ሃይሏን ይዛ ጉዞዋን ትቀጥላለች። ምክንያቱም፣ አይኖቿ ሁሌም በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩሩ የማድረግ ችሎታ አግኝታለች።

ለወጣት ሴቶች የመስከረም ምክር እንዲህ ይላል – “አንድ ቀላል የሕይወት መመሪያ አለ። መመሪያው፣ ከተፈጥሮ ጋር ተጣጥማችሁ ኑሩ የሚል ነው። መመሪያውን አክብረን የምንጓዝ ከሆነ፤ ተፈጥሮ የተትረፈረፈ ፀጋ መስጠቷን ትቀጥላለች”


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከመስከረም አሰግድ ባንቲሁን ጋር መጋቢት 28/2004 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ
http://survivart.boellblog.org/country/ethiopia/;
http://www.banffcentre.ca/mountainculture/summit/2005/ bios/assegued.asp;
http://www.creativeafricanetwork.com/person/20822/en
አጥኚ
ሊዲያ ቱጁባ አቶምሳ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>