Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሃና ተሾመ ወልደፃዲቅ

Hanna_Teshome 1

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
የሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ መስራችና ዳይሬክተር ናት፡፡ በ26 ለቤተሰብ በሚሆኑ ዓይነት ቤቶች ውስጥ 240 ልጆች ትንከባከባለች፡፡ በሦስት ክልሎች ወላጆቻቸው የታሰሩባቸው ህፃናት ማዕከል ታስተዳድራለች፡፡ ከአጥፊ ወጣቶች ማረምያ ቤት ከተፈቱ ወጣቶች ጋር ትሰራለች፡፡ ለችግረኛ አረጋውያን ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ትምህርት እንዳያቋርጡ እገዛ ታደርጋለች፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ የ“ሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ” መስራችና ዳይሬክተር
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ጥቅምት 18 ቀን 1960 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ሲቢስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ት/ቤት፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ንፋስ ስልክ አጠቃላይ የቴክኒክ ት/ቤት፣ዲፕሎማ፣ በኤሌክትሪክሲቲ፤ ጉድሼፐርድ፣ ናይሮቢ፣ ኬንያ፤ቅድስት ማርያም ኮሌጅ የአመራር ተቋም፣በአመራር
ዋና የስራ ዘርፍ
የማህበራዊ ደህንነት አገልግሎት
የሕይወት ታሪክ
ሃና ተሾመ ወላጅ አልባ ህፃናትን እንዲሁም አዛውንትን፣ በወህኒ ቤት ያሉ እናቶችንና በችግረኛ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ልጆችን ጨምሮ ሌሎች ችግረኞችን ለመርዳት ህይወቷን የሰጠች ሴት ናት፡፡  በ1984 ዓ.ም  እናቱን በኤችአይቪ/ኤድስ ያጣ የአራት  አመት ህፃን በጉዲፈቻ ማሳደግ የጀመረችው ሃና፤ የበጎ  አድራጎት ድርጅት ከመክፈቷ በፊት 46 ገደማ ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን ያለምንም ድጋፍ ለብቻዋ ለማሳደግ ታትራለች፡፡  በ2096 ዓ.ም “ሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ” የተባለውን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ከከፈተች በኋላ ከለጋሾች ድጋፍ ማግኘት ጀመረች፡፡ ዛሬ የሃና ማሳደጊያ ከ240 በላይ ህፃናትን ይንከባከባል፡፡ ወላጆቻቸው በወህኒ ቤት ያሉ ህፃናትን በቡድን በቡድን  በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ያስተዳድራል፡፡ በከተማዋ ላሉ ችግረኛ ህፃናት ምግብና መሰረታዊ ፍላጎቶችን ያሟላል፡፡ በራሳቸው ቤት ውስጥ ድጋፍ የሚደረግላቸው ከ20 የሚበልጡ አረጋውያንን ይንከባከባል፡፡ ከፈጣሪ የተሰጣትን የህይወት አላማ ፈልጋ ያገኘችው ሃና፤ ለብዙ ተጨማሪ ችግረኞች ድጋፍና እንክብካቤ መስጠቷን ቀጥላለች፡፡

የፈለገ ፈተና ቢገጥማት ወይም መስዋዕትነት ቢያስከፍላት ይሄን ሥራዋን ከማከናወን ቸል አትልም፡፡

በአዲስ አበባ የተወለደችው ሃና፤ ስድስት ልጆች ላሏቸው ወላጆቿ የበኩር ልጅ ስትሆን አብዛኛውን ጊዜ 20 ገደማ ልጆች በማይጠፉበት ቤት ውስጥ ነው ያደገችው፡፡ ወላጆቿ የአጐትና የአክስት ልጆችን እንዲሁም ለትምህርት አዲስ አበባ የሚመጡ ዘመዶችን እያስጠጉ ይረዱ ነበር፡፡ በህፃንነቷ እንኳን እርህሩህ የነበረችው ሃና፤ መንገድ ላይ የተጣሉ ሴት ቡችሎች ሲያለቅሱ ስለማያስችላት እቤቷ ወስዳ ትንንሽ ቤቶች ትሰራና ከምትበላው ታካፍላቸው ነበር፡፡ ለቤተሰቡ የመጀመርያ ልጅ እንደመሆኗ አባቷ ራሷን እንድትጠብቅና ጥቃት ከተሰነዘረባት ራሷን በቅጡ እንድትከላከል አስተምረዋታል፡፡ ሃና ያሰበችውን ነገር በቁርጠኝነት ከመፈፀም ያፈገፈገችበት አንድም ጊዜ የለም፡፡ በስነስርአት  ያሳደጓት እናቷ፤ ሁሌም ከእሷ ከፍ ያለ ነገር ይጠብቁ ነበር፡፡ እናታቸው ምስጋና ይግባቸውና ስድስቱም ልጆች ተፈቅረውና ተከብረው ነው ያደጉት፡፡

ወላጅ አልባ ህፃናትን ማሳደጊያና ጧሪ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን መንከባከብያ ስፍራ የመክፈት ህልም የነበራት ገና የ14 አመት ታዳጊ ሳለች ነው፡፡ ይሄን  ህልሟን  ለብዙ አመታት ስታስብበት ቆይታለች፡፡  በ1983 ዓ.ም በምትሰራበት “ጉድ ሼፐርድ ሲስተርስ ሴንተር” የተዘጋጀ ዎርክሾፕ ነበር፡፡ ያኔ የ24 አመት ወጣት ስትሆን ባለትዳርና የሁለት እናት ልጆች ነበረች፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ ዙሪያ ለወጣቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተዘጋጀው በዚህ ዎርክሾፕ ላይ የተካፈለችው ሃና፤ ህፃናት ወላጆቻቸውን በኤድስ እየተነጠቁ ለችግር እንደሚዳረጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገነዘበችው ይሄኔ ነው፡፡ ወዲያው “በዚህ ውስጥ የእኔ ሚና ምንድነው? እውነተኛ ፍቅር አለኝ የምል ከሆነ በበሽታው ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በመርዳት ማሳየት አለብኝ” በማለት በሃሳብ ባቡር ወደ ኋላ ተንሻታ ከልጅነት ህልሟ ጋር ተገናኘች፡፡  በዚያችው ቅፅበት እዚያው ቦታ አምስት ህፃናትን ለማሳደግ ወሰነች፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደ ጤና ጥበቃ ሚ/ር በመሄድ ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ አምስት ወላጅ አልባ ህፃናትን ለማሳደግ ማቀዷን ነገረቻቸው፡፡ (ከቫይረሱ ነፃ የሆኑትን የመረጠችው ያኔ መድሃኒት ስላልነበረ በኤችአይሺ የተያዙትን ህፃናት ህይወት ማትረፍ እንደማትችል አስባ ነው) ሆኖም ለህፃናቱ የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው ቫይረሱ የሌለባቸውን ህፃናት እንደማይሰጧት ስታውቅ ለጊዜው ሃሳቧን ተወችው – በስሜት ሳልወሰድ አልቀርም በሚል ሃሳብ፡፡

ሦስተኛ ልጇን በወለደችበት በቀጣዩ ዓመት በመኖርያዋ አካባቢ፣ አንዲት በእሷው እድሜ ላይ ያለች ሴት ታገኛለች፡፡ ሴትየዋ በኤድስ የተያዘች ሲሆን ስትሞት የ4 አመት ልጇ ምን እንደሚውጠው ተጨንቃ ነበር፡፡ ሃናም ልጁን ለማሳደግ ቃል ገባች፡፡ ለቤተሰቧ የመጀመርያ ልጅ በመሆንም ማደግ ጀመረ፡፡ መጀመርያ ላይ ባለቤቷ ሃሳቧን አልገፈውም ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን አሳመነችው፡፡ ከስድስት ወር በኋላ በጓደኛዋ የተላከችላትን የ7 አመት ልጅ ወደ ቤቷ አስገባች፡፡ እቅዷ አምስት ልጆችን ለማሳደግ ስለነበረ ተጨማሪ ቦታ አስፈለጋት፡፡ አባቷ ሁለት ተጨማሪ ክፍሎች ሰጧት፡፡ ክፍሎቹን ካዘጋጀችና ሞግዚቶች ከቀጠረች በኋላ፣ “ሜዲካል ሚሽነሪ ኦፍ ሜሪ” ወደተባለ፣ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ካለ ህፃናት ጋር የሚሰራ የካቶሊክ ድርጅት በመሄድ ሦስት ህፃናትን የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው እንደሚሰጧት ነገሯት፡፡ ማዕከሉን ስትጐበኝ ግን ህፃናቱ ያሉበትን ስቃይ አይታ ስሜቷ በጣም በመነካቱ፣ ሰባት ህፃናትን ልታሳድግ ወሰደች፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ አንድ ልጅ ጨመረች፡፡ ከዚያም ሁለት ወንድማማቾች መጡ፡፡ ሃና ወንድማማቾቹ እንዳይለያዩ በሚል ሁለቱንም ተቀበለች፡፡ ከዚያም ሌላ ህፃን፣ እንደገና ሌላ መጣ፡፡ ህፃናቱ 16 ሲደርሱ ሁለተኛ ቤት ተከራየችና ወንዶቹንና ሴቶቹን ለየብቻ አደረገቻቸው፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ የሚሰሩ እንደ እነተስፋ ጐህ ያሉ ድርጅቶችና ሌሎች ሰዎች ስለምትሰራው ስራ ሲሰሙ እርዳታዋን የሚፈልጉ ህፃናትን ያመጡላት ጀመር፡፡ ሃና ለእኒህ ህፃናት ጀርባዋን ልትሰጥ አልቻለችም፡፡ ይልቁንም ተጨማሪ ቤቶችን ተከራየች፡፡ እያንዳንዱን ክፍል ከስድስት እስከ አስር ለሚሆኑ ህፃናት ከከፋፈለች በኋላ፣ ለአንዱ ክፍል አንድ ወይም ሁለት እናቶችን መደበች – ክፍሎቹን የሚያስተዳድሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ሃና ወጪዎቿን ሁሉ የምትሸፍነው በደሞዟ ነበር፡፡ የልጆቹን የት/ቤት ክፍያ ለመሸፈንም ማታ ማታ የእደጥበባት ሥራዎችን መስራት ጀመረች፡፡  በ1996 ዓ.ም በደሞዟና በራሷ ጥረት ብቻ 46 ህፃናትን ታሳድግ  ነበር፡፡

ልጆቹ ሁሉ ትምህርታቸውን ከሁለተኛ ደረጃም አልፈው እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ እንዲቀጥሉ ለማስቻል ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋት አልጠፋትም፡፡ እናም “ሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ” የተባለውን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አቋቋመች፡፡ ድርጅቱ በቴሌቪዥንና በጋዜጦች በተሰጠው ሽፋን የለጋሾችን ትኩረት መሳብ ጀመረ፡፡ ትኩረቷን ሙሉ በሙሉ በህፃናት ማሳደጊያ ድርጅቱ ውስጥ ለማድረግም፣ በ “ጉድሼፐርድ ሲስተርስ ሴንተር” የነበራትን ስራ ለቅቃ ወጣች፡፡ ለድርጅቱ የገቢ ምንጭ ይሆናል ብላ የከፈተችው የህፃናት እንክብካቤ ማዕከል ትርፋማ ባለመሆኑ ከአራት አመት በኋላ ተዘጋ፡፡ ዛሬ የመጀመርያ ልጇን ለማሳደግ ከወሰደች ከ19 አመት በኋላ፣ ድርጅቱ የ5 ሚሊዮን ብር አመታዊ በጀት ሲኖረው 246 ልጆችን በ26 የተለያዩ ቤቶች (በአንድ ቤት ከ6-10 የሚደርሱ ህፃናት) ውስጥ ይንከባከባል፡፡ ህፃናቱ በአንድ ትልቅ የማሳደጊያ ማዕከል ውስጥ ተሰባስበው ከሚኖሩ ይልቅ በትንሽ በትንሽ ቡድን ተከፋፍለው መኖራቸው እንክብካቤ ለማድረግና ቤተሰባዊ ስሜት ለመፍጠር ያስችላል ብላ ታምናለች- ሃና፡፡ በዚህ ሁኔታ በጐረቤቶቻቸው መሃል እየኖሩና በአካባቢው ማህበራዊ ክንውኖች እየተካፈሉ ቤተሰባዊ ህይወት ይመራሉ ትላለች – ሃና፡፡ እኒህ ህፃናት ወደ ማሳደጊያ ማዕከሉ ከመምጣታቸው በፊት አሳዛኝ የስቃይ ህይወት አሳልፈዋል፡፡ አንዳንዶቹ የፆታ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዓይናቸው እያየ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ናቸው፡፡ የስቃያቸው ብዛትና አይነት ተነግሮ አያልቅም፡፡ በእርግጥ አሁን አዲስ ህይወት ጀምረዋል፡፡ በራስ የመተማመን ስሜት ማዳበርም ችለዋል፡፡ ራሳቸውን ወላጅ እንዳጡ  ህፃናት አይመለከቱም – በቤተሰቦቻቸው መሃል እንደሚኖሩ ልጆች እንጂ፡፡ “ሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ” ከእያንዳንዱ የማዕከሉ ቤት የተውጣጡ ልጆች የተወከሉበት ፓርላማ ያለው ሲሆን እያንዳንዱ የፓርላማ ተወካይ በተረጋጋ ስሜትና በተፍታታ ቋንቋ ሃሳቡን ያቀርባል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ያደጉና ትምህርታቸውን አጠናቀው ራሳቸውን የቻሉ ጥቂት ልጆች፣ አሁን በማሳደጊያው ውስጥ ላሉ ህፃናት ከገቢያቸው ላይ መዋጮ በማድረግ ማዕከሉን እየደገፉ ናቸው፡፡

ሁሉም የድርጅቱ ህፃናት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሚማሩት በግል ት/ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ከት/ቤቶቹ ጋር በተደረገ ስምምነት እስከ 10ኛ ክፍል ልዩ የክፍያ ቅናሽ ተደርጐላቸው ከተማሩ በኋላ፣  ለመሰናዶ ትምህርት ወደ መንግሥት ት/ቤቶች ይላካሉ፡፡ ድርጅቱ የትምህርታቸውን ነገር ለት/ቤቶች ብቻ ጥሎ አልተቀመጠም፡፡ ከት/ቤት በኋላ የቤት ስራቸውን እንዲሰሩ የሚያግዝ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ መኖርያ ክፍል ውስጥም  የኮምፒውተርና የአነስተኛ ቤተ መፃህፍት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ዩኒቨርስቲ ገብተዋል – ሁለት ህክምናና ቢዝነስ የሚያጠኑ ተማሪዎች በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ፣ አንድ የግብርና ተማሪ በአሶሳ ዩኒቨርስቲ፣ አንድ የኢንጂነሪንግ ተማሪ በጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አንድ የጂኦሎጂና አንድ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያ የጉዲፈቻ ልጇ አሁን ፀጉር አስተካካይ ሆኗል፡፡ ሃና ቅድሚያ የምትሰጠው ትልቁ ጉዳይ ሁሉም ህፃናት በደንብ ተምረው ራሳቸውን ሲችሉ ማየት ነው፡፡

ድርጅቱ ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን ከመደገፍ በተጨማሪ፣ ከወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ ቤት የወጡ ታዳጊዎችንም እየተቀበለ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ አገዛ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች እድሜያቸው ከ9-15 ሲሆን ወንጀል ወይም አነስተኛ ጥፋት ፈፅመው ማረሚያ ቤት የገቡና ፍርዳቸውን ጨርሰው የተለቀቁ ናቸው፡፡ ሆኖም ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ቤተሰቦቻቸው ሊቀበሏቸው አይፈቅዱም፡፡ ምንም መጠጊያ ስለሌላቸው ወደ ጐዳና ህይወት ይመለሳሉ፡፡ የሃና ድርጅት ለእነዚህ ታዳጊዎች መኖርያ ከመስጠትም ባሻገር፣ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በልጆቹ ላይ ትልቅ መሻሻል እየታየ እንደሆነ የምትናገረው ሃና፤ አይለወጡም ተብለው ተስፋ የተቆረጠባቸው እንኳን ሳይቀሩ እየተቀየሩ መሆኑን ትገልፃለች፡፡

በጅማ፤ ሐረር እና ወላይታ ደግሞ እናቶቻቸው በወህኒ ቤት ላሉ ህፃናት እንክብካቤ የሚያደርግ ማዕከል ከፍቷል – የሃና ድርጅት፡፡ ህፃናቱ በተዘጋጀላቸው ቤቶች ውስጥ እየኖሩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ሲሆን ከፍ ከፍ ያሉትም ት/ቤት ይላካሉ፡፡ ልጆቹ እናቶቻቸውን በወር አንዴ እንዲጐበኙም ይደረጋል – የእናትና የልጅ ቁርኝታቸውን ለመጠበቅ፡፡ ድርጅቱ የማህበረሰብ ፕሮግራምም አለው፡፡ በአንደኛው ፕሮግራሙ በመንግስት ት/ቤት ለሚማሩ 70 የችግረኛ ቤተሰብ ህፃናት ምሳ ያቀርባል፡፡ ሌላኛው ፕሮግራም ከገጠር አካባቢ ለመጡ የቃጠሎ ተጐጂ ህፃናት በኮሪያ ሆስፒታል ነፃ ህክምና እንዲያገኙ የሚያግዝ ሲሆን ትራንስፖርት፣ ክፍልና ሰሌዳም ያቀርባል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ለ21 አረጋውያን ትንሽ ገንዘብ በመስጠትና የህክምና ወጪያቸውን በመሸፈን እንዲሁም መኖርያ ቤታቸውን በማደስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ሃና  ወደፊት ህፃናት ጐዳና ላይ እንዳይወጡ እንዲሁም ሁሉም ህፃናት በደንብ እንዲመገቡና ጥሩ ትምህርት የማግኘት እድል እንዲኖራቸው ታልማለች፡፡ ይሄንን ደግሞ ከውጭ አገራት ምንም ድጋፍ ሳንጠብቅ፣ ራሳችን እውን ማድረግ እንዳለብን ታምናለች፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ባለፀጐች አሉ – አብዛኞቹም ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ በትክክለኛ አደረጃጀትና ተጠያቂነት ይሄንን እውን ማድረግ መቻል አለብን” ባይ ናት፡፡ ህፃናት ከቤታቸው ሳይወጡ ከቤተሰባቸው ጋር እንዳሉ ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ ቢኖር ደስ ይላታል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ የጐዳና ህፃናት ቤተሰብ ያላቸው እንደሆኑ ታውቃለች፡፡ ሆኖም በሚደርስባቸው ድብደባና ከወላጆቻቸው ጋር በሚፈጠር አለመግባባት ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ ወላጆች እንዴት ልጆቻቸውን መያዝ እንዳለባቸው የሚያስተምር ጥሩ የስልጠና ፕሮግራም መቀረፅ አለበት ትላለች – ሃና፡፡

በስራዋ ትልቅ ፈተና የሆነባት በአዲስ አበባ ያለው የመኖሪያ ቤት ችግር እንደሆነ የምትናገረው ሃና፤ ለለጋሾች የምታቀርበው አጣዳፊ ጥያቄ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ለህፃናቱ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲገዙላቸው ነው፡፡ ትልቅ የወጣቶች ማዕከል ለመገንባትም ታልማለች – ልጆች ተሰባስበው የሚጫወቱበት፤ የሚያጠኑበት እንዲሁም ስልጠናና ዎርክሾፖች የሚካፈሉበት፡፡

ሃና የህይወት ጥሪዋን ለመፈፀም ስትታትር ከባድ  ፈተናዎችን ተጋፍጣለች፡፡ የቤተሰብ ህይወቷንና ሥራዋን አስማምታ ለማስኬድ ከፍተኛ ትግል ብታደርግም ከባሏ ጋር ከመለያየት አልዳነችም፡፡ “ሴት ህልም ሊኖራት አይችልም” በሚል ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን የማሳደግ ስራዋን እንድታቆም ባለቤቷ አሳስቧት ነበር፡፡ በጄ አልል ስትለው ምርጫ ሰጣት “ከእኔ ወይም ከህፃናቱ ምረጪ” በማለት፡፡

“መምረጥ አልችልም” ስትል መለሰችለት፡፡

“እንዴት?” ጠየቃት ባለቤቷ፡፡

“አንተንም ህፃናቱንም የሰጠኝ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ መምረጥ አልችልም”

“እንግዲያውስ እኔ ምርጫ አለኝ” በማለት ጥሏት ሄደ፡፡ ተለያይተው ግን አልቀሩም፡፡ ከሁለት አመት በኋላ አብረው መኖር ጀመሩ – አንዳቸው የሌላቸውን ሃሳብና ጭንቀት በመረዳዳት፡፡ በእርግጥ ሃና ለራሷ ሦስት ልጆች በቂ ጊዜ እንዳልሰጠች ታምናለች፡፡ ብዙ ሰዎች ለሴት ዝቅተኛ ግምት ቢኖራቸውም  ነገሬ  እንደማትላቸው ሃና  ትናገራለች፡፡ ህብረተሰቡና መንግስት መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አሉታዊ አመለካከት አንዳላቸው የምታምነው ሃና፤ ሁሉም ድርጅቶች ገንዘብ የተትረፈረፋቸው ይመስላቸዋል ባይ ናት፡፡

መንግሥት፤ መያዶችን ከአቅማቸው በላይ ይጠይቃል፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ሁሉንም ችግር እንዲፈቱለት ይጠብቃል፡፡ “ሃና ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ” ለህፃናት መኖርያ ለተከራያቸው ቤቶች ተጨማሪ ክፍያ እንደሚጠየቅ ሃና ትናገራለች፡፡ በዋጋ ግሽበት የተነሳ ክፉኛ እየተጐዳ ነው፡፡ የማሳደጊያው ወጣቶች ትምህርታቸውን ትተው ወደ ስራ እንዲገቡ (ሴተኛ አዳሪነትም እንኳን) የሚደረግባቸውን ግፊት መከላከል ከባድ ነው ትላለች፡፡ አንዳንዴ ሥራዋ ተስፋ አስቆራጭ ነው – ጥላው ልትሄድ ሁሉ ይዳዳታል፡፡ ግን “የህይወቴ ግብ ነው” ብላ ስለያዘችው የትም ልትሄድ አይቻላትም፡፡ ለሃና ፍቱን መድሃኒቷ እንቅልፍ ነው፡፡ ማታ ማታ አራት ሰአት ላይ ትተኛና ጠዋት አዳዲስ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ዝግጁ ሆና ከእንቅልፏ ትነቃለች፡፡ ችግር ሲገጥማት ጮሃ ይወጣላታል ወይም ደግሞ በእግሯ ረዥም ጉዞ ታደርጋለች፡፡ ወደ ስራው ከገባች ጊዜ ጀምሮ ግን እረፍት ወስዳ አታውቅም፡፡ ድርጅቷን የመቆጣጠር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባት ይሰማታል፡፡ ትልቁ አርአያዋ መምህር፤ ፈዋሽና መሪ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እሱ የተራበ አብልቷል፡፡ የታመመ ፈውሷል፡፡ ለተገለሉና ማንም ለሌላቸው ደርሷል፡፡ የእሱ ህይወት ለሃና መነቃቃትና መበረታታት ይሰጣታል፡፡ እናቷም ትልቅ ምሳሌዎች ናቸው – ልጆቻቸውን በስነስርአትና እርስ በርስ እንዲከባበሩ አድርገው በማሳደጋቸው፡፡

ስለ ሴትነት ስታስብ ሦስተኛ ልጇን እስክትወልድ ድረስ ሴት መሆኗን አትወደውም ነበር፡፡ በሌላ ምክንያት ግን አልነበረም፡፡ ሴት መሆን ለጥቃት ያጋልጣል ብላ ታስብ ስለነበረ ነው፡፡ ጓደኞቿ ሁሉ ወንዶች ነበሩ፡፡ ሴቶች ስለመልካቸውና አለባበሳቸው በቀር ለሌላ ነገር አይጨነቁም የሚል እምነት ነበራት፡፡ በኋላ ግን ሴትም ትልቅ ህልምና ተስፋ ሊኖራት እንደሚችል ተገነዘበች – ከሌላ ሳይሆን ከራሷ ህይወት፡፡

ሃና ለኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ስትመክር እንዲህ ትላለች – “ጠንካራ ሁኑ” አላማ ይኑራችሁ፡፡ ለምን ወደዚህ አለም እንደመጣችሁና ምን መስራት እንዳለባችሁ ጠይቁ፡፡ ወደ ትክክለኛው ጐዳና የሚያመላክታችሁና የሚመራችሁ አላማ ያስፈልጋችኋል፡፡ አላማችሁን ስታገኙ በቁርጠኝነት ታትሩ፡፡ ህይወት በውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም አላማ ካላችሁ በአሸናፊነት ትወጡታላችሁ፡፡ ሽንፈትን መቀበል የለባችሁም፡፡ እናንተ የመጀመርያውን እርምጃ ስትጀምሩ የቀረውን እግዚአብሄር ያግዛችኋል፡፡ ከባዶ ተነስቶ ትልቅ ስኬት ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

ዋና የመረጃ ምንጮች
ሀምሌ 2004 ዓ.ም ከሃና ተሾመ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
ሌላ ምንጮች
http://www.hannaorphanshome.org/
አጥኚ
ትዝታ ታደሰ ተክለፃዲቅ፤ ሜላት ተክለፃዲቅ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>