Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

መክሊት አየለ ሀዴሮ

Meklit Hadero small

ዋና ዋና ስኬቶች:
የቴድ ግሎባል “ፌሎው” ሆና ተመርጣለች፤ ከትውልድ አገራቸው ጋር ትስስራቸውን ለማጎልበት በቁርጠኝነት የሚታትሩ የዳያስፖራ አርቲስቶች ቡድን ያካተተው  የአርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ  መስራች አባል ናት፤ የምስራቅ አፍሪካ ሙዚቀኞችን በማሰባሰብ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ለማግኘት፣ ጥንታዊ  የሙዚቃ ባህላቸውን ለመለዋወጥ፣ ትብብር ለመፍጠርና ሙዚቃ ለመስራት ያለመው የናይል ፕሮጀክት መስራች አባልም ናት፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ የራሷን  መንገድ የምትከተል ሙዚቀኛ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ሚያዝያ 2 ቀን 1972 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: ሳንፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩኤስኤ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
PS 321 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣  ኒውዮርክ፣
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ኢስትሳይድ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣  ጌይንስቪል፣  ኤፍኤል
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመርያ ድግሪ፣  /ቢኤ/ ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ ዬል ዩኒቨርስቲ
ዋና የስራ ዘርፍ
ሙዚቀኛ
የሕይወት ታሪክ
ትውልደ ኢትዮጵያዊ – አሜሪካዊቷ  ዘፋኝ  መክሊት አየለ ሃዴሮ፣ ስኬታማ የሙዚቃ ሙያዋን የጀመረችው የዛሬ ሰባት ዓመት፣ በ20ዎቹ እድሜዋ አጋማሽ ላይ ሳለች ነው፡፡ የሙዚቃ ሙያዋን ለማህበረሰብ ጠቃሚ ለሆኑ የኪነጥበብ ሥራዎች መድረክ ከመፍጠር ቁርጠኝነት ጋር ያዋሃደችው መክሊት፤ በተለያዩ የኪነጥበብ ዘርፎችና ባህሎች መካከል ግንኙነትና  ትብብር  በመፍጠር ፣ ለጥበቡ አዲስ እይታና ፈጠራ ለማነቃቃት የምትተጋ አርቲስት ናት፡፡ ከትውልድ አገራቸው ጋር  ትስስራቸውን  ለማጠናከር በቁርጠኝነት የሚታትሩ የዳያስፖራ አርቲስቶችን ቡድን ያካተተው የአርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ  መስራች አባል ናት፡፡ በቅርቡ ደግሞ  የምስራቅ አፍሪካ ሙዚቀኞችን ያሰባሰበውንና ልምድ ለመለዋወጥ፣ ለመተባበርና የምስራቅ አፍሪካን ጥንታዊ የሙዚቃ ባህል በስፋት ለማስተዋወቅ  ያለመውን የናይል ፕሮጀክት መሥርታለች፡፡ በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ “ዲ ያንግ ሙዚየም” እና በ“ሬድ ፖፒ አርት ሃውስ“ በተጋባዥ አርቲስትነት ያገለገለችው መክሊት፤ በ2001 ዓ.ም የ“ቴድ ግሎባል ፌሎው ” ተብላ የተሰየመች ሲሆን በ2004 ዓ.ም ደግሞ የ“ቴድ ሲኒየር ፌሎው”  በሚል ተመርጣለች፡፡

በ1972  ዓ.ም በኢትዮጵያ የተወለደችው መክሊት፤ ሶስት ሴት ልጆች ላፈሩት ወላጆቿ የመጨረሻ ልጅ ናት፡፡  ቤተሰቧ ከደርግ የኮሙኒስት አገዛዝ አስከፊ ጥፋት ለማምለጥ ከአገር የወጡት የአንድ ዓመት ተኩል ህፃን ልጅ ሳለች ሲሆን መጀመርያ ጀርመን፣  ከዚያ አሜሪካ ገቡ፡፡ በሙያቸው ሃኪም የሆኑት ወላጆቿ፤ የመጀመርያውን ጥቂት ዓመታት በአዮዋ፣ በኒውዮርክና በፍሎሪዳ እየተዘዋወሩ የህክምና ሙያ ፈቃድ እስኪሰጣቸው መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም በአሜሪካ በህክምና ሙያ ለመሥራት የሚያስችለውን  ፈቃድ ማግኘት እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኒውዮርክ ያጠናቀቀችው መክሊት፤ ዬል ዩኒቨርስቲ ገብታ በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመርያ ድግሪዋን አግኝታለች፡፡ ሁሌም አይዞሽ በርቺ እያሉ የሚያበረታቷት ወላጆቿ፤ የፈለገችውንና የመረጠችውን  መስራት እንደምትችል በመንገር፣ በራስ የመተማመን ስሜቷን እንድታዳብር አግዘዋታል፡፡ “ወላጆቼ የቱን ያህል ነፃነት እንደሰጡኝ የሚያውቁት አይመስለኝም” ትላለች – መክሊት፡፡ ትምህርት እንደነፍሷ ትወድ የነበረችው መክሊት፤ የላቀ ውጤት ለማምጣት ተቸግራ አታውቅም፡፡ ትንሽ ልጅ ሳለች በክረምት የእረፍት ጊዜ ቀናቱን ለጥናትና ለጨዋታ እያፈራረቀች ትጠቀም ነበር – አንዱን ቀን ስታጠና ከዋለች፣ ቀጣዩን ቀን  ስትጫወት፣ ስትሯሯጥና ስፖርት ስትሰራ በማሳለፍ፡፡ ለመክሊት የህክምና ባለሙያ ከሆነችው እናቷ ከወ/ሮ የምስራች ክፍሌ የሚልቅ ጀግና የለም፡፡ በ1966 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተመረቀችው እናቷ፤ በክፍሏ ውስጥ ብቸኛዋ ሴት የህክምና ተማሪ  ነበረች፡፡ መክሊት ማድረግ የምትፈልገውን ሁሉ ማድረግ እንደምትችል እናቷ ሁሌም ትነግራት ነበር፡፡ መንገር ብቻ ሳይሆን የነገረቻትን በራሷ ህይወት እየኖረች አሳይታታለች፡፡ የመክሊት እናት ዶክተር ለመሆን የወሰነችው ገና በልጅነቷ ነበር፡፡ የ6 ዓመት ልጅ ሳለች አፍንጫዋ ይደማባትና  አባቷ  ሃኪም ጋ ይዘዋት ይሄዳሉ፡፡ ሃኪሟ ሩሲያዊት ሴት ነበረች፡፡ ትንሿ የምስራች ስታያት ተገርማ “ሴት ሆነሽ ሃኪም? ሴቶች ሃኪም መሆን እንደሚችሉ አላውቅም ነበር” አለቻት፡፡ ዶክተሯም “አንቺም ሃኪም መሆን ከፈለግሽ ትችያለሽ” ስትል መለሰችላት፡፡ በዚያች ቅፅበት ነው ሃኪም ለመሆን የወሰነችው፡፡ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ራዕይዋን እውን ከማድረግ ፍንክች ብላ አታውቅም፡፡

መክሊት የወጣችው በእናቷ ቢሆንም ዝንባሌያቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ መክሊት ሁሌም ምኞቷ ሙዚቀኛ  መሆን  ነበር፡፡ እንዴት እውን እንደምታደርገው ግን ፍንጭ አልነበራትም፡፡ በእርግጥ እሷና ሙዚቃ ተለያይተው አያውቁም፡፡ ዘፈን  መዝፈንና  ሙዚቃ ማዳመጥ ነፍሷ ነበር፡፡ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች የሙዚቃ አስተማሪዋ ሚ/ር ዊዴንፌልድ፣ የዘማሪ ቡድን ውስጥ እንድትገባ የፈቀዱላት ዝንባሌዋን በማየት ነው – ዕድሜዋ ባይፈቅድም፡፡  በ6ኛ ክፍል የህብረት ትርዒት ፕሮግራም  ላይ የዝነኛዋን  የጃዝ ሙዚቃ አቀንቃኝ የቢሊ ሆሊዴይ “ጋድ ብሌስ ዘ ቻይልድ” የተሰኘ ዘፈን  እንድትዘፍን አስተማሪዋ  ያበረታቷት ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለችም አልፎ አልፎ  በሙዚቃ ስራዎች ላይ ትሳተፍ ነበር፡፡ ሆኖም ሙዚቃን እንደ ሙያ  እይዘዋለሁ ብላ አስባ አታውቅም፡፡  ስለ ሙዚቃ ስታስብ፣ ሃያልነቱ በሰዎች ላይ በሚፈጥረው ስሜት ታከብረዋለች፡፡   ሙያው፤ የዝናና የጉረኝነት ምኞት ማሳኪያ ብቻ  ሆኖ መታየቱን  ግን አትወደውም ነበር፡፡

መክሊት ከዬል ዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ በቀጥታ ያመራችው ወላጆቿ ወደነበሩበት ሲያትል ነው፡፡ ወላጆቿ ብቻ ሳይሆኑ እሷ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ከኢትዮጵያ የመጡት አያቶቿ፣ አክስቶቿ፣ አጎቶቿና ልጆቻቸው የከተሙትም እዚያው ሲያትል ነበር፡፡ ከህፃንነቷ ጀምሮ ከዘመድ አዝማዶቿ  ርቃ ያደገችው መክሊት፤ በዚህ አጋጣሚ ከዘመዶቿ ጋር ለመተዋወቅና ለመቀራረብ ፈልጋ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ለትርፍ ያልተቋቋመ የኢኮኖሚ ልማት ድርጅት ውስጥ እየሰራች፣   የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ህይወት ውስጥ ጠልቃ በመግባት፣ በሲያትል ኑሮ የጀመረችው፡፡ ሆኖም  ብዙ መቆየት አልቻለችም፡፡ ማብቂያ የለሹ የሲያትል ዝናብ መንፈስን የሚጨፈግግ ሆነባት ፡፡  በአሜሪካ ፀሐይ ከሚናፍቃቸው ዝናባማ ከተሞች አንዷ በሆነችው ሲያትል፣ ስላሳለፈችው ጊዜ ስትገልፅ “ውስጤ የበሰበሰ መሰለኝ” ትላለች፡፡

መክሊት በቀጥታ ያመራችው ወደ ሳንፍራንሲስኮ ነበር – የከተማውን ህይወት ለመሞከር፡፡ እዚያም “ኢቬሊን ኤንድ ዋልተር ሃስ  ጄአር ፋውንዴሽን” የተባለ ድርጅት ውስጥ የአስተዳደር ስራ ያገኘች ሲሆን  ሥራው  ዝንባሌዎቿን  ለመፈተሽ  ብዙ እድልና ነፃነት የሚሰጥ ነበር፡፡ በጅምር ተቋርጦ ከነበረው  የህይወት ዘመን ጉዞዋ ጋር ተገናኝታ ሙዚቃ ለመስራት የተለያዩ  መንገዶችን መፈተሽ ጀመረች፡፡ ፈትሻም ዝም አላለችም፡፡ አማራጮችን ለመጠቀም ወሰነች፡፡ ወዲያው  የድምፅ አወጣጥ ስልጠናዎችን  መውሰድ ጀመረች፡፡  በ1997 ዓ.ም በሳንፍራንሲስኮ ብሉ ቢር የአሜሪካ ሙዚቃ ት/ቤት ነፃ የትምህርት እድል ያሸነፈችው  መክሊት፤ ለአንድ ዓመት ያህል  የጃዝ ሙዚቃ ፣ የጊታር አጨዋወትና የዘፈን ግጥሞች አፃፃፍን ተምራለች፡፡

ሳንፍራንሲስኮ ከገባች  ከስድስት ወር በኋላ  እግር ጥሏት በሳንፍራንሲስኮ ሚሽን ዲስትሪክት፣ ጥበቡንና ማህበረሰቡን ለማስተሳሰር ያለመ “ሬድ ፖፒ አርት ሃውስ” የተባለ የኪነጥበብ ማዕከል   አገኘች፡፡  አዘወትራ ከመመላለስና ቤተኛ ከመሆን አልፋ፣ “ሚሽን አርትስ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፕሮጀክት” የተሰኘ የጐዳና ኪነጥበብ ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ሆነች፡፡ በወር ሁለቴ የሚቀርበው ይሄ ፕሮጀክት፣ ከመደበኛ የኪነጥበብ ተቋማትና ሥፍራዎች በተለዩ  ቦታዎች  (ለምሳሌ – ጋራዦች፣ ሳሎኖች፣ መናፈሻዎች፣ ጓሮዎችና የመሳሰሉት)  ጊዜያዊ የኪነጥበብ መድረክ በመፍጠር፣  ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ  የክዋኔ ጥበብ ባለሙያዎችንና የጥበብ ዘርፎችን የማህበረሰቡ ኑሮ  ውስጥ በማስገባት “ድርና ማግ” አድርጎ ያስተሳስራቸዋል፡፡ “ሚሽን አርትስ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፕሮጀክት”፤ በማህበረሰባቸው ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣትና ሰዎችን እርስ በርስ ለማስተሳሰር ፍላጐት ያላቸውን አርቲስቶች ቀልብ የሳበ  ሲሆን  ይሄ  ህዝቦችን የማስተሳሰርና ባህላዊ መድረክ የመፍጠር ሂደትም  ለመክሊት ልዩ ስሜት የሚፈጥር ተመክሮ ነበር፡፡

ለተለያዩ የጥበብ ዘርፎች መድረክ ስትፈጥርና ስታመቻች የቆየችው መክሊት፤ የሙዚቃ ሥራዎቿን ማቀንቀን የጀመረች ሲሆን ጎን ለጎንም  “ሬድ ፖፒ አርት ሃውስ”ን  ከመስራቹ ቶድ ብራውን ጋር በመሆን መምራት ያዘች፡፡ በዚህ አጋጣሚም መክሊት ዘርፈብዙ የኪነጥበብ ተመክሮዎችን አግኝታለች፡፡ ትዕይንተ ጥበባትን መርታለች፡፡ ከበርካታ  ሙዚቀኞች ጋር ተዋውቃለች፡፡  ስለድምፅ መሳሪያዎች እውቀት ቀስማለች፡፡ ስለመድረክ ዝግጅትና ለመድረክ የሚያገለግሉ ቦታዎች ስለሚያሳድሩት ተፅዕኖም  ትምህርት መውሰድ ችላለች፡፡  ለመክሊት ለጥበቡ መድረክ መፍጠርና  የጥበብ ባለሙያ መሆን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ እንደ ሙዚቃ ባለሙያነቷ የተለያዩ ሙዚቃዎችን የምትፈጥረው መክሊት፤ በዚህ ብቻ ሳትወሰን  ጊዜ፣ ቦታና ባህል ያልገደበው የህዝቦች ግንኙነትን አጉልተው የሚያሳዩ የክዋኔ ጥበባትን ለመጠቀም በሚያስችላት መንገድም  ሙዚቃን እንደምትፈጥር ትናገራለች፡፡

ለሶስት ዓመታት በ“ሚሽን አርትስ ፐርፎርማንስ” ዝግጅቶች ላይ  ስታቀነቅን ቆይታ በሳንፍራሲስኮ  አድማጮችን ማፍራት የጀመረችው መክሊት፤ በ2002 ዓ.ም  “One day Like this” የተሰኘ የመጀመሪያ ሲዲዋን ከለቀቀች በኋላ፣ በመላው አሜሪካ አድማጮችን ማግኘት ችላለች፡፡ ለፈጠራ የሚያነሳሱና የሚነሽጡ የሙዚቃ ሥራዎች ሞልተዋታል  – በልጅነቷ እየሰማች ያደገችው ተወዳጅ  የጃዝና  የሶል ሙዚቃ፣ የምትወዳቸው የሂፕ ሆፕና አርት – ሮክ፣ ከምትኖርበት አሜሪካና  የትውልድ መሠረቷ ከሆነችው ኢትዮጵያ የተገኙ ሐገረሰባዊ ሙዚቃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ካሉ የአገሯ ልጆች  ልብ የሚያሞቅ ድጋፍ እንደምታገኝ የምትናገረው መክሊት፤ ይሄ ድጋፍ ልብ የሚያሞቅ ትርጉም አለው ትላለች፡፡ የመጀመሪያ ሲዲዋን የገመገመ አንድ የሙዚቃ ሃያሲ ሲፅፍ ፤ “በኢትዮጵያ የተወለደችው መክሊት ሃዴሮ፤ ምንም ዓይነት ዘፈን ብታቀነቅን የሚያስጨፍር የአፍሪካ ሙዚቃ ሞገስ ተላብሳ ነው እናም ሃዴሮ በዘፈኖቹ  በምትገልፀው ጥልቅ ውበት ውስጥ፣ የዚያች ጥንታዊ ምድር ዘላለማዊነት ይንፀባረቃል” ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የአዘፋፈን ዘይቤዎች በአዘፋፈን ስልቷ ላይ ተጽእኖ እንዳሳደሩባት ትናገራለች፡፡ ይሄ ተፅዕኖ ደግሞ በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ ስታቀነቅን በቀላሉ ይታያል፡፡ ምንም እንኳን እንደ “አባይ ማዶ” ያሉ የኢትዮጵያ የጥንት ዘፈኖችን ብትጫወትም፣ እስካሁን የራሷን የአማርኛ ዘፈን አልፃፈችም፡፡ ምክንያቱም ሃሳቡን በትክክል ወደ አማርኛ ልተርጉመው ስትል የልብ አላደርስ እያለ ያስቸግራታል፡፡ ምናልባት አንድ ቀን ግን—- ጊታርን በክራር የአጨዋወት ስልት የምትጫወትበት ዘዴ እፈጥራለሁ የሚል ከፍተኛ ጉጉት አላት፡፡  ሁለተኛ የሙዚቃ ሲዲዋን ኮፐርዋየርስ ኧርዝባውንድ  ከተባሉ የሙያ ባልደረቦቿ ጋር በመሥራት  በ2004 ዓ.ም የለቀቀች ሲሆን ሲዲው እስካሁን ያልተሞከረ የሙዚቃ ሥልት አስተዋውቋል – “Ethiopian Sci-Fi-Hip-Hop Space opera” የተባለ፡፡  ቀጣዩን ሲዲዋን የኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ የሶል ሙዚቃ አቀንቃኝ ከሆነው ኪውይን ደ ቫክስ ጋር በመተባበር ለማውጣት እየተዘጋጀች ሲሆን፤ለኢንዲ ሮክና ለአርት ሮክ ምንጭ የሆኑ የሶል ሙዚቃ ስልቶችን የሚፈትሽ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ በባህሎችና በኪነጥበብ ዘርፎች መካከል ድልድይ ሆኖ የማቀራረብ፣ ግንኙነታቸውን የማስፋፋትና  አንዳንዴም ገፍቶ የማስተሳሰር ፍላጎት የመክሊት ጉልህ መለያ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ-አሜሪካውያን ጥናቶች ተቋም ተጋባዥ አርቲስት ሳለች፣ የሊንከን ማዕከልንና ዩኒቨርስቲውን በማስተባበር የክዋኔ ጥበብ ፌስቲቫል አዘጋጅታለች- በሊንከን ማዕከል፡፡ በአፍሪካ ዳያስፖራ ብዙሃነት ላይ ያተኮረው የመክሊት ፌስቲቫል፤በአፍሪካ አሜሪካውያንና በአፍሪካውያን መካከል ባለው ውጥረት ዙሪያ  ውይይት ለመክፈት ያለመ ነበር፡፡ መክሊት የአርባምንጭ ኮሌክቲቭ የተሰኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አርቲስቶች ቡድን መስራች ስትሆን ቡድኑ በዳያስፖራና በኢትዮጵያ ባሉ አርቲስቶች መካከል በየጊዜው የልምድ  ልውውጥ  መፍጠርና ማስፋፋት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው፡፡ የአርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ  በታህሳስ 2001 እና በግንቦት 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጓል፡፡ የናይል ስብስብ  የተባለው አዲሱ ፕሮጀክቷ ደግሞ አስራ አንድ የምስራቅ አፍሪካ የአባይ ተፋሰስ አገራትን አርቲስቶች ያሰባሰበ ሲሆን ዓላማውም ሙዚቃ በጋራ መስራት፣ ሙዚቃዊ ዘይቤዎችን  መጋራትና የክልሉን ሙዚቃ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ማምጣት ነው፡፡ የናይል ኮሌክቲቭ  በየጊዜው በክልሉ ተገናኝቶ የመወያየት እቅድ ያለው ሲሆን በጋራ የሚሰራውንም ሙዚቃ በኒውዮርክ የሊንከን ማዕከል፣ በዋሺንግተን የስሚዝሶንያን ማዕከልና ሌሎች ትላልቅ መድረኮች ለማቅረብ እየተጋ ይገኛል፡፡

በ2001 ዓ.ም የ“ቴድ ግሎባል ፌሎው” ተብላ መሰየሟ፣ በቅርቡ ደግሞ “ሲኒየር ፌሎው” በሚል መመረጧ አስደሳችና አቅም የሚያጎለብት መሆኑን መክሊት ትናገራለች፡፡ ምክንያቱም በየመንፈቁ  በሚካሄደው የቴድ ግሎባል ጉባኤዎች ላይ ንግግር ከሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ተሳታፊዎችና በተለይም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከተሰማሩ አቻዎቿ ጋር ጋር የመገናኘት ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ በምት የሙዚቃ መሣሪያና በድምፅ ከታፕ የዳንስ ባለሙያ ጋር ተባብራ የሰራችው መክሊት፤ ከጥላ ትዕይንት (shadow Theater)አዘጋጅ ጋር የሙዚቃ ቪዲዮ ሰርታለች፡፡ ከዶክመንታሪ ፊልም ባለሙያ ጋር ደግሞ በናይል ፕሮጀክት ላይ ፊልምን እንደ አንድ የፕሮጀክቱ አካል መጠቀም በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ትብብር ፈጥራለች፡፡ መክሊት ይሄንን አጋጣሚ እንደልዩ  የትምህርት እድል ትቆጥረዋለች፡፡ ምክንያቱም በአባላቱ መካከል የሚፈጠረው ትስስር እንዲሁም እርስ በእርስ የሚማማሩበትና የሚተጋገዙበት መንገድ በከፍተኛ ደረጃ አቅምን የሚያጎለብት ነው፡፡  ማንኛውም ትምህርትም እንዲህ ሊሆን ይገባው ነበር!

መክሊት እንደማንኛውም ሰው ፈተናዎችን ተጋፍጣለች፡፡ ነገር ግን ፈተናዎች ለእሷ እንደ አንድ የህይወት አካል እንጂ እንደ ፍርሃት ምንጭ አይቆጠሩም፡፡ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በመጋፈጥ   ጎበዝ እንደሆኑ ታስባለች፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን  ሴቶች እጅግ ጠንካራ ሰብዕና አላቸው የምትለው መክሊት፤ ስኬት ለመቀዳጀት የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ በውስጣቸው እንዳለ ማወቅ እንደሚገባቸው ትናገራለች፡፡ ትልቁ ፈተና የገጠማት የኮሌጅ ተማሪ ሳለች የአንጎል እጢ እንዳለባት ሃኪሙ የነገራት ጊዜ ነው፡፡ እንደመታደል ሆኖ  ካንሰር አልሆነባትም ፤ ሆኖም ለጥቂት ዓመታት ከህመም ጋር መታገል ነበረባት፡፡ ይሄ መቼም ከባድ ፈተና ነው፡፡ በርካታ ሰዎች እንዲህ ያለውን ፈተና በየራሳቸው ልዩ ልዩ መንገዶች መወጣት አለባቸው፡፡ “በራስ መተማመን ጠቀሜታው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በራስ የመተማመን ስሜታችሁን የሚነጥቃችሁ ምንም ኃይል የሌለበት ደረጃ ላይ ስትደርሱና ከፈተናው የምታገግሙት በእሱ ብቻ  ሲሆን እምነታችሁ ይፀናል፤ፈተናውንም ተሻግራችሁ ታልፉታላችሁ”

ሌላው ፈተናዋ ደግሞ የመረጠችው የህይወት ጐዳና  ነው –  እርግጠኛ መሆን የማትችልበት ጎዳና በመከተሏ፡፡ እሷም ሌላም ያልተጓዘበት፡፡ ይሄ ደግሞ ማስፈራቱ አይቀርም፡፡ ለምን ቢሉ ደህንነታችሁን፣ ሰላም መሆናችሁንና ትክክለኛውን ጎዳና መያዛችሁን የሚጠቁሙ ምልክቶች በሙሉ የሉም፡፡ ይሄኔ በራስ መተማመን ወሳኝ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንዲህ ያሉ ቅጽበቶች ያጋጥሙታል፡፡ ለእኒህ ዓይነቶቹ ቅፅበቶች ጽናትና ግልፅ ኮምፓስ ያስፈልጋችኋል – ለየራሳችሁ የሚበጃችሁን ነገር ለማወቅ፡፡ የራሳችሁን ድምጽ እንዴት ማዳመጥ እንደምትችሉ መማር ይሄን ሁኔታ ለማለፍ  ያግዛል የምትለው መክሊት፤ “ከምታስቡት በላይ ጠንካራ መሆን እንዳለባችሁ ማወቅ አስፈላጊ ነው” ትላለች፡፡ ማንም ቢሆን ከዚህ ማምለጥ አይችልም፡፡ “እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት ጊዜ፣ ህይወት እርግጠኛ ሆና እንደማታውቅ መቀበልና እንደምንም ወደፊት መግፋት አስፈላጊ ነው፡፡” ባይ ናት – መክሊት፡፡

ሥራዎቿን አንዳንዶች እንደሚወዱትና አንዳንዶች እንደማይወዱት ብታውቅም፤ ሌሎች ሰዎች ስለሷ ያላቸው አስተያየት አያስጨንቃትም፡፡ “ማንነታችሁ ሰዎች ስለናንተ ካላቸው አስተያየት ጋር ይበልጥ በተያያዘ ቁጥር ለራሳችሁ ያላችሁ ግምት፣ ስኬትና ውድቀታችሁን ተከትሎ ከፍ ዝቅ ይላል -” ትላለች፡፡ ለሷ ሁሌም የማይቀየረውና ትልቁ ነገር በዓለም ውስጥ  ያለችበት ሁኔታ ነው፡፡

መክሊት የኢትዮጵያውያንን ኩሩነት ታደንቃለች – “ከዚህ የላቀ ምን ሃብት አለ!” በማለት፡፡     ኢትዮጵያውያን፤ ባህላቸው በዓለም ቅርስ መድረክ  ውስጥ ያለውን  ልዩ ሥፍራም በትክክል ያውቃሉ ብላ ተስፋ ታደርጋለች፡፡

ዋና የመረጃ ምንጮች
www.meklithadero.com ; በነሐሴ 2004 ዓ.ም  ከሜሪ-ጄን ዋግል ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ቤቴል በቀለ ብርሐን፤ ሜሪ-ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>