Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሳባ ኪዳነማርያም ገብሩ

Saba Kidanemariam Gebru Small

ዋና ዋና ስኬቶች:
ለሴቶች የሥነተዋልዶ ጤና አገልግሎት እና መብቶች የሚሟገተውን IPAS ኢትዮጵያ መርታለች፣ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ የመሆን እንዲሁም አስተማማኝና ህጋዊ ጽንስ የማቋረጥ መብት ለማስከበር የሚያስችል ህግ የማስፀደቅ እና አፈፃፀማቸው ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን ለማረጋገጥ በከፈተኛ ሃላፊነት ተግታለች፤ አይፓስን ከመቀላቀሏ በፊት በተለያዩ የመንግስት ሴክተር ድርጅቶች ውስጥ ከፆታና አካባቢ ጥበቃ፤ ከልማት፣ ከድህነት ቅነሳና የኢኮኖሚ አመራር ጋር በተያያዙ ልማታዊ ጉዳዮች ላይ ሰርታለች፡፡ በደርግ አገዛዝ በተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪነቷ ሳቢያ ለአምስት ዓመት ታስራለች፡፡
ወቅታዊ ሁኔታ IPAS የተባለው ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር
የትውልድ ቦታ: አክሱም፣ ትግራይ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: ሰኔ 13 ቀን 1952 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ፣
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አጋዚ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አዲግራት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
በሽሬ መካከለኛ ት/ቤት፤ ንግስት ሳባ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ አድዋ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የመጀመሪያ ዲግሪ፣ (ቢኤ) በኢኮኖሚክስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ( 1970 ዓ.ም)
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ሁለተኛ ድግሪ፣ (ኤምኤ) በኦርጋናይዜሽናል ዴቨሎፕመንት፣ አዙሳ ፓስፊክ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሌፎርኒያ ( 1997ዓ.ም)
ዋና የስራ ዘርፍ
የማህበረሰብ ተሟጋች – የሴቶች የስነተዋልዶ መብቶች
የሕይወት ታሪክ

የሴቶች የሥነተዋልዶ ጤና መብቶች ሙሉ ዕውቅና እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት በመሪነት የምትሳተፈው ሳባ ኪዳነማርያም ፤ ለሴቶችና ለሰው ልጆች መብቶች ተሟጋች ናት፡፡ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ አስተማማኝ የጽንስ ማቋረጥን ጨምሮ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲስፋፋ የሚሰራው IPAS የተባለ ዓለምአቀፍ መንግስታዊ በንጉሱ ዘመን በትውልድ ቀዬው የአስተዳደር አመራር ላይ ተሳታፊ ከነበረ ቤተሰብ፣ በአክሱም ትግራይ የተወለደችው ሳባ ፤ በ1962 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመግባቷ በፊት በአዲግራት፣ ሽሬና አድዋ ነው ያደገችው፡፡ በወጣትነቷ በአመራር የሃላፊነት ቦታ ላይ ለመውጣት ታልም ነበር፡፡ ሆኖም እዚያ የሚያደርሰው ጐዳና የትኛው እንደሆነ ቅንጣት የምታውቀው ነገር አልነበራትም፡፡ መጀመሪያ ላይ በእናቷ አበረታችነት ጠበቃ የመሆን ፍላጐት አድሮባት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ዩኒቨርስቲ ገብታ ህግ ሳይሆን ኢኮኖሚክስ ማጥናት ጀመረች፡፡

ታላቅ እህቷ ታደለች ኪዳነማርያም ንጉሱን በመቃወም በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የአመራር ሚና የነበራት ሲሆን ከአምስት ተባባሪዎቿ ጋር አውሮፕላን ለመጥለፍ ስትሞክር ተያዘች፡፡ ከእሷ በቀር የተቀሩት ጠላፊዎች በሙሉ ተገድለዋል፡፡ ይሄ አጋጣሚ ነው ሳባን ያነቃት፡፡ የምትኖረው ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሰፊው ህዝብም ጭምር እንደሆነ ተገነዘበች፡፡ የማርክሲስት – ሌኒንስት ርዕዮተዓለም ቀንደኛ ተከታይ በመሆንም የራሷን የፍለጋና የምርመራ ጉዞ ጀመረች፡፡ ይሄ ለሰፊው ህዝብ መኖር የሚል ሃሳቧ፤  በቀሪው ህይወቷ ላመነችበት ዓላማ ልባዊ ፍቅር፣ ድፍረትና ጥንካሬ ያላት ተሟጋች እንድትሆን  አደረጋት፡፡

በዩኒቨርስቲም ሆነ በገጠር የመሰረተ ትምህርት ዘመቻዎች ላይ ሳለች፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪነት የተሳተፈችው ሳባ፤ ከ1969 እስከ 1975 ዓ.ም በደርግ መንግስት ታስራ ቆይታለች፡፡ እንደእድል ሆኖ ግን የሌሎች እስረኞች ዕጣ አልደረሳትም፡፡ በህይወት ተርፋ ከወህኒ ቤት ተመክሮዋ ብዙ ልትማርበት ችላለች፡፡ በወህኒ ቤት ሳለች በርካታ ተማሪዎችንና ሌሎች ታሳሪዎችን የሚያስተምረውን ት/ቤት በመሪነት አስተዳድራለች፡፡ የስፖርት ክለብም መሪ ነበረች፡፡ የወህኒ ቤት ተመክሮዋን እንደ ኮሌጅ ትቆጥረዋለች፡፡ አካውንቲንግና የህግ ትምህርትን ጨምሮ ትልቅ ፋይዳ የምትሰጣቸውን የህይወት ቁምነገሮች የተማረችው የኢትዮጵያ “ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ” ከምትለው ወህኒ ቤት  ነው፡፡

ከአምስት ዓመት በኋላ ከእስር ስትለቀቅ፤ በተለያዩ ልማት – ተኮር የሥራ ሃላፊነቶች ላይ መስራት ጀመረች፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በለጋሾች የሚደገፉ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ በመሆን ያገለገለችው ሳባ፤ከአይዞሽ ባይ አለቆች ጋር የመስራት ዕድል ማግኘቷ ጠቅሟታል፡፡ እዚያ ሳለች ነው ስለአዋጭ ጥናቶች፣ስለ አተገባበር፣ ስለ ክትትልና ማርኬቲንግ የፕሮጀክት ሃሳቦች ትምህርት የቀሰመችው፡፡ የሽግግር መንግስቱ ሥልጣን ሲይዝ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮን የተቀላቀለችው ሳባ፤የአደጋ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ክትትል ዩኒት አስተባባሪ በመሆን የኢንዱስትሪ፣ ሃይልና ኢነርጂ ዘርፎችን በማስተባበር ሰርታለች፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተሃድሶ እና ልማት ፈንድ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነች፡፡ በተቋሙ ለሶስት ዓመት በቆየችባቸው ጊዜያት በፆታ እና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ በአማካሪነት አገልግላለች፡፡ ፈንዱ በተለያዩ በክልሎች 11 ቢሮዎች የነበሩት ሲሆን በርካታ ት/ቤቶች፣ ክሊኒኮችና መንገዶችን ከመገንባቱም ሌላ ገቢ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶችንም ቀርጿል፡፡ ይሄ የስራ ሃላፊነቷ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ለመስራትና ገና ያልተሟሉ ሰፊ  ፍላጐቶች እንዳሉ በቅጡ ለመገንዘብ አስችሏታል፡፡

በ1992 ዓ.ም IPAS Ethiopia የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ዓለምአቀፍ ድርጅት በመግባት የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሆና ስራ ጀመረች፡፡ ድርጅቱ በሥነተዋልዶ ጤና እና መብቶች ላይ በማተኮር የሚሰራ ሲሆን ሳባ ድርጅቱን የመረጠችው ስለ ስነተዋልዶ ጤና ብዙም ስለማታውቅ ነበር፡፡ በእርግጥ ስራው ፈታኝ እንደሚሆን ታውቋታል፤ ሆኖም አልሰጋችም፡፡ ግሩም የመማርያ አጋጣሚ አገኘሁ ብላ ፈነደቀች፡፡ አዲሱ ስራዋ ከቀድሞው ጋር አራምባና ቆቦ መሆኑ ስጋት ቢደቅንባት አይፈረድባትም፡፡ ሳባ ግን ምንም አልመሰላትም፡፡ እንደውም አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎችን  ለመጋፈጥ  ጓጉታ ነበር ፡፡

በIPAS ሳለች አስተማማኝና ህጋዊ የጽንስ ማቋረጥን ጨምሮ የሴቶች የስነተዋልዶ መብቶችን ለማስከበር የሚካሄደው ትግል መሪ በመሆን ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ይሄ ድፍረት የተሞላበት ተሟጋችነቷ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛውን ጠንካራ የስነ ተዋልዶ መብቶችና አገልግሎቶች የህግ ማዕቀፍ ለማስቀረፅ አግዟታል፡፡  በአሁኑ ወቅት የህጉን ውጤታማ አፈፃፀምና ደህንነቱ ባልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ የሚከሰተውን የእናት ሞት መጠን ቅነሳ ለማረጋገጥ የሚካሄደው ዘመቻ መሪ ናት፡፡

በ1992 ዓ.ም ገና IPAS ገብታ በጽንስ ማቋረጥ ጉዳዮች ላይ መስራት ስትጀምር በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮች አይገቧትም ነበር፡፡ ለሷ አስተማማኝ የጽንስ ማቋረጥ ማለት፤ለሴቶች ጥሩ የጤና እንክብካቤ ማግኘት ማለት ነበር፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ምናልባት ወላጆቿ ሃይማኖታቸውን በእሷና በወንድም እህቶቿ ላይ ስላልጫኑባቸው ሊሆን እንደሚችል ታምናለች፡፡ ሳባ ያደገችው ባልታጠረና ነፃ አስተሳሰብ በሚንፀባረቅበት ከባቢ ውስጥ ነው፡፡

የመብት ተሟጋቿ ሳባ፤ ጽንስ ማቋረጥን ማየት ያለብን ልንታገልለትና ልንሟገትለት እንደሚገባ የጤና መብት ነው ብላ ታምናለች፡፡ የድርጅቷ እሴቶች ከራሷ የግል እሴቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው፡፡ በስነተዋልዶ ጉዳይ የራስን ምርጫ መወሰን ሰብአዊ መብት ነው – የእሷ መብት፣ የእናቷ መብት፣ የሴት ልጇ መብት እና በአጠቃላይ የሰው ልጆች  መብት፡፡ በጤና አገልግሎት መብትና ከዚያም ባሻገር ባሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ለመጪው ትውልድ የተሻለች ዓለም መፍጠር እንችላለን ብላ ታምናለች፡፡ የሳባ ልባዊ ፍቅርና ራዕይ የሰዎችንና የሴቶችን ህይወት ለማሻሻል በመስራት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የበለጠ በመስራትና ትላልቅ ግስጋሴዎች በማድረግ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ትሻለች፡፡ ለእሷ ስኬት ማለት ሴቶች በዓለም ላይ ከወንዶች እኩል መኖር እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ባላት የህይወት ዘመን እፈፅመዋለሁ ብላ ታልማለች፡፡ የሚገባውን ያህል ሰርቻለሁ ብላ ባታስብም፣ ለሰዎች አንዳች ቁምነገር አስተምሬ ይሆናል የሚል ተስፋ አላት፡፡

ልጇ የእሷን አንዳንድ ባህርያት በመውረሷ ከፍተኛ ደስታ ይሰማታል፡፡ ለምሳሌ ለላቀ ውጤት መትጋትን፣ለሴቶች ጉዳዮች ልባዊ ትኩረት መስጠትንና ራስን መፍጠርን ከእናቷ ወስዳለች፡፡ ይሄ ደግሞ ለሳባ ትልቅ ዋጋ ከምትሰጣቸው ስኬቶቿ እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው፡፡ ሳባ  ላመነችበት ዓላማ በጽናት የምትቆም፤ ታማኝና ግልጽ ሴት ተብላ መታወስ ትሻለች፡፡

የሚቀጥራት ድርጅት ባሰመራቸው መስመሮች ውስጥ ታጥሮ መስራት ለሳባ ፈተና ነው፡፡ በተፈጥሮዋ ጠያቂና መርማሪ በመሆኗ ሁልጊዜ “ለምን?” ብላ ትጠይቃለች፡፡ ከተበጀው አጥር  ተሻግራ መጓዝ ስለምትሻ አንዳንዴ ከሰዎች ጋር ያጋጫታል፡፡ ሁሉን “አሜን” ብላ የማትቀበል ሰው መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምንም ነገር ከመስማማቷ በፊት ያሉትን አማራጮች ሁሉ ትፈትሻለች፡፡

ከምንም ተነስተው ግዙፍ ዝናን የገነቡትን ኦፕራ ዊንፍሬይና ማይክል ጃክሰንን ከልቧ ታደንቃለች፡፡ ወደ አገር ቤት ስትመጣ ደግሞ በ1960ዎቹ በወህኒ ቤት የምታውቃትን ሲስተር ጀምበሬ (አሁን ዶ/ር ጀምበሬ) እንደ አነቃቂ አርአያ ትመለከታታለች፡፡ ለሌሎች ምቾትና ደህንነት የምትጨነቀው ዶ/ር ጀምበሬ፤ ራሷን ወይም ቤተሰቦቿን የማታስቀድም፣ ሁሌም እርዳታዋን ከሚፈልጉ በርካታ ሰዎች አጠገብ የማትጠፋ ሴት እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ የሰዎችን እውነተኛ ማንነት የምትረዱት በከባድ ችግርና መከራ ወቅት ሁለመናቸውን ለሌሎች ሰዎች ሲሰጡ ነው ትላለች – ሳባ፡፡ ለልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች ስትመክር፤ “በአሁኑ ዘመን ብዙ የምትጠቀሙበት አማራጭ እንዳላችሁ ተገንዘቡ፡፡ ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው እንኳ የአሁኑ ዓለም የተሻለ ነው” ትላለች፡፡

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከሳባ ኪዳነማርያም ገብሩ ጋር ነሐሴ 2004 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ሜላት ተክለፃዲቅ፤ ወደርየለሽ አበበ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>