Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

ምንትዋብ (ንግስት:እቴጌ)

Mintewab small

ዋና ዋና ስኬቶች:
አስልታና አርቃ የምታቅድ፣ የሰዎችን ቀልብ የምትይዝራ ብርቱ የኢትዮጵያ ንግስት፣ የአፄ በካፋ ሚስት፣ የልጇ የአፄ ኢያሱ ዳግማዊ እንዲሁም የልጅ ልጇ የአፄ ኢዮአስ ቀዳማዊ ሞግዚት (እንደራሴ)፤ የጎንደር ነገስታት ዘመን ማብቂያ ላይ የገነነች የፖለቲካ ተዋናይ፣፤ የኪነ ጥበብ በተለይም የሥነ ሕንፃና የሥነ ሥዕል ተቆርቋሪ አለኝታ በመሆን የቤተመንግስትና የቤተክርስትያን ሕንፃዎችን ያስገነባች
የትውልድ ቦታ: ቋራ፣ ኢትዮጵያ
የትውልድ ዘመን: 1706 እ.ኤ.አ
ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
  ገና በሕፃንነቱ ከነገሰው ልጇ ከኢያሱ ጋር ዙፋን ተጋርታ ዘውድ የደፋችው ንግስት ምንትዋብ፤ የልጅ ልጇ ከነገ|ሠ በኋላም ጭምር የሞግዚት እንደራሴነቷ ሳይቋረጥ፣ ለ40 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በበላይነት ገዝታለች። ባለቤቷ አፄ በካፋ፣ እ.ኤ.አ በ1730 በሞተበት ወቅት በሀያዎቹ የእድሜ ክልል የነበረችው ወጣት ምንትዋብ፣ ሴት መሪዎች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን የፖለቲካ መዘውሩን በመጨበጥ ስድሳ አመት እስኪያልፋት ድረስ በአገር መሪነት ዘልቃለች። ውበቷ እንደ ሥሟ ወደር የለሽ ነው ከሚለው ውዳሴ በተጨማሪ በአእምሮ ብቃቷና በብልህነቷ አድናቆትን ያተረፈች የፖለቲካ ጥበበኛ እንደሆነች ስራዎቿ ይመሰክራሉ። በራሷና በቤተሰቧ የተያዘውን ስልጣን ለረዥም ጊዜ ለማቆየት፣ የቅርቡንና የሩቁን እያሰላች ብልጠት በተሞላበት መንገድ፣ የምታምንባቸው ወገኖቿን ለቁልፍ የስልጣን ቦታ አብቅታለች፤ ከአጎራባች ገዢዎች ጋር ሽርክና ፈጥራለች። በሥነ ጥበብ እና በሥነ ሕንፃ አለኝታነቷ፣ በዋና ከተማዋ በጎንደርና በአካባቢዋ፣ በማራኪ የዘመነ ጎንደር ውበታቸው የሚታወቁ፣ በርካታ የቤተመንግስትና የቤተክርስትያን ሕንፃዎችን አስገንብታለች። የልጅ ልጇ አፄ ኢዮአስ በነገሠበት ዘመን፣ በአያትነቷ የሞግዚት እንደራሴ ሆና ስልጣን ላይ ብትቆይም፣ የኋላ ኋላ ሃያል ባላጋራ ገጥሟታል – የንጉሡ እናት የስልጣን ተቀናቃኝ ሆና መጣችባት። ምንትዋብ የስልጣን መንበሯን ይዛ ለመቀጠል አስልታ እንደወትሮው በዘረጋችው መረብ ነው የራሷን ውድቀት የደገሰችው። በንጉሡ አያት እና በንጉሡ እናት መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ ፍጥጫ፣ ወደ ግጭትና ወደ ጦርነት ሊያመራ ሲል፣ ከትግራይ ራስ ሚካኤል ስሁል ለሽምግልና እንዲመጣ የጠራችው ራሷ እቴጌ ምንትዋብ ነች። ሚካኤል ስሁል ግጭቱን ቢያበርድም አፄ ኢዮአስን ገድሎ ስልጣኑን ተቆጣጠረና፤ የምንትዋብ ስልጣን ብቻ ሳይሆን የያኔው የጎንደር ነገስታት ዘመንም አበቃለት፤ የዘመነ መሳፍንት መባቻም ሆነ። ዘመነ መሳፍንት አጭር ጊዜ አይደለም፤ አፄ ቴዎድሮስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ስልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ብዙ አመታትን አስቆጥሯል።

ከጣና ሀይቅ በስተምዕራብ፣ እስከ ሱዳን ድንበር በተዘረጋው የቋራ ክፍለ ግዛት፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ እ.ኤ.አ በ1706 ዓ.ም እንደተወለደች የሚነገርላት ምንትዋብ፤ አባቷ ደጃዝማች መንበረ የደንቢያው ባላባት ሲሆን፣ እናቷ ወይዘሮ እንኮዬ ደግሞ የመሳፍንት ተወላጅ ነች። ከሁለት መቶ አመታት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያን ሲገዛ ከነበረው ከአፄ ሚናስ የሚመዘዘው ንጉሣዊ የትውልድ ሀረግ ምንትዋብ ላይ የሚደርሰው በእናቷ ወገን ነው። ብዙ ሳትቆይም፣ በጋብቻ ሌላ የንጉስ ቤተሰብ ውስጥ ገባች። የመጀመሪያ ሚስቱን በሞት ያጣው አፄ በካፋ፣ የ16 አመቷን ምንትዋብ እ.ኤ.አ በ1722 ዓ.ም ወደ ቤተመንግስቱ አምጥቶ አገባት። አመት ቆይታ ወንድ ልጅ፤ ከዚያም ሴት ልጅ ወለደች። በጎን ከጋብቻ ውጭ፣ መልምል ኢያሱ ከሚባል የንጉሡ የወንድም ልጅ ጋር በነበራት የፍቅር ግንኙነት፣ ሶስት ሴቶችን እንደወለደችም ይነገራል።

የፖለቲካውንና የስልጣን መውጫ መግቢያውን አብጠርጥራ ለማወቅ ጊዜ ያልፈጀባት ምንትዋብ፤ ባለቤቷ አፄ በካፋ እ.ኤ.አ በ1730 ዓ.ም በሞተ ማግስት ነው፣ በ24 አመት እድሜዋ አገር መግዛት የጀመረችው። የ7 አመት ህፃን የነበረው ልጇ፣ “አፄ ኢያሱ ዳግማዊ” ተብሎ ዙፋን ላይ ሲወጣ፤ ምንትዋብም የዙፋኑ ተጋሪና ሞግዚት እንደራሴ ሆና ዘውድ ደፋች። “ብርሃን ሞገስ” የሚል የዙፋን ስምም ተሰጣት። ሞግዚት እንደራሴ በመሆን የያዘችው ስልጣን ግን፤ በጥቂት አመታት ውስጥ የሚያበቃ አልነበረም። አፄ እያሱ የአዋቂ እድሜ ላይ ከደረሰ በኋላም፣ ስልጣኗን አላስረከበችውም። የልጅ ልጇ አፄ ኢዮአስ በነገሠባቸው አመታትም ጭምር፤  የምንትዋብ ስልጣን አልተቋረጠም። ወንድሟን ጨምሮ ከጎኗ ባሰለፈቻቸው ወገኖቿ እየታገዘች፤ ለአርባ አመታት ያህል፤ የጎንደር ነገስታት ዘመን እስካበቃበት የዘመነ መሳፍንት መባቻ ድረስ፣ ምንትዋብ አገሪቱን ገዝታለች።

ከብሩህ አእምሮ ጋር፣ ትልቅ ትልቁን የማለም ድፍረት የነበራት ምንትዋብ፣ ባለቤቷ አፄ በካፋ በህይወት በነበረበት ጊዜ ነው፣ የሩቁን አቅዳ የቅርቡን አስልታ መረብ መዘርጋት የጀመረችው። ማራኪ ሰብዕናዋንና ቤተመንግስት ውስጥ የገነባችውን ተሰሚነት በመጠቀም የመሰረት ድንጋይ ማበጃጀት ያዘች። ወደፊት አገሪቱን የመግዛት አላማዋን ለማመቻቸት የሚችሉ ወገኖቿን እየመረጠች ከወዲሁ የስልጣን ቦታ እንዲይዙ አድርጋለች። በአፄ በካፋ ዘመን በተፈጠረው የሃይማኖት ብጥብጥና የቤተክህነት ሽኩቻ ውስጥ የምንትዋብ እጅ እንደነበረበት የሚናገሩ ታሪክ ፀሃፊዎች፤ ቅባት የተሰኘውን የክርስትና አስተምህሮ ትከተል እንደነበረና ባለቤቷ አፄ በካፋ የተዋህዶ አስተምህሮውን እንዲተው እንዳግባባችው ይናገራሉ። ምንትዋብ እንደ ፈረንጅ የመልኳን ንጣትና የካቶሊክ እምነት ዝንባሌዋን የወረሰችው ከፖርቱጋላዊ አያቷ ነው የሚል ወሬ ይናፈስ እንደነበር ስኮትላንዳዊው ተጓዥ ጄምስ ብሩስ ይጠቅሳል። የሃይማኖት ሽኩቻው በምንትዋብ የስልጣን ዘመንም ታይቷል።
ከባለቤቷ ህልፈት በኋላ ወደ ስልጣን የወጣችው፤ ለህፃን ልጇ ለዳግማዊ ኢያሱ ሞግዚት (እንደራሴ) እና የዙፋን ተጋሪ በመሆን ነው ቢባልም፤ ልጇ የአዋቂ እድሜ ላይ ከደረሰ በኋላም ራሱን ችሎ አገር እንዲገዛ እድል አልሰጠችውም። የስልጣን መንበሯን እንዳደላደለች፤ የቅባት አስተምህሮ በቤተመንግስትና በቤተክርስትያን ብቸኛ ሃይማኖታዊ ቀኖና እንዲሆን ወሰነች። በነገስታቱ መዲና ከጎንደር የአገር ግዛት ስልጣኗን ለማጠናከር፤ በፖለቲካ ስሌት ልጇ እያሱና የወሎ ኦሮሞ ተወላጅ የሆነችው ውቢት (ወለተ ቤርሳቤህ) በጋብቻ እንዲተሳሰሩ አደረገች – ከወሎ ኦሮሞ ተወላጆች ወታደራዊ አቅም ለማግኘት በማሰብ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ የወሎ ኦሮሞ ተወላጆች፤ የስልጣን መቆናጠጫ በማግኘት ቀስ በቀስም ዋና የፖለቲካ ድርሻና ሚና ተቀዳጅተዋል። ዳግማዊ ኢያሱ እ.ኤ.አ በ1755 ከሞተ በኋላ፤ ቀዳማዊ ኢዮአስ ዙፋኑን ወረሰ፤ አያቱ ምንትዋብም የሞግዚት እንደራሴና የዙፋን ተጋሪ በመሆን ስልጣኗን እንደያዘች ቀጠለች።

ነገር ግን፤ ተቀናቃኝ መጣባት። ከምንትዋብ ፊት ውቢት ቆመች – የቀድሞው ንጉሥ የኢያሱ ሚስትና የኢዮአስ እናት ናት። ውቢት (ወለተ ቤርሳቤህ) ጊዜው የኔ ነው አለች። የልጄ የኢዮአስ ሞግዚትና እንደራሴ ሆኜ ስልጣን መያዝ አለብኝ አለች። በሁለቱ ሴቶች መካከል የተፈጠረው ተቀናቃኝነት፤ ከእነሱ አልፎ እየሰፋ የቋራ እና የወሎ ኦሮሞ ተወላጆች ግጭት ወደ መሆን ተሸጋገረ። የስልጣን መንበሯ አደጋ ላይ የወደቀባት ምንትዋብ፣ ዘመናዊ ጠመንጃ የታጠቀ ብዙ ጦር ያደራጀውን ራስ ሚካኤል ስሁልን ከትግራይ ለመጥራት ወሰነች። የስልጣን ግብግቡን ለማብረድና ደም አፋሳሽ ግጨትን ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን፤ የስልጣን መንበሯንም መልሳ ለማጠናከር እንደምትችል ምንትዋብ ተስፋ ነበራት። እንዳሰበችውም ራስ ሚካኤል፤ ግብግቡን በማብረድና ግጭቶችን በአጭሩ በመቅጨት ሰላም ለማስፈን ችሏል። ለዚህም ከንግስና በታች የመጨረሻው ከፍተኛ ማዕረግ ተሰጥቷቸው “ራስ ቢትወደድ” ተብለዋል። ነገር ግን የምንትዋብ ሃሳብ አልተሟላም። በተቃራኒው የፈራችው ደረሰ፤- ከፈራችውም በላይ እንጂ። ራስ ሚካኤል ጎንደር ውስጥ ሰላም ፈጥሮ በሰላም ለመሰናበት ፈቃደኛ አልሆነም። አፄ ኢዮአስን በመግደል፤ መንበረ ስልጣኑን ተቆጣጠረ። የምንትዋብ የስልጣን አመታት የተቋጨውና ለምእተአመት የሚዘልቀው ዘመነ መሳፍንት የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው።

በልጅ ልጇ መገደል ቅስሟ የተሰበረው ምንትዋብ፤ ጎንደርን ለቅቃ ወደ ቁስቋም በመሄድ ለብቻዋ ወደ ተገለለ ኑሮ ገባች – እስከ ህይወቷ ፍፃሜ ድረስ። ህይወቷ ያለፈው እ.ኤ.አ በ1773 ዓ.ም እንደሆነ የሚገልፁ ሰዎች ቢኖሩም፤ በታሪክ መዛግብት ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የታየችውም፤ ጄምስ ብሩስ ኢትዮጵያን ለቅቆ ለመውጣት በሚዘጋጅበት ወቅት እ.ኤ.አ በዲሰምበር 1771 ዓ.ም የጎበኛት ጊዜ ነው።

ዛሬ በጎንደር ለምናያቸው የሥነ ሕንፃ ቅርሶች፣ የምንትዋብ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በስልጣን ዘመኗ፣ በርካታ ህንፃዎች በጎንደር እንዲገነቡ አድርጋለች፤ ከእነዚህም መካከል የምንትዋብ ቤተመንግስት የሚባለው የራሷ ቤተመንግስትና ትልቅ ግብር መጣያ (የመመገቢያ) አዳራሽ ይጠቀሳሉ። በቁስቋም፤ ለድንግል ማርያም መታሰቢያነት ከተሰሩት የደብረ ፀሐይ እና የንርጋ ስላሴ ቤተክርስትያኖች በተጨማሪ እዚያው እንደ መኖሪያ የተጠቀመችበትን ቤተመንግስት አስገንብታለች። በያኔው የጎንደር ነገስታት ዘመን ዘይቤ ተገንብተው እስከዛሬ የዘለቁት ሕንፃዎች፤ በምንትዋብ መሪነት የተሰሩት ግንባታዎች መንፈስን የሚያድስ ማራኪ ውበት እንደነበራቸው ይመሰክራሉ።

ምንም እንኳ ስህተቶችን ብትፈፅምም፤ እቴጌ ምንትዋብ ከብዙዎች ልቃ ለረዥም አመታት ስልጣን ላይ የቆየች ጠንካራ መሪ ነበረች። የ18ኛው ክፍለዘመን ሴት ብትሆንም፤ ለአርባ አመታት ያህል አገሪቱን ከመምራት አላገዳትም። ስኮትላንዳዊው ተጓዥ የምንትዋብን የወጣትነት እድሜ ለመግለፅ ባሰፈረው ፅሁፍ፤ እውነትም “ሲበዛ የተዋበች፣ ጨዋ፣ የተረጋጋች፣ ተጫዋች፣ እንዲሁም ከእድሜዋ በላይ ትልቅ አዋቂና ብልህ” ነች ብሏል። ሴት መሪዎች ባልነበሩትና ወንዶች የገነኑበት ዘመን ውስጥ የኖረች ሴት ነች፤ ግን ደፋር፣ ቁርጠኛና ጥበበኛ ሴት!

 


ዋና የመረጃ ምንጮች
  en.wikipedia.org/wiki/Mentewab, Encyclopedia Aethiopica Volume 1
አጥኚ
ምንትዋብ አፈወርቅ

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Required fields are marked *
Your email address will not be published.

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>