Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሮማን ዴቅሲሶ በዳሶ

Roman Deksiso 1

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
የባለቤቷን መታሰር ተከትሎ፣ በአዳማ የተከበረና ስኬታማ የእህል ንግድ መስርታለች፤ የአዳማ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ማህበርን በመስራችነት አቋቁማ ትመራለች፤ የኦሮሚያ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ነች።
ወቅታዊ ሁኔታ የአዳማ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ የኦሮሚያ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት
የትውልድ ቦታ: አሰላ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1958
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዳማ፣ ኢትዮጵያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
አሰላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ሮማን ዴቅሲሶ፣ የአዳማ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበርን ለማቋቋም ስትል ንብረቷን ሁሉ ያጣች አስገራሚ ሴት ነች። በእህል ንግድ ስኬታማ ድርጅት የፈጠረችው ሮማን፤ ሃብት ለማፍራት ብትችልም እርካታ አልተሰማትም። የአካባቢዋን ድሃ ሴቶች ለመርዳት አለመቻሏ እረፍት ነሳት። ይህን የውስጥ ህመም ለመፈወስ ነው፤ ለማህበር ምስረታ ቅድሚያ ሰጥታ ለመሥራት የወሰነችው። በአነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶችን በአባልነት ያቀፈው ማህበር፤ ሙያዊ ስልጠናና ምክር በመስጠት የሴቶችን አቅም ለማጠናከር እየሠራ ነው።

በአሰላ አርሲ ተወልዳ ያደገችው ሮማን፤ እዚያው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ነው ገላውዲዮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመግባት ኑሮዋን ወደ አዳማ ያዛወረችው። የጀመረችውን ትምህርት ሳትጨርስ ትዳር ብትመሰርትም፤ ትምህርቷን አላቋረጠችም። ባረገዘችበትና በወለደችበት ጊዜ ሁሉ ሳይቀር አንዴም ሳታቋርጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ ሃዋሳ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብታለች። በሰርቲፊኬት ከተመረቀች በኋላ፤ በተለያዩ የመንግሥት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የባልትና የአማርኛና የእንግሊዝኛ አስተማሪ ሆና ሰርታለች። ግን የአስተማሪነት ህይወቷ ለብዙ ጊዜ አልቆየም። በ1980 ዓ.ም ባለቤቷ ሲታሰር፤ የሮማንና የቤተሰቦቿ ኑሮ ፈተና ላይ ወደቀ። በአስተማሪነት የምታገኛት አነስተኛ ደሞዝ ቤተሰቧን ለማስተዳደር  የምትበቃ አይደለችም። በዚህ ችግር ሳቢያ ስራዋን ለመልቀቅ የተገደደችው ሮማን፤ አራት ልጆቿን ለማሳደግ ወደ ንግድ ዓለም ገባች። ግን ለመነሻ የሚሆን ገንዘብ አልነበራትም። ከዘመድ አዝማድ ተበድራ ነው የእህል ንግድ የጀመረችው። “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” እንዲሉ፤ ሮማን ዙሪያዋን ከከበባት የድህነት ችግር ተመንጥቃ አመለጠች። ቀስ በቀስ ንግዷ እየደራ፣ አቅሟም እየፈረጠመ በስኬት መጓዝ ጀመረች። በዚያ ላይ፣ የተዋዋለችውን የማታፈርስና በቃሏ የምትገኝ እምነት የሚጣልባት ነጋዴ መሆኗን በተግባር ስላስመሰከረች፤ ስኬቷ ለተጨማሪ ስኬት በር ከፈተላት። በአዲስ አበባ ለሚገኙት ለዲኤች ገዳ እና ለአድዋ ዱቄት ፋብሪካዎች፣ በኮንትራት እህል ለማቅረብ ተደራድራ ተዋዋለች። ያለማቋረጥ እያደገ በመጣው የሮማን ንግድ ላይ፣ ሁለቱን የኮንትራት ውሎች የጨመረችበት ጊዜ፤ በአዳማ ውስጥ ስመጥር ነጋዴነቷን በአለት መሰረት ላይ ተተከለ ማለት ይቻላል። ታዲያ አጀማመሯ ፈተና አልነበረውም ማለት አይደለም። ለንግድ የምታስመጣውን እህል የምታስቀምጥበት መጋዘን አልነበራትም። በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ነበር መጋዘን የምትከራየው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የከተማዋ አስተዳደር በከተማዋ ዳርቻ አነስተኛ መሬት ስለሰጣት፤ ተለቅ ያለ መጋዘንና መኖሪያ ቤት በ200ሺ ብር ወጪ ሰርታለች።

እንዲህ እንዲህ እያለች ንግዷን እያስፋፋች እስከ 1996 ዓ.ም ብትቀጥልም፤ የውስጥ እርካታ አልተሰማትም። ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ዝቅተኛ ቦታ፣ የአእምሮ እረፍት አልሰጣትም። በዙሪያዋ በርካታ ሴቶች በድህነት ተዘፍቀው እያየች፤ በሃብት ንብረቷ መደሰት አልዋጥልሽ አላት። እናም፣ ውሎና ሃሳቧ ተቀየረ። ሴቶች በማህበር መደራጀት እንዳለባቸው በማሰብ መቀስቀስ ጀመረች። ተደራጅተው ሴቶችን ከጓዳ ወደ አደባባይ እንዲወጡ፤ በጋራ እየሰሩም ህይወታቸውን ለማሻሻል እንዲደራጁ ለማነሳሳት ያደረገችው ጥረት እንዲህ ቀላል አልነበረም። ከጎኗ ሆነው የሚያግዙ ጥቂት ሴቶችን አግኝታለች። ግን በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም። ጊዜንና ጉልበትን ይጠይቃል። ስለ ራሷ ንግድ ማሰብና መሥራት የምትችልበት ጊዜ እያጠረ መጣ። በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩና በድህነት የሚኖሩ ሴቶችን የሚወክልና የሚደግፍ ማህበር ማቋቋም ያስፈልጋል እያሉ በአዳማ ጎዳናዎች ሲቀሰቅሱና ሲሰብኩ መዋል ሆኗል፤ የሮማንና የፈር ቀዳጅ ባልደረቦቿ የእለት ተእለት ሥራ። በዚህ ወከባ መሃል ነው በመጋዘን የተከማቸው የሮማን እህል ተበላሽቶ ከጥቅም ውጭ የሆነው። ምንም ልታደርገው አትችልም፤ ያ ብዙ ገንዘብ ያወጣችበት እህል አፈር ሆኗል። ነገር ግን፤ ቅስሟ አልተሰበረም። እንዲያውም፤ በንግድ ሥራዋ ላይ የደረሰባት ታላቅ ውድቀት፤ ሴቶችን የማደራጀት እምነቷን ይዛ ይበልጥ በጥረቷ እንድትበረታ ቁጭት ፈጥሮባታል። ደግነቱ ጥረቷ ከንቱ አልቀረም። በ1993 ዓ.ም የአዳማ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ተመስርቶ ከኦሮሚያ የፍትህ ቢሮ የምዝገባ ፈቃድ አግኝቷል። ማህበሩ ቢመሠረትም፤ ቁምነገር ሰርቶ ለማሳየት የሚበቃ አቅም አልነበራቸውም። የገንዘብ ድጋፍም ሆነ ቢሮ፤ ወንበር ጠረጴዛም ሆነ የሥራ ቁሳቁስ አላገኙም። 28 የማህበሩ አባላት በሚከፍሏት 10 ብር ወርሃዊ መዋጮ ብቻ ነው እንቅስቃሴ የጀመሩት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፤ በአዳማ ቪዥን ከተሰኘ የረድኤድ ደርጅት ድጋፍ አገኙ። የማህበሩ አባላት ተገናኝተው የሚነጋገሩበት ቢሮ ከነቁሳቁሱ  በማዘጋጀት እገዛ የሰጣቸው ቪዥን፤ አንድ የቢሮ ሰራተኛ እንዲቀጥሩም ለ18 ወራት የሚዘልቅ ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። ነገር ግን፤ ማህበሩ አልተጠናከረም። የአባላቱ ሕይወት ላይ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ለውጥ ለማምጣት ስለተሳነው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአባላቱ ተስፋ እየተመናመነ ማህበሩን ጥለው መውጣት ጀመሩ።

እየከፋ የመጣው የማሕበሩ አባላት ቅሬታ ለሮማን የተደበቀ አልነበረም። የማሕበሩ ፕሬዚዳንት እንደመሆኗም፤ አንዳች መፍትሄ ለማግኘት ማሰብ ማሰላሰል ያዘች።  በጉልትና በተመሳሳይ አነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩት ድሃ ሴቶች ላይ ተጨባጭ የህይወት  ለውጥ ማምጣት የግድ ነው። ለዚህ የሚያግዙ ለጋሽ ድርጅቶችን በማፈላለግ ላይ እያለች ነው፤ አንድ ቀን የመፍትሄ ጭላንጭል የታያት። ለሴት ሥራ ፈጣሪ ማሕበራት የተዘጋጀ ውድድር አጋጠማት። በውድድሩ የሚያሸንፍ ማሕበር፤ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትለታል። ነገር ግን የመወዳደሪያ ጊዜው ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፤ አንድ ቀን ብቻ ነበር የቀረው። ሮማን እንደምንም የማሕበሩን አባላት አስተባብራ፤ ከክልሉ መስተዳድርም የድጋፍ ደብዳቤ አስፅፋ የመወዳደሪያ ሃሳብ አቀረበች፤ በውድድሩም ማሕበሩ አሸንፎ ገንዘብ ተሸለመ። ለማሕበሩ ስራ የሚያስፈልጉ የተወሰኑ ቁሳቁሶችን ለመግዛት የተቻለው በሽልማት በተገኘው ገንዘብ ነው። 75 ሺ ብር ደግሞ፣ ለማሕበሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የተሃድሶ ፕሮግራም እንዲመደብ ታስቧል። ሮማን ግን ይህንን ሰርዛ፤ በገንዘቡ 10 ጠንካራ ድንኳኖችን ለመግዛት ወሰነች። ውሳኔዋ በማሕበሩ ላይ ያመጣው ለውጥ፤ ልዩ ነው። የምትታለብ ላም ከማግኘት አይተናነስም። በአዳማ ለሚዘጋጁ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች የሚከራዩት ድንኳኖች፣ ለማሕበሩ የማያቋርጥ የገቢ ምንጭ ሆነውለታል። በመጀመሪያው ባዛር ብቻ 48ሺ ብር አስገብቶላቸዋል። ማሕበሩ የራሱን ገቢ ማግኘት ከጀመረ በኋላ ዋና አላማው ላይ በማተኮር፤ ለአባላቱ 11 የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን አዘጋጅቷል። የሶስት ወር፣ የስድስት ወር እና የአንድ አመት  የሙያ ስልጠና ያጠናቀቁ የማሕበሩ አባላትም፤ በሰርቲፊኬትና በዲፕሎማ ለመመረቅ በቅተዋል። ይሄኔ በማሕበሩ አባላት ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መታየት ጀመረ። የሙያ ስልጠናው በንግድ ሥራቸው ላይ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋልና።

ሮማን፤ የአዳማ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ማሕበርን በፕሬዚዳንትነት፤ የኦሮሚያ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ማሕበርን በምክትል ፕሬዚዳንትነት፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪዎች ማሕበርን በፀሃፊነት ያለ ደሞዝ ለበርካታ ዓመታት አገልግላለች። በበርካታ ክልላዊ ስራዎችና ድርጅቶች ውስጥም በቦርድ አባልነት ትሳተፋለች። ልቧ እንደተመኘው የአዳማ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ማሕበር፣ ውጤታማ የሙያ ተቋም ለመሆን በመብቃቱና እንደተመኘችውም የሴቶች ሕይወት ሲሻሻል በማየቷ፤ ስትፈልገው የነበረውን እርካታ አግኝታለች። \”ሴቶች የተሰጣቸውን ማንኛውንም ስራ መተግበር ይችላሉ። ስለዚህ፣ በራሳችን አቅምና ስራ እንተማመን\” ትላለች – ሮማን።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከሮማን ዴቅሲሶ ጋር በሐምሌ 2ዐዐ4 ዓ.ም. የተደረገ ቃለምልልስ
አጥኚ
ቤተል በቀለ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>