Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ምህረት አያሌው ማንደፍሮ፣ ዶ/ር

AlmazDj

ዋና ዋና ስኬቶች:
 

ህብረተሰቡን ስለ ኤድስ የሚያስተምር ትሩዝኤድስ የተሰኘ ደርጅት አቋቁማለች። የድርጅቱ ዌብሳይት(www.truthaids.org) ዋና አዘጋጅ ናት። በአሜሪካና በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሴቶችን ሕይወትየሚዳስስ \\\”ኦል ኦፍ አስ\\\” የተሰኘ ፊልም ሰርታለች። ኋይት ሃውስ ፌሎ በተሰኘው ፕሮግራም ተወዳድራበመመረጧ የአሜሪካ ተሰናባች ወታደሮችን የአእምሮና የሥነልቦና ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ሰርታለች።

 

ወቅታዊ ሁኔታ ጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ፣ የጤና አጠባበቅና የጤና አገልግሎት ትምህርትቤት አስተማሪ – ጥናትና ምርምር ለማካሄድና ለመፃፍ ከአስተማሪነት ሥራእረፍት ወስዳለች
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ
የትውልድ ዘመን: ሰኔ 28 ቀን 1968 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት

ሞንቴሶሪ ትምህርት ቤት፣ ዋይኔ ኦክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ቨርጂኒያ

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ሆልም መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ቶማስ ጄፈርሰን ሁለተኛ ደረጃ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት፣ አሌክሳንድሪያ፣ ቨርጂኒያ

የዩኒቨርስቲ ትምህርት

የመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤበአንትሮፖሎጂ፣ ካም ላውድ፣ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ፣ ዩኤስኤ

የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ

የህክምና ዶክተር (ኤምዲሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ፣ ዩኤስኤ፤ ማስተርስ ዲግሪ (ኤምኤስሲ) ለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲስን (ፉልብራይት ስኮላር) ዩኬ፤የአንትሮፖሎጂ ፒኤችዲ ለመያዝ በመስራት ላይ ትገኛለች፣ ቴምፕል ዩኒቨርስቲ፣ ፊላደልፊያ፣ ፔንሰልቫንያ፣ ዩኤስኤ

ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
 

የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሐኪሟና የማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ተሟጋቿ ዶ/ር ምህረት አያሌው፤ በማህበረሰብ ውስጥ የጤና አጠባበቅ ግንዛቤ ለማሳደግና መፍትሄዎችን ለማበጀት ተመራማሪነትንና አስተማሪነትን፣ የረድኤት ድርጅት መሪነትንና ፊልም ሠሪነትን ያቀናጀች ሴት ናት። የሕክምና ዶክተር፣ የጤና አጠባበቅ ባለሙያና የአንትሮፖሎጂ ምሁር የሆነችው ምህረት፤ በአሜሪካና በአለም ደረጃ ኤችአይቪ ኤድስን ለመግታት እንዲሁም የፆታ ጥቃቶችን ለመዋጋት በሙሉ አቅሟና ከልብ በመነጨ ፍላጎት ሰርታለች። በአሜሪካ የተሰናባች ወታደሮችን የአእምሮና የሥነልቦና ጤና አገልግሎት ሥርዓት ለማሻሻልም አስተዋፅኦ አበርክታለች። በፊላደልፊያ ቴምፕል ዩኒቨርስቲ በአንትሮፖሎጂ ፒኤችዲ ለማግኘት እየሰራች ያለችው ምህረት፤ በጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ የጤና አጠባበቅና የጤና አገልግሎት ክፍል አስተማሪ ከመሆኗም በተጨማሪ፤ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎቿ ጋር በጤናና በማህበራዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ የመማሪያ መፅሀፍ እያዘጋጀት ትገኛለች።

 በአዲስ አበባ ሰኔ 1968 ዓ.ም የተወለደችው ምህረት፤ ከአመት በኋላ አባቷ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ስለተሾሙ ነው ከታናሽ ወንድሟ ጋር ወደ አሜሪካ የተጓዘችው። ቀደም ሲል በንጉሡ ዘመን በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የምህረት አባት፤ አሜሪካ ወደሚገኘው ኤምባሲ ተዛውረው በከፍተኛ ዲፕሎማትነት አገልግለዋል። በደርግ ሳይባረሩ ወይም ሳይታሰሩ በሃላፊነት ቦታ እንዲቀጥሉ ከተደረጉት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ከመሆናቸውም ባሻገር፤ ለመከላከያ ሚኒስትርነት የተሾሙ የመጀመሪያው ሲቪል ባለስልጣን ናቸው። ከግድያ ሙከራ ለጥቂት ካመለጡ በኋላ በወዳጅ ጓደኛ እገዛ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ሹመት ያገኙት የምህረት አባት፤ ከነቤተሰባቸው ወደ አሜሪካ ያቀኑት በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር  ዘመን ነው። የተዋጣላቸው ዲፕሎማት ቢሆኑም፣ የአምባሳደርነት ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አልሞከሩም። ለሕይወታቸው ሰግተው ከነቤተሰባቸው በፖለቲካ ጥገኝነት እዚያው አሜሪካ ቀሩ።

በሕፃኗ ምህረት ውስጥ ጨርሶ የማይደበዝዝ የሕይወት አሻራ ያሳረፉት ወላጆቿ፤ እነሱ ያገኙትን ትምህርትና እድል ልጆቻቸውም እንዲያገኙ የአቅማቸውን ሁሉ መስዋእት ከፍለዋል። በተለይ የትምህርት ነገር አይሆንላቸውም። ኢትዮጵያን ከልብ የሚወዱት የምህረት አባት፤ ከሁሉም በፊት የአገርን ፍቅር ያስቀድማሉ። አስገራሚው ነገር፤ ልጆቻቸው ኢትዮጵያ ሄደው እንዲሰሩ የወተወቱበት ጊዜ የለም። ውትወታው የእናታቸው ድርሻ ነው። ወደ አገር ቤት ተመልሳችሁ ለኢትዮጵያ አንዳች ቁምነገር ሥሩ ብሎ መምከር የምህረት እናት የዘወትር መዝሙር ነበር። ምህረት ይህንን የእናቷን ፍላጎት ትጋራለች። በመጋራት ብቻ እንደማትቀር ደግሞ ይታወቃል። በዚህም በዚያም ብላ ትፈፅመዋለች። ውጥንን ወደ ተግባር የመለወጥ ዘዴ የሚል የራሷ መፅሃፍ ሳይኖራት አይቀርም ይሉ ነበር እናቷ። በሁሉም ቦታ ሁሉንም ነገር ስትሞክር ያያሏ።

የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህቷን በቨርጂኒያ የተተከታተለችው ምህረት፤ በተለይ በቶማስ ጄፈርሰን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምንኛ የሳይንስ ትምህርቶችን ትወድ እንደነበር ታስታውሳለች። በውጤትም የሚስተካከላት አልነበረም። ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በአንትሮፖሎጂ የዲግሪ መርሀግብር የተመዘገበችው ምህረት፤ ሕክምና ለመማር የሚያስፈልጉ ኮርሶችን በሁለት አመት ውስጥ ካጠናቀቀች በኋላ፤ ሶስተኛውን አመት ያሳለፈችው በኬንያ ነው – ለመስክ ትምህርት። ያኔ ነው የሕክምና ሙያ ፍላጎቷ ስር የሰደደው። ከፋታ የለሽ የስዋህሊኛ ቋንቋ ስልጠና ጋር የአንትሮፖሎጂ ኮርሶች በናይሮቢ እየተማረች፣  በማሳይ ማህበረሰብ ውስጥ የመስክ ጥናት ስታካሂድ ለአራት ወራት የቆየችው ምህረት፤ ለመስክ ስራ በሰሜናዊ ኬንያ እልም ወዳለ ገጠር ተመደበች። የቤተሰብ አኗኗር የስልጠና ማዕከል ውስጥ በተሰጣት ስራ፤ በምግብ እጦት እጅግ የተጎዱ በርካታ ሕፃናትን ያስተናገደችው ምህረት፤ አስተሳሰቧን  አናግቶ አቅጣጫ የቀየረ ሥራ እንደሆነ ታምናለች። አስተሳሰቧ መልክ የያዘው ግን በ1989 ዓ.ም ወደ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ተመልሳ፤ የአለም ጤና ድርጅት የማኔንጃይትስና የኤድስ ፐሮግራም የመጀመሪያው ዳሬክተር በነበረው ታዋቂው ምሁር ጆናታን ማን የሚቀርበውን ትምህርት ስትከታተል ነው። ኤድስ፣ ጤና እና ሰብአዊ መብት የተሰኘው ኮርስ፤ በኬንያ ቆይታዋ አስተሳሰቧን ያናጉ ትዝብቶቿና ገጠመኞቿን ትርጉም ባለው መንገድ እንድትገነዘባቸው ያስቻላት ብቸኛ ኮርስ ነበር። ሕክምና ለመማር ከወሰነች በኋላ፤ በመኖሪያ ከተማዋ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጆች የእንግሊዝኛ ቋንቋና የኮሌጅ ማዘጋጃ ትምህርት በመስጠት ለአንድ አመት ሰርታለች።

በሃርቫርድ ሕክምና በምትማርበት ወቅት፤ ወደ አፍሪካ ተመልሳ ጥናትና ምርምር የምታካሂድበት እድል እንዲያመልጣት ስለማትፈልግ ማንኛውንም አጋጣሚ ትጠቀም ነበር። ለዚህም ነው በቦትስዋና፣ በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ የተካሄዱ የኤችአይቪ የክትባት ሙከራዎች ላይ እንዲሁም በሌሎች የኤችአይቪ መከላከያ መንገዶች ላይ ጥናት ለማካሄድ የቻለችው። ለመመረቅ አንድ አመት ሲቀራት፣ የፉልብራይት ስኮላርሺፕ አሸንፋ በታዳጊ አገራት የጤና አጠባበቅ ዙሪያ የማስተርስ ዲግሪ ለመያዝ ወደ ለንደን የሃይጂንና የትሮፒካል ሜዲሲን ተቋም ሄደች። የመመረቂያ የጥናት ወረቀት ለማዘጋጀት አዲስ አበባ መጥታ የሴቶች ጥናት አለማቀፍ ማዕከል ውስጥ የሰራቸው ምህረት፤ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሰዎች የሚገጥማቸው መድልዎና መገለል ላይ የተሰባሰቡ ገላጭ መረጃዎችን የመተንተን ሃላፊነት ነበረባት። ይሄኔ ነው፤ በውስጧ ካለው የአስተማሪነት አላማ በተጨማሪ፤ ጥናትንና ምርምርንም የሚጨምር የሕይወት አቅጣጫ የተለመችው።

የማስተርስ ዲግሪዋን ይዛ፤ የሕክምና ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ወደ ሃርቫርድ የተመለሰችው ምህረት፤ ለሁለተኛ ጊዜ ለራዕይ የሚያነሳሳ የምሁር አባት ዶ/ር ፖል ፋርመርን አገኘች። በሃይቲ፣ በፔሩ እና ችግረኛ ሰዎች በበዛባቸው ሌሎች አገራት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተው ዶ/ር ፖል ፋርመር፣ ለባህላዊ እሴቶችና ለማህበረሰብ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጥ          በማህበረሰብ ላይ የተመሰረተ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ አድርጓል። በወቅቱ ምህረት ያደረባት ምኞት፣ ተመሳሳይ የጤና አገልግሎት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ነበር። የሕክምና ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ፣ ሐኪም ለመባል ሆስፒታል ውስጥ የተግባር ስልጠናና ልምምድ ስለሚያስፈልግ በኒው ዮርክ ከተማ የሞንቴፊዮሪ ሆስፒታል በጠቅላላ የአካል ውስጥ ሕክምና ስልጠናዋን ደመደመች። እዚያው እያለች ነው፣ ለጉዳት በተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የጤና ግንዛቤ ለማሳደግ በማሰብ ትሩዝኤድስ የተሰኘ የረድኤት ድርጅት ያቋቋመችው። የመጀመሪያ ድጋፍ ያገኘችውም እዚያው ኒውዮር ከምትኖር ኢትዮጵያዊት ከጁሊ ምህረቱ ነው። የድርጅቱ ዌብ ሳይት (www.truthaids.org) ዋና አዘጋጅ የሆነችው ዶ/ር ምህረት፤ የጤና ግንዛቤን የሚያስፋፉ ስልጠናዎችንና ውይይቶችን አዘጋጅታለች። የኤችአይቪ መከላከያ ዘዴዎችን፤ በተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚታዩ የጤና ሁኔታ ልዩነቶችን፣ እንዲሁም በጤና አጠባበቅ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ጠቀሜታንና በተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ አገራዊና አለማቀፋዊ ስልጠናዎችን አካሂዳለች። ጥቁሮች በሚበዙበት የተጎሳቆለ የኒው ዮርክ ክፍል (South Bronx) እና በኢትዮጵያ ውስጥ ባካሄደችው ጥናት፣ የኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሴቶችን ሕይወት የሚዳስስ ማህበረሰብ ተኮር ፊልም ሰርታለች። \\\”ኦል ኦፍ አስ\\\” በሚል የተዘጋጀው ጥናታዊ ፊልም በአለም የኤድስ ቀን በሾውታይም ኔትዎርክስ ለእይታ ቀርቧል። ይህም ብቻ አይደለም። በመላ አገሪቱ፤ የተለያዩ የማህበረሰብ ድርጅቶችና ዩኒቨርስቲዎች ፊልሙን ለማስተማሪያነት አውለውታል። ከዚህ ተመክሮዋ ነው፤ የጤና አጠባበቅ አላማዎችን ለማስተጋባትና ግንዛቤ ለማስፋፋት፤ ፊልምና ማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ምትክ የለሽ ሃያል መሣሪያዎች እንደሆኑ ያመነችው።

በአሜሪካ በትልቅነታቸው ከሚታወቁት ፋውንዴሽኖች መካከል አንዱ በሆነው ሮበርት ዉድ ጆንሰን የጤና እና የህብረተሰብ ምሁር ተብላ ፔንሰልቫንያ ዩኒቨርስቲ የተሰየመችው ምህረት፤ በሎናርድ ዳቪስ የጤና ኢኮኖሚክስ ተቋም አንጋፋ ተጋባዥ ምሁር ተብላለች። አንትሮፖሎጂንና ሕክምናን ያዋሃዱ ጥናቶችን ከማዘጋጀት አልፋ፤ ጥናቶችን  በዲጂታል ሚዲያ ለህዝብ የማድረስ ዘዴዎችን መገንባት ሥራዬ ብላ ተያይዛዋለች። ጥናቶቿ በማህበረሰብ ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መከላከልና ኤችአይቪን መከላከል ዘንድ ያሉ ትስስሮችን ይዳስሳል – ጥናቶችን ለአብዛኛው ሰው በሚገባ መንገድ በዲጂታል ሚዲያ የማቅረብ ጉዳይንም በማካተት። ኤችአይቪንና ጥቁር ሴቶችን በሚመለከት ሃሳቧን ስታቀርብ፤ የራሷን የፍቅር ታሪክ ጥሩ እና መጥፎ ውሳኔዎቿን ጨምራ ትተርካለች። በአድልዎና በወንዶች ገናናነት ሳቢያ፣ በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶች ለኤችአይቪ ኤድስ በእጅጉ የተጋለጡ መሆናቸውን የምታስረዳው አንትሮፖሎጂንና ሕክምናን ባዋሃደ ጥናት ነው። የራሷን የግል ታሪክ መተረክ ድፍረትን የሚጠይቅ ፈተና ቢሆንባትም፤ የተማሩና ደህና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች የሁሉንም ሴቶች ጥያቄ እንዲያነሱ ያደፋፍራቸዋል በሚል እምነት እንደተወጣችው ትናገራለች።

በፔንሰልቫንያ ዩኒቨርስቲ ሳለች በፊላዴልፊያ የሕፃናት ሆስፒታል ውስጥ ከምታያቸው በኤችአይቪ ኤድስ የተጎዱ ሕፃናት ጋር አያይዛ የወደፊት ሕይወቷን ስትተልም ነው ስሜቷን የሚቀሰቅስ ክስተት የተፈጠረው። ባራክ ኦባማ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመፎካከር በእጩነት ሲቀርቡ ውስጧ በስሜት ተሞልቶ ለምርጫ ዘመቻው የድርሻዋን ድጋፍ አሰባስባለች። በጥር 2001 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ የተመለከተችው የኦባማ በዓለ ሲመት ነሽጧት የበኩሏን ለማበርከት የወሰነችው ምህረት፤ ብዙዎች በሚያከብሩትና በሚመኙት \\\”ኋይት ሃውስ ፌሎ\\\” የተሰኘ ፕሮግራም ለመስራት ተወዳደረች። ለ2001-2002 ዓ.ም ከተመረጡት 15 ሰዎች አንዷ ለመሆንም በቃች። የተሰናባች ወታደሮች የጤና ፕሮግራም ላይ ተመድባ፤ የተሰናባች ወታደሮች ጉዳይ መስሪያ ቤትና የመከላከያ ሚኒስቴር በጥምረት በሚያዘጋጁት የአእምሮ ጤና ጉባኤ የመጀመሪያውን የጋራ ሪፖርትና የመፍትሄ ሃሳብ አዘጋጅታለች – ከስራ ባልደረቦቿ ጋር። እነ ምህረት ያዘጋጁት ሰነድ፤ ከስቃይና ከጉዳት በኋላ የሚከሰት የጤና እክልን ጨምሮ የተሰናባች ወታደሮችን የአእምሮ ጤና የሚዳስስና በጤና አገልግሎት ሥርአት ላይ ያተኮረ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን በጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ፤ የጤና አጠባበቅና የጤና አገልግሎት የትምህርት ክፍል በአስተማሪነት የተቀጠረችው ምህረት፤ ጤና እና ማህበራዊ ለውጥ በሚል ስያሜ የፈጠረችውን ኮርስ ማስተማር ጀመረች። ለኮርሱ የመማሪያ መፅሃፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም የምርምር ሥራዎቿን ለማካሄድና ለመፃፍ ዩኒቨርስቲው በሰጣት የእረፍት ጊዜ እየተጠቀመች ትገኛለች። ለሦስት አመታት የኋይት ሃውስ ፌሎ ሆና በምትሰራበት ወቅትም ነው፤ ቀድሞ ከምታውቀው ኢትዮጵያዊ ፊልም ሠሪ ጋር እንደገና ግንኙነት የፈጠረችው። የኋላ ኋላ ተጋብተው ትዳር ቢመሰርቱም፤ ለጊዜው ያገናኛቸው ግን ፊልም ሠሪው በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ የወጠነው የፊልም ሥራ ከምህረት ዝንባሌ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነበር። የፊልሙ ጭብጥ ዋና ማጠንጠኛ፤ ለረዥም ጊዜ ጥቃት ያደርሰባት የነበረ ባለቤቷን ገድላ የተከሰሰች ሴት ላይ ነው። የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መሪ የነበረችው መዓዛ አሸናፊ የተከሳሿ ጠበቃ ሆና ፍርድ ቤት መቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ጥፋተኛ አይደለችም ተብላ በነፃ ተለቃለች። ምህረት በፆታ ጥቃትና በጤና መካከል ያለው ግንኙነት ትልቅ ትርጉም እንዳለው በማመን፤ “Oblivion” በሚል ርዕስ የተወጠነውን የፊልም ሥራ ለመርዳት ወሰነች። እንደገና በጁሊ ምህረቱ ከፍተኛ ልግስና  የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ፊልም ሠሪውን ለማገዝ ጥራለች። የተወጠነው የፊልም ሥራ ተጀመረ። በዚሁ መሃል የተወጠነው ፍቅርም ለትዳር በቃ፤ ለሴቶች መብት አጥብቆ ከሚከራከር  ፊልም ሠሪ ጋር ተጋባች።

ምህረት በየጊዜውና በየቦታው የተጋፈጠቻቸውን ፈተናዎች፤ ለፈጠራ የሚያነሳሱ አጋጣሚዎች ናቸው ብላ ታምናለች – አዳዲስ መንገዶችን ለመሞከርና አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር መነሻ ይሆናሉ። በተደጋጋሚ የሚያጋጥሟት ፈተናዎች ሁለት ናቸው። አንደኛ ነገር፤ ለሥራዎቿ እውቅና ለመስጠት የሚቸገሩ ሰዎች ይፈትኗታል። ሁለተኛ ነገር፤ የአመራር ዘዴዋና አቀራረቧ ለየት ያለ በመሆኑ ምቾት ይነሳታል። በሕክምናው አለም ብቻ ሳይሆን፤ የኋይት ሃውስ ፌሎው ሆና በወታደራዊው ዓለም ውስጥ ስትሠራ ያስተዋለችው ነገር ቢኖር፤ የተለሳለሰ አመራር ዘዴዋና አቀራረቧ በዙሪያዋ ከምታየው የሌሎች ሰዎች አዝማሚያ ይለያል። በሰዎች መሃል ልዩ ሆኖ መገኘት ምቾትን የሚነሳ ቢሆንም፤ ሌሎች ሰዎችን   ለመምሰል አልሞከረችም። የራሷን ዘዴና አቀራረብ ተቀብላ መጓዝን ለመልመድ ነው የጣረችው። ስልጣንን አግንኖ በማሳየት ሳይሆን በተለሳለሰ አቀራረብ ሰዎችን መማረክ ተመራጭ እንደሆነ ታምናለች። ከዚህም በተጨማሪ፤ ሴት መሆኗን፣ በተለይም ጥቁር ሴት መሆኗን በማየት ብቻ ብቃቷን የሚጠራጠሩ ሰዎች ያጋጥሟታል።  በጥረቷ ያላገኘቻቸው ይመስል ለሥራዎቿና ለስኬቶቿ እውቅና ለመስጠት ይቸገራሉ። ደግነቱ እንዲህ አይነቱን ጭፍንነት ወደ ጎን እያንገዋለለች ወደፊት መራመድን ታውቅበታለች። የአመራር ዘዴዋና አቀራረቧ ከሌሎች የተለየ በመሆኑ፤ እንዲሁም ጥቁር ሴት በመሆኗ በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም፤ አሸንፋ የማለፍ ብልሃት ተምራባቸዋለች። ሴቶች በተለይም ወጣት ሴቶች ከሁሉም በላይ በጥዋቱ ምን ማዳበር እንዳለባቸው ስትገልፅ፤ ዋናው ነገር ማንነትን አውቆ በራስ ሰብዕና መተማመን ነው፤ ምክንያቱም ፍቱን መድሃኒት ነው ትላለች። በየራሳችን ስብዕና ከተማመንን፤ በየቦታውና በየጊዜው የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ሊያንብረከርኩን አይችሉም። በራሳችን ስብዕና ሳንተማመን ስንቀር ነው፤ የሌሎች ሰዎች አስተያየትና ፍረጃ በጣም ከብዶ የሚታየን።

ምህረት ብዙ ነገሮችን የምትሞክርና በብቃት የምትሠራ ቢሆንም፤ ትልቁ ተሰጥኦዋ አስተማሪነት እንደሆነ ታምናለች። ለነገሩ ተማሪዎቿም ይመሰክራሉ (የፈተና ውጤታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ማለት ነው)። በአስተማሪነቷ እንደምትቀጥል ባትጠራጠርም፤ እንደወትሮው ችግር ፈቺ ሥራዎቿንም አታቋርጥም – የጥናት ፅሁፎችን በማቅረብ፣ መፅሃፍ በማዘጋጀት፣ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶችን በማሻሻል ወዘተ። በተለይ የአእምሮና የአካል ጤንነትን ለማዋሃድ ያለመ አዲስ ፕሮጀክት ላይ ብትሠራ ደስታውን አትችለውም። በቃ፤ ወደፊትም፤ ዘላቂ ለውጥ የሚያስገኙ አዳዲስ አቅጣጫዎችን የምታመነጭ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሰው መሆን ነው የዘወትር ምኞቷ።

ኢትዮጵያ የላይ ታች ውጣውረድ ውስጥ የምትባክን አገር ሳትሆን፤ በላይ በላዩ የምትመነደግ አገር እንደሆነች ምህረት ታስባለች። ምንም እንኳን በክርስቲያንና በሙስሊም መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ቢያሳስቧትም፤ ኢትዮጵያ በሃይማኖቶች መካከል ለረዥም ጊዜ በተሻለ ደረጃ ሰላማዊ ታሪክ ያላት በመሆኑ ምህረት ትኮራበታለች። ለምን ቢሉ፤ የኢትዮጵውያንን ትልቅ ነገር የሚመሰክር ነው፤ ኢትዮጵያውያን ለበርካታ ምዕተ አመታት ድንቅ የመቻቻል ምግባርን የተከተሉ መንፈሳዊ አማኞች እንደሆኑ ታሪካቸው ይናገራል። ይሄ እንዳይለወጥ ነው ተስፋዋ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአገር ቤት ውስጥ እየጨመረ የመጣው እንቅስቃሴአቸው  ወደ ፊትም እንዲቀጥል የምትመኘው ምህረት፤ ለእድገት ትልቅ ጉልበት የሚሆን የእውቀትና የፋይናንስ አቅም ይሆናሉ ትላለች። በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በጤና አጠባበቅና በትምህርት የተከናወነው አስደናቂ ሥራ፤ በአገሪቱ የወደፊት ግስጋሴም እንዲቀጥል ተስፋ ታደርጋለች። ኢትዮጵያ ገና ብዙ ቢቀራትም ለትልቅ ነገር የተፈጠረች ልዩ አገር ነች ብላ ታምናለች – ምህረት።

ምህረት ለልጃገረዶችና ለወጣት ሴቶች የምትሰጠው ምክር እንዲህ የሚል ነው፡ በፅናት ለራሳችሁ ታማኝ ሁኑ፤ ከቶ ተስፋ ቆርጣችሁ እጅ አትስጡ። \\\’ለሌሎች ሰዎች ሁሉም ነገር ቀላል ሆኖላቸዋል፤ ለኔም ሁሉም ነገር ቀላል መሆን ነበረበት\\\’ ወደሚል እምነት ተጎትተው የሚገቡ ሰዎች አሉ። እውነት እንናገር ከተባለ ግን፤ ከቁጥር የሚገባ ማንኛውም ስኬት ተግቶ መስራትን ይጠይቃል። ሥራችሁን የሙጢኝ ይዛችሁ በፅናት መቀጠል ነው ቁምነገሩ። ስለወደፊት ህይወታችሁ በጥዋቱ ማሰብ ብትጀምሩና ብትወስኑ ይመረጣል። ለምን ቢባል፣ በመረጣችሁት መስክ ገና በወጣትነታችሁ ሊቅ ለመሆንና ብዙ ስኬት ለመቀዳጀት ሰፊ ጊዜ ይኖራችኋል።


ዋና የመረጃ ምንጮች
  ከምህረት አያሌው ማንደፍሮ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ ሀምሌ 2004
አጥኚ
ትዝታ ተክለጻዲቅ፣ ሜሪ-ጄን ዋግል

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>