Category: Uncategorized

ጁሊ ምህረቱ

Julie Mehretu with copyright

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
 

በዎከር የስነጥበብ ማዕከል (ኤም ኤን)፣ በጉግኒህም ሙዚየም (ኒውዮርክና በርሊን) በግሏ ኤግዚቢሽን ያቀረበች የእይታ ጥበብ አርቲስት ናት፡፡ በቬኒስ ቢናሌ እና dOCUMENTA (13)  ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፋለች፡፡ የዊትኒ ሙዚየም አሜሪካን አርት አዋርድና የማክአርተር ፌሎውሺፕን አግኝታለች፡፡ ሥራዎቿ በኒውዮርክ ዘመናዊ የጥበብ ሙዚየም፣ በዋሺንግተን ዲሲ ብሔራዊ የጥበብ ጋለሪ እና ስሚዝሶንያን ተቋም እንዲሁም በሳንፍራንሲስኮ ዘመናዊ የጥበብ ሙዚየም ቋሚ ስብስብ ለመሆን በቅተዋል፡፡  

 

ወቅታዊ ሁኔታ ሰዓሊ
የትውልድ ቦታ: አዲስ አበባ፣
የትውልድ ዘመን: ህዳር 19 1963 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: ኒውዮርክ ሲቲ፣ ዩኤስኤ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት

             ጉድሼፐርድ ት/ቤት፣ አዲስ አበባ (1ኛ ክፍል)፣  ሬድ ሴዳር አንደኛ ደረጃ እና ሃና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ኢስት ላንሲንግ፣ ሚቺጋን፣ ዩኤስኤ 

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ኢስት ላንሲንግ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ኢስት ላንሲንግ፣ ሚቺጋን፣ ዩኤስኤ

የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ

ሁለተኛ ድግሪ፣ (ኤምኤፍ ኤ)፣ በስዕል፣ ርሆድ አይላንድ የዲዛይን ት/ቤት፣ ፕሮቪደንስ፣ ርሆድ አይላንድ፣ ዩኤስኤ

ዋና የስራ ዘርፍ

  የሕይወት ታሪክ
 

ጁሊ ምህረቱ ጥቅጥቅ ብለው በተነባበሩ ረቂቅ የስዕል፣ የህትመት እና  የንድፍ ሥራዎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈች ሰዓሊ ናት፡፡ በግሏ የፈጠረቻቸው የትዕምርቶችና ምልክቶች ቋንቋዋ ፤ ታሪክን፣ ምናባዊ መልክአምድሮችን፣ የሰው መኖርያ አካባቢን እንዲሁም ረቂቅ ሃሳቦችን የሚፈትሹ ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡  ጁሊ በአሁኑ ጊዜ የምትኖረውና የምትሰራው በኒውዮርክ ሲቲና በበርሊን፣ ጀርመን ነው፡፡ 

ከአሜሪካዊት እናቷና ከኢትዮጵያዊ አባቷ በ1962 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደችው ጁሊ፤ እስከ በኢትዮጵያ የቆየችው እስከ ሰባት ዓመቷ ድረስ ብቻ ነበር፡፡  በደርግ ወታደራዊ መንግስት በተቀሰቀሰውና እያየለ በመጣው ብጥብጥ የተነሳ፣ አሜሪካውያን አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሲነገሯቸው፣ እናቷ እሷንና ሁለት ታናናሾቿን ይዘው አሜሪካ ገቡ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በአላባማ ግዛት ከተቀመጡ በኋላ፣ አባቷ ሥራ ባገኙበት በሚቺጋን  መኖር ጀመሩ፡፡ የጂኦግራፊ ኢኮኖሚክ መምህር አባቷ ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትስስር ባለው የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ ነበር ሥራ የተቀጠሩት፡፡

ጁሊ በራሳቸው የህይወት ጎዳና መጓዝ  የሚሹ ጠንካራ ግለሰቦችን ካቀፈ  ቤተሰብ ውስጥ ነው የወጣችው፡፡ ኢትዮጵያዊት አያቷ፣ ባሏን የፈታችው የጁሊ አባት ገና ህፃን ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ሁለት ጊዜ አግብታ ከፈታች በኋላ የትዳሩን ነገር እርግፍ አድርጋ ትታ አዲስ አበባ ልጆቿን ማሳደግ ያዘች፡፡  ለህክምና ወደ ስውዲን ተወስዶ የነበረው ቅድመአያቷ ደግሞ የሉተራን ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው፡፡ ከጥንታዊቷ የአክሱም ከተማ አጠገብ ባለችው አድዋ  የመጀመርያውን የሉተራን ቤ/ክርስትያን በመክፈት የመጀመርያው የሉተራን ቄስ ሊሆን በቅቷል፡፡ የጁሊ ወላጆች በ1950ዎቹ መጀመርያ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ ሲተዋወቁ፣ በአሜሪካ የተለያየ ዘር ጋብቻን የሚከለክል አንቀፅ ከአገሪቱ የህግ መፅሃፍ አልተፋቀም ነበረ፡፡ ሆኖም ጥንዶቹን ከመጋባት አላገዳቸውም – በ1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጋብቻቸውን ሊፈፅሙ ችለዋል፡፡ ቤተሰቧ ወደ አሜሪካ ተመልሶ ሲሄድ ከ65 በመቶ በላይ አሜሪካውያን የተለያየ ዘር ጋብቻን ይቃወሙ ነበር፡፡  ሆኖም ወላጆቿ እጅ አልሰጡም፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የመኖር አስደናቂ ብርታት የነበራቸው ወላጆቿ ፤ ለጁሊ ማለፊያ የብርታት አርአያ ሆነዋታል፡፡  በአዲስ ማህበረሰብ ውስጥ ተላምዶ መኖር የባዕድነት ስሜት ለሚፈጥርባት ጁሊ፤ ነገሩ ፈታኝ ነበር፡፡ ይሄን ፈተና ተጋፍጣ ማሸነፏ ግን  በራስ የመተማመን ስሜትን እንዳሳደረባት ትናገራለች፡፡

     በአዲስ አበባ ጉድሼፐርድ ት/ቤት አንደኛ ክፍልን የተማረችው ጁሊ፤ የአንደኛና ሁለተኛ  ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በኢስት ላንሲንግ ሚቺጋን ነው፡፡ ስዕል መስራትና መቀባት የጀመረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ትንሽ ልጅ ሳለች ሲሆን አባትና እናቷም ያበረታቷት  እንደነበር  ታስታውሳለች፡፡ አሜሪካዊት አያቷ፤ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የተማረችና ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላት ሰዓሊ ነበረች፡፡ የወታደር ሚስት እንደመሆኗ፤ በየጊዜው ከቦታ ቦታ መዘዋወሯ ግን ለስዕል ሙያዋ ምቹ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያዊት አያቷ፤ ቅርጫቶችና የሽመና ሥራዎችን የምትሰራ፤ ድንቅ የፈጠራ ተሰጥኦ ባለቤት እንደነበረች ጁሊ ታስታውሳለች፡፡

 በአዲስ አበባም ሆነ በኢስት ላንሲግ ስታድግ፣ ስዕልን እየሰሩ መኖር ይቻላል የሚል ሃሳብ ወደ አእምሮዋ መጥቶላት አያውቅም፡፡ ካላማዙ ኮሌጅ ስትገባ ግን  የመጀመርያ ድግሪዋን በስነጥበብ ለመስራት ወሰነች፡፡ በዚህ ኮሌጅ ሶስተኛ ዓመት ስትደርስ ወደ ሴኔጋል የሄደችው ጁሊ ፣ ዓመቱን ዳካር በሚገኘው ቼይክ አንታ ዲዮፕ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያሳለፈች ሲሆን ከባቲክ አርቲስት ጋር ሰርታለች፡፡ (በጨርቃጨርቅ ላይ ሰም በማቅለጥ የተለያዩ  ዲዛይኖችን የሚሰራ)

ከኮሌጁ ከተመረቀች በኋላ የሰዓሊነትን ህይወት ለመሞከር ብታስብም፣ በወቅቱ ስዕልን እየሰሩ መኖር  ምን ማለት እንደሆነ በተጨባጭ አታውቅም ነበር፡፡ የሰዓሊነትን  ህይወት በቅጡ የተገነዘበችው ኒውዮርክ ከሄደችና ሬስቶራንት ውስጥ እየሰራች ስዕል ለመሳል ስትሞክር ነው፡፡ ያኔ የስዕሉን ዓለም የተለያዩ ገፅታዎች ማየት የቻለችው  ጁሊት፤ ብዙ መማር እንዳለባት ተረዳች፡፡ የስዕል ስራዎቿን አሰባስባም ለበርካታ ት/ቤቶች ላከች፡፡ የማታ ማታ  እድል ቀናትና በፕሮቪደንስ ርሆድ አይላንድ በሚገኘው የርሆድ አይላንድ የዲዛይን ት/ቤት ሙሉ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝታ፣ በ1989 ዓ.ም በሥነጥበብ የማስተርስ ድግሪዋን አገኘች፡፡ እዚያ ሳለች ከታላላቅ መምህራን ጋር የመስራት ዕድል ያገኘች ሲሆን  በተለይ ሥራዎቿን እንድታሳድግ በማገዝ ረገድ ማይክል ያንግ ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ታስታውሳለች፡፡

ከዲዛይን ት/ቤት ከተመረቀች በኋላ በግላሴል የስነጥበብ ት/ቤት ኮር ፕሮግራም አማካኝነት በሂዩስተን፣  ቴክሳስ የስነጥበብ ሙዚየም ውስጥ ለሁለት ዓመት በተጋባዥነት የመስራት ዕድል አገኘች፡፡ እዚያ ሳለች ነው ለስዕሎቿ ተመልካቾችን ማፍራትና ለኤግዚቢሽኖች መመረጥ የጀመረችው፡፡ ባገኘችው ዕውቅና በመበረታታቷና በስዕል ሥራ ገቢ ማግኘት በመጀመሯም  ወደ ኒውዮርክ ሲቲ ተመልሳ ሄደች፡፡

በኒውዮርክም ቢሆን የጁሊ ሥራዎች ትኩረትና ድጋፍ ማግኘታቸውን ቀጠሉ፡፡ ከቀደምት የሙያ ዘመን ስኬቶቿ መካከል በ1992 ዓ.ም ከፋውንዴሽን ፎር ኮንቴምፖራሪ አርትስ ግራንትስ የተሸለመችው አርቲስት አዋርድ እንዲሁም የፔኒ ማክኮል አዋርድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ሥራዎቿ ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በበርካታ የቡድን የሥዕል ትዕይንቶች ላይ የቀረበላት ሲሆን ካርኒጅ ኢንተርናሽናል፣ የዊትኒ ቤኒያል እና በርካታ ዓለምአቀፍ ቤኒያሎች ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ በቡሳን፣  በሲድኒ፣  በፕራግ፣  በሳኦ ፓኦሎ፣ በሴቪሌ እና በኢስታንቡል እንዲሁም በሌሎች ስመጥር ኤግዚቢሽኖች ላይ ተሳትፋለች፡፡ በ1997 ዓ.ም ደግሞ ብዙ ጊዜ የባለምጡቅ አዕምሮ ሽልማት” በሚል የሚጠራውየማክአርተር ፌሎውሺፕ ተቀባዮች መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጁሊ ሥራዎች በታዋቂ ሙዚየሞችና በትላልቅ የግል ስብስቦች ውስጥ በቋሚነት ለመቀመጥ የበቁ ሲሆን ከሙዚየሞቹ መካከልም የኒውዮርኩ ዘመናዊ የስነጥበብ ሙዚየም፤ የዋሺንግተኑ ብሔራዊ የስነጥበብ ጋለሪና የስሚዝሶንያን ተቋም እንዲሁም የሳንፍራንሲስኮው የዘመናዊ የስነጥበብ ሙዚየም ይገኙበታል፡፡

ጁሊ ማንም ባልደፈራቸው ትላልቅ እውቅ ማዕከሎች ውስጥ የግሏን ኤግዚቢሽኖች አቅርባለች – በዎከር የስነጥበብ ማዕከል፣ ሚኒያፖሊስ (1995)፣ በREDCAT፣ ሎስ አንጀለስ (1995)፣በአልብራይት-ኖክስ የስነጥበብ ጋለሪ፣ ቡፋሎ (1995)፣ በሴንት ሉዊስ የስነጥበብ ሙዚየም (1997)፣በMUSAC፣ ሊዎን፣ ስፔን (1998)፣ “ሲቲ ሳይቲንግስ” በሚል ርዕስ በዴትሮይት የስነጥበብ ተቋም (1999)፣ “ብላክ ሲቲ” በተሰኘ ርዕስ በሉስያና ሙዚየም፣ ዴንማርክ (1999)፣ በሰሜን ካሮሊና የስነጥበብ ሙዚየም፣ ራሊግ (2002)፣ “Grey Area” በሚል ርዕስ በደች ጉግኒህም፣ በርሊን (2001) እና በሰሎሞን አር. ጉግኒህም ሙዚየም፣ ኒውዮርክ (2002) ናቸው፡፡

ጁሊ በ1995 ዓ.ም በሚኒያፖሊስ፣ የዎከር ስነጥበብ ማዕከል ያቀረበችውን የመጀመሪያ የግል  ኤግዚቢሽን፣ የህይወቷን አቅጣጫ ከወሰኑላት አጋጣሚዎች እንደ አንዱ ትቆጥረዋለች፡፡ በ33 ዓመት የወጣትነት ዕድሜ፣  እንደ ዎከር ባሉ ትላልቅ ተቋማት ዕውቅና ማግኘት፣ እንደብርቅ የሚታይ እድል ነው፡፡ ጁሊ ግን አራት በጣም ትላልቅና ስድስት ትናንሽ ስዕሎች የቀረቡበት ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ችላለች፡፡ ሁለተኛው ትልቅ ስኬቷ ደግሞ በ2002 ዓ.ም በኒውዮርኩ የጉግኒህም ሙዚየም በግሏ ያቀረበችው ኤግዚቢሽን ነበር –ግሬይ ኤርያ” በሚል ስያሜ፡፡ በጉግኒህም የ51 ዓመት ታሪክ አፍሪካዊ ዘር  ያለው ሰዓሊ በግል ኤግዚቢሽን ሲያቀርብ ጁሊ የመጀመሪያዋ  ናት፡፡ በቅርቡ በኒውዮርክ ሲቲ እምብርት ለሚገኘው የGoldman Sachs ዋና መ/ቤት የሰራችው ግዙፍ የግድግዳ ስዕል ፕሮጀክት ደግሞ ሌላው አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበችበት ሥራዋ ነው፡፡ ይሄ ፕሮጀክት ሃሳቡን ከማመንጨት ፕሮፖዛል እስከ ማርቀቅ እንዲሁም ረዳቶች አሰባስቦ እስከ ማጠናቀቅ ድረስ ድፍን ሦስት ዓመት ተኩል ፈጅቶባታል፡፡ “ሙራል” የሚል ስያሜ የተሰጠውንና 23 x በ80 ጫማ (7×24.4ሜ) የሆነውን ስዕል ሰርቶ ለማጠናቀቅ ብቻ ሁለት ዓመት የወሰደባት ሲሆን ከፕሮጀክቱ አስኳል ቡድን ጋር የሥራ ቦታዋን ወደ በርሊን አዛውራ ሥራውን እንዳጠናቀቀች ትናገራለች፡፡ በመጨረሻ ደግሞ 13 ወራትን የፈጁ አራት ትላልቅ ሙሉ ስዕሎችን ሰርታለች – 15ሜ ቁመትና 12 ጫማ ስፋት ያላቸው፡፡ እነዚህ አራት ስዕሎች በ2004 ዓ.ም በካሴል፣ ጀርመን dOCUMENTA XIII ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ጁሊ ስዕልና ጥበብ እውነታ የሚገለጥበት የህይወት አካል እንደሆነ ከልቧ ታምናለች፡፡ የረዥም ዘመን ጥንታዊ የስዕል አመለካከትና አሳሳል ጎልቶ በቀጠለበት ዓለም ውስጥ አዲስ የስዕል ቋንቋ በመፍጠር የስዕልን የለውጥ ሂደት የሚያራምድ ሥራ ማፍለቅ፣ ለእሷ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፡፡ በአብዛኛው  አብስትራክት የአሳሳል ዘይቤን የምትከተለው ጁሊ፤ ተለይተው የሚታዩ ምስሎችን የሚጠቀም የአሳሳል ዘይቤ፣ባለብዙ ቅርንጫፍ ሥዕሎችን ለመግለፅ አይችልም ብላ ታስባለች፡፡ ጁሊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እውነታን ለመግለፅ የሚያስችላትን የአብስትራክት መንገድ ለማግኘት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ በእሷ አስተያየት፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እውነታ፣ከአብስትራክት ስዕል ታሪክና የለውጥ ሂደት ጋር ተነጣጥለው  አያውቁም፡፡ ዛሬ ግን የአብስትራክት ቋንቋ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አድበስብሶ የሚያልፍ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ስዕሎቿ እኒህን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መልሰው ለማገናኘት ይሞክራሉ –  አዲስ ቋንቋ በመፍጠርና እነዚህን ጉዳዮች በመዳሰስ፡፡ ይሄ ዓላማዋ ቢቀጥልም፤ የአሳሳል ዘይቤዋ ሁሌም በለውጥ ሂደት ላይ ነው፡፡

ጁሊ፤በጉግንሂም ሙዚየም ኤግዚቢሽን ስታቀርብ የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ስዕሎቿን እንዲህ ገልፆታል፡   “ምስሎችን ስንመለከት የሚያጋጥመውን ዓይነት የስፋትና የጥልቀት ስሜት እንዲያድርብን ማድረግ የስዕሎቿ ባህሪ ነው፡፡ ለስዕሎቿ ፈሳሽ ቀለምና አክሪሊክ ነው የምትጠቀመው፡፡ የህንፃዎችና የከተማ ሰፊ ገፅታዎችን በዝርዝር የሚያሳዩ፣ በአብስትራክት ቅርፆችና መስመሮች የተሰሩ ንድፎችን አንዱን በሌላው ላይ እየደራረበች ትስላለች – የቅንብሩን ርቀትና ጥልቀት እየቀያየረች፡፡”  በለውጥ ሂደት በሚጓዘው የዘመናችን ሰፊ የከተሜነት ህይወት ውስጥ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን በስዕሎቿ ለማሳየት የምትጥረው ጁሊ፤ የሥነህንፃ ቋንቋ ታሪክን በተምሳሌትነት ትጠቀማለች፡፡ ምንም ዓይነት ቅርፆችን ከአውዱና ከአካባቢው መነጠል አይቻልም፡፡ ሥራው የራሱን እውነታ ይፈጥራል፡፡ እውነታው ግን ለእያንዳንዱ ተመልካች ይለያያል – ሰዎች ከማህበራዊና ፖለቲካዊ ታሪካቸው ጋር በሚፈጥሩት ትስስር እንዲሁም ስዕሉን ሲመለከቱ እንደሚያገኙት ግንዛቤ፡፡

ጁሊ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሷን ፕሮጀክቶች የመስራት ዕድል ባታገኝም ከኢትዮጵያውያን ጋር በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር ለመሥራት ችላለች፡፡ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች በዓለም የስዕል መድረክ እንደሚሳተፉ ከፍተኛ እምነት ያላት ጁሊ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ዘመናዊ ስዕሎችን መስራት እንደሚችሉ በእጅጉ ተስፋ ታደርጋለች፡፡ “ወጣት ሰዓሊዎች ከተለመደው ወጣ ያለ ሥራ ማበርከትና ስዕልን ፍፁም ባልተሞከረ አዲስ መንገድ ለመስራት ማሰብ ይችላሉ፡፡ ይሄ በተወሰነ መንገድ እየሆነ ያለ ይመስለኛል ፤ ግን የተለየ ዓይነት ትምህርት ይፈልጋል፡፡ ክፋቱ ግን እንዲህ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ተነፍጐ ስለቆየ መልሶ ለማምጣት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን፤ እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከሆነ ጊዜ በኋላ መምጣቱ አይቀርም” ትላለች፡፡

ለኢትዮጵያ የምትመኘው የተደላደለ ኢኮኖሚ፤ እድገትና ለውጥ እንዲሁም፤ ሁሉም እኩል መብቶች የተረጋገጡበት፣ የበለጠ ግልጽና አሳታፊ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ነው፡፡ ሰዎች ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ይምጡ፣ በማንነታቸው ሳያፍሩ ራሳቸውን የመሆን መብት አላቸው ብላ ታምናለች፡፡ በህብረተሰቡና በፖለቲካው ውስጥ የበለጠ ነፃና ያልተገደበ በሆነ መንገድ የመሳተፍ መብት እንዳላቸውም እምነቷ ነው፡፡

ጁሊ ለወጣት ሴቶች ከመምከር ይልቅ እነሱኑ ማድመጥ ትሻለች፡፡ አሁን ካሉበት ሁኔታ የተለየ ህልምና ምኞት ካላቸው አይሳካም ብለው ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም ባይ ናት፡፡ ለምን ቢሉ ያሉበትን ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ማዳበር ይችላሉ” ትላለች፡፡ ጁሊ ያለችበት ተጨባጭ እውነታ ከወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች በጣም የተለየ በመሆኑ ማጋራት የምትችለው ልምዷን፣ ታሪኳንና ሥራዋን ብቻ ነው፡፡ ወጣት ሴቶች እንዲያውቁ የምትሻው፤ ሴት ቢሆኑም ሰዓሊ ከመሆን የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ከፈለጉ  ሊመርጡ የሚችሉት ሙያ ነው ትላለች – ጁሊ፡፡ 


ዋና የመረጃ ምንጮች
  በግንቦት 2004 ዓ.ም ከጁሊ ምህረቱ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ 
ሌላ ምንጮች
 

KM Fine Arts, Accessed July 12, 2011; Available at:

http://www.artinfo.com/galleryguide/24110/10628/3317/km-fine-arts-km-fine-arts/artist/julie-mehretu/biography/

http://www.guggenheim.org/new-york/press-room/releases/press-release-archive/2010/3359-mehretu-release accessed July 1, 2012

አጥኚ
ቤተል በቀለ፤ ሜሪ – ጄን ዋግል

Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments

አቻምየለሽ ክፍሌ፣ ኮሎኔል ዶ/ር

AlmazDj

 

ዋና ዋና ስኬቶች:
በጦር ኃይሉ ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩት ሴት ሐኪሞች መካከል አንዷ በመሆን ሥራ የጀመረችየኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያዋ ሴት ሐኪም ናት። ለመከላከያ ኃይል የሕክምና ተቋማትበሙሉ የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎቶች ዳሬክተር በመሆን፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሰው ኃይልቅጥርና ምደባ፣ የአሰራር መመሪያዎች መስፈርት ዝግጅትና አፈፃፀም፣ የሕክምና መሳርያዎችና ቁሳቁስአቅርቦት፣ መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥና ተመሳሳይ ሥራዎችን በሃላፊነት ትመራለች። በዚህምበጦር ኃይሉ ውስጥ የሥራ አመራርና የአገልግሎት እንዲሁም የአሰራር መስፈርቶችና ደረጃዎች ዙሪያበተተገበሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች የአመራር አስተዋፅኦ አበርክታለች። ባልቲሞር ሜሪላንድ ከሚገኘውከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ለተመረጡ ተመራቂዎች የሚበረከት የክብር ሽልማት አግኝታለች። ሁለትጊዜ የተፋጠነ የማዕረግ እድገት በማግኘት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የኮሎኔልነት ደረጃ ላይ ደርሳለች።
ወቅታዊ ሁኔታ በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በጤና ዋና ዳሬክቶሬት፣ የሕክምናና የድጋፍአገልግሎት ዳሬክተር
የትውልድ ቦታ: ጋምቤላ
የትውልድ ዘመን: ሐምሌ 22 ቀን 1957 ዓ.ም
ወቅታዊ መኖሪያ ስፍራ: አዲስ አበባ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ጎሬ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት፣ ጎሬ፣ ኢሉባቦር
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ጎሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጎሬ፣ ኢሉባቦር፤ ተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (12ኛ ክፍል)፣ አዲስ አበባ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት
የሕክምና ዶክተር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የድህረ ምረቃ ትምህርትፖስት ግራጅዌት ዩኒቨርስቲ
ፖስትዶክቶራል ዲግሪ፣ በሕፃናት ሕክምናና ጤና፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በ1984 ዓ.ም፤ ማስተርስ ዲግሪ በጤና አጠባበቅ፣ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ፣ 1998 ዓ.ም
ዋና የስራ ዘርፍ
ሕክምና፣ የጦር ኃይል ሕክምና አገልግሎት አስተዳደር
የሕይወት ታሪክ
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያዋ ሴት ሐኪም የሆነችው ኮሎኔል ዶ/ር አቻምየለሽ ክፍሌ፤ ከደረጃ ደረጃ እያደገችና በበርካታ የሃላፊነት ቦታዎች እየሰራች፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የጤና ዋና ዳሬክቶሬት የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎት ዳሬክተር ለመሆን በቅታለች። የሠራችበትና ሃላፊነት የያዘችባቸውን ቦታዎች ዘርዝሮ ለመጨረስ ይከብዳል። በደብረ ዘይት የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተማሪና ዲን ሆና ሰርታለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ረዳት ፕሮፌሰር ናት። በጦር ኃይሎች የሪፈራልና የስልጠና ሆስፒታል፣ በሐኪምነት፣ በአስተማሪነት፣ በዲፓርትመንት ሃላፊነት እንዲሁም በሜዲካል ዳሬክተርነት አገልግላለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በሚካሄዱ ጥረቶች ያበረከተቻቸው የአመራር አስተዋፅኦዎች በርካታ ናቸው። ኤችአይቪን በሚመለከት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ያገለገለችው ኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፤ በብሄራዊ የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚከታተል ብሄራዊ ቦርድ ውስጥም ሰርታለች። ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በተመሰረተው ብሄራዊ የሴቶች ጥምረት ውስጥ የቦርድ አባል ናት። ለአገሪቱ ጦር ኃይል የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ የአምስት አመት የስትራቴጂ እቅድ፣  የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት አጠቃቀም መመሪያና ሌሎች የአሰራር ሰነዶችን አዘጋጅታለች፤ በዝግጅት ላይ ተሳትፋለች። በአገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ።

የነፃነት መንፈስ የተላበሰ ዘመናዊ ቤተሰብ ውስጥ የወላጆቿ ፍቅርና ድጋፍ ሳይለያት በጋምቤላ እንዲሁም በጎሬ ኢሉባቦር ያደገችው አቻምየለሽ፣ ሴትና ወንድ ልጆች በሙሉ በእኩል አይን ይታዩ እንደነበር ታስታውሳለች። ቤት ውስጥ እኩል ይሠራሉ፤ የጨዋታ ጊዜም ይፈቀድላቸዋል። በትምህርት ቤቷ የድራማ ክበብ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የክርክር ክበብ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቤተክርስትያን የፀሎት ቡድን አባል ነበረች። የወደፊት ሕይወቷን ለመምረጥ የቻለችው ታላቅ እህቷን በማየት ነው። ሆስፒታል በሌለባቸው አካባቢዎች ሐኪም ሆነው ሲያገለግሉ ከነበሩት ነርሶች መካከል የአቻምየለሽ ታላቅ እህት አንዷ ነች። የእህቷን ፈለግ በመከተል  በሕክምና ሙያ የተማረከችው አቻምየለሽ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብታ ሕክምና ስታጠና ደግሞ ሌላ የሚማርክ ነገር አየች። ለተግባራዊ ስልጠና ወደተለያዩ ሆስፒታሎች ለመሄድና አሰራራቸውን ለመቃኘት እድል ነበራት። ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮችንም አስተውላለች። ከሁሉም በላይ ግን፣ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተመሰጠች። ምንም እንኳ ቤተሰቧ ውስጥ ውትድርናን የሚያውቅ ሰው ባይኖርም፣ በጦር ኃይሎች ያየቻቸው ነገሮች… የደንብ ልብሱ፣ ስነ ስርዓቱ፣ አደረጃጀቱ…  ነሸጧት። ተግባራዊ ስልጠናውንና የሕክምና ሃላፊነቷን እየተወጣች፤ ጎን ለጎን በሆስፒታሉ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መሳተፍ ጀመረች። ከሰዎች ጋር መግባባት ያስደስታታል። በዚያ ላይ ከታካሚዎቿ ጋር ቀረቤታ መፍጠርና ቤተሰብ መሆን የምትወድ ሐኪም ነች። ወደ ጦር ኃይል የመቀላቀል አዝማሚያዋ እየዋለ ሲያድር ስር ሰዶ የሕይወት አላማዋ ሆኖ ተተከለ። የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ለመሆን ፍላጎት እንዳደረባት ያወቁ አንዳንድ ጓደኞቿና የሥራ ባልደረቦቿ ሃሳቧን ለማስቀየር ቢሞክሩም የራሷን ፍላጎት ለመከተል ቆረጠች።

የትምህርቷ የመጨረሻ አመት ላይ የሙያ አቅጣጫዋን መርጣ የወሰነችው አቻምየለሽ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተመራቂዎችን በሚመለምልበት ወቅት ተመዘገበች። በእርግጥ የአየር ኃይል ሰዎች ወንድ ተመራቂዎችን ለመመልመል ነበር ያሰቡት። ቢሆንም እሷም ተቀባይነት አግኝታ በእጩ መኮንንነት ወደ ወታደራዊው የሙያ ሕይወት ገባች። የመኮንኖች ስልጠና ከወሰደች በኋላ በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ሥራ ጀመረች። በአየር ኃይል ውስጥ ብቸኛዋ ሴት ዶክተር እንደመሆኗ፣ ከጦሩ ቤተሰቦች ጋር ተቀራርባ በተለይም በሕፃናትና በእናቶች ጤና ላይ በልዩ ትኩረት ለመሥራት ጥራለች። ደብረዘይት በሚገኘው የአየር ኃይል ዋና የማዘዣ ካምፕ ውስጥ ከመደበኛው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ፣ በሰው ኃይል ቅጥር፣ በሕክምና ቦርድና በሌሎች ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ አገልግላለች።

ለአንድ አመት ያህል በሕክምና ከሰራች በኋላ፣ በ1979 ዓ.ም እንደገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመለሰች። በሕፃናት ሕክምና የድሕረ ምረቃ ትምህርቷን በ1984 ዓ.ም ያጠናቀቀችው አቻምየለሽ፣ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሕፃናት ሐኪም እንድትሆን ስትመደብ፣ በሆስፒታሉ የሕክምና ኮሌጅ በአስተማሪነት  ሰርታለች። ቀስ በቀስም ተጨማሪ ሃላፊነቶችን እየተረከበችና የአመራር ቦታዎችን እየያዘች የእድገት ጉዞዋን ጀመረች። የሆስፒታሉ የህፃናት ሕክምና ክፍል ሃላፊ፣ የሆስፒታሉ ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የስልጠናና የዶኩመንቴሽን ክፍል ሃላፊ በመሆን ስትሰራ ቆይታ፣ የጦር ኃይሎች የስልጠና ሆስፒታል ምክትል ዳሬክተር ከዚያም ዳሬክተር ሆናለች። ታዲያ ለጦር ሰራዊት ቤተሰቦች ሕክምና መስጠቷን ሳታቋርጥ ነው፣ የአመራር ድርሻዋን እንዲሁም ጥናትና ምርምሯን የምታካሄደው። ግን በዚህ አልተወሰነችም። ይበልጥ በስፋት መሥራት እንዳለባት ተገነዘበች። በ”ደ ቢርስ” የገንዘብ ድጋፍ በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የመማር እድል ያገኘችው አቻምየለሽ፣ በ1999 ዓ.ም በጤና አጠባበቅ የማስተርስ ዲግሪዋን የተቀበለችው ከከፍተኛ ማዕረግ ሽልማት ጋር ነው።

በጤና አጠባበቅ ከተመረቀች በኋላ፣ ደብረዘይት በሚገኘው የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን እንድትሆን ተመርጣ ተመደበች። በተለያዩ ዘርፎች ኮሌጁ የሚያቀርባቸው ስልጠናዎች ከመከላከያ ኃይል ፍላጎቶች ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ፣ በሥርአተ ትምህርት ዝግጅቶችና ማሻሻያዎች ላይ ሰርታለች። በከፍተኛ መኮንንነትና በተቆጣጣሪነት ወደ መከላከያ ኃይል የሰላም አስከባሪ ማዕከል የተዛወረችው አቻምየለሽ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ተልእኮዎችን በሙሉ የሚያካትት ሃላፊነት ነበረባት። በዚህ ሃላፊነቷም፣ ጠቅላላ የጤና ሥርዓትና አሰራሮችን በበላይነት ከመቆጣጠርም በተጨማሪ የፖሊሲ አማካሪ በመሆንም ሰርታለች። ከዚያም እንደገና ወደ ሌላ ሃላፊነት ተዛወረች። ዩናሚድ በሚል ስያሜ ወደ ዳርፉር ሱዳን በተሰማራው የሰላም አስከባሪ ሃይል፣ ዋና ወታደራዊ የሕዝብ ግንኙነትና የመረጃ መኮንን እንድትሆን የተመደበችው አቻምየለሽ፣ ለአስር ወራት የሰላም አስከባሪው ዋና አዛዥ ቃል አቀባይ በመሆን አገልግላለች። አሁን በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና የጤና ዳሬክቶሬት፣ የሕክምናና የድጋፍ አገልግሎቶች ዳሬክተር ሆና እየሰራች ነው። የፖሊሲና የአሰራር መስፈርቶችን ጨምሮ ጠቅላላ የሥራ አመራርና ሌሎች ተቋማዊ ሃላፊነቶችን ትወጣለች። በሐኪምነት የማማከር ስራዋን ግን አላቋረጠችም። በመከላከያ የጤና ኮሌጅም ታስተምራለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፋኩልቲ ደግሞ የክብር ረዳት ፕሮፌሰር ናት።

ዶ/ር አቻምየለሽ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ወታደራዊ የሙያ ሕይወቷን ያዋለችው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የጤና ተቋማትን አወቃቀር፣ የአገልገልግሎት ደረጃ እና አሰራርን ለመገንባት መሆኑ ያኮራታል። በአንድ ዘርፍ ብቻ የስፔሻላይዜሽን ስልጠና በመስጠት ሥራ የጀመረው የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ አሁን የሕክምና ዶክተሮችንና በማስተርስ ዲግሪ የሰለጠኑ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ በ12 የጤና ዘርፎች በርካታ ተመራቂዎችን እያፈራ ነው።

ኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፣ የሙያና የሕይወት አድማሳቸውን ለሚያስፋፉ እንዲሁም፣ የቤተሰብ ሕይወትንና የሙያ ሕይወትን አቻችለው ለሚመሩ ሰዎች ያላት ክብር እጅግ ትልቅ ነው። ተማሪ ሳለች የምታደንቃቸው ጄነራል ዶ/ር ኃይሉ ክፍሌ፤ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ከመሆናቸውም በላይ፣ ሐኪም፣ መሪ እና የሆስፒታሉ ዋና አዛዥ  ነበሩ። ለታካሚዎች ጊዜ ሰጥተው ከልብ የሚንከባከቡ ሴት ሐኪሞችም መንፈሷን ለሥራ ያነቃቁታል። ሌሎችን ለማገልገል ወደ ኋላ ሳይሉ በፅናት የሚሠሩ ሰዎች፣ አርአያዎቿ ናቸው።

በሙያ ሕይወቷ እንዳስተዋለችው፣ ሴቶች በትጋትና በሥራ ውጤት ብቃታቸውን ቢያስመሰክሩ እንኳ የአመራር ቦታ ለማግኘት ብዙ ፈተና ይገጥማቸዋል። ይሁን እንጂ በፈተናዎች አልተበገረችም። አስተዳደጓ፣ ፅኑ አቋሟ፣ አላማዋና በራስ የመተማመን ስሜቷ ፈተናዎችን ተጋፍጣ ለማሸነፍ ረድተዋታል። ትምህርት ላይ ፈጣን ነች፤ ነገሮችን በቅርበት አስተውላ ቶሎ ትገነዘባለች። በትኩረት ታዳምጣለች። እና ደግሞ፣ በቅን ልቦና ትሠራለች። በሙያ ሕይወት ላይ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በቁንፅል ሳይሆን ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር አስተሳስራ በትክክለኛ መነፅር እንደምትመለከት የምትገልፀው አቻምየለሽ፤ ትምህርቷ በዚህ በኩል እንደተቀማት ትጠቅሳለች።

ለኮ/ል ዶ/ር አቻምየለሽ፣ የሚሌኒየም የልማት ግቦች ከልብ አጓጊ ናቸው። ሰዎች ንፁሕ ውኃ፣ ምግብና ትምህርት የተሟላለት ሕይወት ሲያገኙ ማየት ሕልሟ ነው። በተለይም ሴቶች የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ትመኛለች። ማህበረሰቡም በሴቶች ሚና ላይም የማሕበረሰቡ አስተሳሰብ እንደሚለወጥ ተስፋ አላት። ለኢትዮጵያ ያላት ሕልም፣ ሕይወት የሞላላቸው ዜጎች የሚኖሩባት አገር እንድትሆንና ጠንካራ እድገት እንድትቀዳጅ ነው። የጦር ኃይል ሴት አባላት አስተዋፅኦም እውቅና እንደሚያገኝ ተስፋ ታደርጋለች።

ምንም እንኳ ጎልቶ የሚታይ አስተዋፅኦ በማበርከት ስኬቶችን ብታስመዘግብም፣ ገና እጅግ ብዙ ትሠራለች። የእናቶችና የሕፃናት ማዕከል ለመገንባት የጀመረችውን ውጥን ለማጠናቀቅ የምትፈልገው አቻምየለሽ፣ ወታደራዊ የሙያ ሥራዋን ስትጨርስ በማህበረሰብ ደረጃ ሴቶችን፣ ሕፃናትንና ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ታስባለች።

አቻምየለሽ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፣ ባለቤቷና ልጆቿ ሥራዋን  ያውቁላታል፤ የተሻለ ነገር እንድትሠራ አበረታች ድጋፍም ይሰጧታል።

ለወጣት ሴቶች ምክሯን ስታካፍል፤ ሳትዘናጉ በርትታችሁ ሥሩ በማለት ትጀምራለች። ሴቶችን የሚያደናቅፉ ልምዶችንና አስተሳሰቦችን እየታገላችሁ፤ የግልና የሙያ ብቃታችሁን ለማሳደግ ለአፍታ ሳትዘናጉ ሁልጊዜ ትጉ። በእኩል ደረጃ ከወንድ የሥራ ባልደረቦቻችሁ ጋር ተቀላቀሉ። ተጋፍጦና ታግሎ ለማሸነፍ፣ በራስ የመተማመንና በራስ የመኩራት መንፈሳችሁን ገንቡ። በሴቶች ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ዘይቤዎችንና አመለካከቶችን በዝምታ አትለፉ። በጋራ ትብብር ማህበረሰባችሁን ለማሻሻል የበኩላችሁን አበርክቱ።

 

ዋና የመረጃ ምንጮች
ከኮሎኔል ዶ/ር አቻምየለሽ ክፍሌ፣ በነሀሴ 2004 ዓ.ም
አጥኚ
ሜላት ተክለጻዲቅ

Posted on October 7, 2014 By admin With 0 comments