Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

መነን አስፋው (ንግስት: እቴጌ)

empress_mananasfaw

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በአገሪቱ የመጀመሪያ የሴቶች ትምህርት ቤት (እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት) መስራችና ድጋፍ ሰጪ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምስረታ አጋዥ፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር የበላይ ጠባቂ ነበረች። በጣልያን ወረራ ወቅት ሴቶች ቁስለኞችን እንዲንከባከቡ በማደራጀት፤ ለማህበራዊ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት፤ እንዲሁም የልማት እቅዶችን በመርዳት ሰርታለች።
የትውልድ ቦታ: እጓ አምባሰል፣ ወሎ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1883
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  እቴጌ መነን አስፋው፤ የአፄ ኃይለሥላሴ ባለቤት በነበረችበት ወቅት፣ “እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት”ን ጨምሮ በሴቶች ዙሪያ በርካታ ፈርቀዳጅ ተቋማትን የመሰረተችና በበላይ ጠባቂነት ድጋፏን የሰጠች የ20ኛው ክፍለዘመን ንግስት ናት። የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበርን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን ከምስረታ ጀምሮ በቅርበት እያገዘች አለኝታነቷን አሳይታለች። ሲበዛ ሃይማኖተኛ የነበረችው እቴጌ መነን፤ በኢትዮጵያና በኢየሩሳሌም በርካታ ቤተክርስትያናትን በማሳነፅና በማሳደስ ትታወቃለች። በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኗ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ብታሳልፍም፣ የንጉሠ ነገሥቱ የልብ አማካሪ መሆኗ አልቀረም። ቀንደኛ አገር ወዳድ ብሄረተኛ ከመሆኗ የተነሳም፤ የጣልያን ወራሪ ሃይል ከኢትዮጵያ ከተባረረ ዘውዴን እሰጣለሁ ብላ ስለት ገብታ ነበር።

መነን አስፋው፣ በክርስትና ስሟ ወለተ ጊዮርጊስ፤ እቴጌ ከሆነች በኋላም መነን ዳግማዊት በሚል ትታወቃለች። የአምባሰል ተራራ ምሽግ ዋና ጠባቂ ከሚይዘው የማዕረግ ስም ጋር ጃንተራር አስፋው ተብሎ የሚጠራው የመነን አባት፤ በወሎ ከጥንት ጀምሮ ከሚታወቅ ቤተሰብ የተወለደና እንደ ወራሽ የሚታይ ነበር። በእናቷ በወይዘሮ ስህን ሚካኤል ወገን ደግሞ፣ የንጉስ ሚካኤል አሊ የልጅ ልጅ ስትሆን፣ ልጅ እያሱ አጎቷ ነው።

የመሳፍንት ቤተሰብ እንደመሆኗ፤ የመነን የትዳር ህይወት በራሷ ፍላጎትና ውሳኔ የሚመራ አልነበረም። የፖለቲካ ቁርኝት ለመፍጠርና የስልጣን ትስስር ለማጥበቅ በሚያመች መንገድ ወላጆቿና የቅርብ ዘመዶቿ ናቸው የትዳር አጋሯን የመረጡላት – ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ። ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ከመነን አስፋው ጋር ከመጋባቱ በፊት፤ መነን ሦስቴ ተድራ ሦስቴ በፍቺ ተለያይታለች። (ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን፤ ከጊዜ በኋላ “ራስ” የሚል ማዕረግ ከማግኘት አልፎ ዘውድ በመድፋት አፄ ኃይለስላሴ በሚል ስያሜ ይነግሳል)። መነን አስፋው መጀመሪያ የተዳረችው በወሎ ለካራካው ደጃዝማች አሊ ነው። መነን እና አሊ ሁለት ልጆች ቢያፈሩም ብዙም ሳይቆይ ትዳራቸው በፍቺ ፈረሰ። በሁለተኛው ትዳርም በወሎ ትልልቅ ከሚባሉ መኳንንት አንዱ ከሆነው ደጃዝማች አመዴ አሊ “አባ ደያስ” ጋር ተጋብታ ሁለት ልጆችን ወልዳለች። ግን አመዴ አሊ ስለሞተ ትዳራቸው በአጭር ተቀጨ። መነን በአያቷ ውሳኔ ለሶስተኛ ጊዜ የተዳረችው በእድሜ እጅጉን ለሚበልጣት ለሸዋ የመኳንንት ቤተሰብ ለደጃዝማች ልዑል ሰገድ አጥናፍ ሰገድ ነው (ከጊዜ በኋላ “ራስ” ሆኗል)። ትዳራቸው ግን ለአፍታ ብቻ ነው የቆየው። በአጎቷ በኢያሱ ትእዛዝ ከትዳሯ የተፋታችው፤ ከኢያሱ የአጎት ልጅ ከደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ጋር እንድትጋባ ስለታሰበ ነው። እ.ኤ.አ በነሐሴ 1911 ዓ.ም ከተፈሪ መኮንን ጋር በሃያ አመቷ የተጋባችው መነን፤ ለሃምሳ አመት በዘለቀው ትዳሯ ስድስት ልጆችን ወልዳለች። እ.ኤ.አ እስከ 1962 ዓ.ም ህይወቷ እስካለፈበት ጊዜም ሶስት ልጆቿን በሞት አጥታለች። በህይወት የቀሩት ልጆቿ ልዕልት ተናኘ ወርቅ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን እና ልዑል ሳህለ ስላሴ ናቸው። ተፈሪ መኮንን እ.ኤ.አ በ1930 ዓ.ም ንጉሰ ነገስት ሆኖ ሙሉ ስልጣን በጨበጠበት የንግስ በዓል፤ በታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ መነን አስፋውም እቴጌ (ንግስት) በመሆን ዘውድ ደፍታለች።

የሴቶችን ጉዳይ ወደ ፊት ለማራመድ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ትሳተፍ የነበረችው እቴጌ መነን፤ በተለይ የሴቶች ትምህርት እንደ ወንዶች ትምህርት አስፈላጊ ነው በሚለው እምነቷ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሴቶች ትምህርት ቤት መስርታለች። ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ ሴት ተማሪዎች የአዳሪ ትምህርት ቤት፤ ለአዲስ አበባ ሴት ተማሪዎች ደግሞ የቀን ትምህርት ቤትን ያካተተው እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1930 ዓ.ም ቢሆንም፤ ከጣልያን ወረራ በኋላ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም እንደገና ታድሶ ተገንብቷል። ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መጥተው ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚገቡ ሴት ተማሪዎች፤ የእቴጌ መነን ማበረታቻ መቼም ቢሆን አልተለያቸውም። እቴጌ መነን ትምህርት ቤቱን አዘውትራ ትጎበኛለች፤ በምረቃ በዓላት ላይም ቀርታ አታውቅም።

እቴጌ መነን፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሴቶች ማህበር ሲቋቋምም፣ ከምስረታው አንስታ በሞት ከዚህ አለም እስከተለየችበት እለት ድረስ በበላይ ጠባቂነት ማህበሩን ስትደግፍ ኖራለች። የጣልያን ወረራ በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበበ በነበረበት እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም ከመሳፍንትና ከመኳንንት ቤተሰቦች በተውጣጡ 54 ሴቶች የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴቶች ተራድኦ ማህበር፣ የጣልያንን ወረራ ለመከላከል አስተዋፅኦ አደርጓል። ከጦርነቱ በፊትና በጦርነቱ ወቅት፤ የህክምና ቁሳቁሶችን፣ የመርዝ መከላከያ ጭንብሎችንና ለቁስለኞች መታከሚያ መጠቅለያዎችን ማዘጋጀትና ማቅረብ የማህበሩ ቀዳሚ ስራ ነበር። እ.ኤ.አ በ1941 ጦርነቱ ካለቀና ነፃነት ከተገኘ በኋላ ደግሞ፤ በጦርነት የተጎዱ ሴቶችንና ህፃናትን ለመደገፍ ማህበሩ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል። የወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ ተቋማትን በመክፈትና ለድሃ ሴቶች የስልጠና ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ እንዲሁም እደጥበባትንና ባህላዊ ምግብ ቤቶችን በማበረታታት ለሴቶች የስራ እድል ለመፍጠር ጥሯል። በጣልያን ወረራ ዋዜማ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርንም በበላይ ጠባቂነት ያገለገለችው እቴጌ መነን፤ ለነርስ ተማሪዎች አይዞህ ባይና ደጋፊ ሆናላቸዋለች። የጣልያን ጦር የወረራ ዘመቻውን የከፈተ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ቁስለኞችን እንዲንከባበከቡ ከማስተባበሯም በላይ፤ በውጭ አገራት የሚገኙ የሴቶች ማህበራት ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፋቸውን ለኢትዮጵያ እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፋለች። ለአለማቀፉ የሴቶች ማህበር እ.ኤ.አ በ1935 ባሰማችው ንግግር፤ በሴትነቷ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት በማብራራት፤ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የአለም ሴቶች እንዲተባበሩ ጠይቃለች። ከዚህም በተጨማሪ፤ ለጦር ቁስለኞችና በጦርነት ለዳሸቁ ቤተሰቦች የርህራሄ እጃችንን እንዘርጋ በማለት ተማፅናለች።

ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ከባለቤቷ ከአፄ ኃይለሥላሴ ጋር ወደ ታላቋ ብሪታንያ የተሰደደችው መነን፤ በወቅቱ በእንግሊዝ አስተዳደር ስር ወደ ነበረችው ቅድስት ምድር እንዲሁም ወደ ሶሪያና ወደ ሊባኖስ ባደረገቻቸው ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ለኢትዮጵያ ፀልያለች። እናት አገሬ ከወራሪው ሃይል ነፃ ከወጣች፣ ዘውዴን ለቅድስት ማርያም እሰጣለሁ ብላ ስለት የገባችውም በቤተልሄም ነው። ነፃነት ተገኝቶ እ.ኤ.አ በ1941 ዓ.ም ወደ አገር ቤት ስትመለስ፣ ዘውዷን ዳግም ራሷ ላይ ላለማሳረፍ የገባችውን ቃል በማክበር፤ በቤተልሄም ለሚገኘው ቸርች ኦፍ ኔቲቪቲ ስለቷን አስገብታለች።
እጀ እርጥብ ለጋስ የነበረችው እቴጌ መነን፤ የታረዙ፣ የታመሙና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለመርዳት በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት ትታወቃለች። በሃይማኖተኛነቷም፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ከመደገፍ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም። በራሷ ገንዘብ፣ በኢትዮጵያና በቅድስቷ ምድር በርካታ ቤተክርስትያናትን አስገንብታለች፣ አሳድሳለች፤ በገንዘብ ደግፋለች። በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስትያን፤ በእንጦጦ የኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን እንዲሁም፤ በቅድስቷ ምድር በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የቅዱስት ስላሴ ገዳም፤ በእቴጌ ከተገነቡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በአክሱም ለተገነባው የቅድስት ፅዮን ማርያም ቤተክርስትያን ግንባታም ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለግሳለች – የቤተክርስትያኑ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካል ለማየት ሳትታደል ሞት ቢቀድማትም። በዕድሜዋ የመጨረሻ አመታት በጤና መጓደል ህይወቷ ቢታወክም፤ የቤተክርስትያናትና የገዳማት ግንባታ እንዲሁም እደሳ ላይ መልካም ስራዋን አላቋረጠችም።

እቴጌ መነን በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የአደባባይ ሰው አልነበረችም። ከመጋረጃው በስተጀርባ ግን፤ የንጉሠ ነገስቱ ታማኝ የልብ አማካሪ ነበረች፤ ሰው ሳይሰማ በብዙ ጉዳዮች ላይ ምክሯን የምትለግስ።
በመጨረሻ እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም ስትሞት፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ልጆቿ በተቀበሩበት ቦታ ተቀበረች። በቀብር ሥነስርዓት ላይ የእቴጌዋን ለጋስነትና ሃይማኖት ወዳድነት በማወደስ የስንብት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ፤ ርህሩህና ቀና ሰው ነበረች፤ ለንጉሠ ነገስቱም የልብ አማካሪና የቀኝ እጅ ነበረች ብለዋል። በሰልስት የመታሰቢያ እለትም ንጉሠ ነገስቱ የሃምሳ አመት ጋብቻቸው በሰላምና በመተሳሰብ የተሞላ ትዳር እንደነበር ጠቅሰው፤ አንድም ቀን በመካከላችን አስታራቂ ገብቶ አያውቅም ብለዋል። ከ13 አመታት በኋላ የሞቱት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ቀብራቸው በስርዓት ሳይፈፀም በርካታ አመታት እንደተቆጠሩ የሚታወቅ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም ስርዓተ ቀብራቸው ሲፈፀም፤ የእቴጌ አፅምም በቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ሰሜናዊ ክፍል ወደተዘጋጀው የራሳቸው መቃብር ቤት እንዲዛወር ተደርጓል።

“ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘው የንጉሠ ነገስቱ ግለ ታሪክ፤ ጋብቻቸው በጋራ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ክፋት የሚባል ነገር ያልነካት ንፁሕ ሴት ነች በማለት እቴጌ መነንን ያወድሳል።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  Aethiopica Encyclopedia, Vol.III, [p. 720-721]
http://en.wikipedia.org/wiki/Menen_Asfaw accessed August 26, 2012
አጥኚ
ማህሌት ቲ.

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>