Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ሪታ ፓንክረስት

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
ከ1948 -1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመፃህፍት/ወመዘክር/ በቤተመፃህፍት ባለሙያነት ሰርታለች። ከ1956 – 1967 ዓ.ም የቀዳማዊ ኀይለስላሴ  ዩኒቨርስቲ የመጀመርያዋ የቤተመፃህፍት ሃላፊ ሆና አገልግላለች። የለንደን ሲቲ ፖሊቴክኒክ የቤተመፃህፍት አገልግሎት ሃላፊ ነበረች፣ በእንግሊዝ ሴቶች በምርጫ ለመሳተፍ ያደረጉት  ትግል ላይ ያተኮሩ መፃህፍትን የያዘው የፋውሴት ሶሳይቲ ቤተመፃህፍት ክፍል ወደ ፖሊቴክኒክ ቤተመፃህፍት እንዲመጣ  አስተባብራለች፤ በዚሁ ሰበብ  በሴቶች ጉዳይ ንቁ  ተሳታፊ ልትሆን ችላለች።  የኢትዮጵያ ሴቶች የታሪክ ሚና ላይ ያተኮሩ በርካታ መጣጥፎች ፀሃፊ ናት።
ወቅታዊ ሁኔታ ከመደበኛ ስራ ጡረታ የወጣች፤ የማህበረሰብ በጎፈቃድ አገልጋይ እና ደራሲ/ፀሃፊ/
የትውልድ ቦታ: ሮማንያ
የትውልድ ዘመን: በ1919 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ስቴት የመጀመርያ ደረጃ ት/ቤት፣ አያሲ፣ ሮማንያ
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ፐርስ የልጃገረዶች ት/ቤት፣ ካምብሪጅ፣ ዩኬ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
ቢኤ ኤምኤ፣ በዘመናዊ ቋንቋዎች፣ ሌዲ ማርጋሬት ሆል፣ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣  1940፣ 1947 ዓ.ም
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ዲፕሎማ፣ የሩሲያ ቋንቋ፣ ኢኮሌ ናሽናሌ ዴስ ላንጉስ ኦሬንታልስ ቪቫንቴስ፣ ፓሪስ
ዋና የስራ ዘርፍ
የቤተመፃህፍት ባለሙያ
የሕይወት ታሪክ
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመፃህፍት /ወመዘክር/ በቤተመፃህፍት ባለሙያነት የሰራችው ሪታ ፓንክረስት፤ በያኔው የቀዳማዊ ኀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ የቤተመፃህፍቱ ዳይሬክተር ሆና በመሾም ያገለገለች ሲሆን ይሄም በኢትዮጵያ የመጀመርያዋ የዩኒቨርስቲ ቤተመፃህፍት ሃላፊ ያደርጋታል። በአፍሪካም በተመሳሳይ ሃላፊነት ከሰሩ ጥቂት ሴቶች አንዷ ናት። በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገራት የቤተመፃህፍት ባለሙያዎችን ሙያዊ ክህሎት ለማሻሻልና ለማሳደግ በንቃት ተሳትፋለች። ደከመኝ ሰለቸኝ የማታውቀው ሪታ፤ የአፍሪካ ዩኒቨርስቲ የቤተመፃህፍት ባለሙያዎች ማህበርን በአባልነት ከመመስረቷም በተጨማሪ በዋና ፀሃፊነትም አገልግላለች። የኢትዮጵያውያን አኗኗርና ባህል ቀልቧን የማረከው ሪታ፤ የኢትዮጵያ ሴቶችን የታሪክ ሚና የሚያሳዩ በርካታ መጣጥፎችን በመፃፍ ትታወቃለች።  በበርካታ ተቋማት ቦርዶች ውስጥ በማገልገልም በአዲስ አበባ የሲቪል ማህበረሰብ ህይወት ውስጥ በንቃት ተሳትፋለች ።በ1919 ዓ.ም በሮማንያ ለፖለቲካ እንግዳ ከሆነ የአይሁድ ቤተሰብ የተወለደችው ሪታ፤ በ10 ዓመቷ በ1930 ዓ.ም መባቻ ላይ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ እንግሊዝ ሄደች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ላይ ቤተሰቦቿ ከሩማንያ የወጡት ለሽርሽር ወይም አገር ለመለወጥ  አልነበረም። የባንክ ባለሙያ የነበሩት አባቷ፤ የቤተሰባቸው  የወደፊት እጣፈንታ ስላስጨነቃቸው እንጂ። ከእናቷ የጣዕምን ነገር፣ አትክልቶችን መንከባከብ፣ አበቦችን አሳምሮ ማሰናዳት፣ ቤት ማስጌጥን እና ቤተሰብ ማስተዳደርን የተማረችው ሪታ፤ ሙዚቃን ማድነቅና ማጣጣም ደግሞ  ከአባቷ ተምራለች። ዛሬም ድረስ ታዲያ በአዲስ አበባ የማህበረሰብ ዘማሪ ቡድን ውስጥ ትሳተፋለች።  ከት/ቤት የቅርብ ጓደኞቿ አንዷ አርአያ ሆናኛለች የምትለው ሪታ፤ ይጎድለኛል ብላ የምታስበውን /ታሪኳ እንደጎደላት ባያሳይም/ ራስን ለሌሎች የመስጠት መልካምነት ከዚህች ጓደኛዋ መማሯን ትገልፃለች።

በካምብሪጅ ፐርስ የልጃገረዶች ት/ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከተከታተለች በኋላ በሌዲ ማርጋሬት ሆል፣ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ዘመናዊ ቋንቋዎችን /ፈረንሳይኛና ሩሲያኛ / አጥንታ በ1940 ዓ.ም የመጀመርያ ድግሪዋን አግኝታለች። ሆኖም የሩሲያን ስነፅሁፍ ከነጣዕሙ  ለማንበብ አላጠገባትም። ስለዚህም  በቀጣዩ ዓመት በፓሪስ የሩሲያ ቋንቋ ከሚናገር የአርመኒያ ቤተሰብ ጋ እየኖረች፣ በኢኮሌ ናሽናሌ ዴስ ላንጉስ ኦሬንታልስ ቪቫንቴስ፣ የሩሲያ ቋንቋ ተምራ  ዲፕሎማዋን አገኘች። የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ የሆነችው ሪታ፤ የሮማንያ፣ የጀርመንና የፈረንሳይ ስራዎችን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉማ  በለንደን ታትሞላታል።

የመጀመርያ ስራዋን የተቀጠረችው ቻትሃም ተብሎ በሚታወቀው የሮያል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም ውስጥ ባለ የፕሬስ ቤተመፃህፍት ነበር። ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ምሁራዊና ሙያዊ ፅሁፎችን እንደ ዓይነታቸው በስርዓት ማደራጀትና ትኩረት የሚስቡ ማራኪ መጣጥፎች ላይ ምልክት እያደረገች በዓይነታቸው መሰደር ነበር – ስራዋ። እስከ 1947 ዓ.ም የቤተመፃህፍቱ  የሙሉ ሰዓት ተቀጣሪ ሆና ያገለገለችው ሪታ፤ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ደግሞ በትርፍ ሰዓቷ ሰርታለች። ከዚሁ ጎን ለጎን በተከበረውና  «ሺምቡን» በተሰኘው የጃፓን ጋዜጣ የለንደን ቢሮ ውስጥ የፕሬስ መረጃ በማደራጀት ትሰራ ነበር። የቼኾቭን አዲስ የትርጉም ስራም የጀመረችውም በዚሁ ጊዜ ነው።  ማታ ማታ ደግሞ በምስራቅ ለንደን፣ ቶይንቢ ሆል የተባለ የጎልማሶች ትምህርት ተቋም ውስጥ ፈረንሳይኛ ታስተምር ነበር። ይሄኔ ነው በ1947 ዓ.ም የወደፊቱን ባለቤቷን ሪቻርድን የተዋወቀችው። ያስተዋወቃቸው ደግሞ ንጉስ ኀይለስላሴ ባርነትን ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ያማክራቸው የነበረው የቶይንቢ ሆል ተቋም ሬጂስትራሩ ነበር። በሐምሌ 1948 ዓ.ም ሪቻርድ ከእናቱ ከሲልቪያ ጋ ወደኢትዮጵያ ለመጓዝ ሲነሳ፣ ሪታም አብራው እንድትጓዝ ጋበዛት – በኢትዮጵያ ኑሮአቸውን በጋራ መመስረት ይችሉ እንደሆነ ለማየት። የኢትዮጵያ ጉብኝቷ ለሪታ ስኬታማ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ከሪቻርድ ጋር ትዳር ለመመስረት ወሰኑ። በእርግጥ የንጉሱ ልጅ የሃረሩ መስፍን በግንቦት 1949 ዓ.ም በመኪና አደጋ ድንገት በመሞቱና ቤተመንግስት ለቅሶ ስለነበር ሰርጋቸው ከታቀደበት ጊዜ ዘግይቶ ነበር።

ሪታ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመፃህፍት ውስጥ ለመቀጠር ጊዜ አልፈጀባትም።  ሙያዊ ፅሁፎችን  በስርዓት ከማደራጀት በቀር በዘርፉ ብዙ ልምድ አልነበረኝም ብትልም ስራውን መጀመሯ ግን አልቀረም። ወዲያው ግን የቤተመፃህፍት ሙያ  በተልዕኮ መማር ጀመረች። በኋላ ላይ ትምህርቱ ተስተጓጎለ – በወሊድ። በ1956 ዓ.ም የቤተመፃህፍት ማህበርን /ALA/ ሙሉ አባልነት ያገኘችው ሪታ ፤ በኋላም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ላበረከተችው አገልግሎት የክብር አባልነት /Honarary Fellowship/ ተሰጥቷታል – በ1979 ዓ.ም።

በወቅቱ ሪታ የቤተመፃህፍቱን የአንባቢያን አገልግሎት ክፍሉን ስታስተዳድር፣ ጀርመናዊው የቤተመፃህፍት ባለሙያ ሃንስ ሎኮት ደግሞ የተመራማሪዎች አገልግሎት ክፍልን ይመራ ነበር። ስር የሰደደ የመፃህፍት ችግርና የቁሳቁስ እጥረት እንዲሁም ያረጀ ያፈጀ ኋላቀር አስተዳደር የገጠማት ሪታ፤ ቤተመፃህፍቱን በዘመናዊ መንገድ ማዋቀርና የሰለጠነ የሰው ኀይል እንደሚያስፈልግ ተገነዘበች። ያኔ ደግሞ መደበኛ የቤተመፃህፍት ሙያ ስልጠና አልነበረም፤ ስለዚህም ዎርክሾፖችና የክረምት ስልጠናዎችን ማዘጋጀት ጀመረች። ለራሷ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአዲስ አበባ  ቤተመፃህፍት ሰራተኞችም ጭምር።

በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከባህር ማዶ እየተመለሱ መሆናቸውን ያስተዋለችው ሪታ፤ የተማሪዎቹን ፍላጎት የሚያሟላ የመፃህፍት ስብስብ ለማቅረብ አልማ ተነሳች። በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች ጋ በቀጥታ በመሄድም የመፃህፍት እርዳታ ጥያቄ አቀረበች። አላሳፈሯትም። መጀመርያ የህንድ ኤምባሲ ከዚያም የአሜሪካ፣ የብሪቲሽና የሩስያ ኤምባሲዎች እያንዳንዳቸው 1ሺ የሚደርሱ በርካታ መፃህፍትን ለግሰዋል።

ሪታ መፃህፍት በማሰባሰብ ብቻ ግን አልተወሰነችም። ትርጉም ያለው ለውጥ ፈጥሯል ብላ የምታምንበትን አዲስ የፈጠራ ሃሳብ ተግብራለች። ለአፍሪካ ነፃነት የታገሉ ታላላቅ  መሪዎች በአካል የሚገኙበት ምሁራዊ ጉባኤዎችን አዘጋጅታለች። በእርግጥ ብቻዋን አልነበረችም። ባለቤቷ ሪቻርድና እናቱ ከጎኗ አልተለዩዋትም – ድጋፍ በመስጠትና በማበረታታት።  በ1950 ዓ.ም ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት የመጀመርያ ጉባኤ በጋና መዲና፣ አክራ የተካሄደ ሲሆን በዓመቱ ሁለተኛው ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲዘጋጅ ትልቅ ስሜትና ጉጉት ፈጥሮ ነበር። ለስብሰባው የመጡ አንፀባራቂ የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች ሪታ ባዘጋጀችው ምሁራዊ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል። ከእነሱም መካከል ጆሞ ኬንያታ፣ ክዋሜ ንክሩማህ፣ ጁሊየስ ኒሬሬ እና የኬንያ ሰራተኞች ፌደሬሽኑ ቶም ምቦያ እንዲሁም እውቋ ኢትዮጵያዊት ዲፕሎማት ዮዲት እምሩ ይገኙበታል። ዮዲት ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታት በመወከል የመጀመርያይቱ ኢትዮጵያዊ ሴት ናት። ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ጉዳዮች  እምብዛም ፍላጎት የላቸውም ከሚለው የውጭ ሰዎች እሳቤ በተለየ ጉባኤው በርካታ ታዳሚዎችን አሰባስቦ ነበር። ምሁራዊ ጉባኤዎቹ  ወጣት ኢትዮጵያውያንን ከአንጋፋዎቹ  የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች ጋር ማገናኘት ብቻ ሳይሆን አያሌ ወጣቶች ከቤተመፃህፍቱና በእቅፉ ከያዛቸው የዕውቀት ሃብቶቹ ጋር እንዲተዋወቁ አድርጓል።

በዚህ ወቅት ነው ሪታ ከንጉሱ ጥሪ የደረሳት። ንጉሱ በውጭ አገር ጉዟቸው የተበረከቱላቸው ስጦታዎች የሚታዩበት ሙዚየም እንድትከፍት ታዘዘች። የሙዚየም ዝግጅት ስልጠና ባይኖራትም የታዘዘችውን ለመፈፀም መትጋቷ አልቀረም- ከመደበኛ የቤተመፃህፍት ስራዋ ጎን ለጎን። በርካታ ድርጅቶች ቤተመፃህፍት በማቋቋም ስራ እንድታግዛቸውም ጥሪ ይቀርብላት ነበር – ፓርላማ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና ወዘተ ይገኙበታል። በዚህ የስራ ውጥረት ሪቻርድ የመፃህፍት ዝርዝሮችን በማዘጋጀት ሲረዳት፣ እሷ ደግሞ የመፃህፍት ግዢ  ትእዛዝ ትሰጥ  ነበር።

በጊዜው ከነበረው የቤተመፃህፍት ባለሙያዋ  እጥረት አንፃር ሪታ፣ የበጎ ፈቃደኞች እገዛን በእጅጉ መጠቀም ነበረባት። ከእነዚህ በጎ ፈቃድ አገልጋዮች  ሁለቱ በውጤታማ  ስራቸው ተጠቃሽ ናቸው – የንጉሱ የልጅ ልጅ ልዕልት ሩት ደስታና ከበርካታ ዓመታት በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የሆነው አንድርያስ እሸቴ። ትሁትና  ሃይማኖተኛ የነበረችው ልዕልት ሩት፤ ከፍተኛ ሃላፊነት የሚሰማት የቤተመፃህፍት በጎፈቃደኛ እንደነበረች ሪታ ታስታውሳለች። እመጣለሁ ባለች ሰዓት የምትመጣ ቃሏን አክባሪ ሴት ነበረች። በዚህም ለሌሎች በጎ ፈቃደኞችና የቤተመፃህፍቱ ሰራተኞች ግሩም ምሳሌ ነበረች ትላለች- ሪታ። ያኔ አንድ ፍሬ ልጅ የነበረው የ12 ዓመቱ አንድሪያስ፤ አንብቦ የማይጠግብ የመፅሃፍ ቀበኛ እንደነበር የምታስታውሰው ሪታ፤መፅሃፍት ተውሰው ለማይመልሱ አስቸጋሪ አንባቢዎች መድሃኒታቸው ነበር ትላለች። ስልክ እየደወለ «መፅሃፉ ቤተመንግስት ስለተፈለገ በአስቸኳይ መልሱ» ይል ነበር። ይህ ብልሃቱ ሁሌም ይሰራለት እንደነበር ሪታ ትመሰክራለች።

በመስከረም17 ቀን 1952 ዓ.ም የሪታ አማት የነበሩት ዕውቋ ሲልቪያ ፓንክረስት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።  ደከመኝ ታከተኝ የማያውቁት የእኚህ ሴት ህይወት ማክተም ለሪቻርድና ሪታ ከፍተኛ ሃዘን ነበር። የሃዘን ማስረሻ ግን አላጡም። ሪታ በ35 ዓመቷ የመጀመርያ ልጇን አረገዘች። የጥንዶቹ ህይወትም በደስታ ተጣመረ።  በሐምሌ 1954 ዓ.ም ሪታ ልጇን  እንግሊዝ አገር  ለመውለድ ከቤተመፃህፍት ስራዋ  ለመልቀቅ ተገደደች። መስከረም 17 ቀን 1954 ዓ.ም ሲልቭያ በሞቱ በሁለተኛው ዓመት አሉላ ተወለደ።

በዚያው ዓመት ማገባደጃ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ሪታ፤ በህንፃ ኮሌጅ ቤተመፃህፍት ነበር ስራ የጀመረችው – መፃህፍትን በዓይነታቸው በመመዝገብና በማደራጀት።  ኮሌጁ ለቤቷ በሚያመች ቦታ  ስለነበር ምሳ ሰዓት ላይ ቤቷ ጎራ ብላ ልጇን አጥብታ ትመለስ እንደነበር ሪታ ታስታውሳለች። ለጥቂት ጊዜ እዚያ ከቆየች በኋላ በ1956 ዓ.ም ሁለተኛ ልጇን ሄለንን ከመውለዷ በፊት የዩኒቨርስቲ ቤተመፃህፍት ሃላፊ በመሆን ተሾመች። ይሄን ጊዜ ነበር 20 ሺ ገደማ መፃህፍትን ከአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ቤተመፃህፍት ወደ ስድስት ኪሎ ያስመጣችው። ምክንያቱም በፎርድ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራው የጆን ኤፍ ኬኔዲ ህንፃ  እየተጠናቀቀ ነበር። በ1957 ዓ.ም መፃህፍቱ ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ የጆን ኤፍ ኬኔዲ ቤተመፃህፍት ተዛወረ። ሪታ በዩኒቨርስቲ የቤተመፃህፍት ሃላፊነቷ ወቅት ነው የአስራ አንድ ኮሌጆች ወይም ተቋማት ቤተመፃህፍትን ወደ አንድ የአሰራር ስርዓት ያመጣችው  –  እንደ አሜሪካው ኮንግረስ ላይብረሪ ፣ ለተመሳሳይ መፃህፍት ተመሳሳይ መለያ ቁጥር የሚሰጥበት የአሰራር ስርዓትን በመተግበር።

በኢትዮጵያ የሰለጠኑ የቤተመፃህፍት ባለሙያተኞች ለመፍጠር በእጅጉ የሚያስፈልገውን ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘት በወቅቱ ከባድ ፍልሚያ ነበር። ምክንያቱም ከዩኒቨርስቲው ዲፓርትመንቶች ከፍተኛ ፉክክር ስለነበር ለቤተመፃህፍት ባለሙያ ነፃ የትምህርት እድል ማግኘት የማይታሰብ ነው። ሆኖም በወቅቱ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት የነበሩት አክሊሉ ሃብቴ ምስጋና ይግባቸውና፣ በርካታ የነፃ ትምህርት ዕድሎች ለቤተመፃህፍት ባለሙያዎች እንዲደርስ በብልሃት እገዛ አድርገዋል።

በ1968 ዓ.ም ደርግ ስልጣኑን ሲያጠናክርና  የእርስ በእርስ ግጭት አይቀሬ ሲመስል፣ ሪቻርድና ሪታ ተመልሰው ወደ እንግሊዝ ሄዱ – የልጆቻቸው  ትምህርት አለመስተጓጎሉን  ለማረጋገጥና ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ።

እንግሊዝ ከሄዱ በኋላ የለንደን ሲቲ ፖሊቴክኒክን የተቀላቀለችው ሪታ፤ የቤተመፃህፍት አገልግሎት ሃላፊ በመሆን ስራ ጀመረች። እዚያ በነበራት የአስር ዓመት አገልግሎት በዝነኛው የፋውሴት ሶሳይቲ ላይብረሪ ውስጥ የነበሩ ሴቶች በምርጫ ለመሳተፍ ያደረጉት  ትግል ላይ ያተኮሩ መፃህፍትን  ወደ ፖሊቴክኒክ ቤተመፃህፍት በማምጣት ጀብዱ ፈፅማለች። በእርግጥ ያኔ በሴቶች ጥናት ላይ ያተኮሩ ኮርሶች አይሰጡም ነበር። ሆኖም ፅሁፎቹ የቤተመፃህፍቱን የቀድሞ ስብስብ በማበልፀግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ከዚያም ቤተመፃህፍቱ የሴቶች ቤተመፃህፍት የሚል አዲስ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በሴቶች ላይ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችም ሁነኛ የመረጃ ምንጭ ለመሆን በቅቷል። ቀደም ሲል ከፋውሴት ሶሳይቲ ጋር ባደረገችው ድርድር የተመሳ የሴቶች እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሆነችው ሪታ፤ ታላላቅ አርአያዎቼ ከምትላቸው አንዷ ከሆነችው ሜሪ ስቶት ጋር ተዋወቀች። በአንድ ወቅት የ«ማንችስተር ጋርድያን» ጋዜጠኛ የነበረችው ሜሪ ስቶት፤ ሰዎች ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲሰሩ ማደራጀትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ነገሮችን እንዳስተማረቻት ሪታ ታስታውሳለች። በእርግጥ ለሴቶች መታገል በሪታ ብቻ አልቆመም። ልጇ ሄለንና የልጅ ልጇ ላውራ በተራቸው ሴቶች በዓለም መድረክ ያላቸው ቦታ እንዲሻሻል እየሰሩ ነው።

ሪታ  በ1980 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሳትፋለች።  የቤተመፃህፍት የማማከር ስራ በማከናወን፣ የምሁራን መፅሃፍትንና የዩኒቨርስቲ የጥናት ፅሁፎችን በማረምና በማስተካከል እንዲሁም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጊዜዋን አሳልፋለች። በኢትዮጵያ የነበረውና ለውጭ አገር የነፃ  ትምህርት እድል ተማሪዎችን የሚመርጠው የዓለም ኮሌጆች ብሄራዊ ኮሚቴን በሊቀመንበርነትና በአባልነት አገልግላለች። የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም ወዳጆች ማህበርን  የፕሮግራም ኮሚቴን መርታለች። የኢትዮጵያ ጂሚኒ ትረስትና የኢትዮጵያ ቅርስ ጠባቂ ባለአደራ ማህበር የቦርድ አባል በመሆንም ሰርታለች። በ1929 ዓ.ም የጣልያን ወረራ ወቅት ወደ ጣልያን የተወሰደውን የአክሱም ሃውልት ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ከሪቻርድ ጋር በመሆን ከልቧ የተጋች ሲሆን የማታማታ የጥረታቸውን ፍሬ ለማየት በቅተዋል።

በሪታ ህይወት ላይ በጎ ተፅዕኖ ካሳረፉባት ሰዎች ሁሉ ሶስቱ ይበልጥ ባለውለታዋ ናቸው።  ባለቤቷ ሪቻርድ ስለመቻቻልና ሌሎችን ስለማድነቅ አስተምሯታል። ከእናቱ ከሲልቪያ ጋር ሆኖም ስለታታሪነትና ለዓላማ ራስን ስለመስጠት እንዳስተማሯት ሪታ ትናገራለች። ስለሴቶች እንቅስቃሴ እንዲሁም  የማደራጀትና የመሟገትን ትርጉም ደግሞ ከግሩም ባልንጀራዋ ሜሪ ስቶት ተምራለች።

የኢትዮጵያ መጪ ዘመን ብሩህ እንደሚሆን  ከፍተኛ እምነት ያላት ሪታ ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ታላቅ መነቃቃት ይታያታል – ሆኖም በእመርታ መነሳት አለበት ትላለች። የትምህርት እጦት፣ አሳሪ ወግና ልማድ ፣ እንዲሁም ብዙዎች  አስከፊ የኑሮ መከራ ቢጋፈጡም ሴቶችን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ፈፅሞ አልተበገሩም። የኢትዮጵያ ሴቶች የአደባባይ ድርሻቸውን  እየጠየቁ ነው። ቀድሞ ባደጉበት በራስ ያለመተማመን ስሜት መደናቀፋቸውም  እየቀረ ነው። እንደሌላው ዓለም ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ውስጥ ጊዜው የሴቶች ነው። ታሪክ ለሴቶች ግስጋሴና ነፃነት ቆሟል ብላ ታምናለች።

ለኢትዮጵያ ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች የሪታ መልዕክት እንዲህ የሚል ነው – «ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት ከወንዶች የበለጠ ሴቶችን እየጎዳ ቢሆንም ለሴቶች አማራጮች  እየጨመሩ በመጡበት በ21ኛው ክፍለዘመን በመኖራችሁ እድለኞች ናችሁ። ብዙዎቻችሁ ት/ቤት እየሄዳችሁ ነው። ይሄ ደግሞ የተሻሉ ስራዎችን ለማግኘትና በብዙ ዘርፎች ስኬታማ ሙያ ለመፍጠር ብዙ አማራጮችን ይከፍታል – በትምህርት፣ በምህንድስና፣ በግብርና፣  በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በህግ፣ በፖለቲካና መንግስት አስተዳደር፣ በስነፅሁፍና ኪነጥበብ። ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከወንዶች ጋር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አጋርነት ለመፍጠር እንደምትሰሩ አምናለሁ። አጋርነቱ በአደባባይ ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥ ልጆችን በመንከባከብም ሊሆን ይገባል። በመንገዳችሁ ላይ በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥማችሁ እኔ አልነግራችሁም፣ በደንብ ታውቁታላችሁ። ነገር ግን በቁርጠኝነት ከተጋችሁ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ትችላላችሁ፣ ደግሞም ታመጣላችሁ። ግባችሁን እንድታሳኩ፣ በዚህም አገራችሁን አገልግላችሁ፣ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ንቁ ተሳታፊ እንደምታደርጓት ምኞቴ ነው።»

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከሪታ ፓንክረስት ጋር  በ 2004 ዓ.ም የተደረገ ቃለምልልስ
ሌላ ምንጮች
አጥኚ
ሸዊት ወልደሚካኤል እና ሜሪ -ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>